በአውደርእዩ ላይ የቀረቡት ፎቶግራፎች፤ ባህል፣ የማንነት ጥያቄና አብሮነት ላይ የሚያተኩሩ ሲሆን ፎቶግራፎቹ ከ2400 ብር እስከ 10,800 ብር የዋጋ ተመን ወጥቶላቸዋል፡፡ የዋጋውን መወደድ በተመለከተ ተመልካቾች ያነሱትን ጥያቄ ያቀረብንላት አርቲስቷ፤ “ሰው ፎቶግራፍ ማድነቅንና መግዛትን እንዲለምድ ዋጋው ዝቅ ብሎ ነው እንጂ በሌሎች ሀገራት የበለጠ ያወጣል” ብላለች፡፡ በ16 ዓመቷ ወደ ፎቶግራፍ ሙያ የገባችው አይዳ ሙሉነህ፤ በአውደ ርዕዩ ላይ የ12 ዓመት ሥራዎቿን ስብስብ አቅርባለች፡፡ ፎቶግራፈሯ በአሁኑ ወቅት በገብረክርስቶስ ደስታ ሥነጥበብ ቤተመዘክር በዳይሬክተርነት እየሰራች ትገኛለች፡፡