Sunday, 19 February 2017 00:00

ዘሪቱ ከበደ ሙዚቃ፣ ሃይማኖትና የህይወት ፍልስፍና

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(8 votes)

የጠፋሁት “ሰው የመሆን ዓላማዬን” ለማሳካት ነው ትላለች ሰው መሆን፣ሰው ለመውደድ መሰራት ማለት  ነው   
             ራሴን በማንኛውም ሙያ እንደሚያገለግል ሰው፣ የማሰብ ነጻነት ተቀዳጅቻለሁ!

      ከመድረክም ሆነ ከሚዲያ ጠፍታ የከረመችው ተወዳጇ ድምጻዊት ዘሪቱ ከበደ፤ ዛሬ ምሽት በኢንተርኮንትኔንታል ሆቴል በሚካሄደው “ጊዜ” የተሰኘ ኮንሰርት ላይ ታቀነቅናለች። ጆርካ ኤቨንትና ዳኒ ዴቪስ
በጋራ ባዘጋጁት በዚህ ኮንሰርት ላይ የትዝታው ንጉስ፣ አንጋፋው ድምጻዊ ማህሙድ አህመድና ወጣቱ ድምጻዊ ሳሚ ዳንም ስራዎቻቸውን ያቀርባሉ ተብሏል፡፡ ለመሆኑ ድምጻዊቷ ዘሪቱ፤ የት ጠፍታ ከረመች? አልበም ስትሰራ ወይስ አዲስ ፊልም ስትጽፍ? ምክንያቷ ሁለቱም አይደሉም። ከእነዚህ ከሁለቱም ለሚልቅ ጉዳይ ነው የጠፋሁት ትላለች። ድምጻዊቷ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ጋር ባደረገችው አስደማሚ ቃለ-ምልልስ፤ ስለ ሙያዋ፣ ስለ ሃይማኖቷና ስለ እግዚአብሔር፣ እንዲሁም ስለ እናትነቷና አጠቃላይ የህይወት ፍልስፍናዋን ትኩረት በሚስብ ቋንቋ
አውግታለች፡፡ አንብቧት!!

       በጣም ጠፍተሻል፤ በሰላም ነው? አዳዲስ ሙዚቃዎችም ሆነ ኮንሰርት እየሰራሽ አይደለም?
አዎ ጠፋ ብያለሁ፤ ሙዚቀኛ ብቻ ስላልሆንኩኝ ሌሎች ነገሮች ላይ ትኩረት ማድረግ አለብኝ ብዬ ነው የጠፋሁት፡፡
ሌሎች ነገሮች ስትይ --- ከሙዚቃ ሌላ?
በዋናነት ራሴ ላይ ነው ትኩረት አድርጌ የነበረው፤ የአላማ ማስተካከያ ስራ ላይ ነበርኩ፡፡ ዓላማዬ ሰው መሆን ሆነና ሰው መሆን ፈለግኩኝ፡፡
‹‹ሰው መሆን›› የሚለውን ------ እስቲ በደንብ አብራሪልኝ?
እንግዲህ ሰው መሆን ብዙ ነገር ነው። አንድ ሰው ሰው ሲሆን፣ ሰውን መውደድ--- ከልብ መውደድ፣ ከዚያም ማገልገል ይከተላል፡፡ ከማገልገል በፊት ግን መስተካከል፣ ራስን ማየትና መፈተሽ ይጠይቃል፡፡ እርግጥ ሰው የመሆንን መንገድ የጀመርኩት በቅርብ ላይሆን ይችላል፤ ነገር ግን በተለያዩ አጋጣሚዎች እያቋረጥኩት ወጥቻለሁ።  
ይህም በመሆኑ በማንነቴ ላይ ማለቅ የነበረበት ነገር እንዳያልቅ ከራሴ ላይ ጊዜ ወስጃለሁ፡፡ ይህ ሰው የመሆን ሂደት ሙሉ ለሙሉ ያልቃል ባይባልም፣ መሰረታዊ የሆነው ነገር እንዲያልቅ፣ በአንድ ልብ መጥፋትና ተስተካክሎ መምጣት ይሻላል በሚል ጠፍቼ ቆይቻለሁ፡፡
ሰው የመሆን ሂደቱ ----- ከሀይማኖት ጋር የተያያዘ ነው?
ለአንዳንድ ሰው ሀይማኖት ሊሆን ይችላል። በሀይማኖት ውስጥ ይሄ አስተሳሰብ አለ፡፡ ለእኔ በቃ ሰው የመሆን መንገድ ነው፡፡ ይህ ሰው የመሆን መንገድ ለእኔ እንደ ሀይማኖት አልገባኝም፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ሰውን በአምሳሉ በመልኩ እንደፈጠረና፣ ያ የፈጠረው ሰው በሀጢያት ምክንያት እንደተበላሸበት፣ በእግዚአብሔር ፈቃድ ውስጥ ሳይሆን በራሱ ፈቃድ ውስጥ እና በአላስፈላጊ ድምጾች መታለል ውስጥ የተበላሸው ሰው እንደገና ሰው እንዲሆን ምሳሌ ሆኖ በመጣው በኢየሱስ መንገድ ውስጥ ሰው ሲገባ፣ ያ ነው ለእኔ ሰው የመሆን መንገድ። እግዚአብሔር ሲፈጥረን፣ ወደነበርንበት ኦሪጅናል ማንነት ለመመለስ ማለቴ ነው፣ እግዚአብሔር በአምሳሉ ሲፈጥረን፣ ሰው ፈልጎ ቤተሰብ ፈልጎ ነው፡፡ ያንን ትክክለኛ ሰውነት ለማግኘት ራስን ማጣት ያስፈልጋል፤ ራስን ማጣት ደግሞ ቀላል አይደለም፤ ምክንያቱም ነፍስ ስለምትተናነቅና የራስ ፈቃድ ጠንካራ ስለሆነ፣ ብዙ ውጣ ውረድ፣ ብዙ መፎረሽ አለው፡፡ ይሄ ነገር ብዙ ጊዜ ወስዷል፤ ተጀምሮ ቶሎ ባለማለቁ፣ በተለያየ ነገር ላይ ውጤታማ መሆን ሲገባኝ እንዳልሆን አድርጓል። ሆኖም ይህ ጉዞ የምፀፀትበት አይደለም። ለምን? ዝርዝር የሆነው ጉዞም በራሱ ብዙ ልምድ ይሰጣል፡፡ ይህ ሰው የመሆን መሰረታዊ ጉዞ እንዳለቀ፣ በዝግጅት ለማገልገል ተመልሻለሁ፡፡ ያው ቅድም እንዳልኩሽ ሰውን ለማገልገል ሰው መሆን ይቀድማል፡፡ ሰው መሆን፣ ሰው ለመውደድ መሰራት ማለት ነው፡፡ ሰው ወዳድ ለመሆን ደግሞ ራስ ወዳድ ከመሆን መቀነስ ማለት ነው። በራስ ዓለምና በራስ ጉዳይ ላይ ያለ ልክ በማተኮር ሳይታወቅ ራስ አምላኪ እስከመሆን በሚደርስ ጥፋት ውስጥ ልንመሰግ እንችላለን። ነገር ግን ቀሪው ዘመኔን የምጓዝበት አላማ፣ ሰው በመሆን ለመኖር ነው፣ ሰው በመሆን ለመቆየት ነው፤ ያ የሚሆነው ደግሞ በፍቅር ነው፤ እግዚአብሄርን በመውደድ፣ ሰዎችንና ራስን በመውደድ፡፡
ሰዎችን መውደድ ሲባል፣ እንደ ራስ መውደድና ለእኔ እንዲሆን የምፈልገውን ለሌሎች በማድረግ ማለት ነው፡፡ ይሄም በወሬና በሀሳብ ብቻ ሳይሆን በተግባርና በተሞክሮ በማድረግ እንድተጋ፣ መገኘት ያለብኝ ቦታ ላይ ነኝ ብዬ አስባለሁ፡፡ ይህን ያልኩሽን ካላሳካሁት በስተቀር የሚወጣኝም የማወጣውም ነገር ግማሽ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ባገኘሁት መንገድና የማንነት ግልፅነት ውስጥ ለማገልገል ዝግጁ ሆኜ ተመልሻለሁ ማለት ነው፡፡
እግዚአብሄርን ማገልገል ህዝብን ማገልገል ማለት ነው፤ እግዚአብሔርን መውደድ ሰውን መውደድ ነው። ሰውን የእውነት መውደድ፣ ሰው ሲያጨበጭብልኝም ሳያጨበጭብልኝም መውደድ ማለት ነው፡፡ በደስታውም በሀዘኑም፣ በሚያስፈልገው ሁሉ ሰውን ለመውደድ፣ ሰውን ለማገልገል፣ አሁን ዝግጁ ሆኛለሁ ብዬ ነው የማስበው፡፡ ምናልባት ይሄ ቀደም ብሎ በአንዳንድ ዜማዎቼ የተተነበየ ነው፡፡ ‹‹በጊዜ በዘመን›› የሚለው ዘፈን ውስጥ የተነበይኩትን፣ ሰው የመሆን ጉዞ ስጀምር  ነው የፃፍኩት፡፡
ይሄ “ሰው የመሆን ዓላማ” ያልሽውን ጉዞ ከተወጣሽና ከራስሽ ጋር “ስብሰባ ተቀምጠሽ” ከጨረስሽ በኋላ------በህይወትሽ ላይ የተቀዳጀሽው ለውጥ አለ?
ኦ….በፊት እኮ እኔ የለሁም ማለት ትችያለሽ (ሳ…..ቅ) የአሁኑ ሕይወቴ የተለየ ነው፤ያው ዞሮ ዞሮ ፍቅር ነው፡፡ ሰው በትክክል ሰው ሲሆን ሰው ወዳድ ነው የሚሆነው፡፡ ትልቁም ቁምነገር ሆኖ የሚያገኘው ፍቅርን ነው፤በዚያ ውስጥ ነፃነት ይመጣል፤በዚያ ውስጥ እውነትን ታገኛለሽ፤ በዚያ ውስጥ ፍርሃት ይጠፋል፤ አልባሌና እውነት ያልሆኑ ነገሮች ይጠፋሉ። በተለይ በእኛ ሙያ የመድረክ ሰው፣ የታይታ ሰው ስትሆኚ፣ ከሰው ወጣ ያልሽና የተለየሽ አድርጎ የሚያሳይሽ ወይም ያንን እንድታምኚ የሚያደርግሽ ነገር አለ፡፡ እኔ ከዚህ ባርነት ሁሉ ተላቅቄያለሁ፤ አርነት ወጥቼያለሁ። ራሴን እንደ ማንኛውምና በየትኛውም ሙያ እንደሚያገለግል ሰው የማሰብ ዕድል አግኝቻለሁ፡፡ ውሸት በሆነው፣ በጩኸት በጭብጨባው እየተዋጥን፣ ከትክክለኛው ማንነት እየወጣን፣ ወደ መጥፊያው መንገድ ከምንሄድበት ጉዞ ወጥቻለሁ፡፡ ዋናው ነገር ነፃ የመሆን፣ ሰው የመሆንና አፍቃሪ የመሆን ውጤት ነው፡፡ እግዚአብሔር ይመስገን፡፡
አንዳንዶች የጠፋሽበትን ምክንያት ከሀይማኖት መቀየር ጋር ያያይዙታል፡፡ የፕሮቴስታንት ሃይማኖት ተከታይ እንደሆንሽና የሙዚቃ ሙያ እንደተውሽ ሲወራም ቆይቷል፡፡ ሆኖም ዛሬ ኮንሰርት ልታቀርቢ ነው፡፡ ይሄ መቼም ለአንዳንዶች ትንሽ ግርታን መፍጠሩ አይቀርም፡፡ ፈቃድሽ ከሆነ-----የየትኛው ሀይማኖት ተከታይ እንደሆንሽ ልትነግሪኝ ትችያለሽ?
ቅድም ሰው መሆን ነው ዓላማዬ፤ሰው በመሆን ሰውን መውደድ---- ብዬሻለሁ፡፡ እኔ የየትኛውም ሀይማኖት አባል አይደለሁም፤ነገር ግን ከየትኛውም ሀይማኖት ጋር ህብረት ማድረግ እችላለሁ፤ፍቅር ሁሉንም አንድ ስለሚያደርግ ማለቴ ነው፡፡ ይህን የማደርገው ግን በኢየሱስ ክርስቶስ መሰረት ላይ ነው፡፡ ከምንም ነገር በፊት የእኔ ቀዳሚ (ፕራይመሪ) ማንነት የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀመዝሙርነት ነው፡፡ ለአንዳንድ ሰው ፕሮቴስታንትነት ሊመስል ይችላል፤ ግን አይደለሁም፡፡ ያ በሚያሟላው ነገር ላይ ላልገኝ እችላለሁ፡፡ እኔ የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታይ ነኝ። በቃሉ፣ በእውነቱ፣ በመንገዱና ለእኔ ባለው ዓላማ እከተለዋለሁ፤ አገለግለዋለሁ፡፡
በመፅሐፍ ቅዱስ በገላትያ ውስጥ “የአመፃ ፍሬዎች” ተብለው ከተገለጹት ውስጥ አንዱ ዘፈን ወይም መዝፈን ነው፡፡ እስከ አሁን የነገርሽኝንና ዘፈንን እንዴት ማስታረቅ ይቻላል?
ሰው ላይ የሚፈጠረውን ግራ መጋባት ማጣራት አልችልም፤ መኖር የምችለው በገባኝ ልክ ነው፡፡ እኔ የገባኝ ደግሞ እንደ ቃሉ እስከኖርኩ፣ እስካገለገልኩ ድረስ ማለትም በዘፈንም ይሁን በፊልም፣ በንግግርም ይሁን ልጆቼን ስመግብና ማንኛውንም ነገር ስከውን በትክክል እስካደረግሁት ድረስ በኢየሱስ ዘንድ ተቀባይነት አለው፡፡ አከራካሪ የሆኑ የመፅሀፍ ቅዱስ ቃሎች አሉ፤ ለእኔ አከራካሪነቱ አይታየኝም፤በተሻለ ብርሀን ውስጥ እንዳለሁ አምናለሁ፡፡ ባለፉት አመታት በጉዳዩ ላይ አጢኜ፣ ጠይቄ መልስ አግኝቻለሁ፡፡ የዘላለም ሕይወት ቦታዬን የሚያሳጣኝ ቢሆን ኖሮ፣ እንዲህ አይነት ድፍረት አልደፍርም ነበር፡፡ ዘፈን ሁሉ በደፈናው ልክ ነው ወይም ዘፈን ሁሉ በደፈናው ሀጢያት ነው የሚል መልዕክትም ለማስተላለፍ አልፈልግም፡፡ ነገር ግን እኔ አሁን የማደርገውን ነገር ላደርገው ነው፤ ክርክር ውስጥ ባልገባ ደስ ይለኛል። እንደገባኝና ዋነኛ “ኦዲየንሴ” በሆነው በፈጣሪዬ ፊት በትክክል መራመድ ነው የምፈልገው፡፡ ክርክሮቹ ያደክማሉ፤ ጊዜ ይፈጃሉም፤ ለዛም የተመደቡ ሰዎች አሉ ብዬ አምናለሁ፡፡ እኔ በተግባሩ ባገለግል ይሻላል ብዬ ነው የማምነው፡፡
ወደ ፊልም እንግባ፡፡ ሁለተኛው የጉማ አዋርድ ላይ ‹‹ቀሚስ የለበስኩ’ለት›› በተሰኘው ፊልምሽ ለሽልማት ደጋግመሽ ወደ መድረክ ተመላልሰሻል። ‹‹መባ›› የተሰኘው የቅድስት ይልማ ፊልም ላይም የዶክተር ገጸ-ባህሪ ተላብሰሽ ተውነሻል፡፡ ከዚያ በኋላ የፊልም ነገር እንዴት ነው? አዳዲስ ዘፈኖችስ እየጻፍሽ ነው---?
አዎ እፅፋለሁ፡፡ ፀሀፊነት የማይገታው ማንነት ስለሆነ ሀሳብም ፊልምም ይሁን ግጥምና ዜማ ከመፃፍ አልቦዝንም፡፡ ያው የማከማቻ ጊዜ አለ፤ የመልቀቂያ ጊዜም አለ፡፡ ፊልምን በተመለከተ ፕሮዱዩስ በማድረግና በፅሁፍ ሙሉ በሙሉ ባልመለስም፣ እንዳልሺው “መባ” ላይ ተውኛለሁ። ሌላም የተወንኩበት በቅርብ የሚወጣ ፊልም አለ፤ ይቀጥላል ደግሞ፡፡
ልጆችሽ እንዴት ናቸው? ማን ማን ይባላሉ? እድሜያቸውስ ስንት ደረሰ? የእናትነት ጉዞሽ የተዋጣለት ይመስልሻል?
ደህና ናቸው፡፡ ትልቁ ልጄ ክርስቲያን ላቃቸው 10 ዓመት ሆኖታል፡፡ ሁለተኛው መንግስቱ ላቃቸው ሰባት ተኩል ሆኖታል፡፡ ትንሹ ልጄ ፀሎት ላቃቸው አራት አመቱ ነው፡፡ ሁሉም በጣም ሰላም ናቸው። እናትነት የራሱን ጉዞ ተጉዟል፡፡ እናትነት ለእኔ እንደ ወረደ የገባኝ ነገር አይደለም፡፡ በእናትነት ጉዞው የሚቀድምና የሚከተለውን ማወቅ በራሱ ጊዜ ወስዷል፡፡
በቤትም በደጅም እንደምትፈለግ ሴት፣ የሚቀድምና የሚከተለውን ለማወቅና የዛን ጉዳይ እሴት ለመረዳት  (ለየትኛው ቀድማ እንደምትፈለግ፣ የትኛው ጋር ቀድማ መገኘት አለባት-- የሚለውን ለማወቅ----) እንዲሁም ለማመን በሚደረግ ጉዞ ውስጥም ነበርኩኝ፡፡ ከራስ ሲወጣ ለሰው መሆንን ስለሚጨምር፣ለልጆቼም በተሻለ ደረጃ እየሆንኩ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡
አባባሉ ትንሽ ሊያበሳጭ ይችላል-----አንዳንድ አርቲስቶች ሀይማኖትን መርጠው ዘፈን ከተው በኋላ እንደገና  ወደ ዘፈን ሲመለሱ፤‹‹ሲደላ ወደ ፈጣሪ፣ ሲቸግር ወደ አቀናባሪ›› የሚል ሽሙጥ ገጥሟቸዋል። አንቺስ ይሄ ሽሙጥ ያስፈራሽ ይሆን?
እኔ የለሁበትም፣ አይመለከተኝም፤ ምክንያቱም ሲደላም ሲከፋም ወደ ፈጣሪዬ ነኝ፤ ሁሌም ፈጣሪ ባለበት ነው የምገኘው፡፡ መድረክም ላይ መገኘት ሲኖርብኝ በፈጣሪዬ ውስጥ እገኛለሁ። የተከታይ አንዱ ባህሪ ይሄ ነው፡፡ ይሄ የሀሳብ ለውጥም አይደለም፤ ሲደላኝ ጠፍቼ ስቸገር አልመጣሁም፤ ስለዚህ በምንም መስፈርት ብትሄጂ አባባሉ እኔን አይመለከትም፡፡
ከጆርካ የአብረን እንስራ ጥያቄ ሲቀርብልሽ፣ አመነታሽ ወይስ በቶሎ ምላሽ ሰጠሽ?
ማመንታት ይኖራል፤ ከራሴ ጋር ጊዜ መውሰድ ነበረብኝ፤ ውስጤ ወደ መድረክ ለመመለስ ዝግጁ እየሆነ ነበር ብዬሻለሁ፤ ሰው የመሆን ጉዞ እያለቀ ነበረ፤ ሆኖም እንደከዚህ ቀደሙ ቶሎ መልስ አልሰጠሁም፤ አስቤበት ይዘው የመጡትን ሀሳብ አጢኜና አምኜበት ነው ለመስራት የወሰንኩት፡፡  
በዛሬው ኮንሰርት የአድናቂዎችሽ አቀባበል እንዴት ይመስልሻል?
ያው እኔ ከሀይስኩል ትዝታዬ እስከ አራስነቴ በፃፍኳቸው ሙዚቃዎቼ ስደመጥ ቆይቻለሁ። አሁንም ከልቤ ለመስራት በጉጉትና በፍቅር እየጠበቅኩ ነው፤ አድናቂዎቼ ይደሰታሉ ብዬ አምናለሁ፤ ምላሹ  ከዚያ በኋላ የሚመጣ ነው፡፡

Read 7567 times