Saturday, 11 February 2017 14:04

የገነት ዓለም!!

Written by  ሚፍታ ዘለቀ
Rate this item
(1 Vote)

 ስለ ሥዕል ማውራት የገነትን ፊት የሚያበራ፣ መንፈሷን የሚያበረታ፣ ህመሟን የሚያስረሳ፣ ድምጿን ከፍ
የሚያደርግ ጉዳይ ነው፡፡ ------
             
      የዛሬ አምስት አመት ገደማ ማሕበራዊ ኃላፊነቱን በመወጣት በተለይ ለሥነ-ጥበብ ድጋፍ በማድረግ ከሚታወቅ ድርጅት ጋር በምሰራበት ወቅት ከሠዓሊ መሪኮከብ ብርሃኑ ጋር የመስራት እድሉ ነበረኝ። የስራውን ሃሳብ ሳቀርብላት ስሜቷ እየተቀያየረና በሃዘን ውስጥ ሆና፣ “ለart (ሥነ-ጥበብ) ብዙ መስዋዕትነት የከፈሉና ስራቸው ለሕዝብ ሊደርስ የሚገባ ጠንካራ ሠዓልያን እያሉ የኔ ስራዎችን ማቅረብ ከሌሎች ድካምና ጽናት አንጻር.....“ የሚል ብዙ ነገሮችን ማገናዘብ ከሚጠይቅ ረዘም ካለ ንግግር በኋላ እድሉን ለሚገባቸው እንድንሰጥ ጠየቀችኝ፡፡ ከማን ጋር በመስራት ብንጀምር አግባብነት እንደሚኖረው ስጠይቃት ፈጠን ብላ፣ “ገነት” አለችኝ፡፡ ስለ ሠዓሊ ገነት አለሙ ብዙም የማውቀው ስላልነበረኝ አንዳንድ ነገሮች እንድትነግረኝ ስጠይቃትም፣ “ገነት እኔ ልነግርህ ከምችለው የገዘፈ ዓለም ስላላት ራስህ ብታያት ይሻላል”  ብላ አድራሻዋን ሰጠችኝ፡፡
ሠዓሊ ገነት አለሙን ያገኘኋት ከአዲስ አበባ ውጪ የሚመስል፣ ጥሩ አየር ያለበት ሰፈር ውስጥ በተከራየችው መኖሪያና የስራ ቦታዋን ባጣመረ ቅጥር ግቢ ውስጥ ነበር፡፡ ከግቢው እስከ ዋናው ክፍልና ሌሎችም ክፍሎች ጭምር በሰራቻቸው ሥዕሎች፣ እየሰራቻቸው ባሉና ለሥዕል መስሪያ በምትጠቀማቸው ቁሶች የተሞሉ ነበሩ፡፡ በወቅቱ ብቻም ሳይሆን መላው ሕይወቷን በስራ የተጠመደች መሆኗን ከዚያች ቀን ጀምሮ ነበር ማየት የጀመርኩት። በዚያ ላይ ያኔ የሁለት አመት ተኩል እድሜ የነበረው ያሁኑ ባለ ልዩ የሥዕል ተሰጥኦው ብቸኛ ልጇ ልዑል፣ እዚህም እዚያም እያለ ለክፍሎቹ ገጽታ የበኩሉን ያደርግ ነበር፡፡ ስለ ስራዎቿ በስሜት ተሞልታ አጫወተችኝ፡፡ ስለ ሕይወቷ ስትነግረኝ ምሉዕ የሆነ መንፈሰ ጠንካራነቷን አጋራችኝ፡፡ የዚያች ቀን ግዙፉን ብቻ ሳይሆን ጥልቁን የሠዓሊ ገነት አለሙን “የገነት ዓለም” መተዋወቅ ጀመርኩ። የገነት ስራዎች እሰራበት የነበረው ድርጅት ውስጥ ከሚቀርቡ የሥነ-ጥበብ ስራዎች መሃል አንዱ እንዲሆኑ ያቀረብኩት ሃሳብ እንዲህ አይነት ሃሳቦች ላይ ውሳኔ በመስጠት በኃላፊነት ይሰራ ለነበረው ሠዓሊ የሚዋጥ ጉዳይ አልነበረም፤ ጭራሹን “ስራዎቹን ማቅረብ ተመልካችን ማደናገር ይሆናል፤ በዚያ ላይ ማንም ሥዕል መስራት ያቃተው ባቦሰጠኝ የሚሞነጫጭረው ሁሉ ሥዕል አይደለም” የሚል አስገራሚ ምላሽ ሰጥቶ ስራዎቿ ሳይቀርቡ ቀሩ። የተሞነጨረ ሁሉ ሥዕል ይሁን አይሁን ለመረዳት እንዲሁም ገነትን ለማወቅና ዓለሟን ለመረዳት የነበረኝ ፍላጎት ግን  ቀጠለ፡፡
ሠዓሊ ገነት አለሙ ተወልዳ ያደገችው እዚሁ አዲስ አበባ ሲሆን በ1990 ዓ.ም ከአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ አለ የሥነ-ጥበብና ዲዛይን ት/ቤት የተመረቀች ሲሆን በሕትመት ጥበብ ሙከራዎችን በማድረግና የምትሰራበትን ቁስ በራሷ ጥረት በማዳበር ትታወቃለች፡፡ ስራዎቿን በሃገር ውስጥና በውጪ ሃገራት ከማቅረብ ባሻገር በተለያዩ ሰርቶ ማሳያዎች ላይ ተሳትፋለች፡፡ ገነት የታላቁ ፖሎክ-ክራስነር ፍውንዴሽን ሽልማትን እ.ኤ.አ. በ2015 ወስዳለች፡፡
ገነት አለሙ በዘመንኛው የኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ ብቅ ማለት ብቻ ሳይሆን የተሟላ ሥነ-ጥበባዊ ማንነት ተላብሳ ራሷን መፍጠር እንዲሁም የራሷና የሥነ-ጥበባችን ጀግና መሆን የቻለች፤ የዚህን ዘመን ግንባር ቀደም ሠዓልያንን ስናነሳ ከፊተኛው መስመር በብርቱ ጥንካሬ የምናገኛት ሠዓሊ ናት። የስራዎቿን የምርምር አቅም፣ የጥልቅ ማንነቷን ጥንካሬ በስዕሎቿ የምትገልጽባቸው መንገዶችን፣ ለሙያዋ የከፈለቻቸው መስዋዕትነቶችንና ያዳበረችውን ፍቅር፣ ስለ ሥነ-ጥበብ ያላትን መረዳትና በጊዜዋ የሃገራችን ሥነ-ጥበብ ከደረሰበት ደረጃ አንጻር እንዲሻሻል ሊያደርጉ የሚያስችሉ በበኩሏ ያደረገቻቸው አስተዋጽኦዎችን፡ እንዲሁም  የምትሰራበት ቁስ ጥበብን በማዳበር ያደረገችውን ስንመለከት በሕይወት ዘመኗ የላቀ ሥነ-ጥበባዊ እሴት ያበረከተች ሠዓሊ ናት፤ገነት አለሙ፡፡ እኔ ስለ ገኒ ይበልጥ እንዳውቅ ያደረጉኝ ሁለት ትርዒቶችን በመዳሰስ እርስዎ እድለኛውና ውዱ አንባቢዬም የገነትን ዓለም እንዲቃኙ እጋብዝዎታለሁ። የመጀመሪያው ትርዒት እኔው ከአንድ አመት በፊት በጉራምዓይኔ የሥነ-ጥበብ ማዕከል ያጋፈርኩት “እሴት የተቸራቸው እሴቶች” ሲሆን ሌላኛው ደግሞ በአሁኑ ጊዜ እስከ የካቲት 14 ከአራት ኪሎ ወደ መገናኛ ሲሄዱ ራስ አምባ ሆቴል ከመድረስዎ በፊት በሚገኘው በአስኒ ጋለሪ ለዕይታ ክፍት የሆነው “Intimate Red” የተሰኘውና በሃገራችን የሥነ-ጥበብ ታሪክ የዘመንኛ የሥዕል ማሳያ በመክፈትና ሥነ-ጥበብን በማጋፈር ፈር ቀዳጅ በሆነችው ቆንጂት ስዩም የተጋፈረው ትርዒት ነው፡፡ መቼም ነቄ የሆነና የተመቻቸለት አንባቢ ትርዒቱን የመመልከት እድል ከቀናው ገነትንና ቆንጂትን ብቻ ሳይሆን ጥቆማውን ስለሰጠሁት እኔንም ሳያመሰግነኝ እንደማያልፍ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ቆንጂት ስዩምን ለማታውቋት አንባቢዎቼ፣ በሌላ እትም ሰፋ ያለ ጽሁፍ ይዤ እንደምቀርብ ቃል እየገባሁ፣ ስለ ገነት ዓለም በጥቂቱ ወደ ሚያስቃኙን ትርዒቶች እንሻገር፡፡
“እሴት የተቸራቸው እሴቶች” የተሰኘው ትርዒት የተወለደው ገነት እያስተናገደችው ካለው ህመም ነው ማለት ይቻላል፡፡ ህመሟም የጡት ካንሰር ነው። በ2005 ዓ.ም ነበር የካንሰር ታማሚ እንደሆነች ያወቀችው፡፡ ቀስ በቀስም በሰውነቷ ተሰራጭቶ ኃይሏን ሲያዳክምም ህክምና መከታተል ጀመረች። ከመድሃኒትና ከሕክምናው ባልተናነሰ ኃይል የሚሰጣትና የሚያበረታት ሥዕል መስራት እንደሆነ ከቤተሰብ እስከ ጓደኛ፣ ዶክተሮቿ እንዲሁም ማንኛውም ገኒን የሚያውቅ ሁሉ የሚረዳውና የሚገርመው ጉዳይ ነው፡፡ አምና ጥቅምት ወር አካባቢ ህመሙ ጠና እንዳለባት ስሰማ፣ ገኒን ካስተዋወቀችኝ ከሠዓሊ መሪኮከብ ጋር ላያት ሄድኩ፤ እናም ስራዎቿን ለሕዝብ ለማቅረብ የነበረኝ ፍላጎት በተለያዩ ምክንያቶች ባይሳካም “እሴት የተቸራቸው እሴቶች” የሚለው ትርዒትን የወለደው ውይይት ግን ተጀመረ፡፡ ስለ ሥዕል ማውራት የገነትን ፊት የሚያበራ፣ መንፈሷን የሚያበረታ፣ ህመሟን የሚያስረሳ፣ ድምጿን ከፍ የሚያደርግ ጉዳይ ነው፡፡ ቀጠልን፡፡
ከሠዓሊ ገነት አለሙ ጋር ስለ ስራዎቿ ስንወያይ ደጋግማ የምታነሳው ሃሳብ ለነገሮች ስለምትሰጠው ዋጋ፤ ማንኛውንም ነገር ዋጋ እንድንሰጠው የሚያስችሉ እሴቶችን እንዴት እንደምናዳብር የሚስገነዝቡ፣ ስራዎቿ የእሴቶችን ዋጋ የሚመረምሩ ከመሆናቸው አንጻር የሃሳቧንና የስሜቷን ጥግ የመንካት ብቻ ሳይሆን የመጣስ ሃይል ያላቸው መሆኑን ስራዎቿን እያየን ስንነጋገር እንደ ሠዓሊ ብቻ ሳይሆን ወደዚህች ዓለም የራሷን ታሪክ ለመጻፍ እንደ መጣች ሰው እረዳት ጀመር፡፡ ይህ ሁሉ ደግሞ ከአየር የተዛቀ፣ ከሕልም-ዕልም የተጨለፈ ሳይሆን ከኑሮዋ የተቀዳ፣ ከኖረችው እውነታ የተመዘዘ እንጂ የያኔው ባልደረባዬ እንዳለው፤ ሥዕል መስራት አቅቷት ባቦሰጠኝ የሞነጫጨረችው እንዳልነበር ግልጽ ነው፤ ሥነ-ጥበብን የማየት ልምድ ያካበተ ብቻ ሳይሆን የሚያገናዝብ አዕምሮ ያለው ማንኛውም ሰው ትንሽ የማርያም መንገድ የሰጡት ተመልካች ልቦና ሰተት ብለው የሚገቡ ጠንካራ ስራዎችን የምትሰራበት ምክንያትም ለእሴቶች በሰጠችው ዋጋ እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡
ተፈጥሮአዊ በሆኑ አካሎች ላይ የምናገኛቸው ቅርጾች (forms) በአብዛኛው ጂኦሜትሪካዊ ያልሆኑና ከሰው ሰራሽ ቅርጾች በተለየ የመተጣጠፍ፣ የመዟዟር ባሕርይ እንዳላቸው ይታወቃል፡፡ በአንጻሩ ደግሞ የሰው ልጅ አሻራ የሚያርፍባቸው ሰው ሰራሽ ነገሮች ቀጥታና የቅርጾቹ ባሕሪም ውስንነት ያለባቸው ናቸው። ለገነት ሥነ-ጥበባዊ እሳቤዎች ቅርብ የሆኑት ነጻነት በተሞላ መልኩ የሚዟዟሩት፣ የሚተጣጠፉት፣ባሻቸው የውፍረትና የቅጥነት መጠን የሚሰፉትና የሚጠቡት፣ ባሻቸው አቅጣጫ የሚንሰራፉት፣ ረጅምና አጭር ሆነው ዝብርቅርቅ ባለ መዋቅር የራሳቸውን ውበትና ባሕሪይ ለሚያንጸባርቁት የተፈጥሮ ቅርጾች ልዩ ቦታ ስላላት፣ እነሱን በመሳሰሉ ቅርጾች እንደምትማረክ ትገልጻለች። በነዚህ ቅርጾች ከመማረኳ ጀርባ ያለውና ወደ ሥነ-ጥበብ ስራነት እንድትቀይራቸው የሚያስገድዳት ምክንያት ደግሞ የነዚህ ቅርጾች የነጻነት ባሕሪይ እንደሆነ ታስረዳለች፡፡
በዚህም ምክንያት ታላቅ ዋጋና እሴት የምትሰጠው ጉዳይ ሆኖ የስራዎቿ አንድ መገለጫ ሆኗል፡፡ እነዚህ ተፈጥሮአዊ ቅርጾች የሚያካሂዱት ተፈጥሮአዊ ሂደትና ዑደት ደግሞ የተለያዩ እሴቶችን እንደሚወክልላትና ዋጋ ከምትሰጣቸው እሴቶችም መሃል እድገት፣ ማንሰራራት፣ በሕልውና መቆየት..... የመሳሰሉት እሳቤዎች ለተሸከሙት እሴት የምትሰጠው ዋጋ የሥነ-ጥበብ ስራዎቿ አነሳሽ ኃይል እንደሆነ ገነት በጥልቅ ስሜት ትናገራለች፡፡ እነዚህ እሳቤዎች የተሸከሙት እሴት፤በእያንዳንዷ የሕይወታችን ቅጽበት ልዩነት የማምጣት ኃይል እንዳላቸው ስትናገርም፤የራሷን ልምድ እንደ ምሳሌ አድርጋ ነው፡፡ በዚህም ነው በካንሰር የሚሞቱ ህዋሶቿን፣ሥዕል በመስራት የምትሞላቸውና እየሞላቻቸው ያለችውም፡፡ ሳምንት በዚህ ጽሁፍ ቀጣይ ክፍል እስከምንገናኝ ድረስ የሰዓሊ ገነት አለሙን የስዕል ትርኢት በአስሊ አርት ጋለሪ እንድትጎበኙ በአክብሮት እየጋበዝኳችሁ መልካሙን ሁሉ ተመኘሁ፡፡ የሳምንት ሰው ይበለን!!

Read 1017 times