Sunday, 05 February 2017 00:00

ኢትዮጵያዊው፤ የአሜሪካ ብሔራዊ የሳይንስ ፋውንዴሽን ተሸላሚ ሆኑ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 ለምርምራቸው የ600 ሺህ ዶላር የገንዘብ ድጋፍ አግኝተዋል
    አሜሪካ በሚገኘው ኒው ሜክሲኮ ዩኒቨርሲቲ የኬሚስትሪና ኬሚካል ባዮሎጂ የትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ኢትዮጵያዊው ረዳት ፕሮፌሰር ተረፈ ሃብተየስ፣ የአገሪቱ ብሄራዊ የሳይንስ ፋውንዴሽን፣ በምርምር ዘርፍ የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ምሁራን የሚሰጠው “የታላቁ የፋካልቲ ኧርሊ ካሪየር ዲቨሎፕመንት አዋርድ” አሸናፊ መሆናቸው ተዘግቧል፡፡
ረዳት ፕሮፌሰር ተረፈ ሃብተየስ፤ በዩኒቨርሲቲው የላቀ ቴክኖሎጂ ቁሳቁስ ምርምር ማዕከል፣ ከግብረ አበሮቻቸው ጋር ለሚያከናውኑትና አምስት አመታትን ለሚወስደው የምርምር ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ፣ የ600 ሺህ ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ማግኘታቸውን ዩኒቨርሲቲው በሳምንቱ መጀመሪያ በድረገጹ ላይ ባወጣው መረጃ ጠቁሟል፡፡ ረዳት ፕሮፌሰሩ በምርምር ፕሮጀክቱ፣ እጅግ ጥቃቅን የሆኑ ረቂቅ አካላትን ለማየት የሚያስችል በአይነቱ  የተለየ ማይክሮስኮፕ ለመፍጠር እንደሚሰሩ የጠቆመው መረጃው፤ ማይክሮስኮፑ ለቀጣይ ምርምሮች ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም አመልክቷል፡፡
የመጀመሪያና የሁለተኛ ዲግሪያቸውን በኬሚስትሪ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተቀበሉት እኒሁ ኢትዮጵያዊ ምሁር፣ የፒኤችዲ ትምህርታቸውን በዩኒቨርሲቲ ኦፍ አሪዞና ያጠናቀቁ ሲሆን በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ካሊፎርኒያ የፖስት ዶክቶራል ምርምራቸውን እንደሰሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡ እ.ኤ.አ ከ2012 አንስቶ በታዋቂው ኒው ሜክሲኮ ዩኒቨርሲቲ በማስተማር ላይ እንደሚገኙም ተጠቁሟል፡፡

Read 1707 times