Saturday, 11 February 2017 13:21

ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ባምላክ ተሰማ ከጋቦን መልስ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

 • ባምላክ ተሰማ 3 የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዎች አጫውቷል፤ የመራቸው ዓለማቀፍ ጨዋታዎች ከ50 በላይ         ሆነዋል፡፡ ከአፍሪካ 27 ኤሊት ዋና ዳኞች አንዱ ነው፤ በዓለም ዋንጫ እጩ ዳኝነት 10ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡
       • የፌደራል ዳኞች ብዛት ከ250 ወ ደ 412 ከፍ ያለ ሲሆን፤ ለዳኝነት ክፍያ ከተወዳዳሪ ክለቦች ቡድኖች                  የሚሰበሰበው 19.35 ሚሊዮን ብር፤ ለዳኞች የውሎ አበል የሚከፈለው እስከ 30 ሚሊዮን ብር ደርሷል፡፡
       • ዓለም አቀፍ ደረጃ ተሰጥቷቸው በዋና ዳኝነት እና በረዳት ዳኝነት በሁለቱም ፆታዎች የተመዘገቡት 22                 ኢትዮጵያን ናቸው፡፡ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው ኢንተርናሽናል ዋና ዳኞች በወንዶች 7፤ በሴቶች 4 ሲሆኑ         በኢንተርናሽናል ረዳት ዳኝነት የተመዘገቡት ደግሞ 7 ወንዶች 4 ሴቶች ናቸው፡፡
       • በፊፋ የተመዘገቡ ኢንተርናሽናል ዋና ዳኞች እና ረዳት ዳኞች 22 ናቸው፡፡ በዋና ኢንተርናሽናል ዳኝነት 7 ወንድ           4 ሴት፤ በኢንተርናሽናል ረዳት ዳኝነት 7 ወንድ 4 ሴት ደግሞ 7 ወንዶች 4 ሴቶች ናቸው፡፡

     ከኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ባምላክ ተሰማ ጋር ሰሞኑን በተገናኘንበት ወቅት የዳኝነት ሙያ ከሚዲያ ጋር ባለው ግንኙነት እጅግ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልገው በሰጠኝ ልዩ ማብራርያ ነበር ቃለምልልሱን የጀመርነው፡፡ ለ31ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ጋቦን በነበረበት ወቅት በማህበራዊ ሚዲያ እከታተለሁ ስለነበር፤ በሙያ አሁን ያለበት ደረጃ በተምሳሌትነት መዳሰስ እንደሚገባው በመግለፅ ከስፖርት አድማስ ጋር ቃለምልልስ ያደርግ ዘንድ መልዕክቶችን ሳደርሰው ነበር፡፡ 31ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ከተጠናቀቀ ከ4 ቀናት በኋላ ሐሙስ እለት ተገናኝተን በስልክ ይህን ልዩ ቃለምልልስ አድርገናል፡፡ ከጋቦን መልስ ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ባምላክ ተሰማ በተማረበት የህክምና ምርምር ፕሮፌሽናል ሙያው ወደ የሚሰራበት መስርያ ቤት በመግባት ስራን በመቀጠሉ የተጣበበ ግዜ ነው ያለው፡፡
ወደ ቃለምምልሱ ከመግባታችን በፊት ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ባምላክ ተሰማ ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ባምላክ ተሰማ  ያስተላለፈው የምስጋና መልክቶች ነበሩ፡፡ እንዲህ በማለት… ‹‹የእግር ኳስ ዳኝነት የግል ጥረት ብቻ አይደለም፡፡ ዛሬ ለሰደረስኩበት ደረጃ ድጋፎች ለሰጡኝ የስፖርቱ ባለድርሻ አካላት ምሰጋና ማቅረብ እፈልጋለሁ ፡፡ የእግር ኳስ ፌደሬሽን፤ የእግር ኳስ ተመልካች፤ ክለቦች፤ ብሄራዊ ቡድኖች እና ሌሎችም በሙያዬ በተጓዝኩበት ርቀት እና ወደፊት ለምከተለው አቅጣጫ የማይተካ ሚና ስላላቸው ሁሌም  ቅድሚያ የምሰጠው ልባዊ ምስጋናዬን መግለፅ ነው፡፡  ሙያችንን በአግባቡ እና በትኩረት እንድንሰራ ተከታትለው በገንቢ አስተያየቶች ለሚደግፉን የስፖርት ጋዜጠኞችም ልዩ አድናቆት አለኝ፡፡ ከዳኝነት ሙያው ባሻገር በፕሮፌሽናል ሙያዬ በህክምና ምርምር የምሰራበት የጤና ተቋም እና የስራ ባልደረቦቼ የሚሰጡኝ ማበረታቻም  ይመሰገናል። ከሁሉም በላይ ደግሞ በዳኝነት ሙያው ያሉ አጋር ዳኞች፤ መምህራኖች፤ የዳኝነት ሙያ ኢንስትራክተሮች፤ የጨዋታ ታዛቢ እና ገምጋሚ ኮሚሽነሮች አስተዋፅኦዎች ወሳኝ መእንደሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ በእግር ኳስ ፌደሬሽን ስር ሆነን በየጊዜው በምንመራቸው ጨዋታዎች፤ ሙያችንን፤ የአካል ብቃታችን ለማሳደግ በምንሰራቸው ዝግጅቶች እና ስልጠናዎች ላደረጉልኝ እና ለሚያደርጉልኝ ሁሉ መመስገን አለባቸው፡፡›› በሌላ በኩል ሳልጠቅስ የማላልፈው ለኢትዮጵያ የእግር ኳስ ተመልካች ያለኝን ልዩ አድናቆት እና ክብር ነው። የስፖርት አፍቃሪው በሜዳ ውስጥ እና ከሜዳ ውጭ ለእግር ኳስ በሚያሳየው ፍቅር እና እውቀት ሁሌም እንደተማረኩ ነው፡፡ በተለይ በሙያችን ላይ በየጊዜው እና በየአጋጣሚው በሚሰጡት አስተያየት ብዙ ተምሬያለሁ። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ተመልካቾች ኳስን በጥልቀት የሚያዩ ናቸው፤ ከእነሱ አድናቆታቸውን ሳገኝም ትልቅ የሞራል ብርታት ይሆነኛል፡፡ በየክልሉ በየሄድኩበት ሁሉ የእግር ኳስ ተመልካቹ ስለ ስፖርቱ ከልቡ ሲያወያየኝ እና በአገልግሎቴም ተደስቶ ሲያመሰግነኝ ደስ ይለኛል። ስለሆነም ለሁሉም ልባዊ ምስጋናዬን አስተላልፍልኝ››
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ዳኝነቱ ያለበት ደረጃ
ባለፉት አራት ዓመታት በሁለቱም ፆታዎች የዳኝነት ሙያ በኢትዮጵያ እግር ኳስ እየተጠናከረ መጥቷል፡፡ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ በዳኝነት ሙያ በትኩረት በመስራቱም ብዙ እድሎች እየተፈጠሩ ለውጦችም በመታየት ላይ ናቸው። የፌደራል ዳኞች ብዛት ከ250  ወደ 412 ከፍ  ማለቱን የሚጠቅሰው የእግር ኳስ ፈደሬሽኑ የ2008 ዓ.ም ሪፖርት፤ ባለፈው አመት ብቻ በክልል ፌደሬሽኖች ጥያቄ በ23 የስልጠና ፕሮግራሞች ተዘጋጅተው፤ ለ854 ጀማሪ እና 1ኛ ደረጃ ዳኞች በተሰጠው ስልጠና 761 ፈተናውን በማለፍ የብቃት ማረጋገጫ አግኝተዋል፡፡ በተለይ በሶስት የስልጠና ፕሮግራሞች 114 ዳኞችን ወደ ፌደራል ዳኝነት ደረጃ ማደግ ችለዋል፡፡ በሌላ በኩል የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ በ2009 ዓ.ም ሊሰራ ባስቀመጣቸው እቅዶች ዝርዝር በዳኝነት ዙርያ የተጠናከሩ እንቅስቃሴዎች ለማከናወን ይፈልጋል፡፡ የዳኞችን አቅም ለመገንባት በተያዘው እቅድ የተለያዩ የዳኝነት ስልጠናዎችን በማመቻቸት እና ከክልሎች ጋር ተቀናጅቶ በመስራት 400 ጀማሪ/ሁለተኛ ደረጃ/ 100 የአንደኛ ደረጃ 400 የፌደራል ደረጃ በድምሩ 900 የእግር ኳስ ዳኞችን ለማሰልጠን ታስቧል፡፡  በ2009 ዓ.ም በ11 የተለያዩ የውድድሮች ዓይነቶች   1669 ጨዋታዎችን እንደሚያካሂድ የሚገልፀው ፌደሬሽኑ፤ ሁሉንም ውድድሮች 8385 ዳኞች፤ _ኮሚሽነሮች እና ሌሎች ሙያተኞች በመመደብ በብቃት ለመምራት አቅዷል፡፡ በ2008 ዓ.ም የተለያዩ ውድድሮችን ዳኝነት በስኬት ለማካሄድ ፌደሬሽኑ ከክለቦች የዳኝነት ቅድመ ክፍያ 19 ሚሊዮን 348ሺ 320 የሰበሰበ ሲሆን በሁሉም ውድድሮች ለተመደቡ ዳኞች እና የጨዋታ ኮሚሽነሮች አስቀድሞ የነበረውን የሙያ እና የውሎ አበል በእጥፍ በማሳደግ 29 ሚሊዮን 714 ሺህ 294 ብር ከፍሏል፡፡ በ2009 ዓ.ም ከክለቦች የሚሰበሰበው የዳኝነት ቅድመ ክፍያ ወደ 20 ሚሊዮን ብር የሚያድግም ይሆናል፡፡
ከአገር አቀፍ ውድድሮች ባሻገር በዓለም አቀፍ ደረጃ ማረጋገጫ የተሰጣቸው ዳኞችም ብዛ ተሻሽሏል። በፊፋ ኦፊሴላዊ ድረገፅ ዓለም አቀፍ ደረጃ ተሰጥቷቸው በዋና ዳኝነት እና በረዳት ዳኝነት በሁለቱም ፆታዎች የተመዘገቡት 22 ኢትዮጵያን ናቸው፡፡ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው ኢንተርናሽናል ዋና ዳኞች በወንዶች 7፤ በሴቶች 4 ሲሆኑ፤_ በኢንተርናሽናል ረዳት ዳኝነት የተመዘገቡት ደግሞ 7 ወንዶች  4 ሴቶች ናቸው፡፡  
ኢንተርናሽናል ዋና ዳኝነት በ‹‹ኤሊት ኤ›› ደረጃ
በአፍሪካ እግር ኳስ በከፍተኛው የኤሊት ኤ ዳኝነት ደረጃ ይዘው የሚገኙት 27 ዋና ዳኞች ናቸው፡፡ 26ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ደግሞ ባምላክ ተሰማ ነው። የዳኝነት ሙያውን በ2003 እ.ኤ.አ ላይ የጀመረው ባምላክ፤  በ2009 እ.ኤ.አ በፊፋ ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን በኤሊት ኤ ደረጃ የሚሰራ በመሆኑ፤  በአህጉራዊ፤ ዓለም አቀፍዊ የክለብና የብሄራዊ ቡድን ጨዋታዎች እየተመደበ መዳኘት ይችላል፡፡ የእግር ኳስ ዳኝነት በተለያዩ ሂደቶች እያደገ የሚሄድ ነው፡፡ መነሻው ጀማሪ ዳኝነት ሲሆን፤ ያንግ ታለንት፤ ኤሊት ቢ እንዲሁም ኤሊት ኤ በሚባሉ ማዕረጎች የዳኝነት የብቃት ደረጃዎች የሚያልፍባቸው ሂደቶች ናቸው፡፡ ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ባምላክ ተሰማ ይህን አስመልክቶ ለስፖርት አድማስ ማብራሪያን ሲሰጥ…. ‹‹ በኤሊት ኤ ማዕረግ ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ደረጃ ላይ ለመድረስ በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ደንብ መሰረት  ከያንግ ታለንት ከሚለው ማዕረግ በመነሳት ነው፡፡  ይህ ሂደት ቢያንስ  3 ዓመት ቢበዛ ስድስት ዓመት የሚፈጅ ሲሆን እድገቱ እንደ ዳኛው የጨዋታ ልምድ እና ፈጣን መሻሻል የሚወሰን ነው። ኤሊት ኤ ደረጃ የደረስኩት በ2011 እኤአ ላይ በያንግ ታለንት ጀምሬ ከአምስት አመት በኋላ ነው፡፡››
በአፍሪካ ዋንጫ አገርን እንደ ብሄራዊ ቡድን መወከል
ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ባምላክ ተሰማ ጋቦን ባስተናገደችው 31ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ውክልናው በኢትዮጵያ ብቻ የተወሰነ አልነበረም፡፡ በዋና ዳኝነት በአፍሪካ ዋንጫ እንዲሳተፍ ከምሥራቅ አፍሪካ አገሮች በብቸኝነት እንደተመረጠም ይታወቃል፡፡  ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ባምላክ ተሰማ ዘንድሮ በአፍሪካ ዋንጫ  ለሁለተኛ ጊዜ ተሳትፏል፡፡ በዚህ ልምዱም በምስራቅ አፍሪካ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ከደረሱ የወቅቱ ዳኞች ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ይሆናል፡፡ ኢንተርናሽናል ዋና ዳኝነቱን በሴካፋ ሻምፒዮናዎች ሰፊ ተሳትፎ በማግኘት ማጠናከር የቻለ ሲሆን ፤  በተለያዩ የአፍሪካ ክለቦች  ውድድሮች በመስራት የዳበረ ልምድ ነበረው፡፡ በተለይም ደግሞ የአህጉሪቱ ትልቁ ውድድር በሆነው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ  አገሩን  ሲያስጠራ ተምሳሌትነቱ አድጓል፡፡ ከጋቦኑ 31ኛው የአፍሪካ ዋንጫ  በፊት በ2013 እኤአ በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ባያጫውትም በዳኞች ፓናል ተሳትፎ ነበር፡፡ ከዚያም በ2015 እኤአ ላይ ኢኳቶሪያል ጊኒ ባስተናገደችው 30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ደግሞ በዋና ዳኝነት እና ሌሎች ሃላፊነቶች ተመድቦ ሰርቷል፡፡  በአፍሪካ ዋንጫ ደረጃ በዳኝነት ሙያው ስለነበረው ተሳትፎ ሲናገር…. ‹‹በአፍሪካ ዋንጫ ላይ በዳኝነት ሃገርን መወከል ትልቅ ክብር እና ስኬት ነው፡፡ በኢትዮጵያ የእግር ኳስ ታሪክ የነበሩ አንጋፋና ቀደምት ዳኞች  በአፍሪካ ዋንጫ የግማሽ ፍፃሜ እና የዋንጫ ጨዋታዎችን መምራታቸውን አውቃለሁ፡፡ ይህን ታሪካቸውን ለመጋራት በሚያስችለኝ አቅጣጫ እያደግኩ መሆኔን ያረጋገጥኩበት ተሳትፎ ስለሆነም ከፍተኛ ኩራት ይሰማኛል፡፡ በነገራችን ላይ  በአፍሪካ ዋንጫ ላይ ኢትዮጵያን በመወከል በዋና ዳኝነት መሳተፍ ስችል የዘንድሮው ሁለተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ቢሆንም 3ኛዬ ሊሆን ይችል ነበር፡፡  በ2013  እኤአ ላይ ደቡብ አፍሪካ ባዘጋጀችው 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በዋና ዳኝነት ለመሳተፍ  ተስፋ ነበረኝ፡፡ በተካሄደው ምርጫ ለጥቂት ሳይሳካልኝ በመቅረቱ ቁጭት ተፈጥሮብኛል፡፡ በወቅቱ ከ28 ዓመታት  መራቅ በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ ካለፈው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ጋር የመጀመርያውን የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ማሳካት ብችል ትልቅ ክብር ይሆን ነበር፡፡ በ2013 እኤአ ላይ በደቡብ አፍሪካ በዳኞች ፓናል ውስጥ በመካተት የአፍሪካ ዋንጫውን ተከታትየዋለሁ፡፡ ከዚያ በኋላ ግን በ2015 እኤአ ጊኒ ቢሳዎ ባስተናገደችው 30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ የመጀመርያውን የአፍሪካ ዋንጫ በዋና ዳኝነት በመመረጥ አገሬን በመወከል ተሳትፌያለሁ። በአፍሪካ ዋንጫ በዋና ዳኝነት የመራሁት የመጀመርያ ጨዋታዬ  በምድብ ሶስት ካሜሩንና ጊኒ ያካሄዱት ነበር። በወቅቱ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ባለመኖሩ ተሳትፎዬ የብሄራዊ ቡድኑ ውክልናን የተካ በሚል በመደነቁ በጣም ሞራል ያገኘሁበት ነበር፡፡
እነሆ በ2017 እኤአ ጋቦን ባስተናገደችው 31ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ በዋና ዳኝነት ተመርጬ ለመስራ በቅቻለሁ፡፡ በ31ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በአራት ጨዋታዎች የተሳተፍኩ ሲሆን  ሁለቱን ጨዋታዎች በዋና ዳኝነት በሁለቱ ጨዋታዎች ደግሞ በተጠባባቂ ዳኝነት ሃላፊነት ተሰጥቶኝ ነበር፡፡ በዋና ዳኝነት ያጫወትኩት የመጀመርያ ጨዋታ በስታዴ ዴ ፍራንኪቪል በምድብ 2 አልጄርያ እና የዚምባቡዌ የተገናኙበት ጨዋታ ነበረ፡፡ ከዚያ በኋላ በተጠባባቂ ዋና ዳኝነት የሰራሁት ደግሞ ጋቦን ከቡርኪናፋሶ ባደረጉት ጨዋታ ላይ ነው፡፡ በመቀጠል ደግሞ በዋና ዳኝነት የመራሁት በምድብ 1 ጨዋታ ቱኒዚያ ከ ቡርኪናፋሶ ያደረጉት ነበር፡፡ በመጨረሻ ለሁለተኛ ጊዜ በዋና ተጠባባቂ ዳኝነት እንድሰራ በተሰጠኝ ሃላፊነት የሞሮኮና የግብፅን ጨዋታ ላይ ተሳትፊያለሁ፡፡›  በ31ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ባምላክ በሁለት ጨዋታዎች ተጠባባቂ ዋና ዳኛ መሆኑን እንዲያብራራ ከስፖርት አድማስ ጥያቄ ቀርቦለት በሰጠው ምላሽ … ‹‹በነገራችን ላይ ተጠባባቂ ዳኛ ማለት ዋና እና ረዳት ዳኞችን በማንኛውም ሁኔታ ተክቶ ወይንም ቀይሮ በመግባት የሚያጫውት ብቻ አይደለም ሌሎች ሃላፊነቶችም አሉት፡፡ በተጠንቀቅ ሆኖ በስታድዬም ይገኛል፡፡ ከዚያ በፊት ከዳኝነት ስራ ጋር የተያያዙ የአስተዳደር ስራዎችን ያከናውናል፡፡ ተጨዋቾችን ይቀይራል፡፡ ቴክኒካል ጉዳዮችን ይከታተላል፡፡ ለዋና ዳኛ እና ለረዳት ዳኞች በተለያዩ የጨዋታ ሁኔታዎች ዙርያ በቅርበት በመስራት ው ምክሮች ይሰጣል፤ መረጃዎችን ያቀብላል፡፡….›› ሲል ተናግሯል፡፡
በኢንተርናሽናል ዋና ዳኝነት የባምላክ ተሰማ ሌሎች ልምዶች
በዋና ዳኝነት የመጀመርያ ኢንተርናሽናል ጨዋታውን በ2010 እ.ኤ.አ ጅቡቲን ከዩጋንዳ በማጫወት ጀመረ። ከዚያም በሴካፋ ሻምፒዮና በ2010 እ.ኤ.አ 5 ጨዋታዎች፤ በ2011 እ.ኤ.አ 4 ጨዋታዎች እንዲሁም በ2012 እ.ኤ.አ በታንዛኒያ ዳሬሰላም የፍፃሜ ጨዋታን መርቷል፡፡ በ2015 እ.ኤ.አ ላይ በሩዋንዳ አዘጋጅነት በተካሄደው የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ የሰራ ሲሆን፤ በ2016 እ.ኤ.አ በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ እና ኮንፌደሬሽን ካፕ፤ በ2017 ደግሞ የአፍሪካ ዋንጫ የማጣርያ ጨዋታዎችን አጫውቷል፡፡  ባምላክ ተሰማ በሁለቱ የአፍሪካ ዋንጫዎች የነበረውን ተሳትፎ ጨምሮ  በካፍ የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግና ኮንፌዴሬሽን ካፕ፤ በ2013 የአፍሪካ ሀ 20 ሻምፒዮና፤ በዓለም ዋንጫ እና በአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታዎች ፤ በአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ (ቻን) እንዲሁም በሴካፋ ሻምፒዮና እስከ 50 ጨዋታዎችን በዋና ዳኝነት፤ በአራተኛ ዳኝነት እና በሌሎች የሃላፊነት ድርሻዎች ሊመራ ችሏል፡፡
የዳኞች ዝግጅት እና ልምምድ
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮፌደሬሽን በአፍሪካ ዋንጫ  የሚሳተፉ ዋና  ዳኞች እና ለረዳት ዳኞች  የሚመርጠው በተለያዩ ደረጃዎች በሚሰጣቸው ፈተናዎች ነው፡፡ ለዘንድሮው አፍሪካ ዋጫ ዳኞቹ ሲመለመሉ በመጀመርያ ከሁለት ወራት በፊት በግብፅ ካይሮ በአፍሪካ የተለያዩ አገራት ለሚገኙ ኤሊት ወና እና ረዳት ዳኞች የተሰጠ ፈተና ነበር፡፡ ጋቦን ከተገባ በኋላ ውድድሩ ከመጀመሩ በፊት ሌሎች ፈተናዎች የተሰጡ ሲሆን ከመላ አህጉሪቱ የተመረጡት ዳኞች የአንድ ሳምንት የተሃድሶ ስልጠና ማግኘት ነበረባቸው፡፡ በአካል ብቃት እና በቴክኒክ ላይ ያተኮሩ የተለያዩ ስልጠናዎች ፤ ፈተናዎች እና የህክምና ምርመራዎች እና በቡድን በሚካሄዱ የምክክር ስብሰባዎች ዳኞቹ ማለፍ አለባቸው፡፡
ባምላክ ተሰማ በአፍሪካ ዋንጫ ደረጃ በዋና ዳኝነት እና በሌሎች የዳኝነት ደረጃዎች ለሚያገለግልባቸው የሃላፊነት ድርሻዎች በተለያዩ ደረጃዎች የሚጠየቁ መመዘኛዎችን ማለፍ እንደሚያስፈልግ ለስፖርት አድማስ ሲያስረዳ… ‹‹ የአፍሪካ ዋንጫን የሚመሩ ዳኞች  የሚመረጡባቸውን መስፈርቶች በብቃት ለማለፍ እንደማንኛውም ስፖርተኛ ከፍተኛ ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህም  የአፍሪካ ዋንጫው ከመጀመሩ በፊት ከፍተኛ ዝግጅት እና ልምምድ በአካል ብቃት እና በስነልቦና ማረግ ነበረብኝ፡፡ ማንኛውም በኤሊት ኤ ደረጃ ዋና ዳኛ በመሆን ተመድበህ ለምትመራው ጨዋታ  በሜዳ ውስጥ ከ8 እስከ 10 ኪሎሜትር የምትሯሯጥበት የተሟላ የአካል ብቃት ያስፈልገሃል፡፡ አሁን በአፍሪካ  ዋንጫው ላይ ሳጫውት በእጃችን የምናስረው ሰዓት በሜዳ ውስጥ የምትሸፍነውን ጨዋታ የሚለካ ስለነበር እስከ 10.5  ኪሎሜትር መሮጤን አስተውያለሁ፡፡ እናም በአንድ ጨዋታ እነዚህን የጠቀስኳቸውን ኪሎሜትሮች መሸፈን የሚያስፈልግህ ከሆነ ከጨዋታው በፊት ጠንካራ ዝግጅት መስራትህ ግድ ነው፡፡ በአንድ ሳምንት ውስጥ በመደበኛው የልምምድ መርሃ ግብርህ የምትሰራ ከሆነ የእረፍት ቀናቶችህ ሁለት ብቻ ናቸው፡፡ አምስቱን ቀናቶች ልዩ የአካል ብቃት የሚያዳብሩ ልምምዶች  በተለያዩ የጫና ደረጃዎች መስራት ይኖርብሃል፡፡ እነዚያን ልምምዶች በተሟላ ዲስፕሊንና ትጋት መስራ ካልቻልክ ቅድም የጠቀስኩትን ከ8 እስከ 10 ኪሎሜትር በጨዋታ ሜዳ ለመሮጥ አትችልም ማለት ነው፡፡ በየልምምዱ የፍጥነት፤ የአካል ብቃት፤ ቅልጥፍና፤ ትንፋሽ እና ሌሎችንም የምታዳብርባቸው ስፖርቶችን መስራት የሚያስፈልግ ሲሆን፤ በጂም የታገዙ የአካል ብቃት ስራዎችም ወሳኝ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ የዳኞች የልምምድ መርሃ ግብሮች እና ዝግጅቶች  የግድ ለምትመራቸው ጨዋታዎች ብቻ ሳይሆን ጨዋታዎች በሌሉበት ጊዜም አስፈላጊ ነው። እንደውም የሚገርምህ ጨዋታ በሌሉባቸው የእረፍት ቀናት ልክ እንደ እግር ኳስ ተጨዋቾች መጠናኛ እረፍት ቢኖርም መደበኛ የልምምድ እና የዝግጅት መርሃ ግብሮችን አጠናክረህ መስራት ይጠበቅበሃል፡፡ በተለይ ዳኞች የሊግ ውድድሮች በሚዘጉባቸው የእረፍት ቀናት እና ጨዋታዎች ከሌሉ የዝግጅት ጫናው የሚጠናከርም ይሆናል፡፡ ጨዋታ  በሚኖርባቸው ሳምንቶች አስተካክለህ ለምትሰራቸው የልምምድ መርሃ ግብሮች በእረፍት ጊዜያት የምትወስዳቸው የልምምድ ጫናዎች የተሻለ ብቃት እና አፈፃፀም እንዲኖርህ ያደርጋሉ፡፡ በሌላ በኩል ፊፋ በአንድ የውድድር ዘመን ማለትም በየ3 ወሩ ፈተና እየሰጠ ያለህበትን የብቃት ደረጃ ለአራት ጊዜያት ስለሚፈትንም ከዚያ አንፃር ብቁ ሆኖ መገኘት ያስፈልጋል። በአጠቃላይ የዳኝነት ሙያ ዋና የአቋም መለኪያ የአካል ብቃት በተሟላ ሁኔታ መገኘቱ ነው፡፡››
የዳኝነት ክፍያው
ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ባምላክ ተሰማ ከስፖርት አድማስ ዳኞች ከሙያ ስለሚያገኙት ክፍያ ተጠይቆ ‹‹የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግን አንድ ጨዋታ በሃላፊነት ለመምራት ለዋና   ዳኛ   1ሺ ብር ለረዳት ዳኞች ደግሞ 850 ብር በነፍስ ወከፍ ይከፈላቸዋል፡፡ በብሄራዊ ሊግ ደግሞ  ለዋና   ዳኛ   850 ብር ለረዳት ዳኞች ደግሞ 750 ብር በነፍስ ወከፍ ይከፈላል፡፡ በኢንተርናሽናል ደረጃ እንደውም ደካማ ክፍያ ነው ያለው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ አንደኛ ፕሮፌሽናል ዳኛ የሚባለው ማርክ ክላተንበርግ የሚያገኘው ክፍያ ከቼልሲ የአማካይ መስመር ተጨዋች በእጅጉ የሚያንስ ነው፡፡ በአፍሪካ ዋንጫ መስራት የደሞዝ ክፍያ የለውም፡፡ የቀን አበል ይታሰብልሃል፤ ማረፊያ ሆቴል፤ ምግብ እና ትራንስፖርት ተሟልቶልህ ዳኝነቱን ትሰራለህ፡፡ እውነቱን ለመናገር ግን የዳኝነት ሙያ ብዙውን ጊዜ በአማተሪዝም ደረጃ የምታገለግለው በመሆኑ ከፍተኛ ገቢ አገኝበታለሁ ብለህ የምትሰራበት አይደለም፡፡ ወደ ዳኝነት ሙያ የሚገባ ማንም ሰው መነሻው ገቢ አገኝብታለሁ ብሎ መሆን የለበትም፡፡ የሙያውን ፍቅር ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል፡፡ ይገርምሃል ተጨዋቾች ጎል አግብተው የሚደሰቱትን ያህል ዳኞችም በትክክል የመሩት ማንኛውም ጨዋታ የመንፈስ እርካታ ይሰጣቸዋል፡፡ ስለዚህም የዳኝነት ክፍያው በየጊዜው እያደግክበት የምትሄደው የጨዋታዎች ልምድ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የምታገኘው ክብርና ተቀባይነት ነው።››    
የወደፊት እቅዱ
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ከ30 ዓመታት በፊት አንስቶ የአፍሪካ የውድድር መድረኮችን የሚመሩ ኢትዮጵያዊያን ዳኞች ነበሩ፡፡ ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ባምላክ ተሰማ   ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እያገኘ ባለው ልምድ በከፍተኛ ደረጃ እያደገ የመጣ ሲሆን በሚቀጥሉት  አምስት ዓመታት በአፍሪካ ዋንጫ፤  በአፍሪካ ትልልቅ የክለብ ውድድሮች የግማሽ ፍፃሜና የዋንጫ ጨዋታዎችን እንዲሁም በዓለም ዋንጫ ለመሳተፍ በሚችልበት አቅጣጫ ላይ ይገኛል፡፡ የወደፊትእቅዱን አስመልክቶ ለስፖርት አድማስ በሰጠው ምላሽ ‹‹የዳኝነት ሙያን ስጀምር የመጀመርያው እቅዴ  የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ መምራት የሚል ነበር፡፡ በሁለት የአፍሪካ ዋንጫዎች በመሳተፍም ይህ እቅዴ ተሳክቷል። ግን ገና ነው፡፡ ኢትዮጵያያን ቀደምት ዳኞች የሰሩትን ታሪክ መጋራት እፈልጋለሁ፡፡ ስለዚህም ወደፊት በአፍሪካ ዋንጫ ከማጣርያ ጨዋታዎች እና ከዋና ውድድር የምድብ ጨዋታዎች ባሻገር ፍላጎቴ የሩብ ፍፃሜ፤ የግማሽ ፍፃሜ እና የዋንጫ ጨዋታዎችን በሃላፊነት የመምራት ተስፋ አለኝ፡፡ ከዚያም በላይ ዓለም ዋንጫ ላይ ለመሳተፍም እቅድ ይኖረኛል፡፡ በርግጥ ለ2018ቱ 21ኛው የዓለም ዋንጫ እደርሳለሁ በሚል ተስፋ አድርጌ ነበር፡፡ ለዚሁ ታላቅ ውድድር ለአፍሪካ አህጉር በሚሰጠው ኮታ ለመወዳደር ከተያዙ አስር ዳኞች በ10ኛ ደረጃ ተመልምዬ ነበር፡፡ ለአፍሪካ 5 ዳኞች የዓለም ዋንጫ ተሳትፎ እድል የሚሰጥ በመሆኑም እስከ 2018 ሊሳካኝ አይችልም፡፡ ወደ ዓለም ዋንጫ ዳኝነት ለመግባት በአፍሪካ ደረጃ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ልምድ ስለሚያስፈልግ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ፈቃድ ሆኖ፤ እኔም ልምዴን በማሳደግ እና አገልግሎቴን በማጠናከር በ2022 እኤአ ላይ ኳታር በምታዘጋጀው የዓለም ዋንጫ ተሳትፎውን ላገኝ እንደምችል በማቀድ መስራቴን እቀጥላለሁ፡፡›› ብሏል፡፡

Read 2244 times