Print this page
Sunday, 19 February 2017 00:00

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንና ዋና አሰልጣኞቹ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)


            • የአዳማ ከነማው አሸናፊ በቀለ… 35ኛው ዋና አሰልጣኝ ሊሆን ይችላል
        • ባለፉት 60 ዓመታት 11 የውጭ አሰልጣኞች በሃላፊነቱ ሲፈራረቁ፤ 23 ጊዜ የኢትዮጵያዊ አሰልጣኞች    ቅጥር ተፈፅሟል፡፡
  በ35ኛው የዋና አሰልጣኝ ቅጥር ዙርያ
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ለዋናው ብሄራዊ ቡድን ‹‹ዋልያዎቹ›› ዋና አሰልጣኝ ለመቅጠር ማስታወቂያ ያወጣው ከወር በፊት ነበር፡፡ 11 ኢትዮጵያዊ እና 14 የውጭ አገር አሰልጣኞች ሃላፊነቱን ለማግኘት እንዳመለከቱም ሲገለፅ ሰንብቷል፡፡ የፌደሬሽኑ ቴክኒክና ልማት ቋሚ ኮሚቴ ለቅጥሩ ባወጣቸው መስፈርቶች መሰረት አመልካቾችን አወዳድሮ አሸናፊውን ያመለከተበትን የውሳኔ ሃሳብ የሰጠው ደግሞ ባለፈው ሳምንት ነው፡፡ ይህን ተከትሎም የአዳማ ከነማ ክለብ አሰልጣኝ የሆነው አሸናፊ በቀለ ሃላፊነቱን እንደሚረከብ በተለያዩ የመረጃ ምንጮች እየተገለፀ ይገኛል፡፡  ፌደሬሽኑ ተዘጋጅቶ በቀረበው የውሳኔ ሃሳብ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውሳኔ እንዳልሰጠበት  ለሁሉም የስፖርት መገናኛ ብዙሃን  በላከው መግለጫ ያመለከተ ሲሆን በቀጣይ ሳምንት ዋና አሰልጣኙ በይፋ እንደሚገለፅ ይጠበቃል፡፡  
 በአጠቃላይ የዋና አሰልጣኝ የቅጥር ሂደቱ የተለያዩ ሁኔታዎች ዙርያ ግልፅ መረጃዎች በሚመለከታቸው አካላት ባለመቅረባቸው  ልዩ ትንታኔ ለመስጠት ያዳግታል፡፡  በፌደሬሽኑ በኩል ለብሄራዊ ቡድኑ ህልውና እና ውጤታማነት በቂ ትኩረት አለመሰጠቱን በተለያዩ ሁኔታዎች መገንዘብ ይቻላል፡፡ በመጀመርያ ደረጃ ጊዜያዊ አሰልጣኝ የነበረው ገብረመድህን ኃይሌ ከሃላፊነቱ ከተነሳ በኋላ ቡድኑ የሚሳተፍበት ውድድር የለም በሚል ምክንያት   ያለ ዋና አሰልጣኝ ለ3 ወራት ተበትኖ መቆየቱ ተገቢ አልነበረም፡፡  ስለሆነም ዋና አሰልጣኝ  የማፈላለግ ጥድፊያ ውስጥ የተገባበት ሁኔታ ይስተዋላል፡፡ በሌላ በኩል የቅጥር ሂደቱ ከወር በፊት ማስታወቂያ  በማውጣት የተጀመረ ቢሆንም ስለ አመልካች አሰልጣኞች ከታማኝ ምንጮች እና ተባራሪ ወሬዎች ባሻገር በግልፅና ኦፊሴላዊ መረጃዎች የታጀበ አልነበረም፡፡ ይህም በዋና አሰልጣኝ ቅጥሩ ዙርያ በአገር አቀፍ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ  ሊገኙ የሚችሉ የዜና ሽፋኖችን አሳጥቷል፡፡ በተያያዘ ደግሞ የውጭ አሰልጣኝ ቅጥር በደሞዝ ውድነት እንደማይሳካ መነገሩ የፌደሬሽኑን አቅም አስገምቶታል፤ በጂኬ የጨዋታ ፍልስፍና ዙርያ የተለመደው ክርክር መቆስቆሱም በብሄራዊ ቡድኑ አጨዋወት ላይ በስፖርት አፍቃሪው መካከከል ዛሬም አለመግባባት መኖሩ ተስተውሏል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ቅጥር ከጀመረ 60 ዓመታት ተቆጥረዋል። 23 ጊዜ ለኢትዮጵያዊ  እንዲሁም 11 ጊዜ የውጭ ዜግነት ላላቸው  በድምሩ የ34 ዋና አሰልጣኞች ቅጥር ተፈፅሟል፡፡ በታሪክ የመጀመሪያው የዋና አሰልጣኝ ቅጥር የተፈፀመው ለውጭ አሰልጣኝ ሲሆን በዜግነታቸው  ከቀድሞዋ ቼኮስሎቫኪያ የሆኑት ጄሪ ስታሮታ በ1959 እኤአ ላይ የተሾሙበት ነበር፡፡ በቀጣይ ሳምንት  የመጨረሻው ቅጥር ሲፈፀም ደግሞ በብሄራዊ ቡድኑ ታሪክ 35ኛው የዋና አሰልጣኝ ቅጥር ሆኖ ይመዘገባል፡፡
አስራ አንዱ የውጭ አሰልጣኞች
ከመጀመርያው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ቼኮስሎቫኪያዊው ጄሪ ስትሮታ ጀምሮ እስከ ፖርቱጋላዊው ማርያኖ ባሬቶ ድረስ 11 የውጭ አሰልጣኞች በብሄራዊ ቡድኑ ሃላፊነት ላይ ተፈራርቀዋል፡፡ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የሰሩት 11 የውጭ  አሰልጣኞች  በሙሉ ከአውሮፓ የተገኙና በአመዛኙ በሃላፊነት የቆዩት 1 ዓመት እና ከ1 ዓመት ባነሰ የስራ ዘመን ሲሆን  ጀርመን በ3 አሰልጣኞች በመወከል ቀዳሚ ናት፡፡ ጄሪ ስታሮታ ከቼኮስሎቫኪያ  በ1959 እኤአ፤  ስላቭኮ ሚሎዞቪች ከዩጎዝላቪያ  በ1961 እና በ1962 እኤአ፤ ስዙክ ፈረንክ ከሀንጋሪ  በ1968  እኤአ፤ ፒተር ሽናይቲገር ከጀርመን በ1974 እኤአ፤ ክላውስ ኢቤንግሃውሰን ከጀርመን በ1988  እኤአ፤ ኦኮ ኢዲባ በ1997 እኤአ፤ ጆሃን ፊገ ከጀርመን  በ2002 እኤአ፤ ኢፌም ኦኑራ ከስኮትላንድ  በ2010 እኤአ፤ ቶም ሴንትፌት ከቤልጂየም በ2011 እኤአ እንዲሁም ፖርቱጋላዊው ማርያኖ ባሬቶ በ2014 እኤአ ብሄራዊ ቡድኑን በዋና አሰልጣኝት አገልግለዋል፡፡  
ሃያ ሶስቱ የኢትዮጵያዊ አሰልጣኝ ቅጥሮች
በጊዜያዊነት ተሹሞ እስከነበረው ገብረመድህን ሃይሌ ድረስ ለብሄራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝነት  23 ጊዜ የኢትዮጵያዊያን ቅጥር ተፈፅሟል፡፡  በሚቀጥለው ሳምንት አዲሱ የብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ሲሾም ለ24ኛ ጊዜ  ኢትዮጵያዊ የሚቀጠርበት ይሆናል፡፡ የመጀመርያው ኢትዮጵያዊ የብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ  በአፍሪካ እግር ኳስ ከፍተኛ የክብር ቦታ ያላቸው ይድነቃቸው ተሰማ ነበሩ፡፡
ኢንስትራክተር ሰውነት የምንግዜም ምርጡ
የብሄራዊ ቡድኑ የምንግዜም ምርጥ አሰልጣኝ ሊሆኑ የሚችሉት ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው ናቸው።   ከ2004 እሰከ 2006 እኤአ ብሄራዊ ቡድኑን በዋና አሰልጣኝነት ሲመሩ  በዋናው እና በወጣት ብሔራዊ ቡድን ሁለት የሴካፋ ዋንጫዎችን ያሸነፉ ሲሆን፤ ሌላው ስኬታቸው በ2013 እኤአ ብሄራዊ ቡድኑ ከ31 ዓመታት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ እንዲያልፍ ማስቻላቸውና በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ በቻን ውድድር ቡድኑን እንዲሳተፍ በማድረጋቸው ነው፡፡
የኢትዮጵያዊና የውጭ አሰልጣኞች ወርሃዊ ደሞዝ
በብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝነት ከፍተኛውን ደሞዝ በማግኘት የመጀመርያውን ፈርቀዳጅ ታሪክ የሰሩት ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው  ነበሩ፡፡  ከ31 ዓመታት መራቅ በኋላ ቡድኑን ለአፍሪካ ዋንጫ ባሳለፉበት ወቅት ይከፈላቸው የነበረው 50 ሺ ብር  ወርሃዊ ደሞዝ ከፍተኛው ክብረወሰን ነበር፡፡  ከኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው በኋላ ሌላው ኢትዮጵያዊ ዋና አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ በ75ሺ ብር ወርሃዊ  ደሞዛቸው  የከፍተኛ ክፍያ ክብረወሰኑን ተረክበዋል፡፡ ዘንድሮ ለብሄራዊ ቡድኑ የሚቀጠረው አዲስ ኢትዮጵያዊ ዋና አሰልጣኝ ወርሃዊ ደሞዝ ቢያንስ 50 ሺህ ቢበዛ 85  ሺህ  ብር እንደሚሆን  እየተነገረ ነው፡፡
በአንፃሩ በቅርብ ጊዜ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከሰሩት የውጭ አሰልጣኞች ከኢትዮጵያውያኖቹ ሁለት እና ሶስት እጥፍ ደሞዝ የሚያገኙ ነበሩ፡፡ ለመጨረሻ ጊዜ በሃላፊነቱ ላይ የነበሩት ፖርቱጋላዊው ማርያኖ ባሬቶ በወር 18 ሺ ዶላር እየታሰበላቸው የሰሩ ከፍተኛው ተከፋይ ሲሆኑ፤ ፈረንሳዊው ዲያጎ ጋርዚያቶ 10ሺ ዶላር፤ ስኮትላንዳዊው ኢፌም ኦኑራ 13ሺ ዶላር  ይከፈላቸው እንደነበር ይታወሳል፡፡

Read 3048 times