Sunday, 05 February 2017 00:00

እንጀራና - አውዳመት!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(9 votes)

 ይሄ ክብ እንጀራ ያላዞረኝ ቦታ የለም፣ … ያልረገጥኩት መሬት፡፡ … አሁንም ዞሬ ዞሬ አገሬ ገብቻለሁ፡፡ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ምትሀታም ናት፡፡ … የጀግና አገር እያሉ ቢያሞካሹዋትም እኔ ከፍ ብሎ የሚታየኝ የጋራ ባህልዋ፣ የማህበረሰቡ ክብ መሶብ ላይ ታድኖ ማዕድ መቁረሱ ይመስለኛል፡፡
…. አረብ አገር ሄጃለሁ፣ አውሮፓም - አሜሪካም ረግጫለሁ! ይህ ሁሉ ግን ለእንጀራ ነው - ክብ መዞር! … እዚያም እያለሁ ትዝ የሚለኝ እንጀራ ነው፡፡ ወይም ጢቢኛ … የቡሄ ጅራፍ ነው … ጥይትና ጅግንነት የሚያስታውሰኝ፡፡ … አለዚያ ለእንቁጣጣሽ እንጀራ … ለመስቀል እንጀራ … ለገና እንጀራ … ለጥምቀት እንጀራ! …. ተጠራርቶ መብላት፡፡ ዘመድ መጠየቅ … አክፋይ መሄድ! …
ሌላው ችቦ ነው፡፡ የቡሄ ችቦ … የእንቁጣሽ ችቦ … የመስቀል ችቦ! … በቃ ናፍቆቱን … እንደ እሳት የሚያነድደው ይኸው ነው፡፡ የምፈራው ደሞ ጥምቀት ነው፡፡ ናፍቄ … ናፍቄ … አገሬ ገባሁ፡፡ … ይኸው አሁንም እንጀራዬ ካፌ ሆነና፣ ካፌ ከፍቼ ራሴ ባሬስታ ሆኜ እሰራለሁ፡፡
ታዲያ እዚህ ጦር ኃይሎች በከፈትኳት ካፌ ውስጥ ያላየሁት ያልሰማሁት ወሬ የለም፡፡ …. መቸም ያበሻ ወሬ፣ ከፈረንጁ ይልቅ ይጥመኛል፣ ፈረንጆቹ ምግባቸው ላይ ቅመም አያውቁም፤ ወሬያቸውም ያው ነው፡፡ ሀበሻ ግን ወጡ ብቻ ሳይሆን ወሬው በቅመም ያበደ ነው፡፡ “… ነፍሱን ይማረውና … ጌታ ይቅር ይበለኝና … ወዘተ” እያለ እንደጎርፍ ያፈስሰዋል፡፡ … እዚህ ካፌማ ያየሁትና የሰማሁት ልክ የለውም፡፡ በተለይ አንድ ቤንዚን ማደያ የምትሰራ ሴት፤ ከንፈሮችዋ ላይ አጃቢ ሙዚቃ ያላቸው ይመስላል፤ ስታጣፍጥ! ወሬውን ከየት እንደምታመጣው አላውቅም!
ለነገሩ ሌላም ወታደር አሉ፡፡ … ቀድሞ 18ኛው ክፍለ ጦር ነበርኩ ብለው ሻዕቢያን ቀሚስ አልብሰው ይገርፏታል- በምላሳቸው! … “አርዋን ነበር ያበላናት …. ምን ያደርጋል፡፡ ጓድ መንግስቱም ቢሆን ጀግና ነው፡፡ … ጦር ሜዳ አጠገቤ ሆኖ ሲታኮስ አይቼዋለሁ፡፡ ቆራጥ መሪ! … ፎቶዬ ባይጠፋ አሳይህ ነበር!” እያሉ ለገባ ለወጣው ይደሰኩራሉ፡፡
ወጣት ወንዶችና ኮረዶች አፍ ለአፍ ገጥመው ሲያወሩ፣ እቀናለሁ፡፡ ትዝ ይለኛል፡፡ ወጣትነቴ አመድ ነው፤ መች አፈቀርኩበት! … መች አጣጣምኩት! … እንጀራ ሲያዞረኝ … የደረስኩበት አልጋ ላይ ስወድቅ … ሳላጣጥመው ቀርቻለሁ፡፡
በተለይ ሁለት ወጣቶች ነበሩ የሚያስቀኑኝ፤ በኋላ ግን ከቤቱ ቢጠፉ ግራ ገብቶኝ አስቴርን ጠየቅኋት፡፡ አስቴር ማለቴ ቤንዚን ማደያ የምትሰራው … ከንፈሮችዋ ክንፍ አወጡ፤ አለጠለጡ፡፡
“አልሰማህም እንዴ?”
ደነገጥኩ፡፡
“ምኑን?”
“እሱኮ … ሞተ “
ጭንቅላቴን ያዝኩ፡፡
“ምን ሆኖ?”
‹‹ ፍቅረኛው ፈንግለው!››
‹‹አላምንም!›› ተወርውሬ-ወጣሁ-ከባንኮኒ፡፡
‹‹አንዱ ሼባ ከአሜሪካ መጥቶ ገዛት”..
‹‹አይደረግም!” ጭንቅላቴን ያዝኩ፡፡
‹‹አዎ!... ጥሏው ስትሄድ እርሱ ራሱን አጠፋ”
እዚህ አገር ከመጣሁ በኋላ የሰማሁት አንድ አሳዛኝ ወሬ- ይሄ ነው፡፡ ሌሎች አሥቂኞች፤ አሥገራሚዎች… ብዙ ብዙ አይነት ጨዋታዎችና-ምሬቶች እሰማለሁ፡፡
የኑሮ ውድነት፣ የግብር መብዛት፤ የሙስና ጉዳይ.. የትራንስፖርት ችግር ብሶት!... የሰዎች ድንገት በሀብት ተተኩሶ ሰማይ መንካት፤ የብዙ ሀብታሞች የቀድሞ ሚስቶቻቸውን መፍታት… የኔ ዳኞች ጉዞ..የዕድር ዳኞች ዕብሪት.. ሌላም… ሌላም።
የገና እና የጥምቀት አውዳመት ተከታትሎ መምጣትን አሥመልክቶ አስቴር ያወራችው ወሬ አንዳች ክብሪት ነገር ... ትንቢት ይሁን ትዕቢት ውሥጤ ፈጥሯል፡፡
ለጓደኛዋ ነበር የምታወራው፡፡ ባልዋ ይሁን ውሽማዋ አላውቅም … ብቻ ብሥል ቀይ ነው፤ ክልስ ነገር፡፡ ለርሱ ሥታወራ … እኔ እያዳመጥኳት መሆኑን አወቀች፡፡ ድምፅዋን ከፍ አድርጋ አድማጭ ሰበሰበች፡፡
‹‹የዘንድሮ ነገር ሁሁሁ…ኡኡ!›› አለችና ቀጠለች ‹‹..እኛ ሠፈር አንድ አሮጌት አሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያን ሳሚ ናቸው፤ እንዲያውም ሳይሞነኩሱ አይቀሩምም፡ መቸም ሰፈር ውስጥ በልቅሶ ጊዜ … በማስተዛዘን፣ የወለደ በመጠየቅ፤ የሚደርስላቸው የለም፡፡ ሰርግ ቢሆን፤ ክርስትና አይቀሩም፡፡
እናላችሁ … ለእንቁጣጣሽ ችቦ ሲበራ፤ ችቦውን ከልጆች ጋር አምሽተው አበሩና ተኙ፡፡ ጠዋት ልጃገረዶች አበባይሆይ! ሲሉ፤ ልብሳቸው ለባብሰው ብድግ አሉና፣ ለልጃገረዶቹ የሚሰጡትን ብር ጠቅልለው ይዘው ብቅ እንዳሉ፣ ምን እንደሆኑ ሳይታወቅ ድንገት ወድቀው፣ አረፋ ሲደፍቁ ተገኙ፡፡
‹‹ምክንያቱ ምን እንደሆነ ሳይታወቅ ወደ ሆስፒታል ተወሰዱና፣ የሆነ የሆነ ነገር አድርገውላቸው ነፍሳቸው ሲመለስ፤ ምን ሆነው እንደነበር ተጠየቁ በንግግራችው ከማዘን ይልቅ ብዙዎቻችን ሣቅን፡፡ ‹‹ምን መሠላችሁ?›› ብላ ልብ ለማንጠልጠል ሞክረች፡፡
‹‹ምንድነው?››
‹‹እታበባሽ ሊሉ የመጡት ልጃገረዶች በሙሉ ቻይኖች ነበሩ!..›› ሁላችንም ሣቅንላት፡፡
በዚህ ብቻ ግን አልበቃትም፡፡ ቀጠለችበት፤ ‹‹ልጃገረድ መሥለው የመጡት በሙሉ ለካ ወንዶች ናቸው!...ሻሻቸውን- አውልቀው ሲሮጡ ታይተዋል፡፡… በአንድ ሲኖትራክ ተጭነው እልም አ›› አሉ፡፡
‹‹ጉ-ድ!... ጉድ!-ጉድ!››
‹‹ኧረ ወደ ገጠር የተሰማ ሌላም ወሬ አለ፡፡›› አሉ ሌላዋ ወረኛ አሮጊት፡፡
‹‹ምንድነው ደሞ?››
‹‹እንደ ካህን ያደርጋቸዋል አሉ፡፡››
‹‹እንዴት… እንዴት?
‹‹የሆነ ሰው ቁጥር ላይ… ቄስ ይሁን ፓስተር ይሁን፤ አንዱ ቻይና ያወራው ነገር ገርሞኛል፡፡ ብለው የነገሩኝን ስሙ አለችን?!››
ምን ምርጫ አለን፡፡
‹‹… ሰባኪው ስለሞተው ሰውዬ ሲናገር ‹ይህ አሁን አስክሬኑን የምታዩት ሰው፤ በምድር ላይ ሳለ በልማት፣ በስራ ፈጠራና በሕዝብ በማደራጀት የታወቀ ነበር፡፡… በባቡር ሥራ… በመንገድ ስራ.. የተሰጠውን ሃላፊነት በአግባቡ የተወጣ ነው፡፡ ስለዚህ የሚጠየቅበት ምንም ሀጢአት የለም፤… ሀጢአት ማለት ስንፍና ነው፡፡… ይህ ሰው ደግሞ እንደፈረደበት የሚያደርገው ሀጢአት የለም፤ በጣም የሚደንቀው ደግሞ፤ በሞተ ጊዜ ዐይኖቹን፤ ኩላሊቱንና ልቡን ለሌሎች ወገኖቹ ተናዝዞ ነው ያለፈው፡፡”
ብሎ ቻይናዊው ሰባኪ ሲናገር፤ ቤተሰቦቹ ብድግ ሲሉ ጥቂቱን በካራቴ ካሳረፈ በኋላ .. ‹‹.. የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው!›› አልልል… የሚያደርጉትን አያውቁምና በላቸው!›› ነው ትምህርቴ›› ብሎ ሲጨርስ ብዙ ቻይኖች መጥተው ወደ ተቆፈረው ጉድጓድ ወሰዱት፡፡
ይሄ ካፍቴሪያ ያላሰየኝ ምናለ!... እንጀራ ሲያዞረኝ.. ገናና ጥምቀት ሲናፍቀኝ … የቡሄ ጅራፍ ትዝ ሲለኝ …!

Read 2931 times