Sunday, 05 February 2017 00:00

ኦባማ፤ ፕሬዚደንቱ በስደተኞች ላይ ያስተላለፉትን ውሳኔ አወገዙ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፤ አዲሱ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሰባት አገራት ስደተኞች ለተወሰነ ጊዜ ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ከሰሞኑ ያስተላለፉትን ውሳኔ በማውገዝ፣ ከዚሁ ጋር በተያያዘ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የተደረጉ ተቃውሞዎችን እንደሚደግፉ ማስታወቃቸውን ኤንቢሲ ኒውስ ዘግቧል፡፡
ኦባማ በቃል አቀባያቸው በኩል ባስተላለፉት መልዕክት፣ ሃይማኖትን መሰረት ባደረገ መልኩ በህዝቦች ላይ የሚደረግን አድሎአዊ አሰራር እንደሚቃወሙ ማስታወቃቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ ትራምፕ ያስተላለፉትን ውሳኔ በመቃወም አደባባይ የወጡ ዜጎችን ድርጊት እንደሚደግፉ መግለጻቸውንም አብራርቷል፡፡ ኦባማ መንበረ ስልጣኑን ለትራምፕ ካስረከቡ ወዲህ በአዲሱ አገዛዝ ላይ ትችታቸውን ሲሰነዝሩ ይህ የመጀመሪያው እንደሆነ የጠቆመው ዘገባው፤ የሰሞኑ የትራምፕ ውሳኔ ኦባማ ከአምስት አመታት በፊት ኢራቃውያን ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ጥለውት ከነበረው የእገዳ ውሳኔ ጋር መነጻጸር እንደሌለበት ቃል አቀባዩ ይፋ ያደረጉት መግለጫ ማስታወቁን አስረድቷል፡፡
ፎክስ ኒውስ በበኩሉ፤ በአገራቱ ላይ የተወሰደው እርምጃ በኦባማ የስልጣን ዘመን የተጀመረና ህጋዊ እውቅና የተሰጠው ጉዳይ መሆኑን በማስታወስ፣ ሰባቱ አገራት ለአሜሪካ የደህንነት ስጋት መሆናቸው ተጠቅሶ፣ የአገራቱ ዜጎች ላይ የተለየ ቁጥጥር እንዲደረግ የሚደነግጉ ህጎች በ2015 እና በ2016 መውጣታቸውን ዘግቧል፡፡
በተያያዘ ዜናም፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬስ፤ አሜሪካ የወሰደቺው እርምጃ የተመድን መሰረታዊ መርሆዎች የጣሰ መሆኑን ጠቅሰው፣ ትራምፕ በሰባቱ አገራት ስደተኞች ላይ የጣሉትን እገዳ በአፋጣኝ እንዲያነሱ ከትናንት በስቲያ ባስተላለፉት መልእክት ጠይቀዋል፡፡ ሽብርተኞች ወደ አገራት ሰርገው ገብተው አደጋ የመፍጠር ዕድላቸው አሳሳቢ ስጋት መሆኑን የጠቆሙት ጉቴሬስ፤ ይሄም ሆኖ ግን ትራምፕ የወሰዱት እርምጃ አሜሪካንም ሆነ ሌሎች አገራትን ከመሰል ስጋት ለመጠበቅ የሚያስችል ሁነኛ አማራጭ አለመሆኑን አስምረውበታል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ፣ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሰባት የአለማችን አገራት ስደተኞች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ያሳለፉት የእገዳ ውሳኔ እንዳስደሰታቸው አይሲስ እና አልቃይዳን ጨምሮ የተለያዩ ጂሃዲስት ቡድኖች ማስታወቃቸውን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡
“ትራምፕ በአብዛኛው ሙስሊም ህዝብ ያላቸው የኢራን፣ ኢራቅ፣ ሊቢያ፣ ሶርያ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳንና የመን ዜጎች ወደ ግዛታቸው እንዳይገቡ ያስተላለፉት ትዕዛዝ፣ ከዚህ ቀደም እንደተናገርነው አሜሪካ ከእስልምና ጋር ጦርነት ውስጥ መግባቷን የሚያረጋግጥ ነው” ሲሉ በተለያዩ ድረገጾች በኩል ባስተላለፏቸው መልዕክቶች ማስታወቃቸውን ዘገባው ገልጧል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ፣ የትራምፕን የስደተኞች ውሳኔ የተቃወሙ 1.7 ሚሊዮን ያህል እንግሊዛውያን፣ በእንግሊዝ ሊያደርጉት ያቀዱት ይፋዊ የስራ ጉብኝት እንዲሰረዝ የሚጠይቅ ፊርማ ያሰባሰቡ ሲሆን በተቃራኒው የትራምፕን ጉብኝት በመደገፍ፣ ፊርማቸውን ያሰባሰቡ የአገሪቱ ዜጎች ቁጥርም ከ200 ሺህ በላይ መድረሱን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ ይህን ተከትሎም የእንግሊዝ ፓርላማ በጉዳዩ ዙሪያ ከሁለት ሳምንታት በኋላ ለመከራከር ቀጠሮ መያዙንም ዘገባው ጠቁሟል፡፡

Read 3661 times