Monday, 06 February 2017 08:57

በአፍሪካ ዘላቂ የልማት ግብ - ለስነተዋልዶ ጤና መልካም አጋጣሚና ተግዳሮቶች

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

 ጥር 25/2007 ዓ/ም አመሻሹ ላይ የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር 25ኛ አመት በአልና አመታዊ ኮንፍረንስ እንዲሁም የአፍሪካ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ፌደሬሽን 2ኛው አመታዊ ጉባኤ መክፈቻ ስነስርአት ከተካሄደ በሁዋላ ስነስርአቱ ዛሬ ተፈጽሞአል።
የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር 25ኛ አመት በአልና አመታዊ ኮንፍረንስ እንዲሁም የአፍሪካ ጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ፌደሬሽን 2ኛ አመት ጉባኤ ሲካሄድ የተለያዩ ፐሮግራሞች ተከናውዋል። አመታዊ መሪ ቃሉም “SDG: opportunity and challenges for RH in Africa” (በአፍሪካ ዘላቂ የልማት ግብ ለስነተዋልዶ ጤና መልካም አጋጣሚዎችና ተግዳሮት) የሚል ሲሆን ከዚህ ጋር ተያይዞም ሳይንሳዊ ምርምሮች ለታዳሚው ቀርቦአል።
የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር 25ኛ አመት በአል ከመጀመሩ አስቀድሞ ከተካሄዱ ፕሮግራሞች መካከል አባላትን በምርምር ስራ ለማትጋት የሚያስችል የምርምር ጽሁፎችን በምን መንገድ በብቃትና በጥራት መጻፍ እንደሚቻል የሚያሳየው ስልጠና አንዱ ነበር። በተለይም በኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር በአመት ሁለት ጊዜ እየታተመ እንዲወጣ የሚፈለገው በስነተዋልዶ ጤና ላይ የሚያተኩረው ጆርናል ከአሜሪካ የጽንስና ማህጸን ኮሌጅ ጋር በመተባበር በምን መንገድ ማሳደግ እንደሚቻል በተካሄደው በዚህ የአሰልጣኞች ስልጠና ተሳተታፊ ከነበሩት ውስጥ ዶ/ር ሙህዲን አብዶ የጽንስና ማህጸን ሐኪምና የማህበሩ ቦርድ አባል እንዲሁም ዶ/ር ድልአየሁ በቀለ የጽንስና ማህጸን ሕክምና ባለሙያ ይገኙበታል። ለዚህ እትም ስለስልጠናው አንዳንድ እውነታዎችን ነግረውናል።
ስልጠናውን በሚመለከት ዶ/ር ሙህዲን እንደገለጹት ይህ በጃንዋሪ 31/2017 እና ፌብረዋሪ 1/2017 ላይ የተካሄደው ስልጠና በተለይም በ ESOG-ACOG/ በጋራ እንዲካሄድ የታቀደው ፕሮጀክት በአራት ዋና ዋና ዘርፎች የተከፈለ ሲሆን ማህበሩ የሚያሳትመው ጆርናል አንዱ ነው። ይህ ጆርናል የስነተዋልዶ ጤናን የሚመለከቱ ጉዳዮችን በምርምር በማውጣት ረገድ ያለበት ደረጃ ከፍ እንዲልና በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆን ማስቻል ከታለሙት ግቦች አንዱ ነው። ይህ ጆርናል እስከአሁን ባለው ደረጃ ጽሁፎችን ለማውጣትም ሆነ ለመገምገም በሰው እጥረትም ይሁን ጽሁፎች በበቂ ሁኔታ ባለመቅረብ የተነሳ ከፍተኛ የሆነ ችግር አለ። ጆርናሉም እንደታሰበው በአመት ሁለት ጊዜ ይቅርና አንዴም ለመውጣት አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ የሚገኝ ሆኖአል። ስለዚህም ፕሮጀክቱ የዚህን ጆርናል ችግር ይሄ ነው ብሎ በትክክል ለማወቅ እንዲሁም ካለበት ደረጃ ከፍ ለማድረግ በአለም አቀፍ ደረጃም ተቀባይነት ያለውና አዳዲስ ግኝቶችን አፍላቂ እንዲሆን ለማስቻል የሚረዳ የአሰልጣኞች ስልጠና የ25ኛው አመት የበአል አካል ሆኖ ተከናውኖአል።
ዶ/ር ድልአየሁ በቀለ እንደገለጹትም በአሜሪካ የጽንስና ማህጸን ኮሌጅ የሚታተመው የስነተ ዋልዶ ጤና ጆርናል በየወሩ ለንባብ የሚበቃ ሲሆን በኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር የሚታተመው ግን በአመት አንድ ጊዜም ለህትመት የማይበቃበት አጋጣሚ ታይቶአል። ስለዚህም ይሀንን መጽሔት እድገቱን ለማምጣትና ጽሐፊዎችም በምን መንገድ መጻፍ እንዲ ሁም ምርምሮችን ይፋ ማድረግ እንደሚችሉ መንገድ የሚመራ ስልጠና ከአሜሪካ በመጡ ምሁራንና በማህበሩ ትብብር ለሕክምና ባለሙያዎች ተሰጥቶአል። በእርግጥ ሁለቱን መጽሔቶች ለማቀራረብ ሰፊ ልዩነት ቢኖራቸውም ነገር ግን ይህ በኢትዮጵያ የሚታተመው ከውጭው ምን ልምድ ሊያገኝ ይገባል የሚለውም ትኩረትን አግኝቶአል። የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪ ሞች ማህበር የሚያሳትመው ጆርናል በተገቢው መንገድ ለሕትመት አለመብቃቱን ጉዳይ አስመ ልክቶ እንዲሁም የሚቀርቡ ጽሁፎች ጥራትና ብቃት ደረጃው የተራራቀ እንዳይሆን የሚረዳ የዳሰሳ ጥናት ለማድረግ በዝግጅት ላይ እንገኛለን። ስለዚህም እኛም ችግሩ የትጋ እንዳለ አውቀን ከእነርሱም በምናገኘው እርዳታ አብዛኞቹ ነገሮች ሊስተካከሉ ይችላሉ የሚል እምነት አለን። ብለዋል።
የተለያዩ የጽንስና ማህጸን ሕክምና ባለሙያዎች እንዲሁም ተመሳሳይ ሙያ ያላቸው ግለሰቦች ጽሁፎቻቸውን በተለያዩ ሀገራትና በኢትዮጵያም ቢሆን በተለያየ አካል በሚታተሙ መጽሔቶች ላይ እንደሚያወጡና ለዚህም ምክንያታቸው የምርምር ውጤታቸውን በትክክል አመዛዝኖ የሚቀበላቸው ስለሚያጡ መሆኑን የሚገልጡባቸው አጋጣሚዎች መኖራቸው በማንሳት ለዚህ ምክንያት የሚሆነው ምንድነው ስንል ለሁለቱም ባለሙያዎች ባቀረብነው ጥያቄ መልሳቸው እንደሚከተለው ነበር።
ዶ/ር ድልአየሁ በቀለ እንደሚሉት የጽሁፍ አቅራቢዎች መስተንግዶ ምናልባትም እንደችግር ከሚቆጠሩት ምክንያቶች መካከል የሚጠቀሰው አንዱ ነጥብ ሊሆን ይችላል። ይህም የሚያመ ለክተው ጽሁፎችን እንደገና በመመርመር በኩል የተቀመጡ ባለሙያዎች እጥረት ወይንም ጊዜ ማጣት የመሳሰሉት ሊሆኑ ይችላሉ። የቀረቡት ጽሁፎችም ጥራትና ብቃት አነጋጋሪ የሚሆኑበት አጋጣሚም ብዙ ነው። በወደፊቱ አሰራር ግን የጆርናል ኮማው በተደራጀ መልኩ የተዋቀረ ሲሆን ለጽሁፍ አቅራቢዎችም ምላሹ እንዲሁ ቀልጠፍ ያለ ይሆናል የሚል እምነት አለ። ከ25ኛው አመት የኢዮቤልዩ በአል ጋር በተያያዘ የተሰጠው ስልጠና ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ለተውጣጡ የህክምና ባለሙያዎች ሲሆን እነዚህ ባለሙያዎች ወደስራቸው ሲመለሱ አብረዋቸው ላሉ ባለሙያዎች የቀሰሙትን ያካፍላሉ ብለን እናምናለን።
የ25ኛ አመቱን በአል ከጥር 25-27 ያከበረው የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ባለፉት 25 አመታት በስነተዋልዶ ጤና፣ ኤችአይቪ ከእናት ወደልጅ እንዳይተላለፍ እና በመካከለኛ ደረጃ የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች በማዋለድ ተግባር የተሻለ ክህሎት እንዲኖራቸው የሚያስችል ስልጠና በመስጠት በዘርፉ ትልቅ እገዛ አድርጎአል። ከዚህም ባሻገር ሴቶች እና ሕጻናት በወሲባዊ ትንኮሳ ዙሪያ ጥቃት ከደረሰባቸው በሁዋላ ተገቢውን ሕክምናና የምክር አገልግሎት እና የህግ ድጋፍ እሚያገኙበት አሰራር እንዲዘረጋ ከአጋር ድር ጅቶች ጋር በመሆን በተለያዩ መስተዳድሮች ሞዴል ክሊኒኮችን በመመስረት አገልግሎቱን እንዲ ያገኙ አስችሎአል። ማህበሩ የተለያዩ ሙያነክ መመሪያዎችን በማዘጋጀት ተገቢው የህክምና እር ዳታ ለተገልጋዩ ለማዳረስ የበኩሉን ጥረት አድርጎአል። ይህንን ለወደፊቱም በተሻለ መንገድ ለመቀጠል ጥረት በመደረግ ላይ ነው።
ከበአሉ መዳረሻ ጀምሮ በአሉ እስኪጠናቀቅ ድረስ የተከናወኑትን አበይት ተግባራት አስቀ ድሞውኑ በጋዜጣዊ መግለጫ የተሰጠ በመሆኑ ለትውስታ ለንባብ ብለናል።
የማህበሩ የስብሰባ መክፈቻ ቀንና ከዚያ አንድ ቀን በፊት በተከታታይ በአልትራሳውንድና የእርግዝና ክትትልን በሚመለከት የላቀ ሕክምና መስጠትን የሚያስችል ስልጠና ማህበሩ ከቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ጋር በመሆን ሰጥቶአል።
ከሌሎች ሐገሮች ከሚመጡ ተመሳሳይ ሙያ ካላቸው ባለሙያዎች ጋር በመተባበር ማህበሩ የአንድ ቀን ስልጠና አካሂዶአል። በዚሁ ቀን በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል Hysteroscopy የሚባለውን የህክምና ዘዴ በሚመለከት በተለይም የማህጸን ችግሮችን ማወቅና መለየት የሚቻልበትን አዲስ ክህሎት ለማህበሩ አባላት ሰጥቶአል።
የጽንስና ማህጸን ድንገተኛ ሕክምናን በተመለከተ ዘመናዊ ወይንም ወቅታዊ የሆኑ እውቀቶች እና ክህሎቶችን በመፈተሽ አሁን ከሚሰራበት በተሻለ ምን መስራት ይቻላል የሚለውን ማህበሩ ከአሜሪካው የጽንስና ማህጸን ሕክምና ማህበር ጋር በመተባበር አካሂዶአል።
በማህጸን ጫፍ ካንሰርና ከማህጸን ግድግዳ በሚነሳ ካንሰር ላይ ያሉትን ለውጦች ወይንም ወቅታዊ ግኝቶች ከጀርመንና ከአሜሪካ ከሚመጡ ሙያተኞች ጋር በመተባበር ስልጠና ይሰጣል።
በቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ላይ በተለይም በቋሚነትና ለረጅም ጊዜ በሚያገለግሉ የቤተሰብ እቅድ ዘዴዎች ላይ ግማሽ ቀን የሚወስድ ስልጠና ይሰጣል።
የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሕክምና ባለሙያዎች ማህበር ሀያ አምስተኛ አመት የብር ኢዮቤልዩ በአልና አመታዊ ጉባኤ እንዲሁም የአፍሪካው የጽንስና ማህጸን ሕክምና ባለሙያዎች ፌደሬሽን 2ኛ አመታዊ ጉባኤን በሚመለከት በተካሄደው ስነስርአት ላይ የተነሱ አበይት ክንውኖችን በወደፊቱ ሕትመት እናስነብባለን።

Read 1478 times