Sunday, 05 February 2017 00:00

‘የግድ’ ወዲህ፣ ወዲያ

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(13 votes)

 እንዴት ሰነበታችሁሳ!
‘ሰውየው’ እኛንም ስጋት ውስጥ ከተቱንሳ! አሀ… ‘ሲቲዘን’ ያልሆኑ ወዳጆቻችን ብቅ ብለው ለመመለስ አስተማማኝ አይደለማ! የምር ግን እሳቸው ሰውዬ ‘ደረቁን’ ነው እንዴ በሌሊት ቀጭ፣ ቀጭ የሚያደርጉት! ቂ…ቂ..ቂ…
ስሙኝማ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…የሁሉም ነገር ጥግ የሆነችው አማሪካን እንኳን እንዲህ ትንጫጫለች ብሎ ያሰበ አለ! አሀ…የአማሪካን ጋዜጠኞች እንኳን ‘የአሜሪካ ፕሬስ አደጋ ላይ ወድቋል…’ ሲሉ… እውነትም ስምንተኛው ሺህ አያሰኝም፡፡ ሰሞኑን በአሜሪካ ሚዲያ ላይ የሚደረገው ጫና እንዲቆም እንጠይቃለን የሚል ‘ፔቲሽን’ እያዘጋጀ ያለ ሰው ሊኖር ይችላል፡፡  ምንስ ቢሆን የሙያ አጋሮቻችን አይደሉ! ቂ…ቂ…ቂ… “ሰው ከቆየ…” ይሏችኋል እንዲህ ነው፡፡
ምን ግርም ይልሀል አትሉኝም…አይደለም አማሪካኖቹ ራሳቸው፣ እኛ እንኳን ውሸት መሆኑን የምናውቀውን ነገር አዳዲሶቹ ቱባ ባለስልጣኖቻቸው ዓይናቸውን በጨው አጥበው ሲናገሩ እንዲችም ብለው አይሳቀቁም!
‘የሰውየው’ ነገር እኛንም አሳስቦናል፡፡ ልክ ነዋ… “አሜሪካ ለመቆየት የብቃት ማረጋገጫ ያስፈልጋል…” ምናምን የሚል ነገር ያመጡ እንደሁ፣ ምን ሊውጠን ነው! ልክ ነዋ…ዶላሩስ
እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… ይቺን ስሙኝማ…አንዱ ጓደኞቹን ሰብሰብ እንዳሉ፣ እየተፍለቀለቀ…
“የምስራች!” ይላቸዋል፡፡
እነሱም “ምስር ብላ፣” ምናምን እንደ ማለት (አይ የዘንድሮ ሰው!) “የምስራቹ ለምንድነው! በጠዋቱ አረቄ ገጭተህ ነው እንዴ የመጣኸው!”… ይሉታል፡፡ እሱም
“ከባለቤቴ ጋር ከተጋባን ዛሬ አሥራ አንደኛ ዓመታችን ነው…” ይላል፡፡
ይሄን ጊዜ ምን ቢሉት ጥሩ ነው…
“እኛ የተወለድንበትን ቀን ረስተናል፣ አንተ የጋብቻ ዓመትህን ትቆጥራለህ!”
ለምን አይቁጠር!…ልክ ነዋ…የሚቆጥረው ብር ሲያጣስ! የሚቆጥረው ዶላር የሚልክ ዳያስፖራ ሲያጣስ! ሰዉ የጋብቻ ዓመቱን ቢቆጥር ምን ክፋት አለው!
አንድ ሰሞን እንደውም “ተፋተን የተገባንበት ምናምነኛ ዓመት…” የሚሉት አይነት አከባበርም ነበር፡፡
እኔ የምለው…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…አንዳንዴ ነገሬ ብላችሁ በብዙ ቦታዎች ያሉ ነገሮችን ስታዩ… “ማነው የሚሠራው ሥራ ደስ ብሎት የሚሠራ!” ትላላችሁ፡፡ አንዳንድ ቢሮ ስትገቡ ግማሹ ሠራተኛ አኩርፎ፣ ግንባሩን ከስክሶ…በሽክና ሙሉ እንቆቆ የጠጣ ይመስል ሁሉ ነገሩ ተጨማዶ ታዩታላችሁ፡፡
እናላችሁ…ጉዳያችሁን ለማሳወቅ ጠጋ ስትሉ… አለ አይደል… መጀመሪያ ነገር ቀና ብሎ የሚያያችሁ አታገኙም፡፡
“ጉዳይ ነበረኝ…” ትላላችሁ፡፡
ባሏ ሌሊቱን ሙሉ እያሳደደ በመጥረጊያ ሲዠልጣት ያደረችና እልኋ ገና ያልለቀቃት የምትመስል...‘የምናምን የሥራ ሂደት’ አባል የሆንች ‘ሲቪል ሰርቨንት’ ቀና ትልና በዓይኗ እንትን ታያችኋለች፡፡ ገና ስለ ጉዳያችሁ በቅጡ መናገር ሳትጀምሩ አስተያየቷ… “ደግሞ ይሄንን  ከየት አመጡብን!…” የምትል ነው የሚመስለው።
እናላችሁ… ዘንድሮ ሰዉ ሁሉ ሥራውን ጠልቶ የግዱን ወዲህ ወዲያ የሚል ነው የሚመስለው፡፡
እናላችሁ…የምር ሥራውን የማይወድ ሰው አገልግሎት መስጫ ላይ ሲሆን አስቸጋሪ ነው። ብሶቱን ሁሉ እኛ ላይ ነዋ የሚወጣው! ታዲያላችሁ…ለምሳሌ አንዳንድ የአውቶብስና ‘የሀይገር’ ሾፌሮች በዚች መላ ቅጡ የጠፋት በምትመስል ከተማ ውስጥ እንዴት እንደሚያሽከረክሩ አይታችሁልኛል! ልክ እኮ መንገዱን በሊዝ ገዝተው ‘ካርታ የወሰዱበት’ መሬታቸው ላይ ያለ ያስመስሉታል፡፡
አንዳንዱ ሾፌር… “አውቶብስ ከመንዳት፣ ወይም ሰባት ዓመት ቂሊንጦ ከመውረድ!” የሚባል ምርጫ ስለተሰጠው ብቻ ሾፌር የሆነ ነው የሚመስለው፡፡
ወይም ደግሞ…አለ አይደል… “እናቴ ‘አውሮፕላን ነጂ ትሆናለህ፣ ህልም አይቻለሁ…’ ስትለኝ ኖራ የሀይገር ሾፌር ሆኜ ልቅር!” እያለ እየተብከነከነ ይሆናል፡፡ ታዲያ እኛ ምን እናድርግ!
እናማ ደስ ሳይለን ሥራችንን የምንሠራ ሰዎች ‘ጦሳችን’ ለሌላው ነው፡፡
እናላችሁ… ዘንድሮ ሰዉ ሁሉ ሥራውን ጠልቶ፣ የግዱን ወዲህ ወዲያ የሚል ነው የሚመስለው፡፡
ደግሞላችሁ… አንዳንድ የህክምና ተቋማት ውስጥ በሸተኞችን በስርአት ተቀብለው ማስተናገድ ያለባቸው ሰዎች የሚያሳዩት ባህሪይ የምር አስቸጋሪ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ሠራተኞች የህክምና መሀላ ፈጽመው የገበቡት ሙያ ሳይሆን… “ቁጭ ከምል መዋያ ይሆነኛል ብዬ የገባሁበት ነው…” የሚባል አይነት ሥራ ያስመስሉታል፡፡
ወይ ነርስዬዋ…አያቷ ትዝ ይሏታል፡፡ “የእኔ ቆንጆ ትልቅ ስትሆኚ እኔነ ነኝ ያለ ሀብታም አግብተሽ አየደለም ለዘመዶችሽ ሌላውም የምተርፊ ዲታ ትሆኛለሽ ያሏ ትዝ እያላት ሊሆን ይችላል፡፡ ሀብታም አግብታ ሌላ ትተርፋለች የተባለችው ሴት… የሆነ የእኔ ቢጤ የመሥሪያ ቤት፣ የቁጠባ ማህበር፣ የእድር ምናምን ዕዳ ሰብስቦ፣ ከአበዳሪ የሚሸሸው እሱ ብቻ ሳይሆን እሷም ሆናለች፡፡
እናላችሁ… ዘንድሮ ሰዉ ሁሉ ሥራውን ጠልቶ የግዱን ወዲህ ወዲያ የሚል ነው የሚመስለው፡፡
የሆነ ሆቴል በሉት፣ ሬስቱራንት በሉት፣ እንትና ሹሮ ቤት በሉት …ትገባላችሁ፡፡ መጀመሪያ ነገር አስተናጋጅ እስኪመጣ ድረስ አንድ አጭር ልብ ወለድ አንብባችሁ መጨረስ ትችላላችሁ፡፡ እናላችሁ…የሆነች ልጅ መጥታ ፊታችሁ ግትር ትላለች፡፡ የምር…  ልትታዘዛችሁ የቆመች ሳይሆን…አለ አይደል… ”በየት በኩል ታልፍ እንደሆነ ጉድህን አያለሁ!” ብላ መንገድ የዘጋች ነው የምትመስለው፡፡
እናማ… “ምን ላምጣልዎት?” አትል “ምን ልታዘዝ?”  አትል ቆማ ታፈጣለች፡፡
“ሜኑ ታመጪለኛለሽ?”
ፊቷ ቅጭም ይላል፡፡ በሆዷ… “ዝም ብሎ ወይ ሹሮ፣ ወይ ምንቸጽ አብሽ አምጪልኝ አይልም እንዴ! ድንቄም ሜኑ…” ሳትል አትቀርም፡፡ እናላችሁ…ሁለት ጠረጴዛ ዘሎ ያለውን ሜኑ ማምጣቱ ልክ “ከወንዝ ወርደሽ ውሀ ቅጂ…” የተባለች ታስመስለዋለች፡፡
እንደምንም ሜኑውን ታመጣለች፡፡ እናም… አታቀብላችሁም፡፡ ይልቁንም ጠረጴዛው ላይ ታፈርጠዋለች! እኛ ደግሞ ይሄኔ በሆዳችን… “እኛስ ግፋ ቢል ቀማመስን እንወጣለን፣ ይብላኝ ለወደደሽ!” እንላለን፡፡
የመውደድ ነገር ካነሳን አይቀር…አንዱ አለ የተባለውን ስሙኝማ… “ሴቶች በሚሰሙት ንግግር በፍቅር ይወድቃሉ፣ ወንዶች በሚያዩት ነገር በፍቅር ይወድቃሉ፡፡ ሴቶች ብዙ መዋቢያዎች የሚቀባቡትና አብዛኞቹ ወንዶች የሚዋሹትም ለዚህ ነው፡፡” (እኛ መናገር የማንችለው… ‘ኳስ አቀባይ’ ሆነን የቀረንበት ምስጢር ይኸው ተደረሰበት!)
እናላችሁ… ዘንድሮ ሰዉ ሁሉ ሥራውን ጠልቶ የግዱን ወዲህ ወዲያ የሚል ነው የሚመስለው፡፡
አንዳንዴ ስታስቡት ‘ዓለም ጠቅላላ አእምሮውን መጠቀም አቅቶቷል እንዴ!’ ትላላችሁ፡፡ አንዱ የቸገረው ሰው ምን ቢል ጥሩ ነው… “ለሰዎች አእምሮ የሞባይል አፕሊኬሽን ነው ብለን ብንነግራቸው ምናልባትም ይጠቀሙበት ይሆናል፣” ብሏል፡፡ አሪፍ አይደል!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 4624 times