Sunday, 19 February 2017 00:00

አንዳንድ ነገሮች - ከግራሚ መንደር

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 59ኛው ታላቁ የግራሚ ሽልማት ባሳለፍነው እሁድ ምሽት በሎሳንጀለስ በደማቅ ስነስርዓት የተካሄደ ሲሆን፣ የሽልማት ስነስርዓቱን በተመለከተ መገናኛ ብዙሃን ካሰራጯቸው ዘገባዎች በጥቂቱ ቆንጥረን  እንሆ እንበላችሁ!...

      የሁለቱ እንስቶች ፍልሚያ
የዘንድሮው የግራሚ ሽልማት ዕጩዎች ዝርዝር ይፋ መደረጉን ተከትሎ፣ ጉዳዩ በሁለት እንስት የአለማችን ሙዚቃ ከዋክብት መካከል የሚደረግ ፍልሚያ እንደሆነ ሲዘገብ ነበር የሰነበተው - የአዴል እና የቢዮንሴ፡፡
መንታ ልጆችን ማርገዟን በቅርቡ ይፋ ያደረገቺው ተወዳጇ ድምጻዊት ቢዮንሴ ኖውልስ፤ በብዛት በመታጨት ቀዳሚነቱን ይዛ ነበር - ዘጠኝ ጊዜ ሽልማት በመታጨት፡፡ 25 በተሰኘው የሙዚቃ አልበሟ አለማቀፍ ዝናን ያተረፈቺው እንግሊዛዊቷ ድምጻዊት አዴል በበኩሏ፣ በአምስት ዘርፎች ታጭታለች፡፡
በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው  የግራሚ ሽልማት ውጤት ታዲያ፣ እንግሊዛዊቷ ድምጻዊት አዴል የአመቱ ምርጥ አልበም እና የአመቱ ምርጥ ሪከርድን ጨምሮ በታጨችባቸው አምስት ዘርፎች፣ በሁሉም አሸናፊ መሆኗን በማብሰር የፍልሚያው ባለድል መሆኗን አረጋግጧል፡፡
ተፋላሚዋ ቢዮንሴ፤ ማሸነፍ የመታጨትን ያህል አልቀናትም፡፡ ከታጨችባቸው ዘጠኝ ግራሚዎች በእጇ ማስገባት የቻለቺው ሁለቱን ብቻ ሆኗል፡፡
የተጧጧፈው የአልበም ሽያጭ
የዘንድሮው የግራሚ ሽልማት ውጤት እሁድ ምሽት ይፋ መደረጉን ተከትሎ፣ የተሸላሚ ድምጻውያኑ የሙዚቃ አልበሞች ሽያጭ እጅግ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ ተዘግቧል፡፡
የአምስት ሽልማቶች አሸናፊዋ አዴል የሙዚቃ አልበም የሆነው 25 ሽያጭ፣ ማሸነፏ ይፋ በተደረገ በሰዓታት ዕድሜ ውስጥ በ150 በመቶ መጨመሩ የተነገረ ሲሆን” ሄሎ” የተሰኘው ነጠላ ዜማዋ ዳውንሎድ የተደረገበት መጠንም በ308 በመቶ ያህል ጭማሪ አሳይቷል ተብሏል፡፡
በሽልማት ስነስርዓቱ ላይ የተላለፉ ሙዚቃዎች፣ እሁድ ዕለት ዳውንሎድ የተደረጉበት መጠን፣ በ207 በመቶ ያህል ጭማሪ ማሳየቱን የዘገበው ዘ ጋርዲያን፣ ሙዚቃዎቹ በድምሩ 178 ሺህ ጊዜ ዳውንሎድ መደረጋቸውን ጠቁሟል፡፡
26 ሚሊዮን ተመልካች
በሲቢኤስ የቴሌቪዥን ጣቢያ በቀጥታ የተላለፈውን የዘንድሮውን የግራሚ ሽልማት ስነስርዓት በአለም ዙሪያ የሚገኙ 26 ሚሊዮን ያህል ተመልካቾች እንደተመለከቱትና ይህ ቁጥር ከአምናው በ1 ሚሊዮን ያህል እንደሚበልጥ ኒውዮርክ ታይምስ ዘግቧል፡፡
የዘንድሮው ግራሚ በኤቢሲ ቴሌቪዥን ጣቢያ ከተላለፈውና 34 ሚሊዮን ሰው ከተመለከተው፣ የአምናው የአካዳሚ ሽልማት ስነስርዓት ቀጥሎ በታሪክ ሁለተኛው፣ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ፣ በቴሌቪዥን የተከታተለው የሽልማት ስነስርዓት ነው ተብሏል፡፡
ያልተለመደ ፖለቲካዊ ድባብ
የዘንድሮው የግራሚ ሽልማት ስነስርዓት ከወትሮው በተለየ መልኩ፣ ፖለቲካዊ ድባብ ያንዣበበበት እንደነበር ተነግሯል፡፡
የሽልማት ስነስርዓቱን በመድረክ አጋፋሪነት የመራው ጄምስ ኮርዴን፤ ስነስርዓቱን የከፈተው በራፕ መልክ ባቀረበው ፖለቲካዊ ሽንቆጣ ነበር - “ፕሬዚዳንት ትራምፕ እስካሉ ድረስ፣ መጪውን ነገር ማወቅ አንችልም!...” በማለት፡፡
ጄኔፈር ሎፔዝ በበኩሏ፤ በዚያው ምሽት የምርጥ አዲስ አርቲስት ዘርፍ ተሸላሚውን ይፋ ለማድረግ ወደ መድረክ በወጣችበት አጋጣሚ ባደረገቺው አጭር ንግግር፣ አሁን በምንገኝበት የታሪክ ምዕራፍ ላይ፣ ድምጻችን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አስፈላጊ ነው ብላለች፡፡ የሪከርዲን አካዳሚ ፕሬዚዳንት ኒል ፖርትኖው ደግሞ፣ ሙዚቃ ህዝብን አንድ በማድረግ ረገድ ያለውን ብርቱ ሃይል በተመለከተ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ሌሎች በሽልማት ስነስርዓቱ ላይ የታደሙ የአለማችን ድምጻውያንና ዝነኞችም በሙዚቃዎቻቸውና ባቀረቧቸው ንግግሮች፣ ፖለቲካዊ ቃና ያሏቸውን የተለያዩ መልዕክቶች ማስተላለፋቸው ተነግሯል፡፡

Read 1443 times