Monday, 30 January 2017 00:00

ለፖለቲካዊ ችግሮች ፖለቲካዊ ውይይት!!

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

ከውይይቱ ምን ይጠበቃል?

በሀገሪቱ የተፈጠሩ ተቃውሞና ግጭቶችን ተከትሎ አንጋፋዎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከገዥው ፓርቲ ጋር የድርድርና ውይይት መድረክ እንዲዘጋጅላቸው በተደጋጋሚ መወትወታቸው አይዘነጋም፡፡
የመጀመሪያው የድርድርና የውይይት መድረክም ባለፈው ሳምንት በፓርላማ ተካሂዷል። አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ውይይቶቹና ድርድሮቹ ለመገናኛ ብዙኃን ፍጆታ የሚውሉና የይስሙላ እንዳይሆኑ
ስጋት ቢኖራቸውም አብዛኞቹ በመድረኩ መዘጋጀት ደስተኞች ናቸው። ውይይቱ በታቀደው መሰረት በተከታታይ የሚቀጥል ከሆነ፣ እያንዳንዱ ፓርቲ የውይይት አጀንዳዎቹን ማቅረብ ይጠበቅበታል፡፡
ለመሆኑ ተቃዋሚዎች ከኢህአዴግ/መንግስት ጋር መወያየት ያለባቸው ምንድን ነው? ሂደቱ እንዴት ነው መሆን ያለበት? ከውይይቱ ምን የጠበቃል? ከተወያዮቹስ?
የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣ በዚህ ዙሪያ የአንጋፋ ፖለቲከኞችን ሃሳብና አስተያየት አሰባስቦ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡

“ችግሮችን ፈጥሮ የነበረው አካል መጀመሪያ መታወቅ አለበት”

አቶ ሞሼ ሰሙ (የፖለቲካ ተንታኝ)


ውይይት አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ በመሰረተ ሀሳብ ደረጃ የዲሞክራቲክ ስርአት አንድ መገለጫ ነው። ሁልጊዜ ጉዳዮች በተፈለጉበት ቅርፅና መልክ ሊጓዙ አይችሉም፡፡ እንከኖች ሲያጋጥሙ የማረሚያ እርምጃዎችን ለመውሰድ የሚያስችሉ ውይይቶችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ማድረግ አስፈላጊ ነገር ነው፡፡
ውይይቱ ምን ትርጉም ያለው ውጤት ያመጣል የሚለው የሚወሰነው በሚቀረፀው አጀንዳ ወይም ርዕሰ ጉዳይ ነው፡፡ የሚቀረፁት ርዕሰ ጉዳዮች የተፈጠሩትን ችግሮች፣ የተከሰቱትን አላስፈላጊ ግጭቶች፣አለመግባባቶችና ስርአት የጣሱ አካሄዶችን ለማረምና ለማስተካከል የሚካሄዱ ከሆነ ውጤት ያመጣል፡፡ ሌላው ይሄንን ውይይት ከልብ፣በቁርጠኝነት የመያዝ ጉዳይ አንድ የሚነሳ ነጥብ ነው፡፡ ውይይቱ ያለቁርጠኝነት ከተካሄደ፣ ለጊዜያዊ ፍላጎትና ፍጆታ ወይም ለነገር ማብረጃ ብቻ ሊውል ይችላል፡፡ ቁርጠኝነቱ ካለ ደግሞ የሚፈጠሩ ልዩነቶችን አጥብቦ፣ በሁሉም ላይ መግባባት ባይቻልም፣ በተመረጡ አጀንዳዎች ላይ መግባባት ላይ ለመድረስ ያስችላል፡፡ ለዚህ ደግሞ በሰጥቶ መቀበል መርህ ለመስተካከልና ለመታረም አስቀድሞ ቁርጠኛ መሆን ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ ጉዳዮች ከተሟሉ ለእኔ ማንኛውም ውይይት ጠቃሚ ነው፡፡
በእኔ እይታ በሚደረጉት ውይይቶች ሦስት መሰረታዊ ጉዳዮች መነሳት ይኖርባቸዋል። የመጀመሪያው ወደ ዋና አጀንዳ ከመገባቱ በፊት “ሞዳሊቲዎች” መዘጋጀት አለባቸው፡፡ ውይይቶቹ ሲጀመሩ ቀድሞ ያልተያዙ አጀንዳዎች ካሉ፣ውይይቶች ላይሳኩ ይችላሉ፡፡ ከህግ ውጪ የሚነሱ ጥያቄዎች ካሉ፣የተጀመረው ውይይት ባጭሩ ሊከሽፍ ይችላል፡፡ በሌላ በኩል ዝም ብሎ “ችግሮችን ለመፍታት ውይይት እያደረግሁ ነው” ለማለት ብቻ ታስቦ የሚካሄድ ከሆነም ብዙ ርቀት ሳይጓዝ ውይይቱ ሊስተጓጎል ይችላል፡፡ በሶስተኛ ደረጃ የተሳታፊዎቹ ማንነት ወሳኝነት ይኖረዋል። ከዚህ በፊት አንድም ጊዜ ጠቅላላ ጉባኤ አካሂደው የማያውቁ፣ አባሎቻቸውን ሰብስበው በሀገራዊ ጉዳይ ያልተወያዩ፣ ስንት አባላት እንዳላቸው የማያውቁ፣ ዝም ብሎ ብቻ ድርጅትና ማህተም የያዙ ግለሰቦችን ሰብስቦ፣ በሀገራዊ ጉዳይ ላይ እወያያለሁ ማለት የትም አያደርስም፡፡ እኛ ሀገር ውይይት ባህላችን ስላልሆነ በአጭር ጊዜ መጠናቀቅ የሚችል ውጤታማ ውይይት ለማካሄድ፣ የፓርቲያቸው አቅምና የሰው ኃይል ቁጥር ወሳኝ ነው። ከዚህ አንጻር 20 ፓርቲ በመያዝ ውይይት ማካሄድ ለኔ በጣም ከባድ ነው፡፡ ስለዚህ መጥበብ አለበት፡፡ የሚጠበው ደግሞ ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው ህግ መሰረት ነው፡፡ አንድ ፓርቲ ህልውና አለው ለማለት ፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ የሚያካሂድ፣ አባላት ያሉት፣ በየጊዜው አመራሩን የሚመርጥ መሆን አለበት ይላል፡፡ እነዚህ ለተሳትፎው መስፈርት መሆን አለባቸው፤ ፓርቲ ነን ስላሉ ብቻ፣ የድርጅት ማህተም የያዙ ግለሰቦችን ማሳተፍ ውጤት አያመጣም፡፡
አጀንዳዎቹ ምን መሆን አለባቸው ከተባለ፣ አንደኛ ከህዝብ የመጡ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ፓርቲዎች የህዝብ ውክልና አለን ካሉ፣ እነዚህን አጠናክረው ሊያቀርቡ ይገባል፡፡ ኢህአዴግም ያመነባቸው ከህዝቡ የተነሱ አጀንዳዎች አሉ፡፡
እነዚህ ጉዳዮች ነጥረው ወጥተው የውይይት አጀንዳ መሆን አለባቸው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጉዳይ ነው፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች የመድብለ ፓርቲ ስርአት ለማራመድ በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ ብዙ የሚያነሷቸው ችግሮች አሉ፡፡ የምርጫ ቦርድ ጉዳይ፣ ሚዲያ ማጣት፣ ወከባ ----- የመሳሰሉት ቀርበው ሰፊ ውይይት ሊደረግባቸው ይገባል፡፡
እነዚህ አጀንዳዎች ሲቀርቡ መታየት ያለበት አንድ ነገር አለ፡፡ የመጀመሪያው ነገር ፓርቲዎች ወደ ውይይት ብዙ ጊዜ ሲመጡ “የሚዲያ ገለልተኝነት ጥያቄ አለብን፣ የፋይናንስ ችግር አለብን፣ ምርጫው ነፃና ገለልተኛ አይደለም” የሚሉ ጉዳዮችን ያነሳሉ። ለኔ በመጀመሪያ እነዚህ የተዘረዘሩትን ችግሮች ፈጥሮ የቆየው አካል ተለይቶ መታወቅ አለበት፡፡ አንድ ፓርቲ የሚዲያ አቅርቦት አግኝቶ፣ ሠላማዊ ሰልፍ የማድረግ፣ የመደራጀትና ህዝብን ለምርጫ ማዘጋጀት እንዲሁም መንግስት መሆን መቻል ----- ህገ መንግስታዊ መብት ነው፡፡ ይሄን ህገ መንግስታዊ መብትን ነጥቆ የቆየው አካል ተለይቶ መታወቅ አለበት፡፡ በእነዚህ ህገ መንግስታዊ መብቶች ላይ ድርድር የሚደረግበት ሁኔታ መኖር የለበትም፡፡ በዚህ ላይ ቅድመ ውይይት ተደርጎ መግባባት ላይ መደረስ አለበት፡፡ ከህገ መንግስት ውጭ የሆነው ይሄ አይነት ህግ፣ ከየት እንደመጣ መታወቅ አለበት፡፡ ይህ ባልሆነበት መነጋገር ዝም ብሎ ጉንጭ ማልፋት ነው፡፡
ፓርቲዎች የመብት ጥሰት ሲደረግብን ነበር ካሉ፣ ወደ መድረኩ ሲገቡ መጀመሪያ ኢህአዴግ የመብት ጥሰት ማካሄዱን ስምምነት ላይ መድረስ አለባቸው፡፡ ኢህአዴግ ይሄን መቀበል አለበት፡፡ ህገ መንግስት ላይ በሰፈረ ጉዳይ ከሆነ የሚነጋገሩት ምንድነው ጥቅሙ? ዋናው ከህገ መንግስቱ ውጪ የተፃፉ ህጎችን ማን ፃፋቸው? እንዴት ሲተገበሩ ቆዩ? የሚለው ተፍታቶ ስምምነት ላይ መደረሱ ነው። መጀመሪያ ኢህአዴግ የፓርቲዎችን መብት ሲጥስ መቆየቱን አምኖ፣ ”ስህተት ሰርቻለሁ፤ ከአሁን ወዲያ መብታችሁን ላለመጣስ የሚሆነውን ነገር በጋራ እናድርግ” የሚል ድርድር ነው መካሄድ ያለበት እንጂ መብታቸው እንዳልተጣሰ ሆኖ፣ አዲስ ህገ መንግስታዊ መብት የሚቀርፁ አስመስለው ውይይት የሚያደርጉ ከሆነ፣ ትርጉም የሌለው ነገር ነው። ኢህአዴግም ተቃዋሚዎች መብቴን ሲጥሱ ነበር ካለ በዝርዝር ያቅርብ፤ ተቃዋሚዎችም ኢህአዴግ መብታችንን ሲጥስ ነበር ካሉ፣ በዝርዝር ያቅርቡና ተወያይተው መጀመሪያ ይተማመኑ፡፡ ድርጊቱን ያደረገው አካልም ተጣርቶ እርምት ተወስዶበት ነው፣ወደ ቀጣይ ውይይት መገባት ያለበት፡፡ “ነገ የውይይት መድረክ እፈጥርላችኋለሁ፣ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ እፈቅዳለሁ” የመሳሰሉት ከሆነ የሚፈለገው፣ ይሄ ቀድሞም በህገ መንግስቱ ላይ ያለ መብት ነው። በዚህ ላይ ውይይት የሚያስፈልገው ለምንድን ነው? ኢህአዴግ እነዚህን መብቶች ጥሶ የማያውቅ ከሆነ፣ ለምንድነው በጸደቀ ህገ መንግስት ላይ መወያየት የሚያስፈልገው?
ውይይቱ በዚህ መንገድ ካልተመራና ጊዜያዊ ማስተንፈሻ ከሆነ ግን የትም አይደርስም፤ ውጤትም አያመጣም፡፡ የጊዜ ጉዳይም መታሰብ አለበት። ጊዜ እየተራዘመ ምርጫ ደርሶ፣ የተጀመረው ነገር ሳይቋጭ፣ ለምርጫ ክርክር እንቀመጥ የሚባልበት ጊዜ እንዳይመጣ ቁርጠኛ መሆን ያስፈልጋል፡፡

===================================

“ተቃዋሚዎችይሄን እድል በሚገባ መጠቀም አለባቸው”
ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ
(የታሪክ ምሁርና ፖለቲከኛ)

ከዚህ በፊት መንግስት ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ብቻ ሳይሆን ከሀይማኖት አባቶች፣ ከሀገር ሽማግሌዎችና ከሲቪክ ተቋማት ጋር ተቀራርቦ
መነጋገር አለበት ብዬ ነበር፡፡ ፕሬዚዳንቱም በፓርላማው አመታዊ መክፈቻ ላይ የምርጫ ስርአት ለውጥ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡ አሁን የሚደረገው ድርድር ያስገኛቸዋል ብዬ ከምጠብቃቸው ውጤቶች አንዱ ይሄ ነው፡፡ ይሄ ሲሆን ደግሞ የግድህገ መንግስቱን ማሻሻል ያስፈልጋል፡፡
ውይይቱ መጀመሩ በራሱ ጥሩ ነው፡፡ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት ይደረጋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ የሲቪክ ተቋማትም በውይይቱ ቢካተቱ የበለጠ ጥሩ ይሆናል፡፡ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት እንዲህ ያለው ተቀራርቦ መነጋገር ጥሩ ነው፡፡የምርጫ ህጉንም ለማሻሻል  ጠቅማል፡፡ ምርጫው 3 ዓመት ነው ቀረው፤ እስከዚያ ድረስ አንድ ውጤት ይመጣል የሚል ተስፋ አለኝ፡፡ ውይይቱንና ድርድሩን አንቀበልም ያሉ ፓርቲዎች እንዳሉ ሰምቼ ነበር፤ ጥሩ የሚሆነው ሁሉም ቢሳተፉ ነው፡፡ የምርጫ ስርአቱን ለማሻሻል፣ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስተካከል፣ በተለይ የሚዲያ አጠቃቀም፣ የፓርቲዎች ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ፣ የመደራጀት ---- መብቶችን ለማስከበር ድርድሩ ጠቃሚ ነው፡፡ የህገ መንግስቱን አንቀፅ 30 እና አንቀፅ 38 ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ባለፉት ጊዜያት ችግሮች ስለነበሩ፣ ይሄን ለማሻሻል እውነተኛ ድርድር መደረግ አለበት፡፡ እኔ ድርድሩና ውይይቱ ለውጥ ያመጣል የሚል ተስፋ አለኝ፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ይሄን እድል ተጠቅመው ያለማቅማማት መሳተፍ አለባቸው። ገዥው ፓርቲ ደግሞ በሩን በደንብ መክፈትና መስማት እንዲሁም የሚቀርቡ ሀሳቦችን ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጁ መሆንና እነዚህ ውይይቶች ለህዝብ ግልፅ እንዲሆኑ ማመቻቸት ይጠበቅበታል፡፡

===============================

“በዚህ ውይይት ማሳካት የተፈለገው ግልፅ መሆን አለበት”

አቶ ግርማ ሰይፉ (የቀድሞ የፓርላማ አባል)


በመጀመሪያ ደረጃ በገዥው ፓርቲ በኩል ያለው ቁርጠኝነት ምን ያህል ነው የሚለው ያሳስበኛል። እነሱ ቁርጠኛ ከሆኑ፣ አሳሳቢ የሚሆነው ውጤቱ እንዴት የተሻለ ይሁን የሚለው ነው፡፡ ከዚህ ውይይት ምን እንደምናሳካ መታወቅ አለበት፡፡ ግን ይሄ ሳይሆን ድካሙ ሁሉ የአንዱን የበላይነት ለማረጋገጥ ከሆነ ቀልድ ነው የሚሆነው፡፡
ውይይቱና ድርድሩ የሰመረ እንዲሆን በመድረኩ ላይ የሚሳተፉ ፓርቲዎች እንዴት ናቸው የሚለው መገምገም አለበት፡፡
አገር ለመምራት እነዚህ ፓርቲዎች ቁመናቸው ይፈቅዳል ወይ? የሚለው መረጋገጥ አለበት። ይሄ የሚረጋገጥበት አንደኛው መንገድ፣ እነዚህ ፓርቲዎች የስራ አስፈፃሚ ስብሰባ በየጊዜው ስለማድረጋቸው፣ ባስቀመጡት የጊዜ ገደብ ጠቅላላ ጉባኤ ስለማካሄዳቸው በመመርመር ነው፡፡ እነዚህን ትንንሽ ዲሲፕሊኖች የማያሟሉ ፓርቲዎች፣ ሀገርን ይወክላሉ ማለት አንችልም፡፡
በዚህ ድርድርና ውይይት፣ ተቃዋሚዎች ከኢህአዴግ ጋር በአጭር ጊዜ ውስጥ ተስማማን ብለው ከወጡ በጣም እገረማለሁ፡፡ ወይም ደግሞ አፍቃሬ አብዮታዊ ዲሞክራሲ የሆኑ ተቃዋሚዎች፣ ከኢህአዴግ ጋር አንድ መሆናቸውን አረጋግጠው ቢወጡ ጥሩ ነው፡፡
ለህዝቡም ይሄ ጠቃሚ ነው። ማን እውነተኛ ታጋይ ነው? የሚለውን አውቆ ይንቀሳቀሳል፡፡ “ከኢህአዴግ ጋር በመስመር አንገናኝም፤ የራሳችን አለን” የሚሉት በአንድ ወገን ነጥረው የሚወጡበት ሁኔታ ቢፈጠር መልካም ነው።
ውጤቱ  መሆን ያለበት ብዬ የማስበው፣ ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲና ፖለቲከኛ፣ አለኝ የሚለውን ሀሳቡን ያለገደብ የሚያቀርብበት፣ ነፃ እንቅስቃሴ የሚያደርግበት መድረክ የሚፈጠርበት፣ ህዝብ ለማደራጀት፣ ቢሮ ለመከራየት፣ ፓርቲ ለማቋቋም መከራ የማይሆንበት ሁኔታዎች መመቻቸት ናቸው፡፡  
እኔ ኢህአዴግ ተቀይሮ ቢያሳፍረኝ ደስ ይለኛል። ግን የምሰጋው ተቃዋሚዎች አንድ ቅድመ ሁኔታ ያስቀምጡና፣ ኢህአዴግ ደግሞ በመቃብሬ ላይ ካልሆነ በሚለው ግትር አቋሙ ይፀናና፣ “ይኸው ተቃዋሚዎች ድሮም አጀንዳ ስለሌላቸው መወያየት አይፈልጉም” የሚል የፖለቲካ ጨዋታ ውስጥ ይገባል።
እንደኔ ይሄ ባይፈጠርና ለዚህች ሀገር የሚበጅ ነገር ከሁሉም ወገኖች ቢገኝ እመኛለሁ፡፡

==============================

‹‹ድርድሩ የፖለቲካ እስረኞችን ከመፍታት መጀመር አለበት››

ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለማርያም (ዓለማቀፍ የህግ ባለሙያ)


ድርድሩም ሆነ ውይይቱ በመጀመሪያ ዶ/ር መረራ ጉዲናን ጨምሮ የፖለቲካ እስረኞችን ከመፍታት መጀመር አለበት፡፡ ያኔ መነጋገር ይቻላል፡፡ ይህ እስካልተፈፀመ ድረስ ጅማሬውም እንኳ የሚያስደስት አይሆንም፡፡ ጉዳዩን በህዝብ ዘንድ እንዲታመን ለማድረግና እውነተኛ መሆኑን ለማረጋገጥ መጀመር ያለበት፣ የፖለቲካ እስረኞችን ከመፍታት ነው፡፡ ሌላው በሂደት በሚኖረው ውይይትና ድርድር ሊስተካከል ይችላል፡፡
የዚህ ድርድርና ውይይት ዋነኛ ውጤትም ከአንድ ፓርቲ አምባገነንነት ወደ መድበለ ፓርቲ የምንሸጋገርበትን መንገድ የሚያመቻችና የሚያፈላልግ መሆን አለበት፡፡ የድርድሩ ውጤት ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ከኢህአዴግ ጋር ስልጣን የሚጋሩበትን ሁኔታ እስከመፍጠር መሄድ አለበት፡፡ ህዝቡም በየቦታው ሲጠይቅ የነበረው ይሄንን ነው። የድርድሩ አልፋና ኦሜጋ መሆን ያለበት የስልጣን መጋራት ጉዳይ ነው፡፡
ይሄ ድርድር ፋይዳ የሚኖረው ዲሞክራሲ ሊያመጣ ከቻለ ብቻ ነው፡፡ ዲሞክራሲ ደግሞ በአንድ ፓርቲ አምባገነንነት ሊመጣ አይችልም። የተለያዩ ፓርቲዎች ያስፈልጋሉ፡፡ ዲሞክራሲ፣ ፍትህና እኩልነት ሳይኖር፤ ሙስና አጠፋለሁ፣ መልካም አስተዳደር አመጣለሁ ማለት ዘበት ነው። የድርድሩ የመጀመሪያና የመጨረሻ አላማ መሆን ያለበት ዲሞክራሲና ፍትህ መመስረት ነው፡፡
ኢህአዴግ የእውነት ጥልቅ ተሃድሶ የማድረግ ፍላጎት ካለው፣ ከላይ ያስቀመጥኩት ሃሳብ ሊፈፀም የማይችልበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ በአሸባሪነት የተፈረጁ ድርጅቶችም ሆኑ እዚህ ያሉ ፖለቲከኞች የስልጣን መጋራቱ ጉዳይ እንደሚያረካቸው እርግጠኛ ነኝ፡፡ ይሄ እስካልተደረገ ድረስ ግን ውይይቱ ህዝቡን የሚያስደስትና የሚያረጋጋ አይሆንም፤ የገባንበትንም ችግር ይፈታል ብዬ አላምንም፡፡ “አሸባሪ” የተባሉትም ቢሆን በዚህ የሚሣተፉበት ሁኔታ ተፈጥሮ  የሃገሪቱ ችግር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መቃለል አለበት፡፡ በዚህ ወቅት ኢህአዴግም ሆነ ሌላው ተቃዋሚ ሃገርን ከማዳን የበለጠ ምንም የከበደ ሃላፊነት የለባቸውም፡፡ በኢህአዴግ በኩል ሰፊ ፍቃደኝነት መኖር አለበት፤ በተቃዋሚዎችም እንደዚያው፡፡

Read 1705 times Last modified on Saturday, 28 January 2017 11:46