Saturday, 11 February 2017 12:56

አይ ኢትዮጵያ! ... አይ አፍሪካ! ተማሪዎች ማንበብ እያቃታቸው፣ በዝምታ ያያሉ!

Written by  ዮሃንስ ሰ.
Rate this item
(12 votes)


አንዲት ቃል ማንበብ የማይችሉ የሁለተኛ ክፍል
          ተማሪዎች
በኢትዮጵያ     ከመቶ ተማሪዎች 33ቱ
=======
በግብፅ          ከመቶ ተማሪዎች 27ቱ
========
በታንዛንያ        ከመቶ ተማሪዎች 33ቱ
======
በዛምቢያ         ከመቶ ተማሪዎች 70ዎቹ
======
በጋና             ከመቶ ተማሪዎች 75ቱ
======
በማሊ            ከመቶ ተማሪዎች 85ቱ
=======
በጋና              ከመቶ ተማሪዎች 90ዎቹ
=======

“ዘመናዊዎቹ” የመማሪያ መፃህፍት፣ ከሆሄና ከፊደል አይጀምሩም። ሆሄያትና ፊደላት፣ “ትርጉም” የላቸውም ተብለናል። እናም፣ ትምህርት የሚጀመረው፣ ከቃላትና ከዓረፍተነገር ሆኖልናል። ለምን?
ወገኛው የዘመናችን ስርዓተ ትምህርት እንዲህ ይላል።...
ትርጉም አልባ ፊደላትን በቁንፅል ማስተማር፣... “ሀሁሂ...” እና “አቡጊዳ...” እያሉ ፊደል ማስጨበጥ፣ ኋላቀርነት ነው። ደግሞም፣ ትምህርቱ እንደ እንጨት ድርቅ ይላል። ያሰለቻል። ጨዋታ የለውም። የህፃናትን የፈጠራ መንፈስ ይሰብራል። የፊደል ፅሁፍ እና የፊደል ድምፅ... እፍን ጭንቅ ጭንቅንቅ ያደርጋሉ። ለሃሳብ ልዩነትና ለስሜት ብዝሃነት ቦታ አይሰጡም። ያው፣ “ሀ” የሚለው ፊደል፣... ሁሌም “ሀ” የሚል ድምፅን ብቻ ነው የሚወክለው። ከዚህ ውጭ ውልፍት ማለት አይቻልም። ውልፍት ካለ፣ “ስህተት” ተብሎ ይታረማል፣ ማለትም ይታፈናል። እንዲህ አይነት “አፈና”፣ ለውይይት፣ ለሃሳብ ልዩነትና ለድርድር ቦታ አይሰጥም። የህፃናት የመጫወት ፍላጎትን ይደፈጥጣል።
በተቃራኒው፣ ዘመናዊ ትምህርት ማለት፣... ህፃናት የመሪነትን ሚና እንዲጨብጡ የሚያደርግና በእነሱ ፍላጎት የሚታዘዝ የትምህርት አካሄድ ነው።  በጨዋታ የሚያዝናናቸው እና የፈጠራ መንፈሳቸውን የሚያነቃቃ፣ የተለያየ ሃሳብና ስሜት እንዲገልፁ የሚያነሳሳ፣ ከመሳሳት አደጋ የፀዳ፣... ምሉዕነት የተላበሰ ትምህርት፣... እንዲህ አይነት ድንቅ ትምህርት ከምን ይጀምራል? ትርጉም ካላቸው ቃላትና ዓረፍተ ነገር፣... በተለይ ደግሞ ከተረቶች ይጀምራል። ...
አንዳንዶቹ “ወገኛ” አባባሎች፣ “የቀልድ” ወይም “የስካር” ይመስላሉ። ግን “ቀልድና ስካር” የሚመስሉትን ወገኛ አባባሎች የወሰድኳቸው፣ ዩኔስኮ እና ዩኤስኤይድ፣ በትምህርት ዙሪያ ካዘጋጇቸው ሰነዶች ነው።
ለአንደኛ ክፍል ተማሪዎች የተዘጋጁ የንባብ መማሪያ ፅሁፎች፣ በማንኛውም ቋንቋ ቢሆኑ ልዩነት የለውም... በአማርኛ፣ በኦሮሚኛ፣ በትግርኛ፣ በሶማሊኛ ወዘተ...። ዋናው ቁም ነገር ምንድነው? ህፃናቱ፣ ወደዚህ የንባብ ትምህርት የሚገቡት፣ በቅድሚያ ፊደል አውቀው አይደለም።
በቀጥታ፣ ወደ ቃላትና ወደ ዓረፍተ ነገር ንባብ... ወደ ተረት ንባብ ነው ተወርውረው እንዲገቡ የሚደረገው። ንባብ ጀመሩ ማለት ነው። በእርግጥ፣ “ከምር” ያነብባሉ ማለት አይደለም። አስተማሪ ድምፁን ከፍ አድርጎ፣ቃላቱን እየጠቆመ ያነብባል። ልጆች፣ የቃላቱን ድምፅ ከአስተማሪ እየሰሙና የቃላቱን ፅሁፍ ከመፅሃፍ ላይ እያዩ፣ መስማትንና ማንበብን ይለማመዳሉ - ከነትርጉሙ። እንዲህ አይነት ተአምረኛ የንባብ ትምህርት ከወዴት ይገኛል?
ከዚያ ተማሪዎች ተወያዩ ይባላሉ። ይሄ “አዲሱ የመማሪያ ዘዴ ነው”። አስተማሪው፣ “አዋቂ ነኝ” በሚል መንፈስ፣ “ማስረዳት” የለበትም። ያማ ኋላቀርነት ነው። ትምህርት...፣ እንደ ድሮ፣.. “እውቀትን ማስተላለፍ”፣ “እውቀትን መገብየት”... ማለት አይደለም። እውቀት ቋሚ አይደለም። የድሮ እውቀት ሌላ፣ የዛሬ እውቀት ሌላ! ደግሞም፣ እውቀት ሁለንተናዊ አይደለም። አስተማሪ፣ የራሱ እውቀት ሊኖረው ይችላል። ተማሪዎች ደግሞ፣ በውይይትና በድርድር የራሳቸውን እውቀት ይፈጥራሉ። ለዚህም ነው፤ አብዛኞቹ የአገራችን የኤሌመንታሪ አስተማሪዎች፣ ዋነኛ የማስተማሪ ዘዴያቸው፣ “ተማሪዎችን ማስረዳትና የቤት ስራ መስጠት” እንዳልሆነ፣ ምለው እየተገዘቱ የሚናገሩት።
ማስረዳትና የቤት ስራ... እንደ ነውር ነው የሚቆጠረው። ይልቁንስ፣ ዋነኛው የማስተማሪያ ዘዴ፣ “ተማሪዎች እንዲወያዩ ማድረግ” እንደሆነ ብዙዎቹ መምህራን ገልፀዋል። (Perceptions of Ethiopian Teachers and Principals on Quality of Education፣ American Institutes for Research (AIR) በሚል የወጣው ጥናት ላይ ዝርዝሩን ማግኘት ትችላላችሁ)።
እንግዲህ፣ ሰነዶችን መጥቀስ ከጀመርኩ አይቀር፤ ከመማሪያ መፃህፍቱም፣ በተጨባጭ እውነታውን የሚያሳዩ መረጃዎችን እንመልከት።
እንግዲህ፣ በአዲሱ ወገኛ የትምህርት አሰጣጥ ላይ፣ የንባብ ትምህርት የሚጀምረው፣ በሆሄና በፊደል አይደለም ተብለን የለ? የሁለተኛ ክፍል ተማሪዎች፣ በአመቱ መግቢያ፣ በመጀመሪያው ሳምንት፣ ለንባብ የተዘጋጀላቸው ፅሁፍ፣ በመማሪያ መፅሁፉ ገፅ አራት እና አምስት ላይ እንዲህ በሰፊው ቀርቧል። በቢራቢሮ ስዕል የታጀበው ፅሁፍ፣ “የጠፋችው ቢራቢሮ” በሚል ርዕስ ይጀምራል - ወይም ደግሞ “የጠፋው ቢራቢሮ” ልንለው እንችላለን - እንደ ወገኛው ዩኤስኤአይዲ ለፆታ እኩልነት በመንሰፍሰፍ።
The Lost Butterfly
Today is the beginning of the new school week. During lunch Tilahun is sitting near the window and eating bread. He sees Solomon, his new friend. Solomon is sitting on a bench playing with a stick and looking very sad.  Tilahun walks over to Solomon and says, “Hello, how are you?” Solomon answers, “I’m sad because I’ve lost my butterfly.”
Tilahun points to a bag on the floor and asks, “Is it in the bag?” Solomon shakes his head and says, “No.” Tilahun points to the door and asks, “Is it outside the door?”  Solomon shakes his head and says, “No.”
The school bell rings.  All students come inside the classroom. Rahel shouts, “There is a butterfly on the window!”  All the boys and girls gather around to see the butterfly.  Solomon smiles.
ያው፣ አስተማሪው፣ ፅሁፉን ካነበበላቸው በኋላ፣ ግራ ተጋብተው “ቁልጭልጭ” “ቅብጥብጥ” የሚሉ የሁለተኛ ክፍል ተማሪዎች፣ “ተወያዩ” ይባላሉ። አስቸጋሪ ነው። ምንም ሳያውቁ፣ ፊደል ሳይቆጥሩ፣ ምንም ማንበብ ሳይችሉና ምንም ሳይገባቸው፣... እንዴት ይወያያሉ? ግን፣ አልወያይ ቢሉ እንኳ፣ ችግር የለውም።
እንዲወያዩ ማድረግ የአስተማሪው ሃላፊነት ነው። ታዲያ፣ አስተማሪው መጠንቀቅ አለበት። ለውይይት የሚያነሳቸው ጥያቄዎች፣ ደረቅ መሆን የለባቸውም። ተማሪዎች፣ ከፅሁፉ ንባብ በመነሳት፣ ስለ ቢራቢሮዋ ታሪክ ምን ያህል እንደተገነዘቡ ለማወቅ፣ “ቢራቢሮዋ የት ሄደች?” ብሎ መጠየቅ የለበትም። በመጀመሪያ ደረጃ፣ በወገኞቹ አባባል፣ “ትምህርት” ማለት፣ ተጨባጭ ነገሮችን የመገንዘብና የማወቅ ጉዳይ አይደለም። ግንዛቤና እውቀት፣ “ተራና የወረዱ ነገሮች” ናቸው። ዋናው ነገር፣ የፈጠራ መንፈስና የሃሳብ ልዩነት የመግለፅ፣ ከዚያም አዲስ እውቀት የመፍጠር ጉዳይ ነው - የዘመናችን ወገኛ ትምህርት።
ስለዚህ፣... አስተማሪው፣ “ቢራቢሮዋ የት ሄደች?” የሚል ተራና የወረደ ጥያቄ ለተማሪዎች ማቅረብ የለበትም። እንዲያ አይነት ጥያቄ ቢቀርብና፣ አንዱ ተማሪ፣ “ቢራቢሮዋ፣ ጠረጴዛ ስር ገባች” ብሎ ቢመልስስ?
ያኔ አስተማሪው፣ “አይ ተሳስተሃል፣ ቢራቢሮዋ፣ መስኮቱ ላይ ነው ያረፈችው” ሊለው ነው? አስተማሪ እንዲህ ማለት የለበትም። የተማሪዎቹን ስሜት ይጎዳል። የፈጠራ መንፈሳቸውን ይሰብራል። በዚያ ላይ፣ “ተሳስተሃል” ብሎ፣ በበላይነትና በአዋቂነት መንፈስ፣ ተማሪዎች ላይ መደንፋት፣... ከፍተኛ ጥፋት ነው። “የአፋኝነት” እና “የአምባገነንነት” ስሜትን ያሳድራል። አስተማሪዎች፣ “ተሳስተሃል” የሚል ቃል ላለመጠቀም መጠንቀቅ አለባቸው።
ይልቅስ፣ አስተማሪው፣ ተማሪዎችን እንዲህ ብሎ መጠየቅ አለበት።
“ምን ይመስላችኋል? ታሪኩ አስደሰታችሁ? አሳዘናችሁ? እስቲ ሃሳባችሁንና ስሜታችሁን ግለፁ”
“አንቺስ፣ ቢራቢሮዋን ወደድሻት? ቢራቢሮዋ ታምራለች?”
“አንተስ፣ ቢራቢሮ ብትሆን ምን ታደርግ ነበር?”
“ቢራቢሮዋ፣ ወዴት ብትሄድ ይሻላል?”
“የታሪኩ መጨረሻ፣ ምን ቢሆን ትመኛለህ?”
ምናለፋችሁ። ዘመኑ ተቀይሯል። ድሮ ድሮኮ፣ ማለትም ከ15 ዓመት በፊትኮ፣ በተለይ ገና ማንበብ ለማይችሉ ተማሪዎች፣ ፅሁፍን አንብቦ መገንዘብ ማለት፣... በተጨባጭ የቀረቡትን መረጃዎች አጥርቶ መገንዘብ ማለት ነበር። ዛሬ፣ “ተጨባጭ መረጃዎችን መገንዘብ”፣ ወዲያ ተሽቀንጥሮ ተጥሏል። ዛሬ፣ ነገሩ ሁሉ ተቀይሮ፣ “ምን ተሰማሽ? ምን ተመኘህ? ተወያዩ...” የሚል ... ወገኛ ፈሊጥ ተይዟል። “ወገኛ ፈሊጥ” ብቻ አይደለም። ትዕዛዝም ጭምር ነው። መምህራን ለተማሪዎች የሚያቀርቧቸው ጥያቄዎች፣ በተቻለ መጠን “ከተጨባጭ መረጃ የፀዱ ጥያቄዎች” መሆን እንዳለባቸው፣ በመመሪያ ጭምር ተዘርዝሯል። “ምን ተሰማሽ? ምን ተመኘህ?”...
ዩኤስኤአይዲ፣ በትምህርት ሚኒስቴር ፈቃድ፣ ያዘጋጀውን የንባብ መመሪያ ማየት ትችላላችሁ። ከንባብ በፊት፣ በንባብ መሃል እና ከንባብ በኋላ፣ ተማሪዎችን ለማወያየት፣ አስተማሪው ጥያቄዎችን ማንሳት እንዳለበት መመሪያው ያዛል። ለምሳሌ የድመት ታሪክ እያነበበላቸው፣ በመሃል አቋርጦ እነዚህን ጥያቄዎች ማንሳት አለበት ይላል መመሪያው።
ከዚህ ቀጥሎ ምን የሚከሰት ይመስላችኋል?
አንተ፣... ባለታሪኳ [ድመት] ብትሆን፣... ምን ታደርግ ነበር?
ባለታሪኳ [ድመት]፣ ምን አይነት ስሜቶች እየተሰሟት ይሆን?
 ያው፣ ብዙዎቹ የመማሪያና ተዛማጅ መፃህፍት የሚዘጋጁት፣ በዩኤስኤይድ ቅኝትና ገንዘብ አይደል? ይሄ የንባብ ማስተማሪያ ማንዋልም የተዘጋጀው በዩኤስኤይድ ነው (ገፅ 12 - USAID/ READ CO፤ School Level Reading and Writing Skills Development፤ Activity Manual)።
ለማንኛውም፣ በኢትዮጵያውኛ ቋንቋዎችም ሆነ፣ በእንግሊዝኛ ቋንቋ፣ የአንደኛና የሁለተኛ ክፍል ተማሪዎች፣ እንዲህ አይነት የድመትም ሆነ የቢራቢሮ ታሪክ “ካነበቡ” በኋላ፤.... ከብዙ ሳምንታትና ወራት በኋላ ወይም በማግስቱ የፊደላት ዝርዝር ይማራሉ።
የሁለተኛ ክፍል የእንግሊዝኛ መማሪያ መፅሃፍን መመልከት ትችላላችሁ። ከፊደል ትምህርት በፊት፣ የቢራቢሮ ታሪክ፣ የጥራጥሬ ለቀማ ታሪክ፣ የጎጆ ታሪክ፣...
ኧረ የአንደኛ ክፍል የእንግሊዝኛ መፅሃፍ ላይም፣ በርካታ ታሪኮች፣ ለንባብ ቀርበዋል - “የእናት አይጥ” ታሪክን ጨምሮ። የአንደኛ ክፍል ተማሪዎች፣ ያ ሁሉ በእንግሊዝኛ የተፃፈ ታሪክ “እያነበቡ”፣ እንደ ልብ ብዙ ውይይትና ድርድር ያካሂዳሉ።.... ወይ ተአምር!
ይሄ ራሱ፣ የምር ትምህርት ሳይሆን፣ የተረት ዓለም ታሪክ ይመስላል።
ለማንኛውም፣ በምናብም ቢሆን፣ ተማሪዎቹ ብዙ ብዙ ታሪክ፣ ብዙ ብዙ ዓረፍተ ነገር እያነበቡ ነው አሉ። ብዙ የዓረፍተ ነገር አይነቶች፣... “በካፒታል ሌተር” ጀምረው፣ በቃለ አጋንኖ የሚዘጉ ዓረፍተ ነገሮች፤... በጥያቄ ምልክትና በትዕምርተ ጥቅስ የተራቀቁ ዓረፍተ ነገሮች፣... እንዲያውም I’m...  I’ve... በሚሉ የማሳጠሪያ ጥበቦችም ጭምር ያሸበረቁ ዓረፍተ ነገሮች... የቀረ የለም። የአንደኛና የሁለተኛ ክፍል ተማሪዎቹ ደግሞ፣ ምንም ሳይበግራቸው፣ ሁሉንም ነገር በንባብ “ተገንዝበው” በጥልቀት ይወያያሉ። የሃሳብ ልዩነታቸውንና ስሜታቸውን ልብ ለልብ ይለዋወጣሉ። ከሁሉም በላይ ደግሞ፣ በንባብ ምንም አይነት ተጨባጭ መረጃ ለመገንዘብ ባይችሉም፣ ...ምናባዊ የፈጠራ ስሜት፣ ያሰኛቸውንና ያማራቸውን እየተናገሩ፣ የፈጠራ ጥበባቸውን እያራቀቁ ይፈላሰፉሉ። በቃ፣ ዩኤስኤአይዲ እና ትምህርት ሚኒስቴር የሚነግሩንን ካመንን፣... በቃ... ልጆቹ የትና የት ደርሰዋል።
በእርግጥ፣ ገና “ካፒታል ሌተር” ምን እንደሆነ አይተው አያውቁም። የአንደኛ ክፍል መፅሃፍ ውስጥ፣ ያን ሁሉ ንባብ ከጨረሱ በኋላ፤ በአመቱ መዝጊያ ላይ፣ በመፅሃፉ የማጠናቀቂያ ምዕራፍ፣ በመጨረሻዋ ገፅ ላይ ነው፣ ‘ካፒታል ሌተር’ን የሚያሳይ ሰንጠረዥ የቀረበላቸው (ገፅ 92)።
በነገራችን ላይ፣ “b” የተሰኘው ሆሄ፣ በአማርኛ “be” የሚል ድምፅን እንደሚወክል ሰንጠረዡ ይገልፃል። “d” የተሰኘው ሆሄ ደግሞ፣ በአማርኛ “de” የሚል ድምፅን ይወክላል። አሁን... እንዲህ አይነት ግራ የተጋባ አገላለፅ፣ ከመማሪያ መፅሃፍ ይጠበቃል?
ትልቁ ስህተት ግን፣ ተማሪዎችን ከንባብ ችሎታ እያራራቀ የሚገኘው ትልቁ ጥፋት ግን ሌላ ነው። ትልቁ ሃጥያት፣... ለካ እስካሁን፣ የትኛው ሆሄ፣ ከምን አይነት የንግግር ድምፅ ጋር እንደሚዛመድ፣ አንድ ሆሄ ለብቻው ወይም ከየትኛው ሆሄ ጋ ሲቀናጅ፣ ምን አይነት የንግግር ድምፅን (ምን አይነት ፊደልን) እንደሚወክል፣ አንድም ጊዜ አልተማሩም።
ታዲያ፣ እነዚያ ሁሉ ታሪከኛ ፅሁፎችን እንዴት አንብበዋቸው ይሆን? በዩኤስኤይድ የምናብ ዓለም፣ በትምህርት ሚኒስቴር የህልም ዓለም ውስጥ ካልሆነ በቀር፣ ከፊደል በፊት፣ ታሪከኛ ፅሁፎችን ማንበብ አይቻልም።
እንደነሱ አባባልማ፣ ‘ካፒታል ሌተር’፣ ‘ስሞል ሌተር’፣ ምንና ምን እንደሆኑ፣ የትኛውን አይነት ‘የአማርኛ ድምፅ’ እንደሚወክሉ፣ በመጨረሻዋ ገፅ መግለፅም አያስፈልግም ነበር - ለማስታወስ ያህል ካልሆነ በቀር። በአንዳች ተዓምር፣ በአይጥና በቢራቢሮ ታሪኮች አማካኝነት፣ ተማሪዎች፣ ሁሉንም ነገር... ሁሉንም የንባብ ጥበብ፣... በራሳቸው ዘዴ፣ አውቀውታል። የራሳቸውን እውቀት ፈጥረዋል። በቃ፣ ሆሄና ፊደል ማስተማር አያስፈልግም። ወገኛ!
እውነታው ምን መሰላችሁ? በእንግሊዝኛም ሆነ በአማርኛ፣ በኦሮሚኛም ሆነ በሲዳምኛ፣... በትግርኛም ሆነ በሃዲያኛ... ሆሄና ፊደል ሳይማር፣ ሳያውቅ፣... ከማወቅም አልፎ በእልፍ ጊዜ ተደጋጋሚ ልምምድ፣ ከህፃኑ አእምሮ ጋር ሳይዋሃድ፣... በወጉ ማንበብ የመቻል እድል፣ በጣም ኢምንት ነው። ለዚህም ነው፣ የአገራችን የ1ኛ፣ የ2ኛ እና የ3ኛ ክፍል ተማሪዎች፣ ከንባብ ችሎታ ጋር፣ የምድርና የጨረቃ ያህል የተራራቁት።
ሌሎቹን እንተዋቸው። የ3ኛ ክፍል ተማሪዎች እንኳ፣ ለዚያውም በለመዱት ቋንቋ፣... ሁለት መስመር ዓረፍተ ነገሮችን አንብበው የመረዳት ችሎታ ሊኖራቸው አይገባም ነበር? ግን፣ ከመቶ ተማሪዎች፣ አስሩ ብቻ ናቸው፣ አንብበው የመረዳት ችሎታ ለማዳበር የታደሉት።
ሌሎቹ ግን፣ ተምረው እንዳልተማሩ እየሆኑ ነው። በአጭሩ፣ ሆሄንና ፊደልን ትቶ የቃላትና የዓረፍተ ነገር ንባብ ለመጀመር የተካሄደው የአመታት ወገኛ ዘመቻ፣ ይሄውና ሚሊዮኖችን ለመሃይምነት እየዳረገ ነው።
ተጠያቂው ማን ነው? እንዘርዝር ካልን ማን ይተርፋል? የተባበሩት መንግስታትን ልናስቀድም እንችላለን -“ተማሪዎች፣ የራሳቸውን እውቀት ይፈጥራሉ” የሚለውን ወገኛ ፈሊጥ፣ ለ25 ዓመታት ሲሰብክና በአለም ዙሪያ  ሲያስፋፋ የቆየውኮ፣ ሌላ ሳይሆን፣ ዩኔስኮ ነው። ብዙ የአገራችን ምሁራን ደግሞ፣ “ዩኔስኮ እንደሚለው...” ብለው እየጠቀሱ፣ በእቅፍ ተቀብለውታል - መንግስት እና የትምህርት ተቋማትም እንዲሁ።
ከሁሉም በላይ ግን፣ ለአመታት ባልተቋረጠ ዘመቻ፣ ብዙ ቢሊዮን ዶላሮችን አሰልፎ፣ የንባብ ትምህርትን ድምጥማጡን ለማጥፋት የተቃረበው፣ የአሜሪካ የረድኤት ድርጅት ‘ዩኤስኤአይዲ” ነው።
እስቲ አስቡት። እንደ አሜሪካ ወይም እንደ ኖርዌይ፣ እንደ ኢስቶኒያ ወይም እንደ ስፔን፣  የአገራችን የ1ኛ ክፍል ተማሪዎችም በደቂቃ ከ50 በላይ ቃላትን የሚያቀላጥፉ እንዲሆኑ መመኘት ነውር ነው? እሺ እሱስ ይቅር። ግን፣ የ3ኛ ክፍል ተማሪዎች፣ እንዴት ማንበብ ያቅታቸዋል? በአገራችን በደቂቃ ከሃምሳ ቃላት በላይ የሚያነብቡ የ3ኛ ክፍል ተማሪዎችኮ፣ አስር ከመቶ... ገደማ ናቸው። አረፍተ ነገር አንበብው የሚገነዘቡ የ3ኛ ክፍል ተማሪዎች፣... አስር ከመቶዎቹ ብቻ! ለዚያውም ከባባድ ዓረፍተ ነገሮችን አንብቡ አልተባሉም። ለምሳሌ፣ እንደ መመዘኛ የቀረቡትን ዓረፍተ ነገሮች ተመልከቱ።
አበበ ከእናቱ ጋር በደብረሲና ከተማ ይኖራል። እናቱ አንድ ላም ነበረቻቸው።
አበበ ላሚቱን ይጠብቃል።...
ይህንን ማንበብና፣ “አበበ የት ይኖራል?” የሚለውን ጥያቄ መመለስ፣ ለብዙዎቹ የ3ኛ ክፍል ተማሪዎች ከከበዳቸው፣ ምኑን ተማሩት? ተምረው እንዳልተማሩ ሆነዋል።
ምን ይሄ ብቻ! ዓረፍተ ነገርን አንብቦ መረዳትን እርሱት። እንዲሁ፣ እየወደቁ እየተነሱ፣ አንድ ሁለት ቃላት ማንበብም፣ አስቸጋሪ ሆኗል። ሩብ ያህሉ የ3ኛ ክፍል ተማሪዎች፣ አንዲትም ቃል ማንበብ አይችሉም።
በእርግጥ፣ ችግሩ የኢትዮጵያ ብቻ አይደለም። ወረርሽኙ፣ የአፍሪካ አገራትን ከዳር እስከ ዳር አጥለቅልቋቸዋል። በጣም ያስቆጫሉ። አነፃፅሩታ።
ከአውሮፓና ከአሜሪካ ባሻገር፣ እነ ቺሊ እና ጓቲማላ በመሳሰሉ አገራት እንኳ፣ የአንደኛና የሁለተኛ ክፍል ተማሪዎች፣ በደቂቃ ከ40 ቃላት በላይ ማንበብ ይችላሉ።
ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ አገራት ግን፣ የልጆች ትምህርት፣ መሃይምነት ውስጥ የሚያስቀር እስር ቤት እየመሰለ ነው።
በግብፅ፣ እንደ ኢትዮጵያ፣ ሩብ ያህሉ የ3ኛ ክፍል ተማሪዎች፣ አንዲትም ቃል ማንበብ አይችሉም። ከሁለተኛ ክፍል ተማሪዎች መካከል ደግሞ፣ አንዲት ቃል የማንበብ አቅም ያጡ ህፃናት፣ ወደ 30 ከመቶ ገደማ ናቸው።
አንዲት ቃል ማንበብ የማይችሉ የሁለተኛ ክፍል ተማሪዎች፡
በታንዛንያ    ከመቶ ተማሪዎች 33ቱ
በዛምቢያ    ከመቶ ተማሪዎች 70ዎቹ
በጋና        ከመቶ ተማሪዎች 75ቱ
በማሊ         ከመቶ ተማሪዎች 85ቱ
በጋና         ከመቶ ተማሪዎች 90ዎቹ
ዝርዝሩ ብዙዎቹን የአፍሪካ አገራት ያካትታል። በዚህ በዚህ፣ ብዙዎቹ የአፍሪካ አገራት ይመሳሰላሉ።
ሌላ የሚያመሳስላቸው ነገር ምንድነው? በዩኤስኤ አይዲ እርዳታ የተዘጋጁ የመማሪያ መፃህፍት!

Read 5881 times Last modified on Saturday, 11 February 2017 13:08