Sunday, 12 February 2017 00:00

የ“እንባና አሞሌ” … ግጥሞች!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(25 votes)

 “---ሰማይ ከኔ በልጦ፤ ነፋስ ካሰከነ
                    አመድም ይጠቅማል፤ መች እጄ ቦዘነ
                    እውነትም ሳስበው፣ ቀልቤ ተረጋጋ
                    አመድም ተስፋ ነው፣ የሳት ፍም ፍለጋ!”


    ግጥሞች ከአበቦች ጋር የሚናፀሩበት ብዙ ክንፎች አሏቸው፡፡ አበቦች በቀለም አንዱ ካንዱ ይለያሉ፤ ይደምቃሉ፤ ይፈዝዛሉ፡፡ … አበቦች በቅርፅ አንዱ ካንዱ ይለያሉ፤ የአንዱ መዓዛም ከሌላው ይለያል፡፡ ይመሳሰላሉም፣ ይለያያሉም! … ግጥምም እንዲሁ ነው። አንዱ ካንዱ በቅርፅ ይለያል፣ በቀለምም! … በይዘትና በሙዚቃም እንደዚሁ፡፡
አንባቢ ደግሞ ከንብና ቢራቢሮ ጋር ይመሳሰላል። … ቢራቢሮ አበቦች መስክ ላይ ትበራለች … ትከንፋች። … ግን አንዳች አትጨብጥ ይሆናል! … ሽቱ … ተርከፍክፋ ውበት ላይ ሰፍፋ ትመለሳለች፣ ትዝናናለች! … ንቢቱ ደግሞ እጅዋን ተክላ፣ ጣፋጩን መጥጣ ማር ትጋግራለች! … አንባቢውም እንዲህ ነው፡፡ … ለመዝናናትም ለግርምትም ለፍልስፍናም፣ ለህይወት መርህም ያነብባል፡፡ … እሰየው!
እኔም እንደእነ ቢራቢሮ አበቦች፣ መጻህፍት ወደከተሙበት ጎራ ብዬ ካገኘኋቸው ውስጥ ለዛሬ የገጣሚ ቤተልሔም ኒቆዲሞስን “እንባና አሞሌ” ለመቃኘት አሰብኩ፡፡ መጽሐፍዋ የወጎችና የግጥሞች ስንግ ናት፡፡ ፀሐፊዋ ደግሞ ወጣት እንስት፡፡ በጥቂቱ ዐይኔ ገብተዋል ብዬ ያሰብኳቸውን ለመዳሰስ ልሞክር። … መቸም ሀገር ከሁሉ ይቀድማልና ከሀገር ልጀምር! – “አንቺ አገር!” ይላል ርዕሱ፡-
በፈገግታሽ ብቻ፣ ይኸው ሆዴ ሞላ
በናትነት ፍቅርሽ፣ የደነዘው ሰላ
እኔማ የሚገርመኝ!
እንዲህ በባዶ ቤት፣ ጎዶሎሽ ካማረ
የሀዘኔ ካቡ፣ ካንቺ ቤት ከተሻረ (ዜማ ሰብሯል)
ያሳየኝ ያንን ቀን፣ ሞልቶ የደላሽ ለት
የምድርሽ አፈር ላይ፣ መና ሲወርድበት
ይሄ ሁሉ አበሻ፣ የጠገበ ጊዜ
ቆርጦ ይበላሻል፣ በፍቅር አዋዜ ….
ግጥሙ የሚቀጥል ቢሆንም መልዕክቱ ከዚህ አያልፍም፡፡ … ሀሳቡን ስናይ በዚህ ምስኪንነትሽ፣ ባሳየሽን ፈገግታ ካጠገብሽንና ከረካን፣ … የተመቸሽና የሞላልሽ ቀንማ ጉድ ይፈላል፣ ይመስላል፡፡ ሀዘናችን ዛሬ እንደ ጉም ከበነነ፣ (ከብቶች በበረት፣ በጎች በጋጣ ሳይኖሩ እንደማለት፣) ወይም የወይኑ ፍፌ ሳያፈራ፣ … በፍቅርሽ ከነደድን፣ የልቡ የሞላለት ቀን ያገሬ ሰው ድግሱ ምን እንደሆን ታውቂያለሽ ነው ገደምዳሜው! … ጥሬ ሥጋ አድርጎ በአዋዜ ይበላሻል ነው! … እንደ ሥላቅም እንደ ሀቅም ያደርገዋል ነገሩ!
ግና ሰባተኛው ስንኝ ላይ ያለው ሀሳብ፣ ዋናውን ሀሳብ የሚጋፋ ይመስላል፡፡ ሀገር የሚሳካላት፣ መና ሲወርድላት አይደለምና! … መናማ የመከራ ጊዜ፣ የተስፋ ጉዞ ቀን የዕለት ጉርስ ነው፡፡ አንድ ቀን ካደረም ይበላሻል፡፡ የአብርሃም ዘር እስራኤል፣ መና ከሰማይ የወረደለት በደጉ ቀን አይደለም፣ ከግብፅ ባርነት፣ ወደ ከንዐን አርነት በሚያደርገው የቀውጢ ቀን ጉዞ ነው። ማርና ወተት እምታፈሰው የበረከት ምድር ሲገባማ፣ “የምን መና መጣ!” የምድሪቱን ፍሬ መብላት ነው፤ … መስራትም ጭምር፡፡
ይሁንና ሌሎችም ጆሮ ቆንጠጥ የሚያደርጉ፣ ልብን መጠምዘዝ የሚከጅላቸው ግጥሞች አሏት፣ እኛ ግን የግጥም ሃያሲው ኤስኤች ቡርተን እንደሚሉት፤ በእውነት ጥማት፣ በግጥም ፍቅር በተጠቀለለ እንዲሁም በምናብና በጠቅላላ እውቀት ነገሮችን እያነጠርን መሄድ ነው፡፡
ለሁሉም ቀስ በቀስ እግራቸው እየጠና፣ ውስጣቸው አጥንት እየተከለ፣ጫንቃቸው እየበረታ የሚሄድ ግጥሞች አሏትና በእርጋታ ማየት ነው፡፡ “የሌባ ፍቅር” የምትለዋና ገፅ 58 ላይ ያለችው ግጥም ትንሽ ፈርጠም ያለች ትመስላለች፡፡
ካንድ ጎድን ግጠው፣ እኩል የጠገቡ
በበሰበሰው ደም፣ ኮርተው የታጠቡ
አሞራ ጓደኞች፣ የተጣሉ ለታ
ቤታቸው ጠቧቸው፣ ለመንደር ተፈታ
ቀድሞ ያጋለጠ፣ የጩሉሌ ደረቅ
ባልንጀሩን ከድቶ፣ ከተተው መቀመቅ
ድሮስ ገዳይ እንጂ፣ ጀግናና አንበሳ
መች ተማምኖ ያውቃል፤ የወንዜ ጥንብ አንሳ!
ይህ ግጥም በግርድፉ ሲታይ ሁለት ደም የነካቸው ሆዳም አሞሮች ይታያሉ፡፡ እዚህ አሞሮች ይጣላሉ፤ አንዱ አንዱን ያጋልጣል፡፡ ቀድሞ ያጋለጠው ደግሞ ባልንጀራውን ሸምቀቆ ውስጥ ከቶታል፡፡ እንግዲህ አሞሮች ያለቻቸውን እማሬያዊ ፍቺ ወስደን፣ ወደ ፍካሬያዊ ትርጉሙ ጎራ ስንል አሞራ፣ ጥንብ አንሳ፣ በደንብ ሞቅ አድርጋ ቀለም ካነደደችበት ----- የምናብ ድስቷን ካሰፋችው በውበት የሚንተከተክ፣ በሀሳብ የመጠቀ ግጥም የምትፅፍበት ምልክት ሰጥታናለች፡፡  
“መስዋዕት” የሚለው ሌላው ግጥምዋ የፍቅርን ምስጢር፣ … ልመናና ዝምታ፤ ያንድ ወገንን ቸልተኝነት ዋጋ ያመራል፡፡
ውዴ ስሞትልህ፤ ደስታዬን ገድዬ
እንባዬን ስሰጥህ፤ ለስንብት ብዬ
ፍፁም እንዳይሞላህ፤ ሀሴትና ደስታ
የመለመን ምኞት፣ የኩራት ዝምታ (“መለመን” ላልቶ የሚነበብ ነው፡፡)
ጦር ነው ውዴ ልቤ፣ አንተ ተዝናንተሀል
ካናቱ ስትጨፍር፣ ተወግተህ ሞተሃል!
እዚህ ግጥም ውስጥ አንዲት እንባዋን የምታፈሥሥ እንስት አፍቃሪና አንድ በኩራት ያበጠ ተባዕት አለ፡፡ እርሷ ትለምነዋለች፣ እርሱ ግን የገባው አይመስልም። ግና አንድ መርዶ አለ፡- ይህ ለፍቅር አደባባይ የተሰጣ፣ ንፁህ ልብ፣ ሌላ ጣጣ አለው፡፡ በፍቅር መዳን ያልፈለገን ሰው፣ በተዐብዮ ያበጠን ልብ ያስተነፍሳል! … እና “በተማፅኖ ድምፅ፣ በጆሮህ በሚንቆረቆር ሃዘን፣ በልቅሶዬ ዜማ እንዳትፈነጭ----- ጦሩ ጫፍ ላይ ነህ” እያለችው ነው፡፡ .. ይህም የሰላ ሀሳብ ነው፡፡ አሁንም ግን የቃላት ውበት፣ የዘይቤ አበባ ያንሰዋል፡፡
ሌላኛውና ቀልቤን የሳበው ግጥም፣ ገፅ 112 ላይ ያለው “አመድና ተስፋ” ነው፡፡
አመድ አፋሽ እጄን፣ በእድሌ ረግሜ
ጠማማ ነህ ብዬ፤ ስወቅሰው ከርሜ
ታምር አይ ጀመረ፣ አየር አፍሶ ሰማይ
ደመና ሲያዳውር፣ በንፋስ ሲሰቃይ
ደመናም ተሰራ፤ እሱም ውሃ ሆነ
የአየሩ ቱባ ክር፤ ዝናብ ተሸመነ
የገጣሚዋ ገፀ ባህሪ ተስፋ መቁረጥዋን ተወት አድርጋ፣ ዓይኖችዋን ወደ ተፈጥሮ ቅንጅት ስትመልስ፣ ንፋሱና ሰማዩ ደመና ሰርተው ዝናም ተወልዶ፣ እንደ ሸማኔ ክሮች የፈጠሩትን ጥበብ አደነቀ፡፡ እናም በቀጣዮቹ ስንኞች ወደ ቀልቡ ተመልሶ እንዲህ ቀጠለ፡-
ሰማይ ከኔ በልጦ፤ ነፋስ ካሰከነ
አመድም ይጠቅማል፤ መች እጄ ቦዘነ
እውነትም ሳስበው፣ ቀልቤ ተረጋጋ
አመድም ተስፋ ነው፣ የሳት ፍም ፍለጋ!
በዚህ ግጥም ሰማዩ የገፀ ባህሪዋ ትምህርት ቤት ሆኖዋል፡፡ ምክንያቱም ንፋስን የሚያህል ወፈፌ ነገር፣ ሰማይ አረጋግቶ ለዝናም ካበቃ፣ እኔስ ዓመድ ባፍስ ምናለበት? ስራ ነው! … ደግሞስ ዓመድ የሚታፈሰው አንዳንዴ እሳት፣ ያውም ፍም ፍለጋ አይደል እንዴ! … በማለት ጥሩ ተቀኘች፡፡
ቀጣዩና “ለሷ ነው” የሚለው ግጥሟም፣ እንዲሁ አንዳች ኃይል ያለው ነው፡፡
የነገሥታት ልጆች፣ ከግር የወደቅነው
ከመሬት ሲሉን፣ ፈቅደን የተማስነው
ሌላው ሁሉ መና፣ ረሀብና ጠኔ
የችግር የስቃይ፤ የመከፋት ቅኔ
መኖርና ህይወት፣ ልኑር ብቻ እኔ
ሰርዶ ረጋጭ መሆን፣ የጥፋት ሸማኔ
ይቅርብን ብለን ነው፤ እንዲህ የምንለፋ
እሷን እያሳየን፤ ለአይን የምንጠፋ
እኛ ተቀዳደን፤ እሷን የምንሰፋ
ሰንደቃችን ትኑር፣ ዘመን አሳልፋ!
በመጀመሪያው ስንኝ “የነገሥታት ልጆች” የሚለው አሻሚ ሀረግ ነው፡፡ በዚህ ስያሜ የሚጠራው ገፀ ባህሪው ነው? ወይስ … ያኛው ወገን? … የሚለው ያሻማል፡፡ እያነበብን ወደ ታች ስንወርድ ግን ነገሩ ግልፅ ይሆንልናል፡፡ “የነገስታተ ልጆች” የተባሉት፣ ገፀ ባህሪውንና የርሱን የዐላማ ወገኖች ሲገዙ የነበሩትን የሚወክሉ ናቸው፡፡ ገጣሚዋ የፈጠረችው ገፀ ባህርይ ደግሞ “ለሠንደቅ አላማችን ስንል ያላየነው አበሳ፣ ያልከፈልነው ዋጋ የለም፡፡ እሷን እያሳየን፣ እኛ እንጠፋለን፣ እኛ ተቀዳድደን እርሷን እንሰፋለን!” ይላል። ራስን ቀድዶ፣ የሀገርን ክብር መስፋት! ሞቅ ያለና ደመቅ ያለ አተያይ ነው፡፡ ተምሳሌትነቱም በእጅጉ ይመስጣል፡፡ የልባችን ጥግ ድረስ ሰተት ብሎ ይገባል፡፡  
“ሹቀት” የሚል ርዕስ ያለው ግጥምም እንዲህ ተሰናኝቷል፡-
“ቀድሞ በመወለድ፤ ከሆነ ጨዋታ
የሰው ላብ ሰብስቦ፣ መተቸት በተርታ
በሰው ህይወት ፈርዶ፣ ነጥብ መቀጣጠል
ገሚሱን አባሮ፣ ሌላውን ማባበል
ታላቄ ሳይገለኝ፣ በሽንፈት በእንባ
ከናቴ ማህፀን፣ ተመልሼ ልግባ!    
አበብሽ አበባ … እልል ብዬ ልግባ …”
የሰነፍ ዳንኪራ፣ እየመታን ሳለ
በሰው ስናላክክ፣ እድሜ ጥንቡን ጣለ፡፡
ግጥሙ ቀሪ ሁለት ስንኞች ቢኖሩትም፣ ያለ ጣልቃ ገብነትና ስብከት ማለቅ ያለበት እዚህ ጋ ይመስለኛል። ፈሪ ነፍስ፣ ሸምቃቃ ሯጭን ያሳያል - ግጥሙ፡፡ ሳያስበው፣ ዕድሜን እያሰላ፣ ዕድሜ የከዳውን ሰው፡፡ … ተመልሰህ እናትህ ሆድ አትገባት! … ህይወትን መጋፈጥ እንጂ መሸሽ አያዋጣም ነው ነገሩ!
የ“እንባና አሞሌ” ደራሲ፣ አልፎ አልፎ መጽሐፏ ውስጥ እንደሚንፀባረቁት ጥሩ አተያይ፣ የሚያድግ አቅም አላት፡፡ ነገር ግን ቤት ዓመታት ላይ የሚታዩትን ልልነቶች (በተለይ በመካነ ድምፆችና በአናባቢዎች - የድምፅና የንዝረት አቅም ላይ በማተኮር) ለማስወገድና የቋንቋና ቃላት አጠቃቀምን ከፍ ለማድረግ መትጋት አለባት ብዬ አምናለሁ! … እሷ ራሷ አሳምራ እንደገለጸችው፤ፍሙን ፍለጋ ዓመዱን ማፈስ!

Read 15386 times