Monday, 30 January 2017 00:00

በጅግጅጋ የቁም እንስሳት ማቆያ ማዕከልና የስጋ ፋብሪካ ተገንብቷል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

   ትኩስ የስጋ ምርት ለተባበሩት አ ረብ ኢምሬት ያቀርባል
                                    
     ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የቁም እንስሳት መንከባከቢያና የመጀመሪያው ማቆያ በጅግጅጋ ከተማ አቅራቢያ ተገንብቷል፡፡ ሰሞኑን በጅግጅጋ ከተማ የተከበረውን 16ኛውን የአርብቶ አደሮች በአል ምክንያት በማድረግ የእንስሳት ጊዜያዊ ማቆያ ማዕከሉን ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትና ጋዜጠኞች ጎብኝተውታል፡፡
ከ80 ሚ. ብር በላይ እንደፈጀ የተነገረለት የጅግጅጋ የቁም እንስሳት የውጭ ግብይት ማቆያ ማዕከል፤ ከከተማዋ 20 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን በ54.6 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ግንባታው 5 ዓመታት መውሰዱ የተገለፀ ሲሆን ቀድሞ ከተያዘለት ጊዜም መዘግየቱ ተነግሯል። ማዕከሉ በአሁኑ ወቅት እየተጠናቀቀ መሆኑን የጠቆመው የክልሉ መንግስት፤ የግንባታውን ኮንትራት የያዘው “የሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ ኢንተርፕራይዝ” እንደሆነም ጠቅሷል፡፡  
ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የቁም እንስሳት ማቆያ ማዕከሉ በዋናነት ከአርብቶ አደሮች በግዢ የሚሰበሰቡ እንስሳት ቢያንስ ለ3 ወራት የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው የሚቆዩበት ሲሆን ይህም በሽያጭ ወቅት ዋጋቸውን ከፍ እንዲል በማድረግ ከፍተኛ ገቢ ያስገኛል ተብሏል፡፡ ኢትዮጵያ በቁም ከብት ከአፍሪካ በ1ኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ብትሆንም ቀደም ብላ እንዲህ ዓይነት ማዕከል ሳትገነባ መቆየቷ ብዙ ገቢ አሳጥቷል ተብሏል፡፡
ማዕከሉ በአሁን ወቅት የከብት በረትና የተለያዩ የቢሮ አገልግሎት የሚሰጡ ህንፃዎች የተገነቡለት ቢሆንም የውሃ አቅርቦትና የፍሳሽ ማስወገጃ እንዲሁም የላብራቶሪ አገልግሎት እንደሚቀሩት ተነግሯል፡፡ እንዲያም ሆኖ በጥቂት ወራት ውስጥ የጎደለው ተሟልቶ አገልግሎት እንደሚጀምር የተገለጸ ሲሆን ማዕከሉ በአጠቃላይ 21 ሺ 315 የቀንድ ከብቶችን፣ 2184 ግመሎችንና 10 ሺ 528 ፍየሎችን በአንድ ጊዜ ተቀብሎ ማስተናገድ ይችላል ተብሏል፡፡
የማዕከሉ መገንባት ህገ ወጥ የቁም ከብቶች ሽያጭን ከማስቀረቱ በተጨማሪ ጤንነታቸው የተጠበቀ እንስሳትን ለውጭ ሀገር ደንበኞች በማቅረብ ከዚህ ቀደም ከነበረው የበለጠ ገቢም ያስገኛል ተብሏል፡፡ የኢትዮጵያን የቁም ከብት ከሚሸምቱ አገራት አንዷ ሳኡዲ አረቢያ ስትሆን የአገሪቱ የእርሻ ሚኒስትር በቅርቡ ማዕከሉን ጎብኝተው መደሰታቸውም ተገልጿል፡፡
በሌላ በኩል በዚያው በጅግጅጋ ከተማ አቅራቢያ 35 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በ200 ሚ. ብር ተገንብቶ ስራ የጀመረው የስጋ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ፤ትኩስ የስጋ ምርቱን ለተባበሩት አረብ ኢምሬት ደንበኞች በማቅረብ ለሀገሪቱ ተጨማሪ ገቢ እያስገኘ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ 3 ዘመናዊ ግዙፍ ማቀዝቀዣዎች የተገጠሙለት ፋብሪካው፤ በቀን የ3 ሺህ ፍየሎችን፣ የ100 ግመሎችንና የ300 የቀንድ ከብቶችን ስጋ አቀናብሮ፣ ለውጭ ገበያ እያቀረበ እንደሆነ የሥራ ኃላፊዎቹ ገልጸዋል፡፡

Read 1750 times