Monday, 06 February 2017 08:02

ለፖለቲካዊ ችግሮች ፖለቲካዊ ውይይት!!

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 ከውይይቱ ምን ይጠበቃል?

               በሀገሪቱ የተፈጠሩ ተቃውሞና ግጭቶችን ተከትሎ አንጋፋዎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከገዥው ፓርቲ ጋር የድርድርና ውይይት መድረክ እንዲዘጋጅላቸው በተደጋጋሚ መወትወታቸው አይዘነጋም፡፡
የመጀመሪያው የድርድርና የውይይት መድረክም ባለፈው ሳምንት በፓርላማ ተካሂዷል። አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ውይይቶቹና ድርድሮቹ ለመገናኛ ብዙኃን ፍጆታ የሚውሉና የይስሙላ እንዳይሆኑ
ስጋት ቢኖራቸውም አብዛኞቹ በመድረኩ መዘጋጀት ደስተኞች ናቸው። ውይይቱ በታቀደው መሰረት በተከታታይ የሚቀጥል ከሆነ፣ እያንዳንዱ ፓርቲ የውይይት አጀንዳዎቹን ማቅረብ ይጠበቅበታል፡፡
ለመሆኑ ተቃዋሚዎች ከኢህአዴግ/መንግስት ጋር መወያየት ያለባቸው በምን ጉዳዮች ላይ ነው? ሂደቱስ? ከውይይቱ ምን ይጠበቃል? ከተወያዮቹስ?
የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣ በዚህ ዙሪያ የጦማሪያንን ሃሳብና አስተያየት እንደሚከተለው አጠናቅሯል፡፡

             
                  “የተቃዋሚዎችን የመደራደር አቅም እጠራጠራለሁ”
                      አጥናፈ ብርሃኔ (ጦማሪ)

       የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋትና ትንሽ መላወሻ ቦታ የሚያመጣ ከሆነ፣ ድርድሩን እንደ መልካም ውጤት አድርጌ ነው የምወስደው፡፡ አሁን የሚደራደሩት ፓርቲዎች ይሄን ለማድረግ ከቻሉ ትልቅ ነገር ነው፡፡
ኢህአዴግስ እውነት የሚያምንበትን ነው እያደረገ ያለው? በሚለው ላይ ጥርጣሬ አለኝ፡፡ ከዚህ ቀደም የተደረጉ ድርድሮች አሉ፡፡ የምርጫ ስነ ምግባርን በተመለከተ ድርድር ተደርጓል፡፡ ግን ምን ውጤት አመጣ? ያ ድርድር ለማን ነው የጠቀመው? ከዚያ ድርድር በኋላ በምርጫ ምን ውጤት መጣ? ይሄ መመርመር አለበት፡፡ ይህ የምርጫ ስነ ምግባር ድርድር ላልተደራደሩ ፓርቲዎች ማነቆ ሆኖ ነበር። ብዙ ተጎድተውበታል። ችግሮችን ሲፈጥርባቸው ነበር፡፡ አሁን ላይም ተቃዋሚዎቹ የመደራደር አቅማቸውን እጠራጠራለሁ፡፡ ከዚያ ውጪ ገዥው ፓርቲ እስካሁን ምንም አይነት መለሳለስ እያሳየ አለመሆኑ ሌላው ተግዳሮት ነው።
የአድርባይነት ስሜት የህዝብን አመኔታ የሸረሸረ በመሆኑ የገዥው ፓርቲ መጠቀሚያ እንዳይሆኑ ነው የምሰጋው፡፡ አቅም ኖሯቸው መደራደር ቢችሉ እንዲደራደሩባቸው ከሚያስፈልጉ ጉዳዮች ዋናው፡- ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ ጉዳይ፣ የፖለቲካ መጫወቻ ሜዳው መጥበብ፣ የፖለቲካ እስረኞች ጉዳይ ዋናዎቹ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ዶ/ር መረራን ጨምሮ በእስር ላይ የሚገኙ የመድረክ አመራሮች ካሉ፣ እነሱ መፈታት በሚችሉበት ጉዳይ ላይ መደራደር አለባቸው፡፡ በግሌ ውጤት ያመጣል ብዬ ባልጠብቅም ውጤቱን ከሂደቱ መጠበቅ አለብን፡፡

----------------------------------------

                     “ሀገር በድርድር ነው የሚገነባው”
                      አቤል ዋበላ (ጦማሪ)

      እንደ ሀገር ባለፉት ሁለት ስርአቶች የተፈፀሙ ስር ነቀል ለውጦች ብዙ ዋጋ አስከፍለውናል፡፡ ስር ነቀል ሲሆን ብዙ ነገር ወደ ኋላ ይመለሳል፡፡ አሁንም ቢሆን ስር ነቀል ለውጥ የሚታለም ከሆነ፣ለህዝቡ የተሻለ ለውጥ ያመጣል ብዬ አላስብም፡፡ ያለውን ስርአት ለማስተካከል ንግግሩ መጀመሩ በራሱ ጥሩ ነው ብዬ ነው የማስበው፡፡
ድርድር ሲባል የሚታወቀው በተመጣጣኝ ኃይሎች መካከል የሚደረግ ነገር ነው፡፡ አሁን ባለው ተጨባጭ እውነታ፣ተቃዋሚው በመንግስት በደረሰበት ተደጋጋሚ ጫና በጣም ተዳክሞ ነው የሚገኘው፡፡ ድርድሩ የምር ችግር ፈቺ እንዲሆን ከተፈለገ፣ በተቃዋሚው ወገን ያለውን የኃይል መሳሳት የሚቀንስ መሆን አለበት፡፡ ተቃዋሚው እንደፈለገ ህዝቡን በዙሪያው እንዲያሰባስብ ክፍት መሆን አለበት፡፡ መሪዎቻቸው የታሰሩባቸው ፓርቲዎች አሉ፡፡ እነዚህ መሪዎቻቸው እንዲለቀቁላቸው ያስፈልጋል፡፡ ይህ ከሆነ ተቃዋሚዎችም በህዝብ ዘንድ ያላቸው አመኔታ ስለሚጨምር ድርድሩ አቅምና ውጤት እንዲሁም ተአማኒነት ይኖረዋል፡፡ ድርድራቸውን በሚዲያዎች አጠቃቀም፣በፍትህና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ላይ ቢያደርጉ የበለጠ ውጤት ማምጣት ይቻላል፡፡
ኢህአዴግ ለፖለቲካ ትርፍ ሲል ብዙ ጥፋቶች ሰርቷል፡፡ አሁን ግን ስልጣንን የማዳን ሳይሆን ሀገርን የማዳን ስራ ነው መስራት ያለበት፡፡ ይህ ድርድር የዚህ አይነት ውጤት ይዞ መምጣት አለበት፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም እንደ ፊጋ በሬ ኢህአዴግን ሳያስደነግጡት፣ በአግባቡ በኃላፊነት ስሜት ሊደራደሩ ይገባል ብዬ አምናለሁ፡፡ ኢህአዴግም ይሄን እድል ማባከን የለበትም፡፡ ሀገር በድርድር ነው የሚገነባው፡፡

------------------------------------

                          ‹‹ድርድሩ በቅንነትና በቁርጠኝነት መካሄድ አለበት››
                            በላይ ማናዬ (ጦማሪና ጋዜጠኛ)

       ድርድሩ ከልብ የሚካሄድ ከሆነ መልካም ነው። በተለያየ አጋጣሚ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችም ሆኑ ሌሎች በሃገራቸው ጉዳይ ይመለከተናል የሚሉ ሰዎች ሲጠይቁት የነበረው የነበረው ይሄንኑ የድርድና የውይይት መንገድ ነው፡፡ የጋራ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ከልብ መነጋገር፣ መደራደር በየትኛውም ሁኔታ የሚደገፍ ነው፡፡ እኔ በግልም በተደጋጋሚ በፅሁፎቼ ስጠይቅ የነበረው መነጋገር ወሳኝ እንደሆነ ነበር። ይሄ ድርድርና ውይይት ግን ቅንነት በተሞላበት መንገድ፣ በደንብ ችግሮችን እያነሱ በጥንቃቄ መካሄድ አለበት። እንዲሁ ለይስሙላ የአንድ ሰሞን ጫጫታ ብቻ ሆኖ እንዳያልፍ በአንክሮ መከታተል ያስፈልጋል፡፡
በዚህ ድርድር ላይ በተቃዋሚዎች ቢነሳ ብዬ የማስበው፣ በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት ለእስር ተዳርገውብናል ያሏቸው ሰዎች እንዲለቀቁ፣ የፓርቲ አመራሮች፣ ጋዜጠኞች፣ ብሎገሮች ታስረዋል፤ እነዚህ ተፈተው የድርድሩ አካል መሆን አለባቸው። በትክክል የድርድሩ አካል መሆን ያለባቸው የታሠሩ የፖለቲካ አመራሮች አሉ፤ እነሱ እንዲሳተፉ መጠየቅ አለባቸው፡፡ ሌላው ከህገ መንግስቱ ተፃራሪ ናቸው እየተባሉ በህግ ባለሙያዎች አስተያየት ይሰጥባቸው የነበሩ ህጎች ላይ ጠለቅ ያለ ድርድር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ አንዳንዶቹ በህግ ባለሙያዎች ተጠንተው ቢሰረዙ ምኞቴ ነው፡፡ ከኢህአዴግ ጋር በሚደረገው ድርድር ተቃዋሚዎች የህዝቡን ሃሳብና ስሜት በማንፀባረቅ ከልባቸው ሊሰሩ ይገባል ብዬ አምናለሁ፡፡ መንግስት ቁርጠኝነቱን እስከ መጨረሻው የሚቀጥል ከሆነ ጥሩ ነው፡፡ ግን በተደጋጋሚ ካየነው ልምድ ስንነሳ፣ ቁርጠኝነቱ እስከ ምን ድረስ ነው በሚለው ላይ ጥርጣሬ ያድርብኛል። ግን ካለመነጋገር መነጋገሩ የተሻለ በመሆኑ ጠንክሮ መደራደሩ የተቃዋሚዎች ሚና ነው ብዬ አምናለሁ። በሌላ በኩል በድርድሩ የተገለሉ የፖለቲካ ሃይሎች እንዳይኖሩ ቢደረግና ሁሉንም አካታች ቢሆን መልካም ውጤት ያመጣል፡፡
የህዝቡ ድምፅ በሙሉ እንዲሠማ ከተፈለገ፣ አሁን ካሉት ፓርቲዎች በተጨማሪ ሌሎች ያገባናል የሚሉም መካተት አለባቸው፡፡ በዚህ መንገድ የሚካሄድ ከሆነ፣ ድርድሩና ውይይቱ ውጤት ሊያመጣ ይችላል የሚል ተስፋ አለኝ፡፡

------------------------------

                              ‹‹በድርድሩ ሁሉም እኩል መሆን አለባቸው››
                                ናትናኤል ፈለቀ (ጦማሪ)

      በአንድ አካል መልካም ፍቃደኝነት ላይ የተመሰረተ፣ ሌሎች ደግሞ ተለማማጭ ሆነው የሚካሄድ ድርድር ትክክለኛ ውጤት አያስገኝም። ድርድር ከተባለ ሁሉም በእኩልነት መጥተው፣ ለሁሉም ምቹ የሆነ ውጤት እንዲኖረው ነው የሚፈለገው፡፡ ነገር ግን አንዱ የፈለገውን ማድረግ የሚችል፤ ሌሎቹ ደግሞ አሉ ለመባል ያህል የሚገቡበት ድርድር የአንደኛውን ወገን ብቻ ፍላጎት ይዞ እንደሚጠናቀቅ መተንበይ ቀላል ነው። እኔ ለምሳሌ “ከዚህ ድርድር መልካም ውጤት ትጠብቃለህ ወይ?” ብባል፣እንድጠብቅ የሚያደርገኝ ነገር ስላላየሁ አልጠብቅም፡፡ ከዚህ በፊትም እንዲህ ያለው ነገር በተለያዩ ስሞችና ቅርፆች ተሞክሯል፤ ግን ምንም የተለየ ነገር አላመጣም፡፡ ይሄም ያመጣል ብዬ አልጠብቅም፡፡
በድርድሩ ለምሳሌ “ህገ መንግስቱ ይከበር” የሚባል ከሆነ ምንም አዲስ ነገር የለውም፡፡ ዋናው ተግባር ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ተደራድረው ቢለያዩ፣ አንደኛው ወገን ስልጣን ሁሉ በእጁ ያለ በመሆኑ ስምምነቱን እንደፈለገ ሊጠቀምበት ይችላል፡፡ ግን ድርድሩ የታሠሩ ፖለቲከኞች ይፈቱ፣ ሚዲያው ነፃ ይሁን፣ የፖለቲካ ስልጣን እንጋራ ----- ከሆነ ጥሩ ሊሆን ይችላል፡፡ ፓርቲዎቹ የምርጫ ስርአቱ ላይ ብቻ ተደራድረው ሊወጡም ይችላሉ፡፡ ይሄ ደግሞ ያን ያህል ውጤት የለውም፡፡ በየትኛውም ሥርዓት ውስጥ በሃቀኝነትና በቁርጠኝነት ከተሰራ ለውጥ ይመጣል፡፡ ስለዚህ መንግስት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ሊያደርግባቸው በሚገቡ ጉዳዮች ላይ አጠንክረው ቢደራደሩ ነው መልካም የሚሆነው፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ በፖለቲካ መሳተፍ አስፈሪ በሆነበት ሰዓት የተፈጠሩ ፓርቲዎች በመሆናቸው፣ይብዛም ይነስም በዚህ ድፍረት ውስጥ ያሉ ፓርቲዎችን ልናበረታታ ይገባል፡፡ ሌላ ወካይ እስከሌለ ድረስ ህዝቡን ወክለው መደራደር ይችላሉ የሚል እምነትም አለኝ፡፡

Read 4543 times