Monday, 30 January 2017 00:00

አቶ ጁነዲን ባሻ በቀጥታ ከጋቦን

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

 • በ31ኛው የአፍሪካ ዋንጫ መስተንግዶ እና የውድድር ሁኔታዎች በሚገመግመው ኮሚቴ እና በጨዋታ    ኮሚሽነርነት እየሰሩ ናቸው፡፡
    • በ2020 እኤአ ቻንን እናስተናግዳለን፤ በ2025 እኤአ ደግሞ አፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀችት ከመጨረሻዎቹ 3  እጩ አገራት ተርታ እንገኛለን፡፡
    • በካፍ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ለመግባት ፍላጎት አላቸው፡፡
    • የኢንስትራክተሮች ብዛት ከ4 ወደ 8 ማደጉ፤ የዋና እና ረዳት ዳኞች ብዛት 22 መድረሱ፤ የታዳጊ እና ወጣት  ቡድኖች ውድድሮች መጠናከራቸው፤ በቀን እስከ 65 ጨዋታዎች በዓመት እስከ 1ሺ600 ያህል ጨዋታዎች  መካሄዳቸው፤ ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን የሚያስተናግዱ ስታድዬሞች ብዛት ከ5 በላይ መሆኑ፤ የፌደሬሽኑ ገቢ በሪከርድ ደረጃ መጨመሩ፤ ዓለም አቀፍ ግንኙነት መሻሻሉ… ከጠቀሷቸው የፌደሬሽናቸው መልካም ተመክሮዎች
     • ‹‹በተጨማሪ የስራ ዘመን ለመቀጠል የምንችልበትን ሁኔታ ጊዜው ሲደርስ እንመለከተዋለን ፡፡ ስራችንን ግን   ይቀጥላል፡፡››

      የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከተመሰረተ ከ75 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ሲሆን በ1952 እ.ኤ.አ የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ፊፋ ፤ በ1957 የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ካፍ አባልነት እንደተመዘገበ ይታወቃል፡፡ በአሁኑ ወቅት ፌደሬሽኑን በማስተዳደር ላይ የሚገኘው የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በ2006 ዓ.ም በአዲስ መልክ የተመረጠ ሲሆን ላለፉት 3 አመታት በፕሬዝዳንትነት የመሩት አቶ ጁነዲን ባሻ ናቸው፡፡ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በእግር ኳሱ ከፍተኛ ስልጣን ላይ የሚቆየው ለአራት ዓመታት ሲሆን የስራ ዘመኑ የሚያበቃው ከ ዓመት በኋላ ይሆናል፡፡ በትውልዳቸው ከአርሲ ክልል የሆኑት ጁነዲን ባሻ 56ኛ ዓመታቸውን ይዘዋል፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በBSC  እንዲሁም በዩኒቨርስቲ ኦፍ ግሪንዊች በBMA ድግሪዎችን ተቀብለዋል፡፡ በቢዝነስ አስተዳደር ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ሲሆን የሐረር ቢራ ስራ አስኪያጅ እና የንግድ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው ከመስራታቸውም በላይ የሐረር ቢራ የእግር ኳስ ክለብ በፕሪሚዬር  ሊጉ ተወዳዳሪ በሆነበት ጊዜያት የክለቡ ፕሬዝዳንት ሆነው ግልጋሎት ሰጥተዋል፡፡ አቶ ጁነዲን ‹‹የኢንዱስትሪያል ፒስ አዋርድ›› ፤ በኢትዮጵያ የጥራት ምዘና ተቋም  ‹‹ሊደርሺፕ አዋርድ›› እና ‹‹የግሪን አዋርድ›› ሽልማቶችን በተለያዩ ጊዜያት ያገኙም ናቸው፡፡ ከ3 ዓመታት በፊት አቶ ጁነዲን ባሻ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ሆነው ሲመረጡ  የድሬዳዋ ክልልን በመወከል  ሲሆን   በጠቅላላ ጉባኤው አባላት ከሚሰጡት 101 ድምፆችን 55 በማሸነፍ ነበር፡፡  የእግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ሆነው ማገልገል ከጀመሩ በኋላ በፊፋ የማርኬቲንግ እና ቲቪ ኮሚቴ፤ እንዲሁም በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን የአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅት ኮሚቴ አባልነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡  ከ31ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ጋር በተያያዘ በአስተናጋጇ አገር ጋቦን የሚገኙትን የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ ጋር በቀጥታ ስልክ በመገናኘት ስፖርት አድማስ  ይህን ልዩ ቃለምምልስ አድርጓል፡፡

      አቶ ጁነዲን ለስራ ከሚገኙበት ጋቦን ይህን ልዩ  ቃለምልልስ ለማድረግ ፈቃደኛ በመሆንዎ አመሰግናለሁ፡፡ ከ31ኛው አፍሪካ ዋንጫ ጋር በተያያዘ ምን እየሰሩ እንደሆነ ቢገልፁልን?
ወደ ጋቦን የሄድኩት በአፍሪካ ዋንጫ የዝግጅት ኮሚቴ በያዝኩት ሃላፊነት ነው፡፡  በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን  ስር የሚንቀሳቀሰው የአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅት ኮሚቴ፤ በ4 ዞኖች የተከፋፈለ ሲሆን የአፍሪካ ዋንጫውን አጠቃላይ መስተንግዶ፤ የውድድር ሁኔታ በመገምገም ክትትል እያደረገ ይሰራል፡፡ ጋቦን ላይ ይህን ለመስራት የኢትዮጵያ፤ የደቡብ አፍሪካና የናይጄርያ እግር ኳስ ፌደሬሽኖችንን የወከልን ሃላፊዎች በቅንጅት በመስራት ንቁ ተሳትፎ በማረግ ላይ እንገኛለን፡፡ ከዚያም አልፎ በየጨዋታው በኮሚሽነርነት እየተመደብን እየሰራን ነው፡፡ በአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅት ኮሚቴ አባልነት ያላቸው የተለያዩ አገራት ፌዴሬሽኖች ሃላፊዎች  ብዙ አልተገኙም፡፡ ከምስራቅ አፍሪካ አገራት እንኳን ከእኛ ጋር ያለው የሱዳን ፌደሬሽን ብቻ ነው፡፡ እንደሚታወቀው ወደ አፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅ ኮሚቴ የገባሁት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ሆኜ እንደተመረጥኩ ነው፡፡ የአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅት ኮሚቴው በየሁለት ዓመቱ የሚካሄደውን የአፍሪካ ዋንጫ አጠቃላይ የመስተንግዶ፤ የውድድር ሁኔታዎች እየገመገመ ይሰራል፡፡ በተመሳሳይ ሃላፊነት በ2015 እኤአ ላይ ኢኳቶርያል ጊኒ ባዘጋጀችው 30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይም ስሰራ ነበር፡፡ በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ብቻ ሳይሆን ባለፉት ሁለት ዓመታ በፊፋ የማርኬቲንግ እና ቲቪ ኮሚቴ በአባልነት ሳገለግል ቆይቻለሁ፡፡ አሁን ይህ ኮሚቴ በአዲስ መልክ እንዲደራጅ ተወስኖ ተበትኗል፡፡
ኢትዮጵያ በቅርቡ የምታዘጋጀው አህጉራዊ ውድድር በ2020 እኤአ ላይ የሚካሄደው የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ ወይም ቻን እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በዚህ መስተንግዶ ዙርያ  ምን አዳዲስ መረጃዎች አሉ?… ከአፍሪካ ዋንጫ  አዘጋጅነት ጋር በተያያዘስ?
እንደጠቀስከው በ2020  እኤአ ላይ የቻን ውድድርን እንድናስተናግድ ያቀረብነው ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቶ  እድሉ ተሰጥቶናል፡፡ በሌላ በኩል በ2025 እኤአ ላይ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫ የምታዘጋጅበትን እቅድ አቅርበን ጉዳዩ ጠረጴዛ ላይ ነው ያለው፡፡ በኮንፌደሬሽኑ የአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅት ኮሚቴ አባል ከመሆኔ ጋር በተያያዘ እንደተረዳሁት ለአፍሪካ ዋንጫ መስተንግዶው ከቀረቡት ሶስት የመጨረሻ እጩዎች ኢትዮጵያ ትገኝበታለች። በየደረጃው የምናደርገው ጥረት በሚያገኛቸው ምላሾች ተስፋ የሚሰጥ ሆኖም አግኝተነዋል፡፡
በመጋቢት ወር የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን የአዲስ ፕሬዝዳንት ምርጫ ያካሂዳል። ከኢትዮጵያዊው ይድነቃቸው ተሰማ መንበሩን ተረክበው ካፍን ላለፉት 21 ዓመታት በፕሬዝዳንትነት የመሩት ካሜሮናዊው የቀድሞ ምርጥ የአጭር ርቀት ሯጭ ኢሳ ሃያቱ በሃላፊነታቸው ለመቀጠል እንደሚፈልጉ እየተገለፀ ነው፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የመካከለኛውና ምስራቅ አፍሪካ ዞንን በካፍ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ለመወከል እንደሚፈልግ ተሰምቷል፡፡ በካፍ ስራ አስፈፃሚ ለመካተት በሚካሄደው ምርጫ ይወዳደራሉ?
በእርግጥ በካፍ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ሆኖ ለመግባት ፍላጎቱ አለኝ፡፡ ከዚያ በፊት ቅድሚያ የሚሰጠው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ምርጫ ነው፡፡ በርግጥ በአህጉራዊው የእግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ለበርካታ ዓመታት በስራ አስፈፃሚነት የቆዩ አባላት ሃላፊነታቸውን በተመቻቸ ሁኔታ በማስረከብ ለአዲስ ስራ አስፈፃሚዎች እድል እንዲፈጥሩ የአባል አገራት ፌደሬሽኖችን የምንመራ ሁሉ እየተመካከርን ነው፡፡ በካፍ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ለመወዳደር የምገባው በተለያያ መንገድ የምረጡኝ ዘመቻ በመስራት ነው፡፡ ከበርካታ የአህጉሪቱ ፌደሬሽኖች ጋ መልካም ግንኙነት አለኝ፡፡ በምርጫው ተፎካካሪዎቼ ሊሆኑ የሚችሉት የሱዳን፤ የጅቡቲ እና የኡጋንዳ እግር ኳስ ፌደሬሽኖችን የሚመሩ ፕሬዝዳንቶች ናቸው፡፡ የካፍ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ 14 ወንበሮች ያሉት ሲሆን 2 ለመካከለኛውና ምስራቅ አፍሪካዎች ነው፡፡ ስለዚህም ኢትዮጵያ አንዱን ወንበር ማግኘት እንደሚገባት በማመን ጥረት አደርጋለሁ፡፡
እንግዲህ በእርስዎ ፕሬዝዳንትነት  የሚመራው የእግር ኳስ ፌደሬሽን ስራ አስፈፃሚ በሃላፊነቱ ሶስት ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ በእነዚህ ዓመታት በአስተዳደርዎ የተሰሩ ተግባራትና መልካም ተምክሮዎችን ቢዘረዝሩልን…
በመጀመርያ ደረጃ ትኩረት የሰጠነው እግር ኳሱ በመላው አገሪቱ ተስፋፍቶ የሚቀጥልበትን ሁኔታ ነው፡፡ እስከ መቶ ሚሊዮን ህዝብ ባለበት አገር ስፖርቱ በበቂ ሁኔታ መስፋፋት እንዳለበት አምነን ተንቀሳቅሰናል፡፡ ከእኛ አስቀድሞ የእግር ኳስ እንቅስቃሴው በአዲስ አበባ ከተማ፤ በደቡብ ክልልና በኦሮሚያ  በሚገኙ ክለቦች የተወሰነ እንደነበር ይታወቃል፡፡ በአማራ ክልል በፕሪሚዬር ሊግ የሚወዳደር ክለብ አልነበረም፤ በትግራይ የነበረው ተሳትፎም መቀዛቀዙም ይታወቃል። በኦሮሚያም ቢሆን ከአዳማ ከተማ እና ከሙገር በቀር ንቁ ተሳትፎ አለመኖሩን ማስታወስ ይቻላል። በሌሎች ክልሎች እንደውም ጭራሽ ምንም አይነት ተሳትፎ አልነበረም፡፡ እንደጋምቤላ፤ ሶማሌ እና አፋር ክልሎችን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ በአሁን ወቅት ግን በሁሉም ክልል ክለቦች እየተመሰረቱ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ያህል ለብዙ አመታት በትግራ ክልል በእግር ኳስ የነበረው ተሳትፎ ተዳክሞ ነበር፡፡ በቅርብ ዓመታት ግን እነ ሽሬ ፤ አክሱም መቀሌ እና አዲግራት … እንዲሁም በሌሎች ክልሎችና ከተሞች የእግር ኳስ ክለቦች ተመስርተው ወደ ከፍተኛ ሊግ በመግባት ወደ ፕሪሚዬር ሊጉ ለመቀላቀል ከጫፍ ደርሰዋል፡፡ ስለዚህም  እግር ኳሱን ወደ ሁሉም ህዝብ ለማድረስ በተከተልነው አቅጣጫ ለውጦች መፈጠራቸውን ማንም የሚያስተውለው ነው፡፡ በየክልሉ ህዝቡን የሚወክሉ ክለቦች መፈጠራቸው እንደ ትልቅ ውጤት የምንገልፀው ነው፡፡ በፌደሬሽኑ እምነት ክለብ ማቋቋም  የልማት ስራ መሆኑን ነው። ከክለብ ምስረታዎች ጋር በተያያዘ የየአካባቢው ህዝብ የእግር ኳስ አመለካከት እና እውቀት እንዲያድግ፤ ተተኪ ስፖርተኞችን ከመላ ኢትዮጵያ ለማግኘት፤ በክልልና የከተማ መስተዳድሮች ስፖርቱን ለማስፋፋት የሚሰጠው ትኩረት እና የስፖርት ማዘወትርያ ስፍራዎችና መሰረተልማቶችን  በመገንባት ያሉ እንቅስቃሴዎችም  እንዲጠናከሩ እያደረገ ነው፡፡ እግር ኳስ በከተማ ብቻ ሳይወሰን በየክልሉ በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋ መምጣቱ በእኛ የአስተዳደር ዘመን ውጤታማ እየሆንበት ያለ እና የምንኮራበት አቅጣጫ ነው፡፡  እግር ኳስ አሁን በአብዛኞቹ ክልሎች የህዝቡ ባህል መሆኑን ማረጋገጥ ችለናል፡፡
በሌላ በኩል በታዳጊ እና ወጣት ቡድኖች  ውድድሮችን በአገር አቀፍ ደረጃ ፈርቀዳጅ ሆነን በመጀመር ያከናወንናቸው ተግባራትም አበረታች ናቸው፡፡ ፌደሬሽኑ ባለፉት 3 ዓመታት በታዳጊ እና ወጣቶች እግር ኳስ ላይ በትኩረት በመስራቱ ተሳክቶለታል፡፡ ብዙ ተተኪ ተጨዋቾችም በፕሮጀክት ታቅፈው ስልጠና እየተከታተሉ እንደሚገኙ፤ በአካዳሚዎች ውስጥ የሚገኙ የነገ ተስፈኛ እግር ኳስ ተጨዋቾች ቁጥርም መብዛቱንም እንደ ማስረጃ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከዚህ ቀደም በታዳጊ እና ወጣቶች ደረጃ ይዘጋጅ የነበረው  የሀ17 ውድድር ብቻ ነበር፡፡ በአዲስ መልክ የሀ20 ቡድኖች ውድድርን በመጀመራችን ከስር ያሉ ወጣት እና ታዳጊ ተጨዋቾችን ቀጣይነት ያለው የእግር ኳስ ጉዞ ምቹ ያደረግንበት ሁኔታ የሚጠቀስ ነው፡፡ የሁለቱ ውድድሮች ተያይዞ መካሄድ በአገሪቱ እግር ኳስ ያለውን የእድሜ ማጭበርበር ችግርን ለማስተካከል የሚያግዝ እና የተጨዋቾችን ተፈጥሯዊ እድገት የሚደግፍ የእግር ኳሱ እድገት ጠቃሚ አቅጣጫ መሆኑን አረጋግጠንበታል፡፡ የሀ 20 ውድድር በወንዶች ደረጃ በፕሪሚዬር ሊግ፤ በከፍተኛ ሊግ፤ በብሄራዊ ሊግ እየተካሄደ ነው፡፡ በሀ 15 ቡድኖች ደግሞ በየደረጃው እየሰራን ነው፡፡ በተለይ ከኮካኮላ ኩባንያ ጋር በአጋርነት የምንሰራበት ውድድር ለትኩረታችን የሚጠቀስ አካሄድ ነው፡፡
በ3ኛ ደረጃ የምጠቅሰው በባለሙያዎች የአቅም ግንባታ እና ስልጠና ዙርያ በስፋት የተንቀሳቀስንባቸውን ሁኔታዎች ነው፡፡ በተለይ ለአሰልጣኞች እና ለዳኞች በርካታ የስልጠና መድረኮችን እየፈጠርን ሙያቸውን በሚያሳድጉ አቅጣጫዎች እየሰራን ቆይተናል፡፡ ስለሆነም የሚከተሉትን ጉልህ ውጤቶችንም አስመዝግበናል፡፡ በ2008 የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ዝርዝር ሪፖርት የቀረቡ መረጃዎች በአቅም ግንባታው በኩል ያከናወናቸውን አበረታች ተግባራትን የሚያመለክቱ ናቸው፡፡ በካፍ እውቅና የተሰጣቸው የኢንስትራክተሮች ብዛት ከ4 ወደ 8 አድጓል፡፡ በየደረጃው ከታዳጊ ጀምሮ ለ840 አሰልጣኞች ስልጠናም ሰጥተናል፡፡ በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ፊፋ እውቅና አግኝተው የተመዘገቡ 22 ዋና እና ረዳት ዳኞች መሆናቸውና  የፌደራል ዳኞች ብዛት ከ250  ወደ 412 ከፍ ማለቱ በዳኝነት ሙያ ያስመዘገብናቸውን ውጤቶች ያመለክታሉ፡፡ የብሄራዊ ቡድን ወጌሻዎች ብዛት ከ2 ወደ 87 መጨመሩ እንዲሁም በ2008 ከፍተኛ ሊግ እና ብሄራዊ ሊግ 87 የህክምና ሙያተኞች የሙያ ማሻሻያ ማግኘታቸው በፌደሬሽኑ ታሪክ በፈርቀዳጅነት ያከናወንነው ተግባር ነው፡፡
የኢትዮጵያ  እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባለፉት ሶስት ዓመታት በስሩ የተለያዩ ሰባት ያህል ውድድሮችን በዋናነት እያካሄደ መሆኑንም መጥቀስ ተገቢ ነው፡፡  የወንዶች ፕሪሚየር ሊግን፣ የሴቶች ፕሪሚየር ሊግን፣ የከፍተኛ ሊግን፣ የብሄራዊ ሊግን፣ ከ20 ዓመት በታች ፕሪሚየር ሊግን፣ ከ17 ዓመት በታች ፕሪሚየር ሊግን ጨምሮ በርካታ ውድድሮችን እያንቀሳቀስን ነው፡፡ በቀን እስከ 65 ጨዋታዎች  በዓመት እስከ 1ሺ600 ያህል ጨዋታዎችን የምናካሂድበት ደረጃ ላይም ደርሰናል፡፡ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ትኩረቱ ሁሉም ውድድሮች በተቀመጠላቸው ጊዜና ቦታ ያለምንም መቆራረጥ እና የጸጥታ ችግር እንዲጠናቀቁ መስራት ነው፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ብሄራዊ ቡድኑን ማጠናከርና  በቂ ዝግጅት እንዲያደርግ ማገዝም እንፈልጋለን፡፡
በነገራችን ላይ በአገሪቱ የስታድዬም መሰረተ ልማቶች ዙርያም ከፍተኛ መነቃቃት ተፈጥሯል። የሚመሩት ፌደሬሽን በአስተዳደሩ ታሪክ በርካታ ስታድዬሞችን ለኢንተርናሽናል ጨዋታዎች መስተንግዶ በማብቃት እድለኛ ነው ማለት ያስደፍራል…
ልክ ነህ፡፡ በስፖርት መሰረተልማቶች በተለይም በስታድዬም ግንባታ የተመዘገቡ ስኬቶችም እንደመልካም ተመክሮዎች ልናነሳቸው የሚቻል ነው፡፡ አስቀድሞ ከአዲስ አበባ ስታድዬም በስተቀር ኢንተርናሽናል ጨዋታዎችን ለማስተናገድ ፈቃድ ያገኙ ስታድዬሞች አልነበሩም፡፡ ከአዲስ አበባ ስታድዬም በኋላ አበበ ቢቂላ ስታድዬም፤ ድሬዳዋ ስታድዬም፤ ባህርዳር  ስታድዬም፤ ሐዋሳ  ስታድዬም ኢንተርናሽናል ጨዋታዎችን ማስተናገድ የሚችሉበት እውቅና ማግኘት ችለዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት በወልዲያ ከተማ ተመርቆ ስራ የጀመረው መሐመድ ሁሴን አሊ አል አሙዲ ስታዲየምና የስፖርት ማዕከል በዚሁ አቅጣጫ የምንሰራበት ይሆናል፡፡ በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ጨዋታ የማስተናገድ እውቅና እና ብቃት ያላቸው ስታድዬሞች ብዛት የመቀሌ እና የነቀምት ስታድዬሞች ሲያልቁ ደግሞ 7 ይደርሳል። በሚቀጥሉት 5 አመታት ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው ስታድዬሞች ብዛት ከ10 በላይ እንደሚሆን እንጠብቃለን፡፡ በየክልሉ ያሉት ስታድዬሞች አህጉራዊና የአገር ውስጥ እግር ኳስ ጨዋታዎችን በማስተናገድ አገልግሎት መስጠታቸውን በመጀመር  የፈጠሩት መነቃቃት ትልቅ ውጤት ይመስለኛል፡፡
የኢትዮጵያ  እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባለፉት ሶስት ዓመታት በፈርቀዳጅነት አከናውኗቸዋል የሚላቸው ሌሎች እንቅስቃሴዎች  
በ2008 የበጀት አመት ሙሉ ሪፖርት እንደተመለከተው የፌዴሬሽኑ ዓመታዊ በጀት ከ120 ሚሊዮን ብር በላይ ሲሆን ይህም በአስተዳደሩ ታሪክ ከፍተኛው ሆኖ የተመዘገበ ነው፡፡ በ2008 በጀት አመት 158,000,000 ብር የሚሆን ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ ከ118.8 ሚሊዮን ብር በላይ ማስገባት የቻልን ሲሆን፤ ይህም የእቅዳችንን 75 በመቶ እንዳሳካን የሚያመለክት እና በፌደሬሽኑ ታሪክ  ከፍተኛው ገቢ ሆኖ የሚመዘገብ ይሆናል፡፡  በሌላ በኩል በ2008 ፌደሬሽኑ ካስመዘገባቸው ውጤቶች የሚጠቀሰው በእግር ኳስ አስተዳደሩ ታሪክ በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነ የስፖንሰርሺፕ ስምምነት ለብሄራዊ ቡድኑ የተገኘበት ነው፡፡ ከጣሊያናዊው የስፖርት ትጥቅ አምራች ኩባንያ ኤርያ ጋር የፈረምነው የስፖንሰርሺፕ ውል የ90ሺዮሮ ትጥቅ በስጦታ 50ሺ ዮሮ በግዥ የሚስያገኝ ሲሆን በየዓመቱ እስከ አራት ሚሊዮን ብር የሚወጣበትን የትጥቅ ግዢ ማስቀረቱ ፈርቀዳጅ የሆንበት እንቅስቃሴ እንደሆነ በልበሙሉነት መናገር እችላለሁ፡፡
በተጨማሪም የፌደሬሽኑ ዓለም ዓቀፍ ተሳትፎና ተሰሚነት እያደገ መምጣቱ ማንሳት ተገቢ ይሆናል፡፡ የፊፋው ፕሬዝዳንት ጣሊያናዊው ጂያኒ ኢንፋንቲኖ በተመረጡ በአጭር ግዜ ውስጥ በኢትዮጵያ ቀዳሚ የሥራ ጉብኝት  ማድረጋቸው ለዚህ አበይት ማስረጃ ነው፡፡  የፊፋው ፕሬዝዳንት ጉብኝት በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር እና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን ግንኙነት የሚያሻሽል ፤ የአገሪቱን ተጠቃሚት የሚያሳድግ ውይይትና ምክክር የተደረገበት ነበር፡፡ በተጨማሪ ኢትዮጵያ የካፍ እና የፊፋ ሁለት ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችን በቀጣይ ወር ለማስተናገድ ያገኘችው እድል የፌደሬሽኑን የዓለም አቀፍ ግንኙነት መጠናከር የሚያመለክት ነው፡፡ እነዚህ ስብሰባዎች ያለምንም ችግር እንዲጠናቀቁና ሀገሪቱ ስብሰባዎችን የማዘጋጀት አቅሟን ለካፍም ይሁን ለፊፋ እንድታሳይ ከፍተኛ ጥረቶችን በአየአቅጣጫው እያደረግን መሆኑን እገልፃለሁ፡፡
በአጠቃላይ ባለፉት 3 ዓመታት ለፌደሬሽኑ ከመንግስት የሚገኘው ድጋፍ መጠናከር፤ በተለያዩ አቅጣጫዎች የሚያገኛቸው የገንዘብ ድጋፎች ማደግ እና መጨመር የውድድሮች ስፋትና ተደራሽነት በተጠናከረ ደረጃ የሚቀጥልበት መሰረት መደላደሉ፤ ሙያተኞችን የሚስብ አደረጃጀት ተግባራዊ እየሆነ መምጣቱ እና ከባለድርሻ አካላት ጋር መልካም ግንኙነት መፈጠሩ በአስተዳደራችን የታዩ ጉልህ ለውጦችን የሚያመለክቱ ናቸው፡፡
በመጨረሻም አንድ ጥያቄ ማንሳት እፈልጋለሁ። እንግዲህ በእርስዎ የሚመራው ፌደሬሽን የቀረው የስልጣን ዘመን 1 ዓመት ብቻ ነው፡፡ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ የአምስት አመት ስትራቴጂክ እቅድ ደግሞ የሚያበቃው በ2010 ይሆናል፡፡ በሌላ በኩል በ2020 እኤአ ላይ የቻን ውድድርን የማስተናገድ እድሉን ፌደሬሽኑ እንደፈጠረ ይታወቃል፡፡  ባለፉት 3 ዓመታት የጀመራችኋቸውን ስራዎች ለማጠናቀቅና የአምስት ዓመት ስትራቴጂያችሁን ለመተግበር ተጨማሪ የስራ ዘመን ያስፈልጋችሁ ይሆን እንዴ?
በኢትዮጵያ ስፖርት መሾም እና መሻር ያለ ነው። ብዙ አዲስ ይመጣል፤ ይሄዳል፡፡ አሁን በስልጣን ላይ በሚገኘው የእግር ኳስ ፌደሬሽን ዙርያ አንዳንድ አስተያየቶች ሲሰጡ እሰማለሁ፡፡ 1 ዓመት የቀረው ስራ አስፋፃሚ እየተባለ፡፡ በርግጥ ይህ ተገቢ አይደለም፡፡ ለሁሉም ግዜው ሲደርስ የሚለይ እንደሆነ መታወቅ አለበት፡፡ አሁን ያለው ስራ አስፈፃሚ እንዲቀጥል ወይም እንዲቀየር የሚያደርገው የእግር ኳሱ የበላይ አካል የሆነው ጠቅላላ ጉባኤ ነው፡፡ በሚመለከተው አካል ሳይመረጥ መቀጠል የሚፈልግ ማንም የለም። ይሁንና በእኔ አመለካከት የምረዳው ብዙውን ግዜ አዲስ ፊት ማየት ለውጥ ማምጣት አለመሆኑን ነው። በዚህ አይነት አቅጣጫ ስፖርቱን መምራት ብዙ ሃሳቦች እና እቅዶች በእንጥልጥል እንዲቀሩ ያደርጋል። ስለዚህም ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ተመክሮ ልንወስድ ያስፈልጋል፡፡ አሁን ለምሳሌ እንደ ጋና ባሉት አገራት አንድ የፌደሬሽን አመራር  አራት ዓመት የስራ ዘመኑን ካበቃ በኋላ ያገኘውን ተምክሮ ተጠቅሞ የላቁ ስኬቶችን ማስመዝገብ እንዲችል ተጨማሪ የስራ ዘመን እንዲያገኝ መደረጉን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በአጠቃላይ በፌደሬሽኑ አስተዳደር ባከናወንናቸው ፈርቀዳጅ ተግባራት ባስመዘገብናቸው ውጤቶች ደስተኞች ነን፡፡ በተጨማሪ የስራ ዘመን ሃላፊነታችንን ለመቀጠል የምንችልበት ሁኔታ  ጊዜው ሲደርስ እንመለከተዋለን። በኛ በኩል ስራችንን ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

Read 1815 times