Sunday, 19 February 2017 00:00

የገነት ዓለም!!

Written by  በሚፍታ ዘለቀ
Rate this item
(0 votes)

   በባለፈው ሳምንት እትም የሠዓሊ ገነት አለሙን ዓለም የሚያስቃኘውን ጽሁፍ የመጀመሪያ ክፍል ሳቀርብ ሁለት ምክንያቶች ነበሩኝ፡፡ የመጀመሪያውና ዋንኛው በአስኒ ጋለሪ በቆንጂት ስዩም የተጋፈረው “Intimate Red” የተሰኘው የሠዓሊዋ ትርዒት በልዩ አቀራረቡ ስሜቴን ስለነካኝ ነበር፡፡ ሌላኛው ደግሞ ሠዓሊ ገነት አለሙ፤ ለሃገራችን ዘመንኛ ሥነ-ጥበብ ያበረከተችውን አስተዋጽኦ እስትንፋሷ በሕይወት እያለች የመዘከር ተገቢነት ዘወትር ስለ ገኒ ሳስብ የሚጎላብኝ ጉዳይ በመሆኑ ነበር፡፡
ጊዜና ሁኔታዎቹ የተሳኩ መስለውኝ የመጀመሪያውን ክፍል እትም ላነብላት ቀጠሮ ይዤ ነበር፡፡ ሆኖም፤ ከዚህች ምድር ሊለያት ቁርጥ ቀጠሮ የያዘ ስለነበር ውጥኔ አልተሳካም፡፡ ጽሁፉ የወጣበትን እትም በእጄ ይዤ ነበር ዜና እረፍቷን የሰማሁት፡፡ መላዕከ ሞትን በስውር የመጋፈጥ ያህል ድንዛዜ ነበረው፡፡ ለአመታት ሲያዳክማትና ሲያሰቃያት የነበረው የካንሰር ህመምን ለተወሰነ ጊዜያትም ቢሆን የመታገል አቅም እንደሚኖራት ተስፋ ነበረኝ፡፡ ከዜና እረፍቷ በኋላ ገኒን ከሚያውቅ ሰው የሚደመጡት Fighter; Survivor; ታጋይ፡ ጠንካራ፡ ጀግና እና የመሳሰሉት ቃላት ነበሩ። እርግጥ ነው ገነት ከበሽታው ጋር ትግል ገጥማ ጠንካራና ጀግና መሆኗን አስመስክራለች፡፡ ከሞት ጋር ያደረገችው ትግል የጀመረው ግን በጡት ካንሰር ከመያዟም በፊት እንደሆነ አያሌ ማስረጃዎች አሉ፡፡ ከእነዚህ አብዛኛዎቹ ደግሞ ሞትን ረስታ ሕይወትንና ሕይወትን የማለምለም ትርጓሜ ብቻ ሊሰጡ የሚችሉ ማስረጃዎች ሆነው ይገኛሉ፡፡ የገነት ዓለም ስፋትና ጥልቀት ፈላስፋ ሊያደርገኝ ነው መሰል፡፡ ገነት እንዴት ሠዓሊ እንደሆነች አጫውታኝ የነበረውን ላጫውታችሁና ወደ “Intimate Red” ትርዒት እንዲሁም ሁላችሁም ስለተጋበዛችሁበትና ዛሬ ከቀኑ 9፡00 ጀምሮ በአስኒ ጋለሪ ሠዓሊዋን ስለሚዘክረው መሰናዶ ትንሽ እላለሁ፡፡
ለሚያስደስቷት ነገሮች የነበራትን ፈንቃይ ስሜት (excitement) እንዲሁም በዚያው ልክ በነገሮች ያለመርካት ባሕሪዋን ሕይወቷን ሙሉ ሲያጤኑ የነበሩት አባቷ፤ “አንቺ ልጅ፤ ገነትን ፈልገሽ ማግኘት አለብሽ” ይሏት ነበር፡፡ የ12ኛ ክፍል ፈተናን ከተፈተነች በኋላ አርት ስኩል (አዲስ አበባ ዩኒቨርሲት አለ የሥነ-ጥበብና ዲዛይን ት/ቤት) ልትገባ እንደወሰነች ስትነግራቸው፣ “አሁን ገና ጥሩ ዘየድሽ” ነበር ያሏት። ገባች፡፡ ተሰጥኦዋን ማነጽ ጀመረች፡፡ ፈንቃይ ስሜትዋ መፍሰሻ ቦይ፤ ያለመርካት ባሕሪዋ ደግሞ ከእርካታ ጅረት ከሚያዋህዳት የሥዕል ጥበብ ፍቅሯ ጋር ተሰናኝቶ፣ በጅረቱ መንቦራጨቅ ብቻ ሳይሆን ስትንቦራጨቅ የተሰማትን፣ ያሰበችውን፣ ይጠቅማል ያለችውንና ያለመችውን ጭምር፣ እንካችሁ ለማለት በሚያስችል እሳቤ ተሞልታ፣ ቀጠለች፡፡ ትጋት፣ አዲስ ነገር የመፍጠር ጉጉት፣ ለሙያዋ መስዋዕትነት መክፈል፣ ሙያዊ እርካታዋን ዘወትር መፈለግና ግዴታዋን በኃላፊነት መወጣት፣ የገነት መገለጫ ነበር፡፡ ከዚህ የተሻለ ሞትን የመዋጊያ መንገድ ያለ አይመስለኝም፡፡ ቅስም የሚሰብረው የጡት ካንሰርን ስታስተናግድም የመስራትና ሞትን የማሸነፍ እሽቅድድሟ ላይ ኃይል ጨምራበት ይበልጥ መትጋት ቀጠለች እንጂ ፈጽሞ አልተዳከመችም። የበሽታው ታማሚ መሆኗ በሕይወት የመቆየትን ብሩህነት እንድትሰብክ እንጂ ከሕይወት የመለየትን ጨለማነት እንድታላዝን አላስገደዳትም፡፡ በሁለቱ ጽንፎች መሃል ማመሳከሪያ የሚሆኑን ስራዎቿ ናቸው፡፡ እነዚህ ስራዎች በየትኛውም አቅጣጫ ያለገደብ ማደግን፣ ማንሰራራትን፣ በሕልውና መቆየትን፣ ብርቱነትን..... ወዘተ የሚዘክሩ ነበሩ፡፡ በእውነቱ ገነት ታላቅ መማሪያችን ነበረች፡፡
“Intimate Red” በተሰኘው የገነት አለሙ ትርዒት መክፈቻ ላይ የተሰሙኝንና አገኘሁ የምላቸውን ቁም ነገሮች ላካፍላችሁ፡፡ ሠዓሊዋ የለችም፤ ቀይ ቀለምን በዋናነት የተጠቀመችበት ስራዎቿ ግን አሉ፡፡ በሠዓሊ ኤልሳቤጥ ሃብተወልድ የተዘጋጀውና “ድምጿ” ከተሰኘው የሴት ሠዓልያንን ሥነ-ጥበባዊ ጉዞ ከሚያስቃኘው ተከታታይ ቪዲዮ፣ የሠዓሊ ገነት አለሙን የ10 ደቂቃ ዘጋቢ ቪዲዮንም በጋለሪው አንደኛ ክፍል መከታተል ይቻላል። (ይኸው ትርዒት አንዳንድ ገነትን የሚስታውሱ ነገሮች ተጨምረውበት ዛሬ 9፡00 እንደሚቀጥል ለሃምሳኛ ጊዜ ሳስታውሳችሁ ደስታ ይሰማኛል)። ቁምነገር አንድ፡- የአጋፋሪዋ ቆንጂት ስዩም ብልሃታዊ ውሳኔ፡፡ ሳይቃጠል በቅጠል እንዲሉ፣ ገነት በመጨረሻዎቹ የሕይወቷ ቀናት ሆኖ ብታየው ሊያስደስታት ከሚችለው መሃከል ስራዎቿ በሰዎች እየታየ መሆኑን ማወቅ ነው፡፡ የለፋችለትና የኖረችለት ሁሉ ቦታ እንዳለው ማየት መቻል መታደል ነው፡፡ ብልሃተኛዋ አጋፋሪ ይህን እውን ማድረግ ችላለች፡፡ ቁምነገር ሁለት፡- የገነት አንዱ መገለጫ፤ የአጋፋሪዋ ምርጫ፡ ቀይ ቀለምን መሰረት ያደረጉ ስራዎች፡፡ ገነት ቀይ ቀለምን በስራዎቿ ስትጠቀም ብዙ እሳቤዎችን እንዲወክልላት ነው፡፡ እንዲህም ትላለች፡- “ቀይ ስለ እኔ በሕይወት መቆየት ነው፡፡ ቀይ ለእኔ ሴትነት ነው፡፡ ቀይ ማለት የምትሰዋው መስዋዕትነት ነው”። ሠዓሊዋ ከቀይ ጋር ያቆራኛትን ስሜታዊና ሂሳባዊ አመክንዮ ተረድቶና ተመልካችም ሠዓሊዋ ከቀይ ጋር ያላትን ቅርበት እንዲፈትሽ በተለይ ሥዕሎቹ ከተሰቀሉበት ሰፊ ግድግዳ አንጻር መጠናቸው እጅግ አነስተኛ የሆኑ ትናንሽ ሥዕሎችን በመስቀል የስራዎቹን ስሜትና ሃሳብ ጠጋ ብለን እንድንመረምር የሚያግዝ፤ የተዝናና ግን ደግሞ ከስራዎቹ ጋር ቅርበት እንድንፈጥር የሚጋብዝ አደራደርና አሰቃቀል ማበጀት ከአጋፋሪዋ የምንማረው አራተኛ፣ አምስተኛ፣ ካስፈለገም ሃምሳ ሰባተኛ ቁም ነገር ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ይህን ሁሉ የመፈልፈልና የማቅረብ መላ፣ ከምንገድ የሚገኝ ባለመሆኑ ነው። ልምድና አትኩሮት ያላቸው ሚና እንደተጠበቀ ሆኖ፣ አንድ አጋፋሪ አብሮት የሚሰራው ሠዓሊን ስራ ማቅረብ ብቻ ሳይሆን ሠዓሊው የኖረውን ሕይወት፡ የሕይወቱ መገለጫ የሆኑትን ቅመሞች የመለየት እንዲሁም በቀላል፣ በጣፈጠ፣ የሰው ልቦናን መንካት በሚችል አቀራረብ ማቅረብ መቻል የዳበረ የአጋፋሪነት ክሂሎት ከሚያስችለው በላይ በተለይ ገነት በወቅቱ የነበረችበትን የጤና ሁኔታ ከግምት ውስጥ ማስገባት የሚችልና የትርዒቱ መከፈት ለሠዓሊዋ ስነ-ልቦና የሚጨምረውን እሴት ማየት የሚችል የሰብአዊነት እዝነ-ልቦናን የሚከጅል ነው፡፡
የሆነው ሆኖ ግን ሠዓሊ ገነት አለሙ ለአርባ ሁለት አመታት ይህችን ምድር ጎብኝታ፤ በሙያዋ የጀግንነት ተግባሮችን ፈጽማ፡ በተለይ የኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ ያገባኛል ለሚል ለማንኛውም አካልም ሆነ ግለሰብ ስራዎቿን ጠብቆና ተንከባክቦ ለሕዝብ የማድረስ ኃላፊነት፡ በጥናት የማበልጸግ እንዲሁም በአግባቡ ሰንዶ ለትውልድ የማስተላለፍ እዳ የጣለች፤ ለቤተሰቧና ለእህቶቿ ፋና ወጊ፣ የሻማ ብርሃን የነበረች፣ እህቶቿ ፍርሃትን ተቋቁመው በሕይወታቸው ድልን እንዲያጣጥሙ አበረታች ኃይላቸው ሆና የዘለቀች ነበረች፡፡ ገነት የአንድ ልጇ የልዑል ሰፊ ዓለምም ነበረች፤ የልዑል ሥዕል የመስራት የማይሰለች ፍላጎት ለብዙዎቻችን የራሷ ግልባጭን የተወች ያህል ነው የሚሰማን፡፡ ለየጓደኞቿ መነቃቂያ፣ የሃዘናቸው ማስረሻ፣ የጭንቀታቸው መፍትሄ፣ የሸክማቸው ማረፊያም ነበረች - ገነት። በተለይ ቀሪን የሚያስገርም፣ ኗሪን የሚያስገነዝብ ጠባይዋ፣ ህመሟን በጽናትና በዝምታ ብቻ ሳይሆን ያለ አንዳች ማማረር እያስተናገደችም ሥዕል ለመስራት፡ በሕትመት ጥበብ ያካበተችውን ልምድና እውቀት ለማካፈል የነበራት ጉጉትና ስለ ሥነ-ጥበብ ሲወራ የሚፈካው ገጿና ትንፋሿ፣ እየተቆራረጠም ቢሆን ጣል ለማድረግ የምታደርገው ሙከራ ነው፡፡ በመጨረሻም ገነት አረፈች፡፡ ድካሟን የሰላም ያድርግላት፡ የገነት ዓለም እንዲቀጥል፤ የገነትን ብቻም ሳይሆን የበርካታ የሃገራችን ሥነ-ጥበብ ጀግኖቻችንን ልፋት የሚቆጥርና ቦታ የሚያስይዝ የሥነ-ጥበብ አካል እንዲኖር መመኘት ብዙ ዋጋ እያስከፈለን ያለ ጉዳይ በመሆኑ፣ ሁሉም በያለበት የሚሰራውን ማበርታት እንጂ ሌላ አማራጭ እንደሌለው ለመናገር ነብይ መሆን  አይጠበቅብኝም፡፡
በተረፈ ዛሬ 9፡00 በአስኒ ጋለሪ፣ ገነትን በሚዘክረው ዝግጅት ላይ እንድትታደሙ እጋብዛለሁ፡፡ አስኒ ጋለሪ ከአራት ኪሎ ወደ መገናኛ ሲሄዱ፣ 500 ሜ. ላይ ራስ አምባ ሆቴል ከመድረስዎ በፊት ያገኙታል፡፡ ቸር እንሰንብት!!  

Read 964 times