Sunday, 12 February 2017 00:00

አዲስ አበባ በሪልእስቴት ኢንቨስትመንት ከአፍሪካ 3ኛ ሆናለች

Written by 
Rate this item
(7 votes)

6 ቢሊዮን ዶላር ያህል በሪልእስቴት ዘርፍ ኢንቨስት ተደርጓል ተብሏል

  አዲስ አበባ በሪልእስቴት ዘርፍ ኢንቨስትመንት ከአፍሪካ ከተሞች በ3ኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝና የከተማዋ የሪልእስቴት ልማት ዘርፍ ኢንቨስትመንት፣ 6 ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስ የዓለም ባንክ ከትናንት በስቲያ ይፋ ባደረገው የአፍሪካ ዋና ዋና ከተሞች ወቅታዊ ሁኔታ አመላካች ሪፖርት አስታውቋል፡፡
የታንዛንያዋ ዳሬ ሰላም በሪልእስቴት ልማት ዘርፍ ከአፍሪካ ከተሞች በአንደኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን የጠቆመው ሪፖርቱ፣ የከተማዋ የሪልእስቴት ኢንቨስትመንት 12 ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስ የገለጸ ሲሆን፣ የ9 ቢሊዮን ዶላር የሪልእስቴት ኢንቨስትመንት ባለቤት የሆነቺው የኬንያ ርዕሰ መዲና ናይሮቢ፣ በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝም አስረድቷል፡፡
በአፍሪካ ከተሞች የሪልእስቴት ዘርፍ ልማት እየተስፋፋ ቢመጣም፣ የከተማ ነዋሪዎች ከነፍስ ወከፍ ገቢያቸው ጋር ሲነጻጸር የመኖሪያ ቤት ፍላጎታቸውን ለማሟላት ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚያወጡም የጠቆመው ሪፖርቱ፤ በአንዳንድ የአህጉሪቱ ከተሞች የመሬት ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ በመሄድ በአሜሪካ በሚሸጥበት ዋጋ መሸጥ መጀመሩንም አክሎ ገልጧል፡፡
የአህጉሪቱ የከተማ ነዋሪዎች ቁጥር እስከ 2050 ድረስ በ170 ሚሊዮን እንደሚጨምር እንዲሁም አሁን ያለው የከተማ ነዋሪ ህዝብ ቁጥር በ25 አመታት ጊዜ ውስጥ በእጥፍ በማደግ 1 ቢሊዮን ይደርሳል ተብሎ እንደሚገመት የጠቆመው ሪፖርቱ፣ ይህም በመሆኑ የአህጉሪቱ ከተሞች የመኖሪያ ቤት ግንባታን ጨምሮ ከህዝብ ቁጥር እድገቱ ጋር የሚመጣጠን ሰፊ የመሰረተ ልማት አውታሮች ግንባታ ማካሄድ እንደሚጠበቅባቸው አስረድቷል፡፡
የአፍሪካ ከተሞች እጅግ ውድ ከሆኑ የአለማችን ከተሞች ተርታ እንደሚመደቡ የጠቆመው ሪፖርቱ፣ ከሌሎች ተመሳሳይ ገቢ ያላቸው የአለማችን አገራት ከተሞች ጋር ሲነጻጸር በ30 በመቶ ያህል የበለጠ ውድ መሆናቸውንና ይህም ከተሞቹ አለማቀፍ ኢንቬስተሮችን እንዳይስቡ እክል እንደፈጠረባቸው ገልጧል፡፡

Read 5859 times