Sunday, 19 February 2017 00:00

ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር አረጋ ይርዳው የምህንድስና ሳይንስ፣ የአመራር ዘይቤ፣ የሥራ ፍቅር

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(4 votes)

• ስለ”ኢትዮጵያናይዜሽን” ፋይዳ በስፋትና በጥልቀት ያብራራሉ---
            • አገር አደገች የሚባል ከሆነ ቀጣዩ ጥያቄ በምንና በማን የሚለው ነው
            • 100 ሚሊዮን ህዝብ ይዘን ሁልጊዜ በፈረንጅ ልንኖር አንችልም---
            • ወጣቱ ከተሳካለት እኮ አገሪቱም ያልፍላታል---

     ዶክተር አረጋ ይርዳው የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በመካኒካል ኢንጅነሪንግ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ያገኙ ሲሆን ከእንግሊዝ በአየር ትራንስፖርት ምህንድስና የማስተርስ ድግሪ፣ ከአሜሪካ በትምህርት አስተዳደር ዶክትሬታቸውን ተቀብለዋል፡፡ በስራ ዘመናቸው በመጀመርያ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በመምህርነት ለ6 ዓመት ያገለገሉ ሲሆን
ከዚያም በኢትዮጵያ አየር መንገድ በመሃንዲስነት ለአስር ዓመታት ሰርተዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ውጭ በአሜሪካ ካሊፎርንያ ግዛት ከኤሮስፔስና ከአቪዬሽን ጋር ዝምድና ባላቸው የሙያ ዘርፎች በምህንድስና ማኔጅመንትና በአመራር ሰጭነት ለ20 ዓመታት አገልግለዋል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰውም በሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ በዋና ስራ አስፈፃሚነት ሲሰሩ ሁለት አሰርት ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡ ዶ/ር አረጋ በተጨማሪ የዩኒቲ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት፤ የኢትዮጵያ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ቴክኒክ ሙያና ስልጠና ኢንስቲትዩት ማህበር ፕሬዝዳንት እንዲሁም የኢትዮጵያ ማእድን ማህበር ፕሬዝዳንት ሆነውም እያገለገሉ ናቸው፡፡ የአሜሪካው Center for Creative Leadership (CCL) ልዩ ሽልማትን በማግኘት ከአፍሪካ የመጀመሪያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ናቸው። የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ግሩም ሰይፉ፤ ዶ/ር አረጋ ይርዳውን በወልዲያ የስታዲየምና የስፖርት ማዕከል ግንባታ፣ በሥራ ባህልና በአመራር ዘይቤ እንዲሁም በ”ኢትዮጵያናይዜሽን” ሃሳባቸው ዙሪያ በስፋት አነጋግሯቸዋል፡፡ እነሆ፡-

    የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ግዙፍ ኩባንያዎች በወልዲያ ከተማ ከተገነባው ስታዲየምና የስፖርት ማዕከል በፊት በተመሳሳይ ፕሮጀክት በቂ ልምድ ነበራቸው?
በእርግጥ ሙሉ ስታዲየም የመስራት  ልምድ አልነበረንም፡፡ በብረታ ብረት መስክ ያለው ኮስፒ እንዲሁም በኮንስትራክሽን መስክ የተሰማራው ሁዳ ሪል እስቴት በስታዲየም ደረጃ ባይሆንም ለግንባታ አዲስ አልነበሩም፡፡ በሌሎች የግንባታ ስራዎች የዳበረ ልምድ ነበራቸው፡፡ ከስታዲየም ጋር በተያያዘ የተለየ ልምድ አለው ተብሎ ሊጠቀስ የሚችለው  አዲስ ጋዝ እና ፕላስቲክ ፋብሪካ ነው። የአዲስ አበባ ስታዲየም የፕላስቲክ ወንበሮችን በአገር ውስጥ አምርቶ እንደገጠመ ይታወቃል። ለስታዲየም ግንባታ ብለን የመሰረትነው አዲስ ኩባንያ የለም፡፡ የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ 10 ኩባንያዎች በአንድ ላይ ተቀናጅተው ለመስራት የቻሉበት ሙሉ የስታዲየም ፕሮጀክት የወልዲያው ሲሆን የመጀመርያውም ነው። ኩባንያዎቻችን በተለያዩ የመሰረተ ልማት መስኮች የነበራቸውን ልምድ ተጠቅመው፤ ጎን ለጎን አዳዲስ እውቀቶችና ተመክሮዎችን እየቀሰሙ፤ በስፖርት መሰረተ ልማት ከበፊቱ የተሻለ አቅም አዳብረዋል፡፡ የስታዲየሙና ስፖርት ማዕከሉ ፕሮጀክት፣ የቴክኖሎጂ ግሩፑ ወጣት ሰራተኞች ልምዳቸውንና እውቀታቸውን ያሳደጉበት፤ በአገሪቱ የስታዲየሞች ግንባታ ወደፊት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖራቸው ያስመሰከሩበት ነው፡፡
በአፍሪካ ደረጃ ማንኛውንም ግዙፍ ፕሮጀክት  ለመስራት ስታቅድ፤ ሦስት ቅድመ ሁኔታዎችን ማጤን ያስፈልጋል፡፡ አንደኛ፤ ፕሮጀክቱን በአብዛኛው ምናልባትም 80 እና 90 በመቶ በአገር ውስጥ አቅም መፈፀም ይቻላል የሚለው መነሻ ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ፤ ለፕሮጀክቱ የሚሆኑ ልዩ ልዩ ግብዓቶች በአገር ውስጥ ምንም አለመኖራቸውን ተገንዝበህ 90 በመቶ ከውጭ  በማስገባትና መገጣጠሙን ብቻ በማከናወን የምትወስንበት አቅጣጫ ነው፡፡ ሶስተኛው ደግሞ፤ ሁለቱን አማራጮች በማዋሃድ የምትሰራበት ይሆናል። በስታዲየሙና የስፖርት ማዕከሉ ግንባታ፣ ሚድሮክ የተከተለው የፕሮጀክት አፈፃፀም የመጀመርያውን ነው፡፡
በአጠቃላይ ፕሮጀክቱን የጀመርነው በአገር ውስጥ 90 በመቶ አቅም መኖሩን አገናዝበን ነው፡፡ ስለዚህም ኢትዮጵያ ውስጥ በስታዲየምና የስፖርት ማዕከል ግንባታ ፈር-ቀዳጅ መሆን እንዳለብን አምነን ተነሳን፡፡ እኔ በግሌ ከጅምሩ የነበረኝ እምነት፣ ፕሮጀክቱን ለመፈፀም ፈረንጅ አያስፈልገንም፤ ኢትዮጵያውያን አሉን፤ ሊገነቡት ይችላሉ የሚል ነበር፡፡
ከሁሉ አስቀድሞ ለፕሮጀክቱ ሙሉ አቅም ያላቸውን ወጣቶችን መቅጠር ነበረብን፡፡ ከዚያም የግንባታውን ዲዛይንና እቅድ በአዲስ መልክ አሻሽለን በመስራትና በማዘጋጀት፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የተወሰኑ ባለሙያዎችን በማሳተፍ አስገመገምነዋል። በቃ ባለሙያው ካለን እንሰራዋለን ብለን ገባንበት፡፡ ባሉን ባለሙያዎች ስንሰራ ደግሞ ስኬታማ ሳይሆን ቀርቶ ቢፈራርስ ከነበረው ስህተት ተምረን እንደገና እንገነባዋለን ነበር ያልነው፡፡ አንድ ምሳሌ ብጠቅስልህስ… የአሜሪካው ጎልደን ጌት ብሪጅ አሁን ያለው፣ ለሁለተኛ ጊዜ የተገነባ መሆኑን ታውቃለህ፡፡ የመጀመርያው ግንባታ በነፋስ ፈራርሶ በድጋሚ ተሰራ፡፡ ይህ ድልድይ ዛሬ እድሜ ጠገብ ለመሆን የበቃው ከስህተታቸው ተምረው ስለገነቡት ነው፡፡
ከመነሻው የግንባታዎቹ ግብዓቶች 90 በመቶ በአገር ውስጥ ሊገኙና ሊሰሩ ይችላሉ የሚል እምነት ነበረን። የስታዲየሙን ዙርያ ገብ ጣራ ስንሰራ ቆርቆሮዎችን ያመረትን ቢሆንም፤ ከውጭ አገር ‹‹ፕሌቶች››ን አስገብተናል፡፡ ዲዛይን አድርገን ለክተን፤ ቆራርጠን፤ በይደን የገጠምናቸው ግን በራሳችን ነው። ከኮንስትራክሽን ጋር በቀጥታ የሚያያዙ ግብዓቶችን በተመለከተ--- እንደ ድንጋይ፤ አሸዋ፤ ሲሚንቶ፤ ጠጠር---- በአገር ውስጥ በተሟላ ሁኔታ ስለሚገኙ ብዙ አልተቸገርንም፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ የመብራት እቃዎች ለምሳሌ እንደ አምፑል የመሳሰሉት በምንፈልገው የጥራት ደረጃ አይመረቱም፡፡ ስለሆነም ከውጭ አገር የተመረተውን ገዝቶ ማስገባት ይሻላል በሚል የተወሰኑ ግዢዎች ብንፈፅምም፤ አጠቃላይ ስትራክቸሩን፤ አምፖሎቹን አቃፊዎችና የተዘረጉትን የኤሌክትሪክ ገመዶች ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ በማምረት ሰርተናቸዋል፡፡ የመብራቱን የብርሃን አቅም ለማመጣጠን በመጨረሻው ስራ ላይ ከውጭ ባለሙያዎች አስመጣን እንጂ የራሳችን ሙያተኞች ናቸው፡፡ ወደፊትም በዚህ መንገድ ሊሰራ እንደሚችል ተምሳሌት አድርገን ለማሳየት አስበን ነው፡፡
የስታዲየሙን ዙርያ ገብ ጣሪያ በጎበኘንበት ወቅት  ያስተዋልነው ልዩ የምህንድስና ብቃት ነበር፡፡ ጣራው በየትኛውም የስታዲየሙ ክፍል ተመልካችን የሚጋርድ  ቋሚ ሳይተከል የተገጠመ ነው፡፡ ሌላኛው ክቡር ትሪቡኑ ነው፡፡ በተለይ ለሚዲያ የሰጠው ትኩረት በመላው አገሪቱ እየተገነቡ ላሉት ስታዲየሞች ምሳሌ ሊሆን የሚችል ነው። እስቲ ስለ አሰራራቸው ይንገሩኝ?
 ጣሪያውን ለመስራት የተከተልነው የምህንድስና ሳይንስ ‹‹ካንቲሊቨር ዲዛይን›› ይባላል፡፡ ጣሪያውን ዲዛይን አድርገን የገጠምነው ወቅቱን በጠበቀ የቴክኖሎጂ እውቀት መስራት እንዳለበት ወስነን ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት በየትኛም የዓለም ክፍል የሚገነቡ  ስታዲየሞች ይህ አይነቱን ግንባታ ተግባራዊ አድርገውታል፡፡ ጣሪያውን የደገፈውን ስትራክቸር የሰራንበት ምህንድስና ‹‹ስፔስ ትረስት ዲዛይን›› ይሉታል፡፡ በምሳሌ ላስረዳህ እችላለሁ። የቦሌ ተርሚናልን ተመልክተኸዋል? ብዙ ብረቶች እንደ መረብ ተቀጣጥለውና ተገጣጥመው ከተሰሩ በኋላ ጣራውን ያለ አንዳች የቋሚ ድጋፍ ተሸክመውታል፡፡
ክቡር ትሪቡኑ፤ ምድር ቤት ያለውና ባለ ሶስት ፎቅ ዘመናዊ ህንፃ ነው፡፡ ከስታዲየሙና የስፖርት ማዕከሉ የተለያዩ ግንባታዎች፣ ክቡር ትሪቡኑ ቋሚና ከፍተኛ ግልጋሎት የሚሰጥ ነው ብለን በማሰባችን በከፍተኛ ደረጃ ገንብተነዋል፡፡ ክቡር ትሪቡኑ የአራት ቡድኖች ተጨዋቾችን  በተሟላ ሁኔታ እንዲያስተናግድ፤ ለሚዲያ  በቂ ቦታ የተዘጋጀለት እንዲሆን ፈልገን በፈር- ቀዳጅነት የሰራነው ነው፡፡ ለሚዲያው በክቡር ትሪቡኑ ትልቅ ትኩረት የሰጠነው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ማንኛውንም የስፖርት ሂደት ሚዲያው ካልዘገበው የእውቀትና የታሪክ ሽግግር ሊኖር አይችልም፡፡ እናም ትሪቡንን ስንሰራ ሚዲያ ለስፖርቱ ያለውን ሚና፣ እውቅና ለመስጠት አስበንብት ነው፡፡ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ጥራት ያለው የተሟላ ግንባታ ከተሰራለት፣ በጥራት ስራውን ይሰራል ብለን ስላመንም ነው፡፡
ክቡር ትሪቡኑ ተነቅሎ ቢወሰድ የትም ሊተከል የሚችል ነው፡፡ ለየትኛውም ስታዲየም እንዲሆን አድርገን ገንብተነዋል፡፡ 20ሺ፤ 30ሺ ሆነ 60ሺ ተመልካች ለሚያስተናግድ ስታዲየም ምሳሌ የሚሆን  ነው፡፡
የሼህ መሃመድ ሁሴን አሊ አልአሙዲ ስታዲየምና የስፖርት ማዕከል በተገቢው ቦታ ላይ ተገንብቷል ብለው ያስባሉ… ለወልዲያ ከተማ እድገትስ ምን አይነት አስተዋፅኦ ይኖረዋል?
የወልዲያን ከተማ እንደተመለከትካት መሰረተ ልማቶቿን ለማስፋፋት የነበራት ብቸኛ ቦታ አሁን ስታዲየም የገነባንበት አካባቢ  ነው፡፡ ከስታዲየሙ የክቡር ትሪቡን ህንፃ ፊት ለፊት የሚገኘው ሰፊ መሬት በከተማዋ የወደፊት ልማቶች ሊስፋፉበት የሚችል ነው፡፡ የከተማዋ ዘመናዊ  እድገት በስታዲየሙ ተጀምሮ፣ በዚያው ስፍራ እየተስፋፋ የሚሄድ ነው፡፡ ስታዲየምና የስፖርት ማዕከሉን ያካሄድንብት የግንባታ ጥራት በዙርያው ለሚሰሩ የተለያዩ መሰረተ-ልማቶች እንደ መለኪያ ሆኖ የሚያገለግልም ነው፡፡ በአጠቃላይ ስታዲየሙ ከተማዋን ያስተዋወቀ ‹‹ላንድ ማርክ›› ነው፡፡ ወልዲያ ከተማ መኖሯን ማንም ማወቅ አለበት በሚል ከስታዲየሙ ባሻገር በሚገኘው ተራራ ወልዲያ የሚል ፅሁፍ  አስቀምጠናል። ይህ ተምሳሌት እንዲሆን እንፈልጋለን፡፡ በየከተማዎቹ የሚያስፈልግ ነው፡፡ አሁን አዲስ አበባ ላይ እንጦጦን የመሰለ ተራራ እያለ ለምንድነው የማንፅፈው፡፡ ስለዚህ ጅምሩን እኛ ማሳየት ነበረብን፡፡
ፈጠራ ከመሐንዲሶች ይመጣል፡፡ በአንድ ቦታ ፈጠራቸውን ያሳዩታል፤ ሌላ ቀድቶ ሊሰራ ይችላል። እንዲህ አይነት ፈር-ቀዳጅ ተግባራትን ኮርጆ መስራት ነውር የለውም፡፡ ዓለምን የሚያሽከረክሩት የፈጠራ ችሎታ ያላቸው የተወሰኑ ሰዎች ናቸው። ሌላው ተከታይ ነው፡፡ የሚከተለው ደግሞ ጥሩ አድርጎ ከተከተለ እሰየው ነው፡፡ አንዳንዱ ፈጠራ የማይሰራው ስላልተመቸውና ስላልተሳካለት ነው። ምናልባት እውቀቱ ቢኖረው ገንዘቡ አይኖረውም። ገንዘቡ ቢኖረው እውቀቱ የለውም፡፡ በዚህ ረገድ የስታዲየሙና የስፖርት ማዕከሉ ግንባታ ባለሙያውና ባለሃብቱን በማቀናጀት የተጣጣመ ስራ የተከናወነበት ነው፡፡ የእኔና የሼህ መሃመድ ጥምረት ተምሳሌት እንደሚሆን የታየባት ከተማ ናት፤ ወልዲያ፡፡ ገንዘብ ያለውንና ትንሽ እውቀት ያለውን በምታጣምርበት ጊዜ የተሳካለት ስራ ይኖርሃል። ባለሃብት ነኝ፣ አለቃ ነኝ በሚል ያለ ሙያ ገብቶ ማስገደድ ተገቢ አይደለም፡፡ መደገፍ እንጂ፡፡
የአነስታይን ጭንቅላት ያለው ዓለምን የሚያስደንቅ ሃሳብ አፍልቆ፣ ፈጠራ ጠንስሶ ቢገኝ ያን ሃሳቡን ወደ ላብራቶሪ ወስዶ፣ ገንዘብ መድቦ የሚሰራ ባለሃብት ከሌለ ትርጉም የለውም፡፡ ግንባታው የመሃንዲሶች ሙያ ነው ከተባለ፣ሙያቸውን ማክበር ያስፈልጋል፡፡ በአገራችን የሚሰሩ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ይህን የሚያገናዝቡ መሆን አለባቸው፡፡ ባለሃብቶችና ነጋዴዎች ገንዘባቸውን ለማፍሰስ ፈቃደኛ ሆነው፣ በየፕሮጀክቱ ደግሞ ሙያተኞች ክብር ተሰጥቷቸው የሚሰሩ ከሆነ፣ ብዙ ለውጥ ማምጣት ይቻላል። ወልዲያ ይህን ምሳሌ ያደረግንባት ከተማ መሆኗ፣ እንደ ውጤት የሚጠቀስ ነው፡፡ በአጠቃላይ የስታዲየሙና የስፖርት ማዕከሉ ግንባታ የከተማዋን የወደፊት ተስፋና እድገት እንዳማከለ መታወቅ አለበት። ወደፊት በተራራ ከተከበበው የስታዲየሙ ስፍራ አቅራቢያ በሚገኝ ሲሪንካ በሚባል ቦታ አየር ማረፊያ መገንባት አለበት በሚል የከተማው ህዝብ ለመንግስት ጥያቄ አቅርቧል፡፡ ለጊዜው በኮምቦልቻ የሚገኘው አየር ማረፊያ ለስታዲየሙ አገልግሎት አጋዥ ነው፡፡ የሆቴልና የመንገድ ግንባታዎችም በከተማዋ አስተዳደርና በግል ባለሃብቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊሰሩ ይችላሉ፡፡ የባቡር መንገድም የሚያልፍባት ከተማ ሆናለች፡፡ በአጠቃላይ ስታዲየሙና የስፖርት ማዕከሉ የእድገት መስህብ ይሆናል ብለን እናምናለን፡፡
ለወልዲያ ከተማ ምን አይነት ለውጥ ይፈጥራል ብለህ ላነሳኸው ጥያቄ አንድ ወሳኝ ነገር ልገልፅ እፈልጋለሁ። የከተማውን ህዝብ እንግዳ ተቀባይነት የሚያሳድግ መሆኑ ነው፡፡ እንግዳ ወደ ከተማ ሲመጣ እንግዳነቱን ያውቃል፤ የሚያስተናግዱትንም ይታዘባል፡፡ ስለሆነም በዚህ ረገድ ህዝቡ የመስተንግዶ ባህሉን  የሚያጠናክር ነው፡፡ ስታዲየሞች በሚገነቡባቸው ስፍራዎች ላይ ብዙ ሁኔታዎችን ማገናዘብ ያስፈልጋል፡፡ የከተማውን አጠቃላይ እንቅስቃሴ ሊያውኩ በሚችሉ ስፍራዎች መገንባት ተገቢ አይሆንም፡፡ ነዋሪ ህዝብን ሰላም የማይሰጡ፤ የከተማዋን እንቅስቃሴ ግርግር ውስጥ የሚከቱ መሆን የለባቸውም፡፡ በአጠቃላይ  ግዙፍ መሰረተ ልማቶች በምንሰራበት ወቅት ወደፊት 50 እና 60 ዓመት አሻግሮ የሚያይ እቅድ ያስፈልጋል፡፡
በስታዲየሙና የስፖርት ማዕከሉ ግንባታ የላቁ የምህንድስና ደረጃዎችን እንዳሳለፋችሁበት ይነገራል፡፡ የምህንድስና ሙያ እንዲህ የሚያተጋና ልዩ የስራ ፍቅር የሚፈጥር ነው እንዴ?
መሐንዲስ ከሆንክ ማንኛውንም ግንባታ የምትሰራው በልዩ የሙያ ፍቅር ነው፡፡ አውሮፕላን የምትሰራው በምህንድስናው የሙያ ፍቅር ነው። የምህንድስና ሙያን የሚጠይቅ ማንኛውንም ፕሮጀክት በምትችለው አቅም መስራት መቻል አለብህ፡፡ እውቀቱ ኖሮህ መስራት የምትችልበት አቅም ስለሌለና ገና ስለሆነ ማንኛውንም ነገር በአግባቡ ለመስራት ሊያዳግትህ ይችላል፡፡ ሁሉም ላብራቶሪ አንድ አይነት አይደለም፡፡ አሜሪካ ብትሄድ በጥሩ ላብራቶሪ ልትሰራ ትችላለህ፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ  ሁሉም የማይሟላበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ ግን ያለህ ሙያና የብቃት ደረጃ ተመሳሳይ ነው፡፡ ስለዚህም ያንተ ጥበብ መሆን ያለበት ውስን አቅም ባለው ላብራቶሪ ስትሰራ፣ ያለህን ተጠቅመህ ምርጥ ውጤት ማግኘት ነው፡፡ ምህንድስና ዓለም አቀፍ ቋንቋ ነው፡፡ በየጊዜው ይሻሻላል፡፡ ያመራምራል። ባለሙያዎችን ያጨቃጭቃል። በጥቁረት በቅላት የሚለያይ ነገር የለውም፡፡ ምህንድስና በየትኛውም የዓለም ክፍል ምህንድስና ነው፡፡ በሳይንስ የምትመራ ከሆነ መናበቡ አስፈላጊ ነው፡፡  አሁን ውሃ H20 ነው ውህዱ፤ አሜሪካም ሆነ ወልዲያ ውሃ ያው ውሃ ነው።
ያለውን እውቀት መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ መኪና ከመስራት ኤንጂኑን አምጥቶ መገጣጠም ነው የሚቀለውና የሚያዋጣውም። ሞተርን በማምረት ልንደነቅ አይገባም፡፡ ሞተሩን ገዝተህ ትገጣጥማለህ እንጅ። ሞተር ማምረት እችላለሁ ብለህ የመቶ አመት ልምድ ካላቸው የዓለም ግዙፍ ኩባንያዎች ጋር ለመፎካከር ማሰብ ኪሳራ ነው፡፡ የመኪናውን የተለያዩ ክፍሎች ከተለያየ የዓለም ክፍል ገዝተህ አምጥተህ መገጣጠም ነው የሚሻለው፡፡ መገጣጠም ሙያ ነው፡፡ ቦይንግ አሁን አውሮፕላኑን ከተለያዩ ኩባንያዎች በሚገዛቸው የተለያዩ ክፍሎች ይገጣጥማል እንጂ ብቻውን አውሮፕላኑን አይሰራውም፡፡ የትኛውንም ምርት ሙሉ በሙሉ የመፍጠር አሰራር፣ ስራን ለማስተማር ካልሆነ በቀር ካልሰራሁት ብሎ መድከም ጥቅም የለውም፡፡ በከፍተኛ ልምድ፤ በወቅቱ ቴክኖሎጂና የምርት ደረጃ የተሰራ ነገር ገዝተህ መጠቀሙ ይሻላል፡፡ አገሪቷ ባላት አቅምና እውቀት ሊሰሩ የሚችሉ ብዙ ነገሮች ናቸው፡፡ የሌለን ነገር ቢኖር ደግሞ ከውጭ ማስገባት የሚሻልባቸው ሁኔታዎች አሉ፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ መስኮች ያሉ ወጣት ምሁራንን እንዴት ነው ማትጋት የምንችለው ብለን መጨነቅ ያስፈልጋል፡፡ የስታዲየምና የስፖርት ማዕከሉ በተመረቀበት ወቅት ባሰማሁት ንግግር፤ የቴክኖሎጂ ግሩፑ ወጣት ሰራተኞች ልምዳቸውንና እውቀታቸውን በመጠቀም በአገሪቱ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ከፍተኛ አስተዋፅኦ ስለሚኖራቸው መንግስት ትኩረት እንዲሰጣቸው ጥሪ ያቀረብኩትም ይህን በማሰብ ነው፡፡
የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ውበት ኢትዮጵያ ያላትን አውቀናል፡፡ ያሉብንን ውስንነቶች ተገንዝበናል፡፡ ያለንን የተፈጥሮ ሃብትና የሰው ሃይል አውቀናል፡፡ ስለዚህም እምነታችን ባለን አቅም ልክ ምርጥ ስራ ማከናወን እንደምንችል ነው፡፡ በቀጣይ እኛ ያከናወንናቸውን ተግባራት፣ ሌላው በቅብብሎሽ ሊቀጥለው ይችላል፡፡
እስቲ “ኢትዮጵያናይዜሽን” ስለሚሉት ሃሳብ ይንገሩኝ----?
በስታዲየሙና የስፖርት ማዕከሉ ግንባታ አስተዋልኩት የምትለው ልዩ የስራ ፍቅር፣ ከእኔ የግል አመለካከት ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ አየር መንገድ በምሰራበት ወቅት የመጀመርያውን ‹‹ኢትዮጵያናይዜሽን›› - ፈረንጅ ባለሙያዎችን በኢትዮጵያውያን የመተካት ስራ በ10 ዓመታት ውስጥ አከናውነናል፡፡ ከዚያ ቀጥሎ  በለገደምቢ የወርቅ ማዕድን መስራት ስንጀምር በወቅቱ ከ35 በላይ የፈረንጅ ባለሙያዎች ነበሩ፤ በ7 ዓመት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ኢትዮጵያውያንን በመተካት ለውጥ ፈጥረናል፡፡ ኢትዮጵያናይዜሽን ብቃትና እውቀት ላላቸው ዜጎች የስራ እድል የሚፈጠርበት፤ የእውቀት ሽግግር የሚገኝበት አሰራር ነው፡፡ ሁሉንም አይነት ሙያ ኢትዮጵያውያንም በፍቅርና ትጋት ሊሰሩት ይችላሉ ነው፡፡ ብዙ ኢትዮጵያውያን በእውቀትና በልምድ ሌላውን ዓለም ተሽከርክረናል፡፡ የተማርነው በአገራችን ነው፤ የተሰደድነው እውቀት ለመሸጥ ነበር፡፡ አካባቢው የተመቸ ከሆነልህና መሰረታዊ እውቀቱ ካለህ ወደ ኋላ የሚያስቀርህ የሚያሰራህ ባለመኖሩ ነው፡፡ ፈረንጅ በጣም ብልጣብልጥና ዘመናዊ ሆኖ ቢታይህ ስላደገበት ነው እንጂ በእውቀት እኩል እንደሆንክ ማሰብ አለብህ፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ጭንቀት ምንድነው…አንድ ነገር ሊሰራ ይፈለጋል፡፡ መነሻ ውጭ አገር ሄደው የተመለከቱት ይሆናል፡፡ ያ ነገር ካልመጣ ይባላል፡፡ እና መጥቶ እዚህ አይን አይኑን ለምን ያዩታል፡፡ ለምንድነው እዚሁ አገር ውስጥ ልንሰራ የማንችለው? ሰርተን ወይም አሻሽለን መቀየር የማንችለው…?
በትጋቴ አሁን ያለሁበት ደረጃ ስለደረስኩ በተለይ ወጣቶችን በማትጋት መስራት እፈልጋለሁ። ወጣቶቹን ደግሞ ካተጋሃቸው የእውቀት ችግር የለባቸውም፤ የሚሰሩ ናቸው፡፡ በስታዲየምና የስፖርት ማዕከሉ ግንባታ ከወጣት መሃንዲሶችና ሌሎች ባለሙያዎች ጋር ስሰራ፣ከጅምሩ የሙያ ፍቅሩና ትጋቱ ላይ እኔ ብሻልም ግንባታው ሲጋመስና 75 በመቶ ሲያልቅ፣ የእነሱ ትጋትና የሙያ ፍቅር መብለጡን አስተውያለሁ፡፡ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በስራ ዘመናችን ብዙ ተመክሮዎች አሉን፤ ብዙ ልምዶች ቀስመናል፡፡ እነዚያን እድሎች እዚህ አምጥተን ለወጣቱ በር የምንከፍትበት አመራር መስጠት አለብን፡፡
ኢትዮጵያናይዜሽን በጣም ወሳኝና አስፈላጊ ነው። ኢትዮጵያናይዜሽን በትምህርት፤ ኢትዮጵያናይዜሽን በሳይንስ፤ ኢትዮጵያናይዜሽን በኮንስትራሽን፤ ኢትዮጵያናይዜሽን በምህንድስና… አስፈላጊ ነው። 100 ሚሊዮን ህዝብ ይዘን ሁልጊዜ በፈረንጅ ልንኖር አንችልም፡፡ ሰው ሃብት ነው። ይህን የሰው ሃብት እንዴት ነው ተጠናክሮ ሊሰራ የሚችለው ነው፡፡ አገራችን በፈጣን እድገት የምትጓዝበት አቅጣጫ መሆኑ ታምኖበት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኢትዮጵያናይዜሽንን ቋንቋቸው ሊያደርጉት ይገባል። አገር አደገች የሚባል ከሆነ ቀጣዩ ጥያቄ በምንና በማን የሚለው ነው። በሁሉም መስክ በሚዲያ፤ በኮንስትራክሽኑ፤ በምህንድስናው፤ በኪነጥበቡ እድገቱ ተያይዞ መሄድ አለበት፡፡ በዚህ ሂደት ለአገር ውስጥ ምሁራንና ባለሙያዎች ክህሎቱን መፍጠር ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ እኮ ከ30 እና 40 በላይ ዩኒቨርስቲዎች መከፈታቸው እውቀት መኖሩን የሚያመልክት ነው። ለዚህ እውቀት በእኩል ደረጃ እድሎች መፈጠር አለባቸው፡፡ ወጣቶች አበላሽተው እንኳን የሚሰሩበት እድል ሊመቻችላቸው ያስፈልጋል። ፈረንጅ ታመጣለህ፤ አብረህ ኢትዮጵያውያኑን ትከትበታለህ፡፡ እውቀት እንዲያገኙ ታግዛቸዋለህ፡፡ ከዚያም በሙያቸው ፈጠራ እንዲኖራቸው ታተጋቸዋለህ፡፡ ኢትዮጵያናይዜሽን ትርጉሙ ይሄ ነው፡፡ በአገራችን በዚህ አቅጣጫ ለውጦች እየመጡ ናቸው፤ ግን መጠናከር አለባቸው፡፡
ሁሉንም ስራ አከብራለሁ፡፡ እግር ኳስ ብዙ ታሪክ ያለው ተወዳጅ ስፖርት ነው፡፡ ስፖርቱን ለሚወዱት ሁሉ ደግሞ መሃንዲሶች የሚፈለገውን ነገር በጥሩ ሁኔታ ሰርተው ማቅረብ አለባቸው፡፡ ሌላ ምሳሌ ልስጥህ። ጥሩ ሆቴል መኖሩ አይቀርም። ሆቴሉ መገንባቱ ካልቀረ ግን ጥሩ እና የተሟላ ዲዛይን ያስፈልገዋል፡፡ ሆቴሉን ለሚጠቀሙት ግን ሁሉንም ነገር እንዲኖራቸው የምትችለውን ጥረት አድርገህ መስራት ይጠበቅብሃል። አሁን እየተሻሻለ መጣ እንጂ እዚህ አገር ውስጥ ሆቴል ሲገነባ ግብዓት (Input) የተሟላ ቢሆንም ውጤት (out put) የሚጨነቅ እምብዛም አልነበረም፡፡ ሆቴል ቤት ሲገነባ ለመፀዳጃ ቤት የተሟላ አገልግሎት ዝቅተኛ ትኩረት የመስጠት መጥፎ ልማድ እታዘባለሁ። ለማንኛውም ስራ ስትቀጠር በተፈጥሮ ግብዓቱን ወስደህ ለውጤቱም እኩል ግምት መስጠት አለብህ። ሁለቱንም እኩል ማየት ያስፈልጋል፡፡
የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕን 24 ኩባንያዎችና ከ7ሺ በላይ ሰራተኞች በዋና ሥራ አስፈፃሚነት ሲመሩ 18 ዓመታት አስቆጥረዋል፡፡ ግሩፑ የጥረት ምሳሌ፤ ፈር-ቀዳጅና ጀምሮ የመጨረስ ባህል ያዳበረ እንደሆነ ይነገርለታል፡፡ ስለ አመራር ዘይቤዎ ሊነግሩኝ ይችላሉ?
በመጀመሪያ ሙያን ስራን ማክበር ያስፈልጋል። ስራ ለእኔ ከሁሉም በላይ ነው፡፡ ከቤተሰብ፤ ከሃይማኖት፤ ከአገርም-----ከሁሉም በላይ ነው፡፡ ሁሉም የሚፈጠሩት በስራ ነው፡፡ ያለ ስራ ምንም ነገር ህልውና የለውም፡፡ ስለዚህም ኢትዮጵያ ውስጥ ስራ ባህል መሆን አለበት። ፈረንጅ የሚበልጠን በዚህ ብቻ ነው፡፡ እነሱ ሲነሱ ስራን ባህላቸው አድርገው ነው፡፡ እኛስ ስንነሳ ስለ ስራ የምናወራው ተጨንቀን ነው፡፡ በወጣቱ ትውልድ ስራን ባህል ከማድረግ አኳያ ክፍተቶች አሉ፡፡ ቀደም ባለው ዘመን አገራችን ውስጥ ትልቅ ሆኖ ለመታየት ግዴታ መስራት አይጠበቅብህም፡፡ ሌላ ምክንያቶች ነበሩ። ከማህበረሰቡ መወለድ፤ መውረስ ትልቅ ሰው ያደርጋሉ። ያ ዘመን እየጠፋ አሁን በሁለቱ ጆሮዎች መካከል ባለው ጭንቅላትህና አዕምሮህ፣  ትልቅ የምትሆንበት ጊዜ እየተፈጠረ መጥቷል፡፡ ትልቅ ለመሆን ክህሎትና እውቀት  ያስፈልግሃል፡፡ በስራ ብቻ ነው ትልቅነትን የምትገነባው። ስራ ብቻ ነው ሰውን ከፍና ዝቅ የሚያደርገው፡፡ ስለዚህም ስራ ወርቅ ባህል መሆን አለበት፡፡ ጥሩ የሰራን ታደንቀዋለህ፤ ጥሩ ያልሰራውን አታደንቀውም። ስራን ወርቅ ባህል ለማድረግ ደግሞ ትጋትና ልዩ ስነምግባር ያስፈልጋል፡፡ ለስራ ተገዢ መሆን፤ ስራ መጀመርያና መጨረሻ እንደሚኖረው ማመን፡፡
ከሰራተኞቼ ጋር በየጊዜው በማደርጋቸው የውይይት መድረኮች ምሳሌ የማደርገውን ልንገርህ። እርግዝና ነው። በተፈጥሮ ከሄድን ይረገዛል ይወለዳል። መነሻ አለው፤ ከዚያም መጨረሻ። መሃከል ላይ የምታስተጓጉለው፤ የምታዘገየው ነገር የለም፡፡ ፕሮጀክትም እንደዚያ ነው፡፡ ሌላው የአለቅነት ተግባር ነው፡፡ ሁለት አይነት አለቅነት አለ፡፡ የመጀመርያ ከላይ ሆኖ በሁሉም የሃላፊነት መስኮች ብቁ ሰዎችን መድቦ አደራጅቶ፣ ለእነሱ ብቻ መመርያ በመስጠት የምታደርገው ነው፡፡ ሁለተኛው ላብራቶሪው የተዘጋጀ ሆኖ ካላየው፣ ገና በመዘጋጀት ላይ ከሆነ  ዝርዝር ጉዳይ ውስጥ ዘልቆ በመግባት የምትሰራው የአለቅነት ስራ ነው፡፡ ጉድለቶች ባሉባቸው ሁኔታዎች እየገባ መፍትሄዎችን እያስቀመጠና እያስተማረ የሚሰራው ነው። እኔ በምመራው ግሩፕ የምከተለውም ይህን አይነቱን አለቅነት ነው፡፡ ሲሰሩ አብሬ እገባና አግዛቸዋለሁ፡፡ ለእኛ አገር የሚሰራ ነው፡፡ ኋላ የተሰራውን ከመውቀስ ይልቅ አብሮ ሰርቶ ማደፋፈር ያስፈልጋል፡፡ ይህ የአመራር ስልት ብዙ ነገር መስዋዕት እንድታደርግ ይጠይቅሃል፡፡ የእኔ አይነቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ከሆንክ ጉራ አይኖርህም፤ ታች ካለው ሰራተኛ ጋር ወርደህ ስትሰራ ጉራህን ትተህ፣ ደስህ የሚል ሰው መሆን አለብህ፡፡ እንደ አባት፤ እንደ ባለሙያ፤ እንደ አለቃና እንደ ማንንም ጓደኛ ሆነህ የምትሰራበት አመራር ላይ አስተማሪ ነህ፤ አብሮ ሰራተኛ ነህ፤ ቆፋሪ ነህ፤ ዲዛይነር ነህ፤ የገበያ ባለሙያ ነህ፡፡ አመራርነት ጥበብ እንጂ ሳይንስ አይደለም፡፡ ስለሆነም በዚህ አቅጣጫ ብዙ አመራሮች ለመፍጠር፤እውቀት ለማሸጋገር ትችላለህ። በሰራተኞችህ ተቀባይነትን ለማግኘት የምትችለው በጉልበት አይደለም፡፡ በፒራሚዱ ጫፍ ላይ ሳይሆን መሰረቱ ላይ ሆነህ፣ ከላይ ታች እየተመላለስክ፣ ከሁሉም ሰራተኛህ ጋር ተቀራርበህ መስራት አለብህ፡፡ በአጠቃላይ የስራ ትልቅ ትንሽ የለውም፡፡ በስራ ባህላችን ሰዓት ማክበር አለብን፤ ውጤት ማምጣትን ትኩረት ልንሰጠውም ይገባል፡፡
ዶ/ር አረጋ፤ የማጠቃለያ ሃሳብ ወይም መልዕክት----
አገራችን የወጣት አገር ነች፡፡ ይህን  መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ አገራችን ብዙ ህዝብ አላት፡፡ ይህን የሰው ሃይል ሃብት ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ አገራችን ከሌሎች የዓለም አገራት የተለየ፤ ረጅምታሪክ ያለው ባህል አላት፡፡ ይህ ባህል ጠንካራና የሚመች ግን ዘመናዊና ወቅቱን የጠበቀ ሊሆን ነው የሚገባው። ከመስረቅና ከመቀማት ይልቅ እርዳኝ ብሎ የሚጠይቅ ሰው ያለባት ናት፤ኢትዮጵያ፡፡ ሙስና ‹‹ቲዮሪ›› የሆነባት አገር ናት፡፡ አገራችን በስራ ባህል ብዙ ልንማረው የምንችለው ነገር አላት፡፡ ገበሬው ጋ ያለው የስራ ባህል ነው፡፡ በገበሬው ማህበረሰብ ቅድመ ተከተሉን የጠበቀ የስራ ሂደት፣ የስራ ክፍፍል የሚከተል ነው፡፡ ገበሬው ሌት ተቀን መስራት ብቻ ሊያነቃንቀው እንደሚችል የሚያውቅ ነው፡፡ መላው ኢትዮጵያዊ የገበሬውን የስራ ባህል ሊከተለው ሊወርሰው ይገባል፡፡ ከገበሬው ትምህርት ለመቀበል ወጣቱ መትጋት አለበት፡፡ ወጣቱ አገሩን እያከበረ፤ ባህሉን እያወቀ፤እድሉ ተፈጥሮለት እየሰራ መሄድ ይኖርበታል፡፡ የሰራ የለፋ ስኬታማ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ወጣቱ በየተሰማራበት መስክ ውጤታማ ለመሆን የግሉን ጥረት ማድረግ ይኖርበታል። በሌሎች ደግሞ እገዛና ድጋፍ ያስፈልገዋል፡፡ ወጣቱ ከተሳካለት አገሪቱም ያልፍላታል፡፡

Read 6415 times