Sunday, 19 February 2017 00:00

ለምግብ ዋስትና የ3.8 ቢ ብር ፕሮጀክት አፀደቀ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ለኦሮሚያ 2 ቢ ብር ተመድቧል - ከ1 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ
 
ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ፤ በኦሮሚያ ስድስት ወረዳዎች የምግብ ዋስትናቸው ያልተረጋገጠ ከ1 ሚ. በላይ ሰዎችን ለመደገፍ የ2 ቢ. ብር
ፕሮጀክት ይፋ አደረገ፡፡ ባለፈው ሳምንት በአዳማ ከተማ አዩ ኢንተርናሽናል ሆቴል ይፋ ባደረገው በዚህ ፕሮጀክት ላይ፤ የክልሉ ኃላፊዎች፣ የወረዳ ተወካዮች፣ የወርልድ ቪዥን ካንትሪ ዳይሬክተሮችና ፕሮጀክት ማናጀሮች ተገኝተዋል፡፡ አምስት አመት የሚዘልቀው ይሄው ፕሮጀክት የሚተገበርበት ገንዘብ የተገኘው ዩስኤይድ ለዚሁ ተግባር ከመደበው 175 ሚሊዮን ዶላር ላይ እንደሆነ በዕለቱ ተነግሯል። ወርልድ ቪዥን ላለፉት 40 ዓመታት በኦሮሚያ ክልል 24 ወረዳዎችና አምስት ዞኖች የምግብ ዋስትና ድጋፍና ሌሎች የተቀናጁ የልማት ስራዎችን በመስራት ከ6 ሚ. በላይ ህፃናትንና በጣም ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ሲያገለግል መቆየቱም በዕለቱ ተገልጿል፡፡ ወርልድ ቪቪን ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ባጠናቀቀው የአምስት አመት የልማትና የምግብ ድጋፍ ፕሮግራም ከ1.5 ሚ. በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ ማድረጉን የገለፁት የኦሮሚያ ክልል የደህንነት፣ የግብርናና የተፈጥሮ ሀብት ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ አንድነት ደገፋ አሁንም ወርልድ ቪዥን በ6 ወረዳዎች የምግብ የጤናና የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ላይ ለመስራትና ወገኖችን ለመደገፍ ያቀረበውን ትልቅ ሀብት በአግባቡ መጠቀም አለብን ሲሉ ተናግረዋል፡፡የወርልድ ቪዥን የልማትና የምግብ ድጋፍ ፕሮግራም (DFAP) ፕሮጀክት ዳይሬክተር አቶ ጉቱቴሶ እንደገለፁት፤ የዘንድሮው ፕሮጀክት በዋናነት የሚያተኩረው የምግብ ዋስትናቸው ባልተረጋገጠ የኦሮሚያ የአማራና የደቡብ ክልል አካቢዎች ሲሆን ይህን ፕሮጀክት ለማሳካት የ3.8 ቢ. ብር በጀት ማግኘታቸውን ጠቅሰው፣ የአማራው ከሁለት ሳምንት በፊት ይፋ መሆኑንና የደቡቡ በቅርቡ በሀዋሳ እንደሚጀመር ተናግረዋል፡፡ የምግብ ዋስትናቸው ላልተረጋገጠ የሦስቱ ክልል አካባቢ ማህበረሰቦች ከምግብ ድጋፍ በተጨማሪ የተቀናጁ በርካታ ስራዎች ይከናወናሉ ያሉት አቶ ጉቱ ከነዚህም መካከል በግብርና፣በጤና፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በንፁህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት በአኗኗር ዘይቤ በገጠር ስራ ፈጠራና በመሰል ስራዎች ላይ በማተኮር ድርቁን ተከትሎ የመጣውን የምግብ እጥረት እንዲቋቋሙ ይደረጋል ተብሏል፡፡

Read 1007 times