Sunday, 19 February 2017 00:00

የአፍሪካ አሜሪካውያን ወጎች

Written by  ከባየህ ኃይሉ ተሠማ (bayehhailu@gmail.com)
Rate this item
(1 Vote)

     የየካቲት ወር ወይም (February) የጥቁሮች ታሪክ ወር በመባል በየዓመቱ በአሜሪካ ውስጥ ይዘከራል፡፡ የዚህ ዝክር አመጣጥ ወደ ኋላ ዘጠና ዓመት የቆየ ታሪክ አለው፡፡ አከባበሩ የተፀነሰው ካርተር ውደሰን በተባለ የታሪክ ተመራማሪ ጥረትና ይኸው ሰው ባቋቋመው የጥቁሮች ሕይወትና ታሪክ ጥናት ማሕበር አማካይነት ሲሆን እ.ኤ.አ በየካቲት 1926 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ የጥቁሮች ታሪክ ሳምንትን አደራጀ፡፡ የየካቲት ወር ለዚህ ክብር የተመረጠበት ምክንያት የጥቁሮች ነጻነት መሠረት የነበረው 16ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት አብርሃም ሊንከን እና አፍሪካ አሜሪካዊው የሠብዓዊ መብት ተሟጋችና የጥቁሮች ነጻነት አርበኛ ፍሬድሪክ ዳግላስ የተወለዱበት ወር በመሆኑ ነበር፡፡
ይህ አከባበር ከተመሰረተ በኋላ በነበሩት 50 ዓመታት በአፍሪካ አሜሪካውያን ዘንድ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሰፊ ተቀባይነት ለማግኘት ችሏል፡፡ በተለይ የጥቁር አሜሪካውያን ሰብዓዊ መብቶች ንቅናቄ፣ ለበዓሉ ትኩረት ማግኘት ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል፡፡ በዓሉ በሰፊው የአሜሪካ ጥቁሮች ዘንድ ያለው ከበሬታ የአሜሪካ መንግሥት አትኩሮት እንዲሰጠው ስላስገደደው እ.ኤ.አ ከ1976 ዓ.ም ጀምሮ የጥቁሮች ታሪክ ሳምንት ወደ አፍሪካ አሜሪካውያን ታሪክ ወር ከፍ ለማለት ችሏል፡፡
ዛሬ የአፍሪካ አሜሪካውያን ታሪክ ወር በጥቁር አሜሪካውያን ጭቆና፣ ትግል፣ ድልና ፈተና ላይ አተኩሮ በመላዋ አሜሪካ በሚገኙ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ ሙዚየሞችና የጥበብ ማዕከላት የሚከበር ሲሆን የመገናኛ ብዙኃንም ሰፊ ሽፋን የሚሰጡት ታላቅ ዝክር ለመሆን በቅቷል፡፡ እኛም ይህንን ታሪካዊ ወር ምክንያት በማድረግ የአፍሪካ አሜሪካውያንን ሕይወትና ኑሮ የሚያንጸባርቁ ጥቂት ወጎችን እንመለከታለን፡፡
*   *   *
አንደበተ ርቱእ የነበረው አፍሪካ አሜሪካዊው የጥቁሮች ነጻነት ተሟጋች ፍሬድሪክ ዳግላስ፣ ባርነትን በመቃወም ባመቸው ሥፍራ የሚያደርገው ኃይለኛና ብሩህ ንግግር፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ አድማጮችን ለመሳብ ይችል ነበር፡፡ ይህ ሰው በተለይ ሮችስተር በተባለ ቦታ እ.ኤ.አ በ1852 ዓ.ም ያደረገውን ንግግር፣ ጥቁሮች ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተቀባበሉ ሲያስታውሱት ይኖራሉ፡፡
ፍሬድሪክ ዳግላስ በሮችስተር ውስጥ ንግግሩን ለመጀመር የተንደረደረው በየዓመቱ ሐምሌ 4 ቀን የሚከበረውን የአሜሪካ የነጻነት ቀን ጥያቄ ውስጥ በማስገባት ነበር፡፡ ‹‹ለአንድ ባሪያ የሐምሌ 4 ቀን የነጻነት በዓላችሁ ትርጉም ምንድን ነው? የምታከብሩት በዓል በማታለል የተሞላ ነው፤ የምትኩራሩበት ነጻነት ያልተቀደሰ ነው፤ ብሔራዊ ታላቅነታችሁ ከንቱ ነው..›› በማለት ባሮች ነጻነታቸውን እስካልተጎናጸፉ ድረስ የነጻነት በዓሉ የይስሙላ መሆኑን ተናገረ፡፡
ከንግግሩ አድማጮች መካከል ነጮቹ የሮችስተር አጥቢያ መጥምቃውያን ቤተክርስቲያን ቄስና ዲያቆን ተገኝተው ነበር፡፡
ዲያቆኑ በፍሬድሪክ ዳግላስ ንግግር ላይ አስተያየቱን ሲሰጥ፤ ‹‹ከአንድ ጥቁር የማይጠበቅ ታላቅ ንግግር ነው ያደረገው›› አለ፡፡
ቄሱ በማሽሟጠጥ ‹‹ግማሽ ወገኑ ከነጭ ዘር መሆኑን ብታውቅ በንግግሩ ይህንን ያህል አትደነቅም ነበር›› አሉ፡፡
ዲያቆኑ ግን በቄሱ ንግግር ሳይበገር ‹‹እስኪ ልብ በሉ! ግማሽ የጥቁር ዘር ያለው ሰው እንዲህ ያለ ንግግር ካደረገ ሙሉ በሙሉ ጥቁር ቢሆን ደግሞ ደግሞ እንዴት ያለ ኃያል ይሆን ነበር›› በማለት ቄሱን አፋቸውን አስያዛቸው።
*   *   *
ጆሲ የተባለች ጥቁሯ አሜሪካዊ እቤትዋ የደረሰችው እያለቀሰች ነበር፤ ‹‹ምንም ጥፋት ሳይገኝብኝ ፍርድ ቤት 50 ዶላር ቀጣኝ!›› ትላለች፡፡ አያቷ የተቀጣችበትን ምክንያት ጠየቋት፡፡ ‹‹አንድ ጠዋት በፒችትሪ ጎዳና ላይ ሁሉንም የትራፊክ ሕጎች  አክብሬ በእርጋታ ሳሽከረክር አንድ ነጭ የሚነዳው መኪና ከኋላዬ ገጨኝ፡፡ ጥፋቱ የኔ አለመሆኑን የመሰከሩ የዓይን እማኞች ነበሩ፡፡ ፍርድ ቤቱ ግን እኔን ጥፋተኛ አድርጎ ቀጣኝ›› በማለት ተናገረች፡፡
አያትዋ በጥሞና ሲሰሟት ቆዩና ‹‹ማልቀስሽን ትተሽ ይልቅ የምነግርሽን ታሪክ ስሚኝ›› አሏት፡፡
‹‹ከብዙ ዓመታት በፊት አንዲት የሰባች ዳክዬ ወደ ማዶ ያለውን ጫካ ለመጎብኘት ፈልጋ ሐይቁን ትቀዝፍ ነበር፡፡ ከውሃው ወጥታ ገና መሬት እንደነካች ከየት መጣ ሳይባል አንድ ቀበሮ አነቃት፡፡ ለካስ በጫካው ውስጥ አድፍጦ የእርሷን መምጣት ይጠባበቅ ኖሯል፡፡
“ጫካውም ሆነ ሐይቁ የኔ ክልል ነው፤ ድንበር ጥሰሽ በመግባትሽ ወንጀል ፈጽመሻል፡፡ ቅጣቱም በኔ መበላት ይሆናል” አላት፡፡ ነገር ግን ዳክዬዋ፣ “ጫካውም ሆነ ሐይቁ ያንተ ብቻ ሳይሆን የሁላችንም ነው፡፡ የተንቀሳቀስኩት የወል በሆነ ሥፍራ ውስጥ ስለሆነ የጣስኩት ድንበር የለም፤ ጉዳዩ በፍርድ ቤት እንዲታይልኝ እፈልጋለሁ” አለች፡፡
ወደ ዳኛ በመቅረቡ ቀበሮ ተስማማና፣ በአቅራቢያው ካለው ፍርድ ቤት ተያይዘው ሄዱ፡፡ ጉዳዩ ለፍርድ ቤቱ እንደ ቀረበ ግን ዳኛው፣ ዓቃቤ ሕጉና ፍርድ ቤቱ ያቆመላት ጠበቃ ሳይቀር ቀበሮዎች መሆናቸውን ዳክዬ አስተዋለች፡፡
‹‹ጉዳዩን ከሥር መሠረቱ መርምሬያለሁ” ያለው ዳኛ፤ ዳክዬን ጥፋተኛ ነሽ ሲል በየነባት፡፡ የፍርድ ውሳኔውም የሞት ቅጣት ሆነና ዳክዬዋን ሁሉም ቀበሮዎች ተቀራመቷት ይባላል››
በመጨረሻም የጆሲ አያት የልጁን ልጅ ‹‹ልብ በይ፤ ዳኞቹም፣ ዓቃቤ ሕጉም ሆነ ጠበቆቹ ቀበሮዎች በሆኑበት አገር እውነተኛ ፍትሕ ከፍርድ ቤቱ የሚጠብቅ እንደ ዳክዬዋ የዋህ የሆነ ብቻ ነው›› በማለት በነጮች የይስሙላ ፍርድ ቤት በተጣለባት ቅጣት እንዳትበሳጭ አጽናናት፡፡
*   *   *
የፌደራሉ መንግሥት አንድ ሹም፤ ጥቁር አሜሪካውያን በብዛት በሚኖሩበት በሉዊስያና ግዛት ገጠራማ ቀበሌዎች ለሥራ ጉዳይ ይጓዛል፡፡ በሄደበት ሁሉ ጥቁሮች ለዘመናት ሲያነሷቸው የኖሩትን መሠረታዊ ጥያቄዎችን እየደጋገመ ሲጠይቅ ጥቂት እንደ ሰነበተ በአስቸኳይ ወደ ዋሺንግተን ዲ.ሲ ከተማ እንዲመለስ የሚያዝ ቴሌግራም ደረሰው፡፡
ሻንጣዎቹን ከሸካከፈ በኋላ የሆቴሉን እንግዳ ተቀባይ ወደ ባቡር ጣቢያው እንዴት ለመሄድ እንደሚችል ጠየቃት፡፡ እርሷም ባቡሩ በዚያ ከተማ እንደማያልፍ ነግራው፣ እቃዎቹን ወደሚቀጥለው ከተማ የሆቴሉ ሰራተኞች ሊወስዱለት እንደሚችሉ ትጠቁመዋለች፡፡
ሹሙ የጠበቀው ቢያንስ አንድ የእቃ መጫኛ ያለው አሮጌ መኪና ይሰጡኛል ብሎ ነበር፡፡ ነገር ግን የሆቴሉ ሰራተኛ በበቅሎ የሚጎተት ጋሪ ይዞለት ብቅ አለ፡፡ በአስቸጋሪው አቧራማ መንገድ እየተንቀራፈፉ በመጓዝ ላይ ሳሉ ሹሙ በተሰጠው ኋላ ቀር አገልግሎት መበሳጨቱን አልሸሸገም፡፡ አንድ ሠዓት ወይም ከዚያ በላይ ከፈጀው የኤሊ ጉዞ በኋላ ሹሙ በንዴት ተናገረ፡-
‹‹እናንተ ሰዎች፤ (ጥቁሮችን ማለቱ ነው) ከድኅነት ኑሯችሁ አለመውጣታችሁ የሚያስደንቅ አይደለም፤ የባቡር ጣቢያውን ከከተማው ውስጥ የመስራት ሀሳብ በአእምሮአችሁ እንዴት ብልጭ አላለም?›› ሲል አማረረ፡፡
ጥቁሩ ባለጋሪ ጭንቅላቱን በአዎንታ እያነቃነቀ ‹‹እኛም አስበንበት ነበር ጌታዬ፤ በመጨረሻ ግን ጣቢያው እዚያው በሐዲዱ አጠገብ እንዲሆን ወሰንን›› አለው፡፡ (ሐዲዱ ከተማዋን ሳያቋርጥ እያለፈ ጣቢያው እንዴት ከተማ ውስጥ እንዲገነባልህ ፈለግህ እንደማለት)
*   *   *
ጊዜው እ.ኤ.አ የ1955 ዓ.ም የመጨረሻው ወር አጋማሽ ላይ ነበር፡፡ በአላባማ ግዛት በሞንትጎመሪ ከተማ በጥቁሮች የተቀጣጠለው በቆዳ ቀለም አድልዎ በሚያደርጉ አውቶብሶች ያለመጠቀም አድማ ሁለተኛ ሳምንቱን የያዘበት ወቅት ነበር፡፡ ጥቁሮችም ሆነ ነጮች በስሜት በሚነዱበት በዚህ ጊዜ ሁለቱም ወገኖች ‹‹ለወሳኙ ፍልሚያ›› ራሳቸውን ለማዘጋጀት የጦር መሳሪያ እየታጠቁ ነበር፡፡ በዚህ ቀውጢ ጊዜ ጥቁር አሜሪካውያንን ከስሜታዊነት እንዲርቁ የሚጠራው ብቸኛው ምክንያታዊ ድምጽ የሠላማዊ ትግል ሐዋርያው የማርቲን ሉተር ኪንግ ብቻ ነበር፡፡
‹‹ወገኖቼ! ድል ሊገኝ የሚችለው አውቶብሶችን ያለመጠቀም አድማው በሠላማዊ ሁኔታ ሲመራ ብቻ ነው፡፡ የጦር መሳሪያችሁን ወደ ቆሻሻ መጣያ ገንዳ ውስጥ እንድትወረውሩት እለምናችኋለሁ›› ሲል ጥቁር አሜሪካዊ ወንድሞቹን ተማጸነ፡፡
‹‹ሠላማዊ›› የተባለው የትግል ስልት ያልተዋጠለት አንዱ ጥቁር አሜሪካዊ ለማርቲን ሉተር ኪንግ ንግግር ምላሽ ሲሰጥ፤
‹‹መሣሪያዬን ገንዳ ልጥል ዝግጁ ነኝ ፤ግን የነጭ ሰው ዘር ነገር ቢፈልገኝ፣ከቆሻሻው ገንዳ ፈጥኜ ነው የምገኝ›› በማለት የልቡን ተናገረ፡፡
*   *   *
አፍሪካ አሜሪካዊው ወጣት ከሚያነበው ጋዜጣ ላይ ቀና አለና ማርቲን ሉተር ኪንግ፣ በዋይት ሐውስ ቤተ መንግሥት ለምሣ ግብዣ መጠራቱን ለአሮጊት አያቱ ነገራቸው፡፡
‹‹ጋባዡ ማነው ?›› አሉ አያት በመገረም
‹‹የአሜሪካው ፕሬዚደንት ሊንደን ጆንሰን!››
አሮጊቷ በመገረም ‹‹ፕሬዚዳንቱ የኛን ሰዎች (ጥቁሮችን) መውደዳቸውን እጠራጠራለሁ›› ካሉ በኋላ ትንሽ አሰብ አድርገው፣ ‹‹የተጋበዝኩት እኔ ብሆን ኖሮ ‹አመሠግናለሁ፤ አሁን ግን አልራበኝም› እላቸው ነበር›› በማለት ተናገሩ፡፡
*   *   *
በፊንላንድ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩት አፍሪካ አሜሪካዊው ካርል ሮዋን፣ ዋሺንግተን ከተማ ከተዘዋወሩ በኋላ በመጀመሪያው ሣምንት ላይ ያጋጠማቸውን ነገር ለወዳጆቻቸው ማጫወት ይወዱ ነበር ይባላል፡፡
አምባሳደሩ በዋሺንግተን ዲ.ሲ ከተማ ውስጥ ዘመነኛ ቤቶች ከተደረደሩበት የነጮች ሰፈር ካለው ቤታቸው ፊት ለፊት በሚገኘው የአትክልት ሥፍራ ላይ የበቀለውን ሣር በማጨጃ ማሽን ያስተካክላሉ፡፡ ይህንን የተመለከተ አንድ ነጭ ጎረቤታቸው ‹‹የኔ አትክልት ሥፍራ ላይ ያለው ሣር እንዲከረከምልኝ እፈልጋለሁ፤ ይህን ሣር ለማጨድ የቤቱ ባለቤት ምን ያህል ይከፍሉሃል?›› አላቸው፡፡
አምባሳደር ሮዋን በሰውየው ደፋር ንግግር ምንም ሳይበሳጩ ‹‹ግን ለአንተ ብቻ አንድ ምሥጢር ልንገርህ፤ አምስት ሣንቲም አይከፍሉኝም፡፡ ነገር ግን የዚህ ቤት እመቤት አብሬያቸው እንድተኛ ይፈቅዱልኛል›› ሲሉ የቤቱ ባለቤት እንጂ የጉልበት ሠራተኛ አለመሆናቸውን በጨዋ ደንብ በዘዴ ነገሩት፡፡
*   *   *
ጥቁሩ አሜሪካዊ ወጣት ኒውዮርክ ከሚገኘውና ሐርለም ከተባለው የአፍሪካ አሜሪካውያን ሠፈር ተነስቶ በአሮጌ መኪናው ወደ ካሊፎርኒያ ግዛት ይጓዛል፡፡ ረጅም መንገድ ከተጓዘ በኋላ ኒው ሜክሲኮ በተባለው ግዛት ውስጥ እንደ ደረሰ ረሐብና ድካም ሲጫጫነው ወደ አንድ ምግብ ቤት ጎራ ይላል፡፡
መንገደኛው ገና ከወንበር ላይ አረፍ ከማለቱ አስተናጋጁ ይመጣና ‹‹ውጣ! ጥቁሮችን እዚህ አናስተናግድም!›› ይለዋል፡፡ ወጣቱም የመጣው ይምጣ በማለት ‹‹ስማ! እኔ ሜክሲኮአዊ እንጂ ጥቁር አይደለሁም!›› ይላል፡፡
አስተናጋጁም ወደ ባንኮኒው በፍጥነት ሄዶ ከመሳቢያው ውስጥ ኮልት ሽጉጡን እያወጣ ‹‹በጣም ጥሩ! እንግዲህ በስፓኒሽ ቋንቋ ስታወራ መስማት እፈልጋለሁ!›› አለና አፈጠጠ፡፡ የዚህ ጊዜ ነገሩ እንዳላዋጣው የተረዳው አጅሬ ወደ በሩ በፍጥነት እየተራመደ ‹‹Adios!›› (ደህና ሁኑ) በማለት የሚያውቃትን ብቸኛ የስፓኒሽ ቃል ተናግሮ ወጣ ይባላል፡፡
*   *   *
አዛውንቱ ጥቁር አሜሪካዊ Black Panther የተሰኘው የጥቁሮች ራስን መከላከያ ማህበር አባል ስለነበረው ልጃቸው የሚከተለውን አስተያየት ሰጡ፡፡
‹‹የዚህ የBlack Panther ማህበር ሰዎች የሚሉትንና የሚያደርጉትን ሁሉ እደግፋለሁ አልልም፡፡ ይሁንና የማህበሩ መፈጠር ቢያንስ ነጮቹ በእኛ በጥቁሮች ላይ ስላላቸው አስተያየት ቁጥብና ጨዋ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡ አንድ ጠዋት ወደ ስራዬ ስሄድ የገጠመኝ ነገር ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ በሊፍት ውሥጥ አብሮኝ የተሳፈረ አንድ ነጭ የባንክ ባለሙያ የሊፍቱ ኦፕሬተር የሆነውን ጥቁር በትህትና ‹‹ወንድሜ የማያስቸግርህ ከሆነ፣ አምስተኛ ፎቅ ልትወስደኝ ትችላለህ?›› ሲል ሰማሁት፡፡
*   *   *
ዘመኑ በዘር ቀለም ላይ የተመሠረተ የአውቶብስ አገልግሎት የሚሰጥበት ነበር፡፡ ስለሆነም ነጮች በፊተኛው የአውቶብሱ ክፍል ሲቀመጡ ጥቁሮቹ የኋለኛውን ወንበር መያዝ ነበረባቸው፡፡ ድርጊቱ በርሚንግሃም በተባለ ከተማ ውስጥ የሚገኝ የትራንስፖርት ድርጅት በሚያሰማራው አውቶብስ ውሥጥ የተፈጸመ ነው፡፡ ባልተለመደ ሁኔታ ከአውቶብሱ የፊተኛው ክፍል ከተደረደሩ መቀመጫዎች መካከል በአንዱ ላይ ጥቁር አሜሪካዊው ወታደር ዩኒፎርሙን ግጥም አድርጎ ለብሶ ተቀምጧል። በሚቀጥለው ፌርማታ ላይ አንድ ነጭ ሰው ተሳፈረ፡፡ ዋጋውን ከከፈለ በኋላ ወደ ጥቁር አሜሪካዊው ወታደር ተጠግቶ ‹‹ከወንበሩ ተነሳልኝና ለጥቁሮች ከተመደበው ቦታ ላይ ከኋላ ተቀመጥ›› አለው፡፡ ወታደሩም በፍጥነት ‹‹ያለነው በጦር ሜዳ ቢሆን ኖሮ እኔን ወደ ኋላ አድርገህ አንተ እሣቱን ፊት ለፊት ትጋፈጥ ነበር?›› ብሎ ሲመልስለት፣ ነጩ ሰው ምንም ነገር ለመናገር አልቻለም ነበር፡፡
*   *   *
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ፈረንሣይን ከናዚ ጀርመን መንጋጋ ለማላቀቅ የዘመቱት ጥቁር አሜሪካውያን ወታደሮች፣ የፈረንሳይ ሕዝብ ባሳያቸው ክብርና ፍቅር በጣም ተደንቀዋል፡፡ ለብዙዎቹ ጥቁር ወታደሮች ይህ ወቅት ከነጭ ሰው ዘር ጋር እንደ እኩያ የታዩበት የመጀመሪያ አጋጣሚ ሊሆን በቅቷል፡፡ ሆኖም ጥቁሮችን መናቅና ማዋረድን ለለመዱት ነጭ የአሜሪካ የጦር መኮንኖች፣ ይህ የቆዳ ቀለም ያልገደበው የወንድማማችነት መንፈስ ክፉኛ ረበሻቸው፡፡ በዚህ የተነሳም ጥቁሮች ከነጮች ‹‹የተለዩ›› በመሆናቸው የቆዳቸው ቀለም በሚፈቅደው መሠረት መስተናገድ እንደሚኖርባቸው የሚጠይቅ ማዘዣ አወጡ፡፡
ማዘዣው የደረሰው አንድ የፈረንሳይ ወታደራዊ መኮንን፣ ለአሜሪካ ባለሥልጣናት መልስ ሲሰጥ ‹‹የቆዳቸው ቀለም ጥቁር የሆነውን ዜጎቻችሁን አስመልክታችሁ ካወጣችሁት ምዘና ጋር እኔም ለመስማማት እገደዳለሁ። እውነትም ጥቁር አሜሪካውያን ወታደሮቻችሁ ከጠበቅነው በላይ ‹‹የተለዩ›› መሆናቸውን አረጋግጠናል፡፡ ሆኖም እናንተ ነጮቹ ግን አብሮ ለመስራት የምታስቸግሩ ሰዎች ናችሁ›› በማለት ለአፍሪካ አሜሪካውያን ወታደሮች ያለውን አጋርነት አሳየ፡፡
መልካም ጊዜ!!

Read 2154 times