Sunday, 05 February 2017 00:00

በ2009 የ.ተ.መ.ድ ቅድሚያ ለሴቶች የ5 ኪ.ሜ ሩጫ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

‹‹ስለምትችል›› በሚል መርህ ይካሄዳል

      በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አዘጋጅነት የ2009 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቅድሚያ ለሴቶች የ5 ኪ.ሜ የጎዳና ላይ ሩጫ የካቲት 27 በአዲስ አበባ ከተማ  የሚካሄድ ሲሆን 11 ሺ ተሳታፊዎች እንደሚኖሩት ይጠበቃል፡፡ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አዘጋጆች ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት በ5 ኪሎ ሜትር ሩጫው ከ300 በላይ ሴት አትሌቶች የተለያዩ ክለቦችን በመወከል የሚሳተፉ ሲሆን በተለያዩ ደረጃዎች ለሚያሸንፉት ከ100ሺ ብር በላይ ለሽልማት ተዘጋጅቷል፡፡
በ2009 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቅድሚያ ለሴቶች የ5 ኪ.ሜ የጎዳና ላይ ሩጫ ላይ ለመሳተፍ የመሮጫው ቲሸርት ዋጋ 120 ብር በመክፈል የሚከናወነው ምዝገባ የፊታችን ረቡእ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙት 4 የእናት ባንክ ቅርንጫፎች እና በካፒታል ሆቴልና ስፓ ይጀመራል፡፡ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የውድድር አዘጋጅ ዳግማዊት አማረ እንደገለፀችው ምዝገባ ባይጀመርም ሰሞኑን ከ2000 በላይ የተሳትፎ ፍላጎት ያላቸው ስፖርተኞች ወረፋ ለመያዝ መሞከራቸውን ጠቅሳ፤ በየዓመቱ እየገዘፈ ለመጣው ሴቶችን ብቻ ለሚያሳፈው ውድድር በቢሯቸው የሚካሄደው  ምዝገባ እጅግ ፈጣን መሆኑ አዘጋጆቹን የሚያደስት ነው ብላለች፡፡ ቅድሚያ ለሴቶች የ5 ኪ.ሜ የጎዳና ላይ ሩጫው ከ13 ዓመታት በፊት ሲጀመር በ2ሺ ተሳታፊዎች ሲሆን ዘንድሮ የስፖርተኞቹ ብዛት 11ሺ የደረሰው በውድድሩ ለመሳተፍ ያለው ፍላጎት ከፍተኛ በመሆኑ ነው፡፡ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የውድድር አዘጋጅ ዳግማዊት አማረ ለስፖርት አድማስ እንደተናገረችው የሩጫው ዝና እየገዘፈ የመጣባቸውን ምክንያቶች ስታስረዳ፤  በኡጋንዳ ያለ የሴቶች ስፖርት ማህበር በውድድሩ ለመሳተፍ ፍላጎት ማሳየቱ አንዱ ማስረጃ ሊሆን እንደሚችል ጠቅሳ፤ የጎዳና ላይ ሩጫው ሲጀመር በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የምትሰራው እሷ ብቻ እንደነበረች አስታውሳ፤ ዘንድሮ በአጠቃላይ የቅድሚያ ለሴቶች ሩጫው ከሚያዘጋጁ 13 ሰራተኞች ስድስቱ ሴቶች መሆናቸው ከፍተኛ ለውጥ መሆኑን አስገንዝባለች፡፡
‹‹ቅድሚያ ለሴቶች ሩጫ ከተለያየ የህብረተሰብ ክፍል፤  የኑሮ ደረጃ፤ እድሜ፤ ሙያ እና የህይወት ተመክሮ የተሰባሰቡ ሴቶች አንድ አይነት የመሮጫ ቲሸርት ለብሰው በአንድ ስሜት፤ ደስታ እና አብሮነት በድምቀት የሚሳተፉበት ውድድር በመሆኑ ልዩ ድምቀት የሚላበስ ነው፡፡ ስለሆነም በተላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከምናዘጋጃቸው ውድድሮች ሁሌም በየዓመቱ የምናቀው እና የምጓጓበት ነው›› በማለትም የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የውድድር አዘጋጅ ዳማዊት አማረ ለስፖርት አድማስ ተናግራለች፡፡
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ   በየዓመቱ ቅድሚያ ለሴቶች ሩጫን የሚዘጋጀው የኢትዮጵያን ሴቶች ስኬት ለመዘከርና እውቅና ለመስጠት፤  በመላው ዓለም ማርች 8 የሚካሄደውን የዓለም ሴቶች ቀን ለማክበር፤ ሴቶች ሩጫን ስፖርት እንዲያዘወትሩ እና በውድድሮችም ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩ ለማነሳሳት ነው፡፡ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አዘጋጆች በቅድሚያ ለሴቶች ሩጫ ምርጥ የአገሪቱ አትሌቶች ተሳትፈው እንደተሳካላቸው የውድድሩን ስኬት እንደሚያረጋግጥ በየጊዜው ሲገልፅ ታዋቂ የክለብ አትሌቶች  በተለያዩ ጊዜያት ባገኙት የውድድር እድል መነሻ ሆኗቸው በቀጣይ ስኬታማ መሆናቸው በማመልከት ነው፡፡   በምሳሌነትም ሁለቴ አሸናፊ የሆነችው ማራቶኒስት አሰለፈች መርጊያ፤ የ5ሺ ሜትር ምርጥ ሯጮች ከረኒ ጀሊላ እና ሱሌ ኡታራ ይጠቀሳሉ፡፡ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከቅድሚያ ለሴቶች ሩጫ ጋር በተያያዘ ከሚያነግባቸው መርሆች ባሻገር ውድድሩን በ5 ኪሎሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ የሚያካሂደው  የኢትዮጵያ ሴት አትሌቶች በ5ሺ ሜትር ሩጫ በመላው ዓለም ያላቸውን የበላይነት ምክንያት በማድረግ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች በበተለይ በ5ሺ ሜትር ከተመዘገቡ 10 ፈጣን ሰዓቶች 9 የተመዘገቡት በኢትዮጵያ ሴት አትሌቶች እንደሆነም ይታወቃል፡፡
የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አዘጋጆች በቅድሚያ ለሴቶች ሩጫው ከዋናው የክለብ አትሌቶች ፉክክር ባሻገር በተለያዩ ምድቦች ልዩ ውድድሮችንም ያዘጋጃል፡፡ አንደኛው ውድድር የውጭ አገራት ሴት አምባሳደሮች፤ ዲፕሎማቶች በማሳተፍ የሚካሄደው ሲሆን ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ምድብ ለአሸናፊነት የበቁት የዴንማርክ አምባሳደር ሜቴ ታይግሰን አሸናፊነታቸውን ለመድገም ተሳትፏቸውን አረጋግጠዋል፡፡ በሌላ በኩል  የሚካሄደው ልዩ ውድድር በሴት ተምሳሌቶች ምድብ ዘንድሮ ለ3ኛ ጊዜ የሚካሄደው ውድድር ሲሆን በ13ኛው ፕላን ኢትዮጵያ ቅድሚያ ለሴቶች ሩጫ የተምሳሌት ሴቶች ውድድርን ያሸነፉት ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ ነበሩ፡፡  ከትናንት በስቲያ በካፒታል ሆቴልና ስፓ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይም በቅድሚያ ለሴቶች ሩጫው ዘንድሮ የኢትዮጵያ ሴት ተምሳሌቶች የተዋወቁበት መድረክም ከሩጫ ባሻገር ከፍተኛ ሞገስ ያለው ስነስርዓት ሆኖ ይጠቀሳል፡፡ ተምሳሌት ሴቶቹን ባስተዋወቀው ዝግጅት መድረኩን የመራችው የካፒታል ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ወይዘሮ ትዕግስት ይልማ የነበረች ሲሆን በእለቱ የነበረውን ስነስርዓት በማስተናበርና በማስተዋወቅ የሰሩት ሌሎች ሴቶች ታዋቂዋ አርቲስት፤ የሙዚቃ ባለሙያ እና ኢኮኖሚስት ሙኒት መስፍን እንዲሁም የዋኖስ የኮሜድያን ቡድን አባል የሆነችው ቤተልሄም ነበሩ፡፡ የቅድሚያ ለሴቶች 5 ኪሎ ሜትር ሩጫ ሴት ተምሳሌቶች ሆነው ከተዋወቁት መካከል በቅድሚያ ወደ መድረኩ የተጋበዙት እማሆይ ፍቅርተማርያም በቀለ ሲሆኑ የ56 ዓመታት እድሜ ያለው የጌተሰማኒ ቤተደናግል ጠባባት ገዳም መሪ የሆኑና ‹‹አብዮታዊ መነኩሴ›› የተባሉ ናቸው። እማሆይ ፍቅርተ ማርያም ሴቶችን ለማብቃት እንዲሁም ስራን በመፍጠር የተመሰገኑ፤ ገዳማቸውን ለ30 አመታት ያገለገሉ ናቸው፡፡ ሌላዋ ተምሳሌት ዶክተር ቦጋለች ገብሬ ሲሆኑ በተግባራቸው በርካታ ሽልማቶች ያገኙ፤ በስራ ዘመናቸው በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ለሴቶች የተሻለ ህይወት በሚፈጥሩ ተግባራት ከፍተኛ ግልጋሎት ያበረከቱ በተለይ በአንዳንድ አገሪቱ ክልሎች የሴቶች ግርዛት ሙሉ ሙሉ እንዲቀር የሰሩ ናቸው፡፡ ለሴቶች መብት መከበር ፈርቀዳጅ ሆነው የታገሉ፤ የኢትዮጵያ ሴቶች የህግ ባለሙያዎች ማህበርን የመሰረቱና በሙያቸው ግንባርቀደም ሆነው ያገለገሉ፤ በመጠነ ሰፊ ተግባሮቻቸው ለኖቤል የሰላም ሽልማት ለመታጨት የደረሱና በአሁኑ ወቅት በሴቶች ፋይናንስ አገልግሎት የሚመሰገነውን እናት ባንክ በቦርድ ሰብሳቢነት የሚመሩት ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ ከዘንደሮ ተምሳሌቶች አንዷ ሆነው በመድረኩ ተዋውቀዋል፡፡ ሌላዋ ተምሳሌት ብስክሌተኛዋ ወይዘሮ ሂሩት ገድሉ ሲሆኑ በብስክሌት በመላው ኢትዮጵያ በ10ሺዎች የሚለኩ ኪሎሜትሮችን በመንቀሳቀስ ምግባረሰና ተቋማ ባልደረሱባቸው አካባቢዎች  በኤችአይቪ ኤድስ ዙርያ ግንዛቤ በመፍጠር፤ እንክብካቤ በመስጠትና በአራት የተለያዩ ከተሞች ተመሳሳይ የበጎ አድራጎት እንቅስቃሴዎችን የሚሰሩ ተቋማትን በመመስረት አድናቆት ያተረፉ ናቸው። ሌሎቹ ተምሳሌቶች ደግሞ የፖሊስ የማርሽ ቡድን መሪ ራድያ ኢማም  እና በወጣትነቷ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት  የሴቶችን ጥቅምና መብት በሚያስከብሩ በተለይ የመማር አቅም የሌላቸውን ሴቶች በሚደግፉ እንቅስቃሴዎች ንቁ ተሳታፊ የሆነችው ህሊና እስጢፋኖስ ነበሩ፡፡ በሌላ በኩል በተባበሩት መንግስታት የህፃናት ድርጅት የበጎ ፍቃድ አምባሳደር የሆኑት ታላላቆቹ አትሌቶች መሰረት ደፋር እና ብርሃኔ አደሬ በጋዜጣዊ መግለጫ ከተገኙት መካከከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ሁለቱ አትሌቶች በስነስርዓቱ ላይ ለ5 ኪሎሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ የተዘጋጀውን የመሮጫ ቲሸርት ለተምሳሌቶቹ በመስጠት በይፋ ያስተዋወቁ ሲሆን የቅድሚያ ለሴቶች ሩጫ አምባሳደር የሆነችው አትሌት መሰረት ደፋር በዘንድሮው ውድድር ሩጫቸውን ከ35 ደቂቃ በታች ለሚጨርሱ ሴት ስፖርተኞች በስሟ የተዘጋጀውን የምስክር ወረቀት እንደምትሸለም አስታውቃለች፡፡ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አዘጋጆች ለተሳታፊዎቹ ባስተላለፉት መልዕክት ውድድሩ የሚካሄድበት ሲቃረብ መጠነኛ ልምምድ እና ዝግጅት በማድረግ ከ35 ደቂቃ በታች ለመግባት የሚቻል መሆኑን ጠቁመው፤ ተሳታፊዎች ከሚለብሱት የመሮጫ ቲሸርት በስተጀርባ ‹‹ስለምትችል›› በሚል ከሰፈረው የውድድሩ መሪ መፈክር ርእስ ማናቸውንም የሚችሉትን ነገር በጉልህ  በመፃፍ ለውድድሩ ተጨማሪ ድምቀት እንዲፈጥሩም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

Read 1226 times