Monday, 30 January 2017 00:00

ብርሃንና ሰላም የህትመት ማሰልጠኛ ተቋሙን ያስመርቃል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

95ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ዛሬ ያከብራል
                               
      95ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በዛሬው እለት የሚያከብረው አንጋፋው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት፤ ከ2 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በድግሪ መርሃ ግብር ተቀብሎ የሚያስተምር የህትመት ማሰልጠኛ ተቋም ያስመርቃል፡፡ ማተሚያ ቤቱ ለማሰልጠኛ ተቋም ያስገነባውን ባለ 7 ፎቅ ህንፃ፣እንዲሁም የቼክ ፐርሰናላይዜሽን ፕሮጀክትና ህትመቶችን በጥራትና በብዛት ማተም የሚያስችል ባለ 8 ዩኒት የዌብ ኦፍሴት ማሽን እንደሚያስመርቅም ታውቋል፡፡
የህትመት ማሠልጠኛ ተቋሙ፣ ከሚቀጥለው ዓመት መስከረም ወር ጀምሮ ተማሪዎችን በመቀበል ስራውን የሚጀምር ሲሆን ትምህርቱን የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲና ማተሚያ ቤቱ በቅንጅት እንደሚሰጡ ተጠቁሟል፡፡ ተቋሙ በ5 ዲፓርመንቶች ተከፋፍሎ ሥልጠናውን የሚሰጥ ሲሆን በሃገሪቱ የመጀመሪያው የህትመት ማሰልጠኛ ተቋምም ነው፡፡  
የቼክ ፐርሰናላይዜሽን ፕሮጀክቱ የባንኮችን ቼክ በየግለሰቦች መለያ ቁጥርና የተለያዩ መረጃዎች ለማዘጋጀት እንደሚረዳ የገለጹት የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ተካ አባዲ፤ ለጊዜው ህትመቱ በህንድ ሃገር የሚከናወን ሲሆን ማተሚያ ቤቱ ፐርሰናላይዝ አድርጎ ለባንኮች እንደሚያቀርብ ጠቁመዋል። በመጪው ዓመት ግን ሙሉ የቼክ ህትመት ይጀመራል ብለዋል - ሥራ አሥኪያጁ፡፡ በጋዜጦች የማተሚያ ዋጋ ላይ ቅናሽ ያመጣል የተባለው ባለ 8 ዩኒቱ የዌብ ኦፍ ሴት ማሽን፣ በአንድ ጊዜ በርካታ ቅጂዎችን በፍጥነትና በጥራት ለማተም ያስችላል ብለዋል፤ አቶ ተካ፡፡
አንጋፋው ማተሚያ ቤት በዛሬው ዕለት 95ኛ ዓመት የምስረታ በአሉን ሲያከብር ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመን ጨምሮ የተለያዩ ሚኒስትሮችና የመንግስት ሃላፊዎች እንዲሁም ደንበኞች ይገኛሉ ተብሏል፡፡

Read 1231 times