Saturday, 11 February 2017 14:05

“ተዋናይዋ”

Written by  መሐመድ ኢድሪስ
Rate this item
(10 votes)

(ከአሜሪካን አይዶሉ ዳኛ፣ ሳም የተወሰደ ገፀ-ባህሪ)
ዊልያም ስሚዝ በኦሃዮ ግዛት በሳንደስኪ ከተማ፣ ቪሌጅ ሬንዴቩ የሚባል ካፌ ውስጥ ተቀምጦ ቡና እንደወረደ  እየጠጣ ነው፡፡ የለበሰው ጥቁርና ነጭ ጠቃጠቆ ያለበት የበጋ ሸሚዙ ከሰውነቱ ጋር ተስማምቷል፡፡ ጥቁር የሱፍ ሱሪ ለብሶ፣ ማሰሪያው ከብር የተሰራ ኦሜጋ ሰዓት አድርጓል፡፡ ገብስማ ፀጉሩ በጥንቃቄ የተበጠረ ሲሆን ጥቁር የአይን መነፅር ሰክቷል፡፡  
ካፌው ውስጥ ያለው ሰው በሙሉ ትኩረቱ እሱ ላይ ነው፡፡ አንዳንዶቹ በወሬያቸው መሀል ሰረቅ እያደረጉ ያዩታል፡፡ ዊልያም በዚህ ጉዳይ ምንም አልተገረመም፡፡ እንኳን እዚች ትንሽ ከተማ ውስጥ ይቅርና ትላልቅ በተባሉት ከተሞች፡- በኒውዮርክና ሎስ አንጀለስ ውስጥ ዝነኛና የተከበረ ሰው ነው፡፡ እድሜ ለአሜሪካ ብሄራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ! በዚያ ጣቢያ ላይ በሚተላለፈውና በአለም ላይ ከአምስት መቶ ሚሊዮን ህዝብ በላይ በሚከታተለው የታለንት ሾው ፕሮግራም ላይ ዋና ዳኛ ነው፡፡
ዝነኛና ታዋቂ የሆነው በዚህ ምክንያት ብቻ አይደለም፡፡ የዳኝነት ውሳኔውን ሲሰጥ በሚሰነዝራቸው አስተያየቶች የተነሳ “መጥረቢያው” የሚል ቅፅል ስም አትርፏል፡፡ ለማንም ስሜት፣ ክብርና ሞራል ሳይጨነቅ በሚያወርደው የቃላት ውርጅብኝ ተወዳዳሪዎችን አሳፍሮና አሸማቆ ጥፍራቸው ውስጥ እንዲገቡ ሲያደርግ፣ ታዳሚው ደግሞ በሱ ንግግር በሳቅ እያውካካ በአድናቆት ያጨበጭባል፡፡ አንዳንዴ ከውድድሩም በላይ “መጥረቢያው” በዳኝነት ውሳኔው የሚሰነዝራቸውን ተረቦች መስማት ለተመልካቹ የበለጠ አጓጊ ነው፡፡
ለምሳ አንዱን በውድድር ላይ ቀርቦ የነበረውን ዘፋኝ፣ ዘፈኑን ሳይጨርስ መሀል ላይ ካስቆመው በኋላ፤ “የጆሮዬን ክብረ ንፅህና ነው የደፈርከው። ትንሽ ብትቀጥል ኖሮ ፖሊስ ነበር የምጠራው። ገንዘብ ከሆነ የምትፈልገው በየወሩ እኔ እቆርጥልሃለሁ፡፡ ነገር ግን እባክህን ከአሁን በኋላ እንደዚህ ሰው ላይ አትጩህ” ሲል አስተያየት ሰጠው፡፡ አስተያየቱን ተከትሎም ተመልካቹ በሙሉ በሳቅ ሲያወካ፣ ተወዳዳሪው እርምጃው እየተደነቃቀፈ ከመድረክ ወረደ፡፡
ከኦክልሃማ የመጣውንና መድረክ ላይ በአጭር ጊዜ ውስጥ የአበባ ስዕል የሳለውን ሰዓሊ ደግሞ፤ “ኦክልሃማ ውስጥ ግንባታ ቆሟል እንዴ? ለምን እዚያ ስራ አትፈልግም? ለምን መሰለህ እንደዚያ ያልኩህ? አንተ ሰዓሊ ሳትሆን ቀለም ቀቢ ስለሆንክ ነው” ሲለው ሰዓሊው በእፍረት ፊቱ ሳንባ መስሎ ከመድረኩ ወርዶ ሄደ፡፡  
የማክቤዝን ሚስት ገፀ-ባህሪ ተላብሳ መድረክ ላይ ለአምስት ደቂቃ መነባንብ ያሰማችዋን ተወዳዳሪም ፣ትወናዋን መሀል ላይ አቋረጣትና፤ “ሼክስፒር ይሄን ሳያይ በመሞቱ እድለኛ ነው፤ ሥራው እንደዚህ ሲጨማለቅ ባለመኖሩ፡፡ ሥራ ማለት ትወና ብቻ እኮ አይደለም፡፡ አስተናጋጅነት ወይም የፅዳት ስራ ብትሞክሪ ሳይሻልሽ አይቀርም፡፡ አንቺ ተዋናይ አይደለሽም---” ሲላት፣ ልጅቷ ፊቷን በእጆቿ ሸፍና ስቅስቅ ብላ አለቀሰች፡፡
በዚህ ተረቡ ምክንያት ተመልካቹ ከአሁን አሁን ዊልያም ምን አለ በማለት በጉጉት እየተናጠ የእሱን ንግግሮች ለመስማት ያሰፈስፋል፡፡ “መጥረቢያው” አልፈሃል ያለው ተወዳዳሪ፤ እንደ ተአምረኛና እንደ ጉድ ነው የሚታየው፡፡ እሱ ጋ ከደረሱት አስር ተወዳዳሪዎች ሁለቱ እንኳን ካለፉ፣ “መጥረቢያው” መንፈስ ቅዱስ ቀርቦታል ማለት ነው፡፡
ካፌው ውስጥ እንደተቀመጠ ከቡናው ፉት አለለት፡፡ ቶስካኖ ሲጋሩን አወጣና ለኮሰ፡፡ ወዲያው አንድ ሴት አስተናጋጅ መጣችና፣ መተርኮሻ ጠረጴዛው ላይ ካስቀመጠች በኋላ፤ “የካፌው ህግ ሲጋራ እንዳይጤስ ይከለክላል፤ ደንበኞች ሲጋራ ሲያጨሱ ካልከለከልን፣ አምስት ዶላር እንቀጣለን፡፡ ነገር ግን አንተን ከምከለክል አምስት ዶላር ብቀጣ እመርጣለሁ፤ ማስተር ስሚዝ” አለችው፤ ሞቅ ባለ ፈገግታ እያየችው፡፡
“ታውቂኛለሽ ማለት ነው?” ሲል ጠየቀ፡፡
“አንተን የማያውቅ ማን አለ? ትፈርምልኛለህ?” አለችና አንድ ማስታወሻ ደብተር ሰጠችው፡፡ ደብተሩ ላይ ፈረመና ከኪሱ ሃምሳ ዶላር አውጥቶ እየሰጣት፤ “ይሄ ለቅጣቱ ነው፡፡ ባለቤቴን እየጠበቅኩ ነው፤ትንሽ ስለዘገየች ተሰላችቼ ነው ሲጋራ የለኮኩት” አላት ፈገግ ብሎ፡፡
“መልካም ጊዜ፤ ሌላ ቡና ላምጣልህ?”
“እሺ፡፡ ወፍራም ቢሆን እመርጣለሁ”
አስተናጋጇ ቡናውን ልታመጣ ስትሄድ፤ “ምን ሆና ነው የዘገየችው?” ሲል ሚስቱን አሰበ፡፡ ምሳ ከበሉ በኋላ የሴቶች ፀጉር ቤት እንደምትሄድ ነግራው፣ እዚህ እንዲጠብቃት ተስማምተው ነበር። እዚህ ከመምጣቱ በፊት ወደ አንድ ሆቴል ጎራ ብሎ ሶስት ደብል ኩርቫይዘር ኮኛክ ሲጠጣ አንድ ሰዓት አጥፍቷል፡፡ እዚህ ደግሞ ለግማሽ ሰዓት ያህል ተቀምጧል፡፡ ወደ ፀጉር ቤት የሄደችው ጥፍርዋን ለመሰራት ነበር፡፡ አንድ ሰዓት ተኩል ያህል ጊዜ ለምን እንዳልበቃት ግራ ገብቶታል፡፡
ወደ ኦሃዮ ሳንደስኪ የመጡት ለጫጉላ ሽርሽር ቢሆንም ሌላው ምክንያት ደግሞ የእሷ ቤተሰቦች እዚህ ስለሚኖሩም ጭምር ነበር፡፡ ወደዚህ ከመጡ አምስት ቀናት ተቆጥረዋል፡፡ የተጋቡት ግን ከአንድ ሳምንት በፊት ነው፡፡ ከሳምንት በፊት ይጋቡ እንጂ ትውውቃቸው የስድስት ወራት እድሜ ነበረው። አስተናጋጅዋ ያመጣችለትን ቡና እየጠጣ፣እንዴት እንደተዋወቁ አስታወሰ፡፡
ከስድስት ወራት በፊት የአንድ ታዋቂ ሰዓሊ የስዕል ኤግዚቢሽን እንዲጎበኝ የጥሪ ካርድ ደረሰው። እንደ ሌላ ግዜ ቢሆን ኖሮ ባልሄደ ነበር፡፡ ያን ቀን ግን ምንም ስራ ስላልነበረው ወደ ኤግዚቢሽኑ አመራ። ስእሎቹን እየተዘዋወረ ሲመለከት ድንገት አንድ ስዕል ላይ አይኖቹ ተተከሉ፡፡ የራሱ ምስል ነበር፡፡ ሰዓሊው በአስደናቂ ሁኔታ ስሎታል፡፡ በጣም በመገረም ስዕሉን እያየ ፈዞ ቀረ፡፡ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ የኤግዚቢሽኑ አዘጋጆች፣ ስዕሉን በሀምሳ ሺህ ዶላር መነሻ ዋጋ ለጨረታ አቀረቡት፤ ዊልያም በስድሳ ሺህ ዶላር እንደሚወስደው ገለፀ፡፡ አጫራቹ ማግባባቱን ቀጥሏል፡፡ አንድ አዛውንት ጣታቸውን አወጡ ፡- “70 ሺህ ዶላር”
አንድ ሽክ ብሎ የለበሰ ሰው፡- 80 ሺህ ዶላር ጠራ፡፡
እንዲህ እንዲህ እያለ ---- የስዕሉ ዋጋ 200 ሺህ ዶላር ደረሰ፡፡ እንደ ሙዚቃ የሚያምር የሴት ድምፅ፡- 250 ሺህ ዶላር ሲጠራ ነው ዊልያም ማን እንደሆነች ለማየት ወደ ኋላ የዞረው፡፡ አንዲት ነጭ ቀሚስ የለበሰችና ትልቅ እግሮቿን አጣምራ የተቀመጠች፣ የሚያፈዝ ውበት ያላት ሴት፣አቅል የሚያስት ፈገግታ መገበችው፡፡
በመጨረሻ 300 ሺህ ዶላር ከፍሎ ስእሉን በእጁ አስገባ፡፡ የወጣትዋ ሴት ነገር ግን ከአንጀቱ አልወጣም፡፡ የሱን ምስል 250 ሺህ ዶላር ከፍላ ለመግዛት ያሰበችው ለምን እንደሆነ የማወቅ ጉጉቱ፣ አጠገብዋ ቆሞ እጁን ለሰላምታ እንዲዘረጋ አስገደደው፡፡
“ዊልያም ስሚዝ እባላለሁ” አለ፤ ለስላሳ እጅዋን እየጨበጠ፡፡
“አውቅሃለሁ” አለችው፤ አይኖችዋን አይኖቹ ላይ እያፈዘዘች፡፡
“250 ሺህ ዶላር አቅርበሽ ነበር”
“ምን ዋጋ አለው? አንተ አሸነፍክ” አለችው፤ ቀለል ባለ አነጋገር፡፡
“ለምን ያን ያህል ዋጋ?” ጠየቀ
“በህይወቴ የማደንቀውን ሰው ምስል፣ መኝታ ቤቴ ግድግዳ ላይ ለመስቀል አስቤ ይሆናል”
“እውነት?” ልቡ መምታት ጀመረ፡፡
“አትገረም፤ የቤቴ ግድግዳ ባንተ ፎቶግራፍ የተሸፈነ ነው”
ከእሷ መለየት ሞት መስሎ ተሰማው፡፡ እንዲህ አይነት የሚያፈዝ ውበት አይቶ አያውቅም፡፡ ታዋቂና ዝነኛ ስለሆነ ሴቶችን የማግኘት እድሉ ከፍተኛ ቢሆንም አብዛኞቹ ገንዘቡን ፈላጊዎች ነበሩ፡፡ ለእነሱ ደሞ ቦታ አልነበረውም፡፡ እቺ የአማልክት ውበት ያላት ወጣት ሴት ግን የሱን ስእል በሩብ ሚሊዮን ዶላር ልትገዛ ተዘጋጅታ ነበር፡፡  
“እራት ብጋብዝሽ ደስ ይለኛል፤ እባክሽን” የሞት ሞቱን ከአፉ የወጡ ቃላት ነበሩ፡፡
“አስፈላጊ ነው?”
“ከምንም ነገር በላይ”
ዊሊያም ሬንዴቩ ካፌ ተቀምጦ ሲጋሩን እያጨሰ፣ ከሚስቱ ጋር የተዋወቀበትን አጋጣሚ በአይነ ህሊናው እየቃኘ፣ እግረ መንገዱን እሷን እየጠበቀ ነበር፡፡ ይሄን ያህል ጊዜ በመዘግየትዋ ግራ ተጋብቷል፡፡ ተንቀሳቃሽ ስልኩን አወጣና ቁጥርዋን መታ፡፡ ስልኳ ዝግ ነው፡፡ ሄዶ እንዳያገኛት  ፀጉር ቤቱን አያውቀውም፡፡ ምን ማድረግ እንዳለበት ግራ ተጋብቶ ደንዝዞ ቀረ፡፡ ሲጋሩን አጠፋና አንድ ቢራ እንድታመጣለት አስተናጋጅዋን አዘዛት፡፡
ቢራውን እየተጎነጨ የሰጠችውን ፍቅር አስታወሰ፡፡ የመጀመሪያውን እራት ከበሉ በኋላ ወደስዋ አፓርታማ ነበር ያመሩት፡፡ የሳሎንዋ ግድግዳዎች በሱ ፎቶግራፎች ተሸፍኖ ነበር፡፡ ንግግር ሲያደርግ፣ ቃለ መጠይቅ ሲሰጥ፣ ተኮሳትሮ፣ እየሳቀ ---- የሌለ አይነት ፎቶግራፍ አልነበረም። በርካታ ምሽቶችን አብረው አሳለፉ፡፡ ቀይ ወይን እየተጎነጩ፣ ከባህር ዳርቻው ላይ ማምሸት የዘወትር ምርጫቸው ነበር፡፡ ዊልያም በፍቅር አበደ፡፡ “ማመን አልችልም፤ ካንተ ጋር እንደዚህ አይነት ፍቅር ይኖረኛል ብዬ ገምቼ አላውቅም ነበር” አለችው፤ አንድ ምሽት እንደተለመደው ኮኛክ እየጠጡ መናፈሻው ውስጥ ተቀምጠው እያሉ፡፡
“አዲስ ያወቅኩሽ አይመስለኝም፤ ከድሮ ጀምሮ የማውቅሽ እንጂ፡፡ ይሄን ያህል ልቤ ውስጥ ነሽ” አላት፤ አይን አይንዋን እያየ፡፡
“ታዲያ ለምን አንጋባም?” አይኖችዋን አይኖቹ ላይ እያስለመለመች፡፡
በተዋወቁ በስድስተኛው ወር ጋብቻቸውን ለመፈፀም የከተማው ማዘጋጃ ቤት ቢሮ ውስጥ ተገኙ፡፡
“አብረን ባፈራነው ነው ወይስ ሀብትሽ ሀብቴ በሚል ነው የምትስማሙት?” ጠየቀ፤ አዋዋዩ፡፡ “በኔ በኩል ከሱ የሚደበቅ ሀብት የለኝም” አለችና፣ እጅዋን ጭኑ ላይ አሳርፋ፣ ፈገግ እያለች አይኖችዋን አይኖቹ ላይ ተከለች፡፡
“እኔም ከእርሷ የምደብቀው ሀብት የለኝም” አለ፤ የአይኖችዋን ኃይል መቋቋም ተስኖት፡፡
ሁለቱም ሰርግ የመደገስ ሀሳብ ስላልነበራቸው፣ያን ቀን ምሽት ቀለል ያለ ግብዣ ከቅርብ ጓደኞቻቸው ጋር ብቻ አደረጉ፡፡
ቢራውን እየተጎነጨ ሰዓቱን ተመለከተ፡፡ ከቀኑ አስር ሰዓት አልፎአል፡፡ ከሁለት ሰዓት ተኩል በላይ ዘግይታለች፡፡ አሁን ጥርጣሬ አዕምሮው ውስጥ ገባ። ቀላል መስሎት የነበረውን የትናንትናውን ማታ ፀብ አስታወሰ፡፡ በስልክ የወንድ ስም አቆላምጣ እያወራች በሰማ ጊዜ ሞገደኛው አመሉን መግታት አቅቶት፣ ስልኳን ከእጇ ነጥቆ፣ አሽቀንጥሮ ከጣለ በኋላ፣ አንገቷን አንቆ ከማን ጋር እንደምታወራ እየጮኸ ሲጠይቃት፤ “የድሮ ፍቅረኛዬ ነው፤ እኔ ትቸዋለሁ፤ እሱ ግን አሁንም ይወደኛል” አለችው፡፡
“እና ለዚህ ነዋ፣ ስሙን አቆላምጠሽ የጠራሽው” አለና የጥፊና የቡጢ መዓት ፊትዋ ላይ አወረደባት። ጩኸትዋን ስትለቀው፣ ሁለቱ የቤት ሰራተኞች ገላገሏቸውና፣ ቁና ቁና እየተነፈሰ ሶፋው ላይ ተቀመጠ፡፡ ከአይንዋ በታችና ጉንጭዋ በቡጢው በልዟል፡፡
ወጣ ብሎ ቢራውን ሲጨልጥ አምሽቶ እቤቱ ሲገባ፣ ተጠቅልላ አልጋዋ ውስጥ ተኝታ ነበር፤ ይቅርታ ከጠየቃት በኋላ ፊቷን ተመለከተው፡፡
“ሐኪም ቤት ሄጄ ነበር፤የሚችሉትን ሁሉ አድርገዋል አታስብ” አለችው፡፡
 አጠገብዋ ጋደም እንዳለ እንቅልፍ ወሰደው፡፡
ጠዋት ቁርስ ሲበሉ ጥቁር መነፅር አድርጋ ነበር፡፡ ቁርሱን የሰራችው እራስዋ ስለነበረች ሁለቱ ሰራተኞች የት እንደሄዱ ጠየቃት፡፡ ፍቃድ እንደወጡ ነገረችው፡፡ ሁለቱም አንድ ላይ ፍቃድ መውጣታቸው ባይዋጥለትም ዝም ብሎ ቁርሱን በላ፡፡ ረፋድ ላይ የከተማውን ገበያ ሲጎበኙና አንዳንድ እቃዎችን ሲሸማምቱ ዋሉ፡፡ ምሳ አብረው ነበር የበሉት፡፡ ከዚያ “ጥፍሬን ልሰራ፤ በግማሽ ሰዓት ውስጥ እመለሳለሁ” አለችውና፣እዚህ ካፌ እንዲጠብቃት ነግራው ከአይኑ ጠፋች፡፡ እሷን የበላ ጅብ እስካሁን ድረስ አልጮኸም። ቢራውን ጨልጦ ሂሳቡን ለመክፈል እጁን ወደ ኪሲ ሲሰድ፣አንድ ቀጭን ጨበሬ ፀጉር ያለው ወጣት፣ አንድ ፖስታ ይዞ ወደሱ ሲመጣ ተመለከተ፡፡
“ሚስተር ዊልያም ስሚዝ?” አለ አጠገቡ እንደደረሰ፡፡
“ነኝ” አለ - ዊልያም፡፡
“ይሄ ለርስዎ ነው” አለው ፖስታ እየሰጠው፤ “ከባለቤትዎ  ነው” አለና ወደ በሩ አመራ፡፡ ዊልያም ልቡ እየመታ ፖስታውን ከፈተና ማንበብ ጀመረ፡፡ በታይፕ የተመታ ፅሑፍ ነበር፡፡
“ለአራት አመታት ያህል ፎቶዎችህን ሰብስቤ በቀሌን ስደግስ ቆየሁ፤ አንተ ግን ስለማፈቅርህ የለጠፍኳቸው መስሎህ ነበር፡፡ ትወና ይሉሃል ይሄ ነው፡፡ ያንተ ስእል ለጨረታ ሲቀርብ 250 ሺህ ዶላር ስጠራ፣ አካውንቴ ውስጥ ግን ከሁለት ሺህ ዶላር በላይ አልነበረም፡፡ ነገር ግን ስዕሉን ለማንም አሳልፈህ እንደማትሰጥ አውቅ ነበር፡፡ ያንተንም ቀልብ ለመያዝ ቀላሉ መንገድ ነበር፡፡ ትወና ይሉሃል ይሄ ነው፡፡ ስንጋባ ካንተ የሚደበቅ ሀብት እንደሌለኝ መግለፄ፣ አንተም እንደዛ እንድትል ለመጋበዝ ነው፡፡ ትላንት አቆላምጬ የጠራሁት የወንድ ስም ቢሆንም በመስመር ላይ ግን ማንም ሰው አልነበረም፡፡
“በቅናት ተነስተህ ያደረግከውን እንደምታደርግ ስለማውቅ ነበር፡፡ የቤቱ ካሜራ ስትደበድበኝ የቀረፀው ፊልም እጄ ላይ ነው፡፡ ያከመኝ ሐኪምና ሁለቱ ሰራተኞች ካንተ ጋር መኖሬ ለህይወቴ እንደሚያሰጋኝ ለፍርድ ቤቱ ቃላቸውን ይሰጣሉ። ፍቺ እንድንፈፅምና በስምህ ካለው 300 ሚሊዮን ዶላር ግማሹን እንድትሰጠኝ ለፍርድ ቤቱ አመለክታለሁ፡፡ ትወና ይሉሃል ይሄ ነው፡፡
“የማክቤዝን ሚስት ሆኜ ስተውን፣ በህዝብ ፊት ያለ ርህራሄ አዋርደህና መሳለቅያ አድርገህ ከመድረኩ ስታባርረኝ፣ ልቤ ደምቶ ተንሰቅስቄ አልቅሼ ነበር። የማክቤዝን ሚስት ሆኜ መተወን ባልችልም፣ ያንተ አፍቃሪና ሚስት ሆኜ መተወን ግን አላቃተኝም፡፡ ደህና ሁን፡፡”  ዊልያም ወረቀቱን እንደያዘ፣ ደሙ ወደ አናቱ ሽቅብ ሲወጣ ይታወቀው ነበር፡፡

Read 3661 times