Monday, 30 January 2017 00:00

የፊደላት ዓለም

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(8 votes)

 እንደ ዲሞክራተስ አተም … የማይቆረጥ የማይፈለጥ ማንነት ከፈለግንለት ሰውም በመጀመሪያ እንደ ፊደል ነው፡፡ ሰውም ሲወለድ እንደ “ሀይድሮጅን” ባለ አንድ ነፍስ ነው፡፡
“ተ” የምትባለዋ ፊደል እንደ አንድ አተም ናት። በመስቀለኛ መንገድ በየትኛውም አቅጣጫ ለመጓዝ እጣ ፈንታ ይዛ የምትወለድ ፊደል። “ቶ” ሆና ጭንቅላትም ሆነ ማዕረግ ያላካበተች ፊደል። እና እንደማንኛውም ሰው አንዱ “ተ” ሆኖ ተወለደ፡፡ “ተማር” ሲባል ተማረ፡፡ በተማረው ልክ ተመራመረ። እድሜው ለሀላፊነት ሲደርስ ስራ ተቀጠረ፤ ተራ ሰውነቱ እንደማንኛውም ተራ ፊደል ቅጣዮች ማብቀል የእድገት ሂደቱ ነበር፡፡
መስሪያ ቤቱ ውስጥ ከአለቃው ፀሐፊ ጋር የሚስጢር ግንኙነት ከመጀመሩ በፊት “ተመስገን” እያለ ከመኖር ውጭ ከወገብ በታች ቅጥያ እንዳለው አያውቅም ነበር፡፡ ‹‹ቱ!›› የተባለለት አለሌ መሆንም የሂደ ‹‹ቱ›› አካል እንጂ መደምደሚያ አይደለም፡፡
የአለቃው ፀሐፊ በሁለመናዋ “ወ”ን የመሰለች ናት፡፡ ወፍራም ናት፡፡ ልክ እንደ ዳቦ፡፡ ወንድ ትወዳለች እየተባለ ይወራባታል፡፡ በእርግጥ ፀሐፊዋ ብቻ ሳትሆን የተመስገን አለቃም ሴት ናት፡፡ ግን ከእሱ ጋር አልተግባቡም፡፡ እጇን በወገቧ ዙሪያ አድርጋ ማዘዝ የምትወድ፣ ‹‹አለቅነቴ ይታወቅልኝ›› የማለት አባዜ የተጠናወታት ሴት ናት፡፡ “ተ” (ተመስገን) አለቃውን አይወዳትም፡፡ አለቅየዋ ወገቧ ላይ እጇን አሳርፋ ስታዝ ላያት፣ ለፊደል ተርታ “ቀ” መሆኗን መገመት ይችላል፡፡ “ቀ” ነቷ ይጎላል፡፡ ከ“ቀ” ነቷ ባሻገር ሌላ ፊደል ማንነቷን የማሳደግ፣ የመለወጥ አዝማሚያ ተዳብሏት አያውቅም፡፡ ስነ ልቦናዋም ሆነ ቅርጿ በአንድ ፊደል ተወስኖ ቀርቷል፡፡
“ና!” ብላ እሱንም ሆነ ከበታቿ ያሉትን ሁሉንም ማሯሯጥ ብትወድም … የምታዘወትረውን የትዕዛዝ ጥሪ ከማንነቷ ቅርፅ (ቀ) ጋር አዳብሎ አንድም ሰው “ቀና” ብሎ ገልፆት አያውቅም፡፡ ቀና አይደለችም። ደግሞም ማንም ቀና ብሎ አያያትም፡፡ የማንነቷ ቅርጽ “ቀ” የተባለችውን ፊደል ሆኖ ቀርቷል፡፡ በአካል ከታየች በጣም ቀጭን የምትባል ነች፡፡ ግን “ቀጭን” እንድትባል ትንሽ “ጭን” ቢኖራት ይረዳ ነበር፡፡
ፀሐፊዋ ግን “ወ” ናት፡፡ ወይን እሸት፡፡ ሁል ጊዜ ወከክ ብላ የመጣን የምትቀበል… የዋህ ነች። ፀሐፊዋ (ወይንሸት) እና እሱ (ተመስገን) … ተዋደዱ። ፍቅርን በስራም አለም ሆነ በአልጋ ጨዋታ አብረው ተቋደሱ። እስኪሰለቻቹ ድረስ።
ተመስገን ከጠባብ የአንድ መስሪያ ቤት ተሞክሮ ወጥቶ በሌላ አማራጭ የማደግ ፍላጎት ስለነበረው ከወገቡ በታች ከብልት የስነ ልቦና ተሞክሮ የበለጠ የሚያስጉዝ እግር ማቀበል ነበረበት፡፡ አቅጣጫ ለመቀየር እንዲረዳው የድሮ አለባበሱንና የድሮ ጫማውን ቀየረ፡፡ “ተ” የነበረው የዋህ ማንነቱ፣ በ“ቱ” ወሲብ ትኩስ ተሞክሮ ወደ “ቲ” አደገ፡፡
በ“ወ” ውስጥ ወይንም ከወይኗ ጋር ያሳለፈውን የተመሰገነ ቆይታ ሊቆርጥ እንደሆነ ስታውቅ ወይንሸት ውስጧ ተቀየመ፡፡ ንፁህ “ወ”ነቷ … “ዋ!” እያለ ማስጠንቀቅ ወደሚያበዛ ቅርፅ እየተለወጠ መነፋረቅ አበዛ፡፡ ዳቦ ከሚመስል ውፍረቷ፣ ክብ ከነበረው ፀሐይ ፊቷ ውስጥ ቀስ እያለ ቀጭን ጭንቅላትና የከሳ እግር በቀሉ፡፡ ለካ  “ቀ” የመሰለችዋ፣ እጅ ወገብ ላይ አድርጋ ሰው ማዘዝ የሚቀናት፣ የኮመጠጠ ባህርይ ያላት አለቃም፣ እንደዚህ ነበር ቀስ በቀስ በስነ ልቦና ስብራት ሂደት የተፈጠረችው፡፡
“ዋ!” ብላ በማስጠንቀቅ ባለችበት ቢሮ ተቀምጣ፣ ከሚመጣና ከሚሄድ ጋር በመለካከፍ ልትቀጥል አልቻለችም፡፡ ወይንሸት እግር አብቅላ ሁነኛ ባል መፈለግ ጀመረች፡፡ በእግር የፈለገችው በመኪና መጣ፡፡ “ጨ” የመሰለ የግሉን ተሳቢ መኪና እየሾፈረ የሚኖር ሰው ላይ ወደቀች። ወይንሸትን የጠበሳት ይሄ ባለ ተሳቢ፣ “ጨ” የሚባለውን ፊደል የተመሰለበት ምክኒያት፣ በተሳቢው መኪና ላይ ብዙ ባለቀለበት ጎማዎች ስለሚያሽከረክር ከመሰለን ተሳስተናል። “ጨ” የሚለውን ፊደል ለመስራት በ“ጠ” ፊደል ላይ የገቡት ሶስት ቀለበቶች፣ ሰውየው ሶስት ሚስት አግብቶ የፈታ መሆኑን የሚገልፁ መሆናቸውን ማንም አያውቅም፡፡ እንጂማ በመሰረቱ ሰውየው የ “ጠ” ፊደል ባህርይ ያለው ነው፡፡ በሶስት እግሮቹ መሬትን ቆንጥጦ አስተማማኝ ህይወት ለመምራት የመሞከር አዝማሚያና ስነ ልቦና ያለው ነው፡፡ ጠንካራ አቋም ያለው ሰው ነው። ስም ካስፈለገው “ጠንክር” ብለን መሰየም እንችላለን፡፡ ግን ምን ያደርጋል… የትዳር ህይወቱ ግን እንደ ጎማ እያንሸራተተ፣ ከአንድ የሰርግ ቀለበት ወደ ሌላ ይነዳዋል፡፡ አዙሪት ወደ “ጨ” እንደለወጠው፣ ወይንሸትን ሲያገባ በአራተኛ ቀለበት “ጬ” ሆነ፡፡ ከዚህ ላይ ቀለበት መጨመር የፊደል ህጉም አይፈቅድለትም፡፡ ደግነቱ የፊደል ህጉን ያገናዘበ ይመስል የሁለቱ ትዳርም የተረጋጋና ዘላቂ ሆነላቸው፡፡
*       *      *
ተመስገንም እድገቱ ቀጠለ፡፡ “ቱ!” የተባለለት ከይሲ ሴት አውል ሆኖ አልቀረም፡፡ ወደ “ቲቺንግ” ሞያ ገብቶ ጥቂት አመት ሰራ፡፡ በመሀል ላይ በጠና “ታ”መመ… ወደፊት ለማደግ ሲል ያበቀለው እግሩ፣ ወደ ኋላ የተሰበረ ያህል ብዙ ወራት ከስራ ተስተጓጉሎ በአልጋ አቆየው። ከህመሙ ሲያገግም ተመልሶ … ተ - ቱ - ቲ… እያለ ወደ ቀድሞው ጤንነቱ ተመለሰ፡፡ በ ሂደት መልሶ ጤናማ ሲሆን እንደሱ መምህርት የሆነች ፀጥተኛ - ፀይም - ፀሐይ የመሰለች ልጅ ለማግባት አጨ፡፡ በዛው ሰሞን በጋዜጣ አሳውጆ የቀድሞው (ተመስገን) የሚል ስሙን ቀየረ። ጊዜውንና የእድገት እርከኑን የሚመስል ስም። “ቴ” ዎድሮስ ብሎ ራሱን ጠራ። በ “ተ” ነቱ ላይ የምትስማማ፣ “ፀ” የመሰለች ልጅ አግብቶ “ቴዲ” ሆነ፡፡ “ተ” ፀሐይን እግሩ ላይ በቀለበት አስሮ ወደ ትዳር ገባ፡፡
እንዲህ እንዲህ እያሉ የፊደል አቶሞቹ እየተቀጣጠሉ … እየተስማሙ ወይንም እየተፋረሱ መፃፍ ቀጠሉ፡፡ በእያንዳንዱ ፊደል ውስጥ ግን የየራሱ የስነ ልቦና እድገት በተሞክሮው ልክ እስከ መጨረሻው ይቀጥላል። ጋብቻው ከማህበረሰብ ጋር ወይንም ከፆታ ተቃራኒ ጋር ብቻ ሳይሆን ከራሱም የለውጥ ሂደት ጋር ነው፡፡ በስተመጨረሻ ግን የዚህ ሁሉ ፊደል ስብጥር የሚፈጥረው ንባብ፣ ታሪክ መስሎ መነበቡ አይቀሬ ነው፡፡
ተመስገን ቴዲ ከሆነ በኋላ ሰለሞን እና ያየህይራድ የተባሉ ልጆች አፈራ፡፡ ወይንሸትም ሁለት ሴት ወልዳ አንድ ወንድ ለመጨመር መሀል መንገድ ላይ ሳለች፣ ከቀድሞ ወዳጇ ጋር በድንገት ተገናኙ፡፡ ተገናኝተው ብዙ አወሩ። ህይወት ይቀጥላል፡፡ ተመስገን፣ ቴዎድሮስ የሚለውን ስም መቀየሩንና ወደ ካናዳ ለ “ት”ምህርት እስኮላርሺፕ አግኝቶ ሊሄድ መሆኑን ለወይንሸት በነገራት ጊዜ “ተመስገን” ብላ መረቀችው፡፡ የልጆቻቸውን ፎቶ ከሞባይላቸው አውጥተው ተያዩ …፡፡
የቴዲ ሁለተኛው ልጅ ከፊደሎች መሀል “የ”ን እንደሚመስል አባትየው የደረሰበት አይመስልም። “የ” በቅርፅ ከሌላው ነገሩ ጭንቅላቱ የመግዘፍ አዝማሚያ ያለው ነው። “በጣም የማወቅ ፍላጎት ያለው ነው›› ብሎ ስለ ልጁ ዝንባሌ ሲገልፅ፣ ከፊደል አተሞች የትኛውን በቅርፅ እንደሚመስል ለመገመት ፈልጎ አልነበረም፡፡ የወይንሸት ልጆች ሴቶቹ በአብዛኛው እናታቸውን ነው የሚመስሉት። ወፍራም ናቸው፡፡ ወደ “ወ” ከሚያደሉት ግን ወደ “መ” የማድላት አዝማሚያቸው በፊደል ቅርፅ ተርጉሞ ላያቸው የበለጠ ይመስላሉ። ምናልባት “መ” ሁለት ቀለበቶች በአንድ ሰረዝ ሲያያዙ የሚፈጠር ቅርፅ መሆኑ ለገባው … ከእናታቸው ወይንሸት ከወረሱት ይልቅ ከአባታቸው የወረሱት የበለጠ መሆኑ ሊታየው ይችላል፡፡ ግን እንዲያ ለመምሰል የፊደልን አተም ከአፃፃፍ ቅርፁና  ከሚመስለው ሰው የባህርይ አዝማሚያ ጋር አጣምሮ የመመልከት መነፅር ያስፈልጋል፡፡ “መ” ሁለት ቀለበቶችን የሚያገናኝ ሰረዝ ሳይሆን “መነፅር” ሊሆንም ይችላል፡፡
ቴዲ (ተመስገን) ከካናዳ “ት”ምህርቱን ጨርሶ ሲመጣ የላቀ እድገት በራሱ ማንነት ላይ እንደሚጨምር ያምናል፡፡ ሙሉ ሰብዕና እና ሙሉ አቅሜ ላይ የምገኘው ያኔ ነው ብሎ ተስፋ አድርጓል። “ተ” … የመጨረሻ እድገቱ ላይ ሲደርስ “ቶ” ይሆናል ማለቱ ነው፡፡ ከተወለደበት ጊዜ አንስቶ… ከ “ተ” ጀምሮ “ቶ” ላይ ከደረሰ ከምስጋና በቀር የሚለው የለም፡፡ ከዚያ በኋላ ሞ“ቶ” ከመቀበር በስተቀር የሚጠብቀው አይኖርም፡፡
ወይንሸት እና “ተ” ብዙ አውግተው ተለያዩ። ግን ከመለያየታቸው በፊት ድሮው መስሪያ ቤት አለቃቸው የነበረችው “ቀ”፣ የነርቭ እክል ገጥሟት፣ በዊልቸር ስራ ፈትታ መቀመጧን ወይንሸት አስተዛዝና ነገረችው፡፡ ወገቧን ይዛ ከማዘዝ ወደ አካለ ስንኩል መንፏቀቂያ ወንበር  ያቆራኛት አጋጣሚ ምን እንደሆነ እንደማታውቅ ጨምራ ነገረችው፡፡
በፊደል አለም ሁሉም ነገር ይቻላል፡፡ አለቅየዋም በ “ቀ” ቅርፅ … ወገቧን ይዛ ወደ ታች ከምታዝበት… ምንም በቅርፅም ይሁን በባህርይ ወደማይዛመድ የ “ፈ” ፊደል የሚቀይር ምትሀት ሊከሰት ይችላል፡፡
ትንሽ የፊደል አለም ከዲሞክራተስ የአተም ዓለም የሚለየው፣ ፊደል እንደ አስማት መነሻና መድረሻውን መተንበይ አለመቻሉ ነው፡፡ “ቀ” ወገቡ ላይ የያዘው ኩራት ሲተወው እጆቹን መስቀለኛ ዘርግቶ “ተ” ይሆናል ብሎ መተንበይ አይቻልም፡፡ በእጆቹ ፈንታ ወገቡ የተሰበረ፣ ብሽሽቱ ያበጠ የ “ፈ” ፊደልን  ቅርፅ ይዞ ሊገኝ ይችላልና፡፡ 

Read 4072 times