Sunday, 19 February 2017 00:00

የታሪክ ባለውለታው ፕ/ር ፓንክረስ ሰኞ በብሄራዊ ክብር ይሸኛሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(10 votes)

    በ90 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት የኢትዮጵያ ታሪክ ተመራማሪው ፕ/ር ሪቻርድ ፓንክረስት የቀብር ሥነ ስርዓት የፊታችን ሰኞ በመንበረ ፀባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ እንደሚፈፀም ታውቋል፡፡
የአንጋፋው የኢትዮጵያ ታሪክ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ፓንክረስት አስከሬን የክብር አሸኛኘት እንደሚደረግለት የተገለፀ ሲሆን የሽኝት ስነ ስርአቱን የኢትዮጵያ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር እንደሚያስተባብርና በስነ ስርአቱ ላይም ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት እንደሚገኙ ተጠቁሟል፡፡
“መንግስት ለሀገር ያበረከቱትን ውለታ ከግምት በማስገባት ክብሩ ከፍ ባለ ደረጃ ሽኝታቸው እንዲከናወን ጥረት እየተደረገ ነው” ያሉት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የህዝብና አለማቀፍ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ገዛኸኝ አባተ የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናትም ከወዲሁ ሀዘናቸውን እየገለፁ መሆኑን ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያን ታሪክ የተመለከቱ በጣም በርካታ ጥናታዊ ጽሑፎችን በማዘጋጀት ከፍተኛ የታሪክ ባለውለታ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ሪቻርድ ፓንክረስት የተወለዱት እ.ኤ.አ በታህሣስ 1927 በእንግሊዝ ሲሆን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በባንክሮፍት ት/ቤት ተከታትለው፣ ከለንደን የኢኮኖሚክስ ት/ቤት በኢኮኖሚክስ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡
እ.ኤ.አ በ1954 ዓ.ም በኢኮኖሚክስ ታሪክ የትምህርት ዘርፍ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ያገኙት ፓንክረስት፤ ከሁለት ዓመት በኋላ ከዋነኛዋ የኢትዮጵያ ባለውለታ ወላጅ እናታቸው ሲሊቪያ ፓንክረስት ጋር ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በቀጥታ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ በማስተማር ስራ ተቀላቀሉ፡፡
ከምርምርና የማስተማር ስራቸው ጎን ለጎን እ.ኤ.አ በ1962 ዓ.ም የኢትዮጵያ ጥናት ተቋምን በመመስረት የሚታወሱት እኚሁ የኢትዮጵያ ታሪክ ምሁር፤ በ1967 የደርግን ወደ ስልጣን መምጣት ተከትሎ፣ ሁኔታው ስላልተመቻቸው ወደ ትውልድ ሀገራቸው እንግሊዝ በመመለስ፣ በንደን የአፍሪካ ጥናት ማዕከልና የኢኮኖሚክስ ጥናት ማዕከል እንዲሁም በለንደን የኢኮኖሚክስ ት/ቤት በምርምርና ማስተማር ስራ ላይ ተሰማሩ፡፡
በ1978 ዓ.ም በድጋሚ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ስራቸውን የቀጠሉት ፕ/ር ሪቻርድ ፓንክረስት፤ በግላቸው ከ17 በላይ የታሪክ፣ የባህልና የኢኮኖሚ ታሪክ መፅሀፍትን እንዲሁም ከሌሎች ጋር በመጣመር ከ22 በላይ መፅሀፍትን ፅፈው ለምርምር አበርክተዋል፡፡ በተለየ ትኩረት ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ፣ ባህል፣የኢኮኖሚ ታሪክና የማህበረሰብ አኗኗር መጠነ ሰፊ ምርምር በማድረግ በርካታ ጥናታዊ ጽሑፎችን ያበረከቱት ፕ/ር ሪቻርድ ፓንክረስት፣ ከ400 በላይ ፅሁፎችንም በአለማቀፍ መፅሄቶች ላይ አቅርበዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የአክሱም ሀውልት ከሮም እንዲመለስ በግንባር ቀደምትነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከቱ ሲሆን የአፄ ቴዎድሮስን ክታብ ጨምሮ ሌሎች የተዘረፉ በርካታ ቅርሶችንም ከእንግሊዝ ማስመለሳቸው ይነገርላቸዋል፡፡
ከ50 ዓመት በላይ ያገለገሉት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በምርምር ስራቸው የፕሮፌሰርነት ማዕረግ የሰጣቸው ሲሆን ዕድሜልካቸውን በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ላከናወኑት ጥናትና ምርምር ከዩኒቨርሲው የክብር ዶክትሬት ድግሪ ተቀብለዋል፡፡
ለኢትዮጵያ የታሪክ ጥናት ላበረከቱት አስተዋፅኦ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የሽልማት ድርጅት እና ከኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ የእውቅና ሽልማት ከማግኘታቸው በተጨማሪ የእንግሊዝ መንግስት በሀገሪቱ ከሚሰጡ የክብር ሽልማቶች አንዱ የሆነውን የኮቢኢ (Officer of the order of the British Empire) የተሰኘውን ሽልማትና ክብር አግንተዋል፡፡
ወላጅ እናታቸው ወ/ሮ ሲሊቪያ ፓንክረስት “የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ” ሲሆኑ በ5 ዓመቱ የጣሊያን ፋሽስት ወረራ ወቅት በውጭ ሃገር በሚታተሙ ጋዜጦች ላይ በሚያወጧቸው ፅሁፎች ወረራውን በመቃወምና ለአለም በማስተጋባት የማይናቅ የነፃነት ተጋድሎ አድርገዋል፡፡  “Ethiopia Cultural History” የተሠኘ የታሪክ መፅሃፍም በኢትዮጵያ ዙሪያ ፅፈዋል - ወ/ሮ ሲልቪያ ፓንክረስት፡፡
የፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት የሁለት ልጆች አባት ሲሆኑ ወንድ ልጃቸው ዶ/ር አሉላ ፓንክረስትም በታሪክ ተመራማሪነታቸው ይታወቃሉ ሴት ልጃቸው ሄለን ፓንክረስት ይባላሉ፡፡ አራት የልጅ ልጆችም ለማየት በቅተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ተመራማሪውና መምህሩ ፕሮፌሰር አህመድ ዘካሪያ ስለ ፕ/ር ፓንክረስት በሰጡት አስተያየት፤ ‹‹ሃሳቡን በግልፅ የሚናገር፣ ጥሩ ቀን መጥፎ ቀን አለብሎ የማያምን ሰው፤ ስራውን የማያስተጓጉል፤ ለስራው ጊዜውን የሠጠና የሚገባውን ሁሉ የሰራ ሰው ነው›› ብለዋል፡፡
የፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ተማሪ እንደነበሩ የገለፁት ሌላኛው የታሪክ ተመራማሪ ፕ/ር ገብሩ ታረቀ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ተማሪ ሣሉ፣ ኢኮኖሚክስ እንዳስተማሯቸው ጠቁመው፤ ‹‹በትምህርቱ ለማስረዳት ከሚሰጧቸው ምሳሌዎች፣ ጥቅሶች ቀልዶች የተነሣ ለሣቸው ልዩ ትውስታ አለኝ›› ይላሉ፡፡
ለኢትዮጵያ በእውቀታቸው የማይተካ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን የሚመሠክሩት ፕ/ር ገብሩ፤ በተለይ የኢትዮጵያ ጥናት ማዕከልን ማቋቋማቸው ለሃገሪቱ እጅግ ጠቃሚ ተግባር ነው ብለዋል፡፡
ፓንክረስት ለሃገሪቱ ካበረከቱት አስተዋፅኦ አንፃር የሚገባቸውን ክብር እንዳላገኙ በቁጭት ያስረዳሉ - ፕ/ር ገብሩ፡፡ በ2002 ዓ.ም በእሳቸው ስም የተሠየመ አዲስ ቤተ መፅሃፍት በአ.አ.ዩ ግቢ ውስጥ በመሰራት ላይ እንደነበርና ባልታወቀ ምክንያት መቋረጡ ያሳዝነኛል ብለዋል፡፡ “ለዚህ ደግሞ መንግስት” የአ.አ.ዩ አስተዳደር ተወቃሾች ናቸው፡፡” ያሉት ፕ/ር ገብሩ፤ ‹‹ሊያፍሩበትና ሊኮነኑበት ይገባልም›› ብለዋል፡፡ አሁን እሣቸው ካለፉ በኋላ ብዙ ነገር ማውራቱ አይጠበቅምም፤ በዚህ በጣም ሃዘን ይሠማኛል ብለዋል፡፡
ሌላው የታሪክ ተመራማሪ አቶ ብርሃኑ ደቦጭ በበኩላቸው፤ ፓንክረስት ያልፃፈበት ምንም ርዕሰ ጉዳይ እንደሌለ ያስረዳሉ፡፡ በተለይ የመጀመሪያ ድግሪ የታሪክ ተማሪዎች የመጀመሪያ የእውቀት መጨበጫቸውና መነሻ እውቀት የሚሆናቸው የፓንክረስት ፅሁፎች ናቸው ይላሉ፡፡
የሚጠቀሟቸው የምርምር ሰነዶች በቀላሉ የማይገኙ አርከይቮችንና የጉዞ ማስታወሻዎች መሆናቸውን አቶ ብርሃኑ ያስረዳሉ፡፡ ሪቻርድ ፓንክሪስት የኢትዮጵያ ባለውለታ ናቸው ብለዋል - አቶ ብርሃኑ፡፡


Read 6593 times