Print this page
Sunday, 19 February 2017 00:00

“ለአንድዬ ግንባራችንን እናስመታ…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(6 votes)

   እንዴት ሰነበታችሁሳ!
መቼም ዛሬና ነገ… አለ አይደል…አዲስ አበባ ልክ…
“ስማ፣ ስማ ተስማማ፣ ላልሰማ አሰማ፡፡ የምጽአት ቀን እየቀረበ ስለሆነ የቻልከውን ያህል በልተህ የቻልከውን ያህል ጠጣ…”ምናምን የተባለ ነው የሚመስለው፡፡ ለሦስቱ ነይ፣ ነይ እንኳን ያ ሁሉ ግፊያ!
የምር ግን…መቼም የእኛ ነገር እኮ… አለ አይደል…እርስ በእርስ ተሸዋውደን ኖረን በመጨረሻ ሲጠፋ አንድዬን ለመሸወድ እየሞከርን ያለ ነው የሚመስለው፡፡ ልክ እኮ…መንግሥተ ሰማያት ለመግባት… አለ አይደል… “ለአንድዬ ግንባራችንን እናስመታ” የተባባልን ነው የሚመስለው!
ሰውየው ቢቸግረው ምን አለ አሉ መሰላችሁ… “ሁሉም ሰው መንግሥተ ሰማያት መግባት ይፈልጋል፣ ማንም ሰው ግን መሞት አይፈልግም፡፡”
እነ እንትና፣ እስቲ ይሄ ገና ‘ትናንት’ ገብቶ፣ ‘ዛሬ’ የተጋመሰው ዓመት ከገባ ስንት ጊዜ ሥጋ እንደበላን እንተሳሰብ… ለምን ይዋሻል፣ የእኔ ከሦስት ባያንስም ከአምስት አይበልጥም፡፡
እናላችሁ…ሁሉም ነገር ለእይታ ሲሆን አሪፍ አይደለም፡፡
ከታላቁ መጽሐፍ ለመዋስ ያህል…
“ስጦሙም እንደ ግብዞች አትጠውልጉ፣ ለሰዎች እንደ ጾመኛ ሊታዩ ፊታቸውን ያጠፋሉና፤ እውነት እላችኋለሁ ዋጋቸውን ተቀብለዋል፡፡ አንተ ግን ስትጦም በስውር ላለው አባትህ እንጂ እንደ ጦመኛ ለሰዎች እንዳትታይ ራስህን ተቀባ፣ ፊትህንም ታጠብ፣ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ያስረክብሀል፡፡”
ታዲያላችሁ…ይሄ ሁሉ “ጧሚ ነኝ፣ እዩኝማ…” አይነት ‘ከማን አንሼ’ ከብዙ ነገር ወደ ኋላ ያስቀረን ይመስለኛል፡፡ በየክትፎ ቤቱ፣ በየቁርጥ ቤቱ፣ በየሬስቱራንቱ… ያለው ‘የቀበሌ ህብረት ሱቅ ሰልፍ’ ግርም የሚል ነው፡፡
እናማ… “ለአንድዬ ግንባራችንን እናስመታ…” አሪፍ አይደለም፡፡
እኔ የምለው…የሬስቱራንት ነገር ከተነሳ አይቀር፣ ይቺን ስሙኝማ፡፡ እዚህ አገር ግዴለሽነት እንዴት እንደበዛ የምታውቁት እንዴት መሰላችሁ… ምን የመሰለው ሬስቱራንት ውስጥ ያዘዛችሁት ምግብ ተከትሎ ምን ቢመጣ ጥሩ ነው… እግራችሁ ስር የስፔንን ተዋጊ ኮርማዎች የሚያስንቅ ድመት ብቅ ብሎ ይገላምጣችኋል!
“እኔ እዚህ ቅንጣቢ የሚጥልልኝ አጥቻለሁ አንተ ገንዘብ አለህና አሮስቶ ስትበላ የድመት አምላክ አይታዘብህም!” ብሎ የሚዝትባችሁ ነው የሚመስለው፡፡…ነው ወይስ ሼፉ እንዲሰልል ልኮት ነው! ቂ…ቂ…ቂ…
አሳላፊዋ ሳህኑን አንዴ ‘ከወረወረችላችሁ’ በኋላ አንዴ ብቅ ሳትል ድመቱ ስምንት ጊዜ ይሽከረከርላችኋል፡፡ የውሻን ጆሮ ይድፈንልንማ!  ቂ…ቂ…ቂ…
እግረ መንገዴን…ምን መሰላችሁ፣ በአንድ በኩል…እንኳንም ጾም ደረሰ የሚያሰኝ ነገር አለ፡፡ ልክ ነዋ…አንዳንድ ምግብ ቤቶች እኮ የሚገርሙ ናቸው። እናማ…ሥጋ ነክ ነገር መኖሩን፣ ወይንም ከዕለታት አንድ ቀን ሥጋ የሚባል ነገር የነበረ መሆኑን ለማወቅ “ሜኑ አምጣልኝ…” “ምን፣ ምን አላችሁ?” ምናምን ማለት አያስፈልግም…ሽታው ይጠራችኋላ!
እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ይቺን ሁለት ወር… ምን አይነት ምግብ እንድምንወድ የሚጠይቅ ከመጣ…አለ አይደል…የምንለው አናጣም፡፡ ልክ ነዋ…
“እኔ ከምግብ ሁሉ ቁርጥና ክትፎ ነፍሴ ነው…” እንላለና! አሀ…. “ና አንድ ኪሎ ለሁለትም ቢሆን እንትና ቤት ቁርጥ እንብላ…” ብሎ ነገር አይኖርማ። ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል እውነት ለመናገር…
“ከምግብ ሁሉ የምትወደው ምንድነው?” ብሎ መጠየቅ አሪፍ አይደለም፡፡ ያውም እዚቹ እኛ አገር! ብዙ የምግብ ምርጫ ያለን ይመስል እንደዛ ስንጠየቅ ሆድ ይብሰናላ! አብዛኞቹን ምግቦች… አይደለም ጣእማቸውን ስማቸውን እንኳን በማናውቅበት… እንዲህ አይነት ጥያቄ ይታሰብበት፡፡
“አዘውትረህ የምትበላው ምግብ ምንድነው?”
“እንጀራ በሹሮ…
“ሌላስ?”
“ሌላ ምን?”
“ሌላ የምታዘወትረው ምግብ…”
“ከእንጀራና ከሹሮ ሌላ አይነት ምግብ አለ እንዴ!”
“እንዲህ የምንል ብዙ እንደምንኖር ግንዛቤ ይግባልንማ!
እናላችሁ…የዛሬና የነገን ግፊያ ስታዩ… “ሁሉም ነገር ጣራ በነካበት ዘመን ሰዉ ከየት ነው ገንዘቡን የሚያመጣው!” ትላላችሁ፡፡ አሀ…ወደ አማሪካን የምንልከው የ“ደግፉኝ” ጥያቄም እኮ እየተለወጠ ነው፡፡
“ግዴለም…ሥጋውም፣ ጮማውም ይቅርብኝ፣ አሁን የምቆረጥመው ጥሬ እንኳ እየቸገረኝ  አለሁልህ።
አንተንም ብዙ ገንዘብ ላክልኝ ብዬ አላስቸግርህም። እናንተም እንዳልደላችሁ ሰምቻለሁ፡፡ አንድ ሺህ ዶላር ብቻ ብትልክልኝ እንደምንም አብቃቃታለሁ፡፡”
አሁን በዘንድሮ ኑሮ አንድ ሺህ ዶላር ለሽምብር በጨው እንኳን ትበቃለች! ቂ...ቂ…ቂ…
ለነገሩ ስንጋብዝም ብልጥ እየሆንን… አለ አይደል… ‘እንዳያማህ ጥራው፣ እንዳይበላ ግፋው’ የሚሏትን ስትራቴጂ እየተካንንባት ነዋ!
የሆነ እኮ አምስት ሰው እንጠራና ሁለት በያይነቱ አዘን…
“ብሉ እንጂ! በቃኝ ብሎ ነገር የለም፣ ይሄ ምግብ ካላለቀ ንቅንቅ የለም…” እንላለን፡፡ እኛ እኮ ተናግረን እስክንጨርስ ምግቡ አልቋል!
ስሙኝማ…አንዱ ሰውዬ እንዲህ አለ አሉ…
“”ትናንት ማታ ሌባ ቤቴ ገብቶ ገንዘብ ያለበትን ቦታ ሲፈልግ ነበር፡፡
“እና ምን አደረግህ?”
“ተነሳሁና አብሬው መፈለግ ጀመርኳ!”
አሪፍ አይደል! ከዚህ የባሰ መቸሰት ከየት ይመጣል!
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…እኔ የምለው ሰሞኑን ሰዋችን በየስብሰባ አዳራሹ እየተወያየ (‘እየተጠዛጣዘ’ የሚሉ እንዳሉ ልብ ይባልማ!) ነው አሉ፡፡ እናላችሁ…አንዳንድ ቦታ እጅግ የወረደ የእርስ በእርስ ስድድብ አይነት ነገር ነበር አሉ፡፡ የምር ግን…አለ አይደል…  መቼ ነው ሳንሰዳደብ፣ ሳንወነጃጀል በሰላም የምንነጋገረው፡፡ (ነገር ተካሮ ‘ቡጢ ደረጃ እንዳይደርስ’ እንመኛለን! ቂ…ቂ…ቂ…)
እናማ…አተካሮ ከበዛበት ስብሰባ ይሰውራችሁማ!
ሰውየው ረጅም ንግግር አደረገላችሁ፡፡ ቁጥር ሲጠራ፣ ይሄን ያህል ፐርሰንት አደገ፣ ተመነጠቀ እያለ፣ ካለፈው ዓመት በምናምን መቶኛ አደገ… ቅብጥርስዮ ሲል ቆየና አዳራሹ በጭብጨባ ተናጋ ብሎ ቀና ሲል ምን ቢያይ ጥሩ ነው…ተሰብሳቢው በሙሉ ለሽ ብሏል!
ከሀሳብ ይልቅ ዘለፋ፣ ከመተራረም ይልቅ መወነጃጀል፣ ሞራል ከመገነባባት ይልቅ ሞራል ማንኮታኮት ከበዛባቸው ስብሰባዎች፣ አይደለም ተሰብሳቢው ተናጋሪው ራሱ ምን እንደሚል የማያውቅበት ስብሰባ ሳይሻል ይቀራል!
ተናጋሪው ተሰብሳቢዎቹን… “እባካችሁ ጆሮዎቻችሁን አውሱኝ…” ይላል፡፡ ከተሰብሳቢዎቺ አንዱ ምን ቢል ጥሩ ነው…
“ተናግረህ እስክትጨርስ ድረስ የእኔን ጆሮ መዋስ ትችላለህ፡፡” እሱስ ማን ‘አውሱኝ’ በል አለው!
ለጿሚዎች…የ‘እዩኝ፣ እዩኝ’ እና ‘በነጻ የሚታይ ኤግዚብሽን’ አይነት ሳይሆን…አለ አይደል… እውነተኛ የጾም ወራት ይሁንላችሁማ!
“እናንተ አሁን የምትራቡ ብፁዓን ናችሁ፣ ትስቃላችሁና፡፡” ተብሏል፡፡    
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 4959 times