Sunday, 19 February 2017 00:00

ከተራ ፍላጎት በላይ የሆነ ምኞት ለኢትዮጵያ

Written by  ያሬድ አውግቸው
Rate this item
(0 votes)

የአሜሪካዎቹ ፌደራልና ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቶች  የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ  በሰባት  የኣለማችን ሀገራት ዜጎች ላይ  ያስተላለፉትን ወደ ሃገሪቱ ያለመግባት እገዳ ውድቅ  ማድረጋቸውን  የተለያዩ  አለም አቀፍ የዜና ማሰራጫዎች በቅርቡ ዘግበዋል፡፡ ፕሬዝደንቱ ጉዳዩን  ወደ ቀጣዩ ፍርድ ቤት  በይግባኝ እንደሚወስዱ ማስታወቃቸውም ተነግሯል፡፡ በተመሳሳይ የጎረቤታችን ኬንያ ፌደራል ፍርድ ቤት፣ የሃገሪቱ መንግስት የዳዳብ የስደተኞች መጠለያን ለመዝጋት ያስተላለፈውን ውሳኔ  ውድቅ ማድረጉም  ከቅርብ ጊዜ ዜናዎች ይጠቀሳል። ምንም እንኳን ውሳኔዎቹ በላይኛዎቹ ፍርድ ቤቶች ሊለወጡ የሚችሉበት እድል ያለ ቢሆንም ሂደቱ ግን  አስፈጻሚዎቹ ተቆጣጣሪ እንዳላቸው ያሳየናል፡፡ የዚህ ጽሁፍ አላማ ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ የተከለከሉ የሰባቱ ሃገራት ዜጎች አሊያም  የዳዳብ ስደተኞች መጠለያ ነዋሪ ሶማሊያውያን መብት መከበርን  ለማንሳት አይደለም። ይልቁኑም የሁለቱ ሃገራት የፍትህ ስርዓት የደረሰበትን የነጻነት ደረጃ ለማሳየትና ለሃገራችን  የፍትህ ስርዓት ተመሳሳይ ነጻነት በመመኘት እንጂ።
በኔ እምነት በተለይ የኬንያው የፍትህ ስርዓት  ብዙ ልንማርበት የሚገባ እንደሆነ ይሰማኛል። ጉዳዩን ልንማርበት ይገባል ለማለት ያስደፈረኝ ፍርድ  ቤቶቹ ውሳኔ ያስተላለፉበት ጉዳይ ውስብስብና የመንግስት መከራከሪያዎች የመከሰት እድላቸው ሰፊ በሆነባቸው ጉዳዮች መሆኑ ነው። ሁለቱ ሃገራት  በአለም አቀፍ አሸባሪ ተቋማት መዝገብ ላይ ካላቸው የቀዳሚ ኢላማነት ደረጃ አንጻር የሽብር ተግባራት  የመከሰት እድላቸው የእርግጠኛነት ደረጃ  ይደርሳል ለማለት ይቻላል።  ይህም የፍርድ ቤቶቹ ውሳኔዎች  መብትን በማስከበር የሚቆም ሳይሆን በሃገራቱ ላይ ከፍተኛ አደጋ ይዞ ሊመጣ የሚችል ያደርገዋል።  ለዚህም ነው ዶናልድ ትራምፕ የሽብር አደጋ ከተከሰተ ተጠያቂው  የሃገራቸው  የፌደራል ፍርድ ቤት መሆኑን ያስጠነቀቁት፡፡ አስገራሚው ጉዳይ የሁለቱም ሃገራት ፍርድ ቤቶች በዚህ አጣብቂኝ መሃል ቆመው  የሃገራቸውን   ብቻ ሳይሆን አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችን ጭምር ለማስከበር  ወደ ኋላ የማይል ነጻነት ያላቸው መሆኑ ነው።
የሃገራችን የፍትህ ስርዓት  በተግባር ያለበትን ነጻነት ለመናገር ጥናት የሚፈልግ መሆኑ ባያጠያይቅም ምኞቴ ግን  የሃገራችን የሲቪክ ማህበራትና ሌሎች የሚመለከታቸው ተቋማት በፍትህ ስርዓቱ ላይ እምነት ጥለው፣ የኬንያውን ያህል ክብደት ባላቸው ትልልቅ ጉዳዮችም ጭምር  የመንግስትን ከፍተኛ አካል በህግ ፊት መሞገት የሚያስችል ነጻነታቸውን ሲጠቀሙ መመልከት ነው። ለምሳሌ እንደ ኬንያው ውስብስብና ሰፊ ሪስክ /Risk/ ያላቸውን ጉዳዮች ትተን፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በስልጣን ዘመኑ ከሚያስተላልፋቸው ብዛት ያላቸው ውሳኔዎች መካከል ቢያንስ አንዱ እንዲሻሻል የፍርድ ቤት የክርክር መዝገብ የሚከፍቱ  የሲቪክ ማህበራት  ጉዳይ ላይ ፍርድ ቤቶች  ውሳኔ ሰጥተው፣ የነጻ ሚዲያው የትንታኔ  ርእስ ሲሆኑ መመልከት  ህዝቡ በፍትህ ስርዓቱ ላይ ያለውን መተማመን  ይጨምራል። ምክንያቱም የየትኛውም የአለማችን ሃገር ፕሬዝደንት፤ ጠቅላይ ሚኒስትር፤ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ወይም ተመሳሳይ ደረጃ ያለው አካል  እንደ አሜሪካና ኬንያ አስፈጻሚ አካላት፣ የሃገር ውስጥም ህጎችም ይሁን አለም አቀፍ ስምምነቶች  ሊጥሱ  የሚችሉበት ሁኔታ ይኖራል፡፡   
ሌላው ምሳሌ መንግስት  ከአለም አቀፍ ተቋማት ጋር ከሚዋዋላቸው ብዛት ያላቸው የብድር ስምምነቶች መካከል  ቢያንስ አንዱ አዋጪ ባለመሆኑ ሌላ አማራጭ ይፈለግለት ከሚል ሲቪክ ማህበር፣ አስፈጻሚው አካል የፍርድ ቤት ሙግት ሲገጥመው መመልከት  የሲቪክ ማህበራትን ሚና ከቃላት በላቀ ጥልቀት የሚያስተምር ሊሆንም ይችላል። መንግስት በታችኛው ፍርድ ቤት  የሚያካሂደው ክርክር ውድቅ ሆኖበት፣ ወደ ቀጣዩ  ፍርድ ቤት ጉዳዩን  ወስዶ ሲከራከር ማየትም እንዲሁ በፍትህ ስርአቱ ላይ ያለን የዜጎች እምነት ያሳድጋል። እነዚህን ሁሉ ምሳሌዎች ማንሳቴ መንግስት ውሳኔዎቹ ውድቅ ሲሆኑበት  ለመመልከት ካለ ተራ ፍላጎት የመነጨ አይደለም። ይልቁንም  አስፈጻሚው አካል ውሳኔዎቹን በገለልተኝነት የሚፈትሽለት አካል መኖሩ  ለራሱም  ስለሚጠቅመው እንጂ።  ምክንያቱም አስፈጻሚው አካል  ህገ መንግስቱን& ሌሎች ሃገራዊ ህጎች ወይም አለም አቀፍ  ስምምነቶችን ሊጥስ የሚችልበት ሁኔታ  ይኖራልና::
ለማጠቃለል፤ የሲቪክ ማህበራትና የፍርድ ቤቶች ነጻነት መጠናከር ለሰብኣዊ መብቶች  መከበር& ለብልሹ አሰራሮች መወገድ& ሃብትን በተሻለ ለመጠቀም& እንዲሁም የመጭውን ትውልድ መብቶች ከማስጠበቅ ሀላፊነት አንጻር የሁላችንንም በተለይ ደግሞ የመንግስትን  ቁርጠኝነት ይፈልጋል።  

Read 1303 times