Monday, 30 January 2017 00:00

“አግሮፉድ ፕላስትፓክ” የንግድ ትርኢት አርብ ይከፈታል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

 ከ10 በላይ አገራት የመጡ ነጋዴዎች ይሳተፉበታል
               የጀርመኑ የንግድ ትርኢት አዘጋጅ ፌርትሬድና ኢትዮጵያዊው ፕራና ፕሮሞሽን በመተባበር ያዘጋጁት “አግሮፉድ ፕላስትፓክ” ዓለም አቀፍ የንግድ ትርኢት የፊታችን አርብ በሚሊኒየም አዳራሽ ይከፈታል፡፡
ለሶስት ቀናት በሚቆየው በዚህ የንግድ ትርኢት ላይ በግብርና፣ በምግብና መጠጥ፣ በፕላስቲክ፣ በማሸጊያ ቴክኖሎጂና በጥሬ ዕቃ ምርት አቅርቦት ላይ የተሰማሩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሚሳተፉ ሲሆን ከኦስትሪያ፣ ፈረንሳይ፣ ኢትዮጵያ፣ ኔዘርላንድስ፣ ታይዋን፣ ታይላንድ፣ ቶጎ፣ ዩክሬይን፣ እንግሊዝ፣ አሜሪካና ከተባበሩት አረብ ኢምሬትስ የሚመጡ የዘርፉ ነጋዴዎች በንግድ ትርኢቱ ላይ እንደሚካፈሉ ባለፈው ረቡዕ አዘጋጆቹ በራማዳ ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አስታውቀዋል፡፡
የንግድ ትርኢቱ ምርትና አገልግሎትን ከመሸጥና ከማስተዋወቅ ባለፈ ለቴክኖሎጂ ሽግግር የሚረዱ የፓናል ውይይቶች፣ የቢዝነስ ስምምነቶችና የልምድ ልውውጦች እንደሚካሄዱበት የፕራና ፕሮሞሽን መስራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ ነብዩ ለማ ተናግረዋል።
የንግድ ትርኢቱ ኢትዮጵያ ውስጥ መካሄዱ በተለይ የኢትዮጵያ ምርቶች ደረጃቸውን ጠብቀውና እሴት ጨምረው ለዓለም ገበያ እንዲቀርቡና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እድል ይፈጥራል ተብሏል። በአገራችን ምርቶች በብዛት ቢመረቱም የማሸጊያ እቃ ባህሪ አለመጣጣምና የአስተሻሸግ ሂደት ላይ በሚያጋጥም የጥራት ጉድለት የተፈለገውን ያህል ውጤታማ መሆን እንዳልተቻለ የገለጹት አዘጋጆቹ፤ ከንግድ ትርኢቱ ጎን ለጎን በሚካሄድ የፓናል ውይይቶች፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የልምድ ልውውጥ ፕሮግራሞች ላይ ችግሮቹ ሊቀረፉ የሚችሉበት መንገድ እንደሚፈለግ ተናግረዋል። የውጭ ኢንቨስተሮችም የምርት ማቀነባበሪያና የማሸጊያ ምርቶች ላይ ኢንቨስት የሚያደርጉበት መንገድ ይዘረጋል ተብሏል፡፡

Read 1084 times