Sunday, 19 February 2017 00:00

አኮር በአዲስ አበባ 3 ሆቴሎችን ሊከፍት ነው

Written by 
Rate this item
(6 votes)

በአውሮፓ ትልቁ የሆቴል ዘርፍ ኩባንያ የሆነው የፈረንሳዩ አኮር ሆቴልስ ግሩፕ በአዲስ አበባ ሶስት ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎችን ለመክፈት የሚያስችለውን የግንባታና የማኔጅመንት ስምምነት ከኢትዮጵያውያን ባለሃብቶች ጋር መፈጸሙን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ኩባንያው ባለፈው ረቡዕ ያወጣውን መግለጫ ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገነቡት ሶስቱ ሆቴሎች እስከ መጪዎቹ አራት አመታት ጊዜ ውስጥ ግንባታቸው ተጠናቅቆ ስራ ይጀምራሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ሆቴሎቹ በድምሩ 527 ያህል የመኝታ ክፍሎች ይኖሯቸዋል፡፡
ኩባንያው በአዲስ አበባ ከተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ የኢኮኖሚ ኮሚሽን አቅራቢያ የሚከፍተውና 162 መኝታ ክፍሎች የሚኖሩት የመጀመሪያው ሆቴል በሶስት አመታት ውስጥ ተጠናቅቆ ስራ እንደሚጀምር የሚጠበቅ ሲሆን፣ በዚሁ አካባቢ የሚገነባውና 135 የመኝታ ክፍሎች የሚኖሩት ሁለተኛው ሆቴልም በሁለት አመታት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ተነግሯል፡፡
ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን አቅራቢያ የሚገነባውና እ.ኤ.አ በ2021 ግንባታው ተጠናቅቆ ስራ ይጀምራል ተብሎ የሚጠበቀው ሶስተኛው ሆቴል ደግሞ፣ 230 መኝታ ክፍሎች እና 22 ወለሎች እንደሚኖሩት ተገልጧል። አኮር ሄቴልስ ኩባንያ በአፍሪካ የሆቴል ኢንቨስትመንት ዘርፍ ከተሰማራ 40 አመታት ያህል እንደሆነው ያስታወሰው ሮይተርስ፤ በ21 የአፍሪካ አገራት በከፈታቸው 94 ሆቴሎች፤ ከ10 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የስራ ዕድል መፍጠሩንም አክሎ ገልጧል፡፡

Read 3530 times