Sunday, 19 February 2017 00:00

የደ/ ኮርያ ወታደሮች ለኢትዮጵያውያን ዘማቾች እርዳታ እያሰባሰቡ ነው

Written by 
Rate this item
(2 votes)

የደቡብ ኮርያ የጦር ሃይል አባላት የሆኑ ወታደሮች በኮርያ ዘመቻ ወቅት የተሳተፉና በጽናት በመታገል ታላቅ ውለታ የሰሩ ኢትዮጵያውያን ዘማቾችን ለመርዳት የሚውል የገንዘብ ድጋፍ እያሰባሰቡ እንደሚገኙ ተዘግቧል፡፡
የደቡብ ኮርያ ጦር በኦፊሻል የፌስቡክ ገጹ ላይ ያወጣውን መረጃ ጠቅሶ ኮፖጆላ የተባለው ድረገጽ ትናንት እንደዘገበው፣ የአገሪቱ 27ኛ ክፍለ ጦር አባላት የሆኑ ወታደሮች በአበል መልክ ከሚሰጣቸው ገንዘብ የተወሰነውን በማሰባሰብ በአለማቀፉ የእርዳታ ድርጅት በኩል ለኢትዮጵያውያን የኮርያ ዘማቾች ለመላክ እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡
እ.ኤ.አ በ1951 በተጀመረው የሁለቱ ኮርያዎች ጦርነት፣ ከ6 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ዘማቾች ደቡብ ኮርያን በመደገፍ ለአምስት አመታት ያህል በጽናት መታገላቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ 122 ያህሉ ሲሞቱ 536 የሚሆኑት ደግሞ የመቁስል አደጋ እንደደረሰባቸው ገልጧል፡፡
ደቡብ ኮርያውያኑ ወታደሮች የሚያሰባስቡት ገንዘብ፣ በህይወት ለሚገኙ 350 ያህል ኢትዮጵያውያን ዘማቾች እንደሚደርስ የጠቆመው ዘገባው፣ ወታደሮቹ የኢትዮጵያውያን ዘማቾችን ፎቶግራፎች ይዘው በኩራት ስሜት ውለታቸውን እየዘከሩ የሚያሳየው ፎቶግራፍ፣ በጦሩ የፌስቡክ ድረገጽ ላይ መለቀቁንም አክሎ ገልጧል።

Read 2393 times