Sunday, 12 February 2017 00:00

የማናየው፣ የማንዳስሰው ግንብ

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(7 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እኔ የምለው እኚህ የአማሪካውን ሰውዬ እዚህ ለተወሰነ ጊዜ “አግዙን” ብለን ብናመጣቸው ግንብ በግንብ የሚያደርጉን አይመስላችሁም!
“ወደ ቦሌ መንገድ መግቢያ ላይ ግንብ እንገነባለን፣” ይላሉ፡፡
“ጌታዬ፣ ግንብ መገንባቱ እንኳን የከተማዋን መልካም ገጽታ…” ብለን ሳንጨርስ ያቋርጡናል፡፡
“ገባኝ፣ ገባኝ… ግንብ እንኳን ባይሆን ኬላ እናቆማለን፡፡ ያው እሱም የግንቡን አገልግሎት ይሰጣል፡፡”
“ጌታዬ፣ ይሄ ሁሉ ለምን አስፈለገ? ኮንትሮባንድ እቃ እንደሆነ በዛ በኩል አይገባ!”
“ኮንትሮባንድ እቃ ሳይሆን ኮንትሮባንድ ሰዎች እንዳይገቡ ለመከላከል ነው፡፡”
“ቢያብራሩልን…”
“ከሌሎች አካባቢዎች የሚመጡ ሰዎች የቦሌን ልጆች አእምሮ ሊበርዙ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ ቦሌ አካባቢ አንዱ እሷዬዋን ማባበል ሲፈልግ ብዙ ወጪ አለበት፡፡ ቀን ካፑቺኖ አጠጥቶና ክትፎ ጋብዞ፣ ማታ አብሶሉት ቮድካ በኦሬንጅ፣ ሬሚ ማርቲኒ፣ ሳምቡካ የመሳሰሉትን አጠጥቶ… ስሪ ኮርስ እራት አብልቶ ነው፡፡ እነኚህ ከሌላ ቦታ የሚመጡት ግን አንድ በያይነቱና አንድ አምቦ ውሀ ብቻ ለሁለት በመካፈል ሁሉም ነገር ሊሳካ እንደሚችል በማሳየት፣ በቦሌ የንግድ እንቅስቃሴ ላይ አደጋ ሊጋርጡ ይችላሉዋ። በተጨማሪ ካለ ኩርቫይዘር ሌላ መጠጥ ያለ ለማይመስላቸው የቦሌ ሰዎች ኮረፌ የሚባል መጠጥ እንዳለ ሊጠቁሙ ይችላሉ፡፡”
ስሙኝማ…የምር ግን ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ከነገሩ ሁሉ የህግ የበላይነት የሚባለው ነገር የእውነትም ምን እንደሆነና ማንም ሰው ከህግ በላይ ሊሆን እንደማይችል አማሪካኖቹ እያሳዩን ነው፡፡ “ወንበር ከያዝኩ በኋላ ብዘርፍ፣ ብፈልጥ ማንሽስ ምን ያገባሻል!…ትንፍሽ እላለሁ ብትይ ውርድ ከራሴ!…” ብሎ ነገር የለም፡፡
የምር ግን…የ‘አማሪካው’ ሰውዬ ‘አደርጋለሁ ያልኳት አንዲቷም ነገር አትቀረኝም’ ያሉ ነው የሚመስለው፡፡
እግረ መንገዴን…አንዱ ፖለቲከኛ ምን አለ አሉ መሰላችሁ… “በደንብ የተቀረጸ እርሳስና አሥራ አምስት ያህል ባዶ ወረቀት ስጡኝ፣” ይላል፡፡
“ምን ሊያደርግልህ…” ይሉታል፡፡
“በምርጫ ካሸነፍኩ እፈጽማለሁ ብዬ ቃል የገባኋቸውንና ስልጣን ከያዝኩ በኋላ የምረሳቸውን ቃል ኪዳኖች ልጽፍበት…” ብሎ አረፈው፡፡
እኔ የምለው… የግንብ ነገር ካነሳን እንደዛ ስላላሰብነው ነው እንጂ አሻግረን እንዳናይ የሚከልለን የማናየው፣ የማንዳስሰው ግንብ ተደንቅሮብናል፡፡
እናላችሁ…እርስ በእርሳችን እንዳንተማመን፣ ከመናቆር አዙሪት እንዳንወጣ የማናየው፣ የማንዳስሰው ግንብ የተገነባብን ይመስላል፡፡
ለምሳሌ ወደፊት ‘ከአሥር ዓመት በኋላ፣ ከሀያ ዓመት በኋላ’ አይነት ትንሽ ራቅ አድርገን እንዳናይ የሆነ ጋግርት የተደነቀረብን ይመስላል፡፡ እናማ ጭራሽ ከግንቡ ወደ ኋላ እየሄድን፣ “የዛሬ ሀምሳ ዓመት እንዲህ ሆኖ፣ የዛሬ መቶ ዓመት እንዲህ ሳይሆን ቀርቶ…” ምናምን እያልን ነገና ተነገ ወዲያን አጥርተን እንዳናይ የማናየው፣ የማንዳስሰው ግንብ ተገንብቶልናል፡፡
አሻግረን እንዳናይ የሚከልለን የማናየው፣ የማንዳስሰው ግንብ ተደንቅሮብናል፡፡
ኮሚክ እኮ ነው… አውሮፓ እርስ በእርሱ ሲጨራረስ ኖሮ አሁን ሁሉም ከአንድ ማህጸን የወጣ ይመስል ‘አንተ ትብስ፣ አንቺ ትብሽ’ ሲባባል እኛ፤ “የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳም…”  አይነት ካንሰር አልለቅ ብሎናል፡፡ ልክ ነዋ… በአባትና በአያት መካሰስ ቢያቅት እንኳን … “ቅድመ አያቶችህ ቅድም አያቶቼን እንዲህ፣ እንዲህ አድርገዋቸው…” ይባላል፡፡
እናላችሁ…የእኛ ነገር…
‘አንተም ተው፣ አንተም ተው የሚለው ሰው
ጠፍቶ
በሬውን አረደው ከቀንበሩ ፈትቶ’
እየሆነ ተቸግረናል፡፡ እናማ...አንተም ተው፣ አንተም ተው የሚል ያስፈልገናል፡፡ እኛ ‘መቃብሬ ላይ እንዳትቆም’ ስንባባል ዓለም ‘እዛው ስትገላበጡ ኑሩ’ ብሎ ጥሎን እየነጎደ ነው፡፡
ይቺን ስሙኝማ…ሁለት አዛውንቶች ምሳ እየበሉ ነበር፡፡ በደህና ሲነጋገሩ ቆይተው በመሀል በሆነ ጉዳይ ይካረራሉ፡፡ ይሄኔ አንድኛው ምን ቢሉ ጥሩ ነው…
“በጣም ስለተናደድኩብህ ስሞት የሬሳ ሳጥኑን ከሚሸከሙት ሰዎች አንዱ እንዳትሆን ሰርዤሀለሁ።”
እናላችሁ…አሻግረን እንዳናይ የሚከልለን የማናየው፣ የማንዳስሰው ግንብ ተደንቅሮብናል፡፡
እናላችሁ… በገንዘባችሁ ልትገለገሉ የምትገቡባቸው አንዳንድ አገልግሎት መስጫ ቤቶች እንኳን የማታዩት፣ የማትዳስሱት ግንብ ተገንብቶ ይገጥማችኋል፡፡ ልክ ነዋ…ለአንዳንድ ‘ደንበኞች’ የሚደረገውን እንክብካቤ አይታችሁ፣ ለእናንተ የሚደረገውን እንክብካቤ ስትመዝኑት… ልክ እዛ ቦታ ሳትፈለጉ የሆነ ግንብ ዘላችሁ የመጣችሁ ነው የሚያስመስሉት፡፡
ስሙኝማ…እግረ መንገዴን…አንዳንድ መመገቢያ ቤቶች ልክ ምግቡ ሲቀርብ የዝንብ መአት አካባቢያችሁን በቁጥጥር ስር ያውሉታል፡፡ እናማ…መሠረታዊው ጥያቄ … “ዝምቦቹ ከየት መጡ?” የሚል ሳይሆን “የዝምቦች የማሽተት ችሎታ ይህን ያህል የዳበረ ለመሆኑ ምነው ሳይንስ አልነገረን?” የሚለው ነው... ቂ…ቂ…ቂ…
እናላችሁ…አሻግረን እንዳናይ የሚከልለን የማናየው፣ የማንዳስሰው ግንብ ተደንቅሮብናል፡፡
ጉዳዮቻችን በጊዜው እንዳያልቁ የማናየው፣ የማንዳስሰው ግንብ የተገነባብን ይመስላል፡፡ አንዲት በአሥር ደቂቃ ተፈርማ ማለቅ የምትችል ወረቀት ‘የእሳቸውን የበጎ ፍቃድ ፊርማ’ ለማግኘት ሀያ አንድ ቀን ከመጠበቅ ሌላ ምን ግንብ አለ!
በእርግጥ በፊት አንድ ዓመትም፣ ሁለት ዓመትም ወረፋ የሚያስጠብቁ ነገሮች፣ በአንድና በሁለት ሰዓት መጠናቀቅ መቻላቸው አሪፍ ነው፡፡ ለምሳሌ በፊት አንዷን እንትናዬ ለማግኘት ሰባት ወር ጆፌ ከጣሉ በኋላ ተዋውቆ፣ ስምንት ወር ሸኝቶ፣ አሥራ አንድ ወር ቡና በወተትና  ዘቢብ ኬክ ጋብዞ… ‘ኪሶሎጂ’ አጠገብ ለመድረስ ሌላ ሰባት ወር ምናምን ይጠበቃል፡፡ አሁን ልጄ… ሰባት ደቂቃም ከቆየ እንደ ጊዜ ብክነት ሊታይ ይችላል፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…
እናላችሁ…አሻግረን እንዳናይ የሚከልለን የማናየው፣ የማንዳስሰው ግንብ ተደንቅሮብናል፡፡
እናላችሁ…ከሀሜት እንዳንወጣ የሆነ የማይታይና፣ የማይዳሰስ ግንብ የተገነባብን ይመስላል፡፡
“ያቺ ሳባን ታስታውሻት የለ፣ ያቺ ጉረኛ እንኳን ይኸውልሽ ገንዘቡን እሞልጨዋለሁ ብላ ሀብታም ቤት ገብታ ጨርቋን አሸክሞ አበረራት አሉ… አይገርምሽም!  ደግሞ ጀምበሬ ታስታውሽው የለ  እንደዛ እንዳልተዘባነነብን አሁን ብታዪው ------ ኮሶ የያዛት ዶሮ መስሎልሻል፡፡
ያ እኛ መሥሪያ ቤት እቃ ግዢ የነበረው፣ ሳይቸግረው ምን የመሰለ ቪላ ሠርቶ ዓይን አይገባ መሰለሽ!
እናላችሁ …አሻግረን እንዳናይ የሚከልለን የማናየው፣ የማንዳስሰው ግንብ ተደንቅሮብናል፡፡
ለምሳሌ… አንዳንዱ በሆነውም፣ ባልሆነውም፣ “ከእኔ በላይ አዋቂ ለአሳር!” ባይ ለሌላው ፋታ ሳይሰጥ ይለፈልፋል፡፡
እኛም… “ኸረ እባክህ አንዳንድ ቀን ለምላስህ እንኳን የዓመት እረፍት ምናምን ስጠው…” ማለት ትተን እናዳምጠዋለን፡፡
እናላችሁ… ከአጠገባችን ሄድ ሲልልን፣ “እኔ የምለው የዚህ ሰውዬ ምላስ በጄኔሬተር ነው እንዴ የሚሠራው!”  ምናምን እንላለን፡፡  “ሰው እኮ ሲፈጠር ‘በወዝህ ጥረህ፣ ግረህ ብላ’ ተብሎ ነው፡፡ እሱ ‘በምላስህ ለፍልፈህ፣ ቀባጥረህ ብላ’ የተባለ ነው የሚመስለው!”
እናላችሁ… ከጀርባ ሆኖ ከመቦጨቅ አባዜ እንዳንወጣ የተገነባብን የማናየው፣ የማንዳስሰው ግንብ አለ፡፡
በብዙ ነገሮች…አለ አይደል…አሻግረን እንዳናይ የሚከልለን የማናየው፣ የማንዳስሰው ግንብ ተደንቅሮብናል፡፡
አንድዬ…ግንቡን ማፍረሻ ተአምሩን ይላክልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 4538 times