Monday, 30 January 2017 00:00

ከቅሌቶች- በጭልፋ

Written by  አሰፋ ጫቦ Dallas Texas USA
Rate this item
(3 votes)

    አማዞን ላይ ይህንን አዲሱን ቬፐር የሚሉትን ሲጋራ ማጨሻ፣ “$4.99 ለመላኪያ የሚሆን ክፈልና ውሰድ” የሚል አነበብኩና እንደተባለው አዘዝኩ። ለማዘዝ ሁሌ እንደሚደረገው የክሬዲት ካርድ (Credit Card) ቁጥር ሰጠሁ። ከሁለት ቀናት በኋላ “ለመላኪያ $2.99 እንደገና እንጨምራለን” አሉ። ገርሞኝ ለሁለት ብር አልሟገትም ብዬ አለፍኩት። ትላንትና ከባንኬ የተላከ ኢ-ሜይል  አገኘሁ። “አንድ Ecigs የሚባል ከሒሳብህ ላይ $99.99 ቆርጧልና ታውቀዋለህ ወይ?” የሚል ነው። “አውቀዋለሁ ግን ይህንን ገንዘብ ውሰድ አላልኩትም” ብዬ መለስኩኝ፣ “እኛም ጠርጥረን ክፍያውን አግደናል!” አሉ።
ያ ሳያንስ ዛሬ ገና በቅጡ ሳይነጋ ስልክ ተደውሎ፣ “ከFraud Investigation Department ነን” አለችኝ። Fraud ትርጉሙ አጭበርባሪ፤ አወናባጅና ሌላም ሌላም ማለት ይሆን?
“ምነው?” ስላት፣ “ሰሞኑን የተገበያየኸውን  አብረን እንድናይ ነው” ብላ የአንድ ሳምንቱን ግብይቴን ቆጠረችልኝና፤ “ይህ ሁሉ ያንተ ነው ወይ?” ስትለኝ ፤ የEcigs ልክ አለመሆኑን ነግሬ፤ “እኛም አውቀናል ጉድጓድ ምሰናል!” አይነት ብላ ገንዘቤ እንዳልተነካ ነገረችኝ፡፡
ከተጀመረ አይቀር ብዬ፣ ዛሬ ባንኩ ሔጄ፣ ያንን $2,99ኙንም አሰረዝኩ። “አንዴ ቁጥርህን ስለሚያውቁ ሊጠቀሙበት ይችላሉና አዲስ ካርድ ይሻልሃል!” ብላኝ ነባሩን በመቀስ ቆራርጣ ጣለችው። በቋፍ እንድንሔድ እያደረጉን እኮ ነው!!
******
ሌላው ቅሌት የዚህ የጋምቢያ ፕሬዚዳንት ጉዳይ ነው። አሁንማ “የነበረው!” ሆኗል፡፡
ቢሊዮን አመት እነግሳለሁ ብሎም ነበር አሉ። ብቻ ቢሊዮኑ ሲመነዘር፣ ወደ 20 ምናምን አመት ሆነ። ምርጫ ተደረገና፣ “መሸነፌን ተቀብያለሁ!” አለ። በማግስቱ፣ “አልተቀበልኩምና እንደገና ይቆጠርልኝ!” አለ።
በዚያ ማግስት ይሁን እንዲያ ፓርላማ የሚለውን ጠራና፣ “ነገሩ እስኪጣራ 3 ወር ተጨማሪ ጊዜ ሰጥተነዋል!” አለ፤ፓርላማው።
ነገሩ እንዲህ ሲጠነዛ የምእራብ አፍሪቃ ትብብር የሚባለው፣ “ወይ ውረድ፣ ወይ ወዮልህ!” አለና ወታደር ላከበት። “እወርዳለሁ ግን ቀን ስጡኝ” ብሎ ሶስት ቀን ተሰጥቶት፣ አሁን ተሳፍሮ አገር ለቆ ወጣ። ሥራውን ያውቃልና፣ የእጁን እንዳያገኝ መሆኑ ነው። ሶስቱን ተጨማሪ ቀን የፈለገው ወርቅ ፤ዶላርና ሌላም ያከማቸውን ከየተደበቀበት አውጥቶ ለመጫን ነበር።
“አፍሪቃዊ መሆኔ ያሳፍረኛል!”ለማለት ትንሽ ዳድቶኝ ነበር። ከዚያ ኢትዮጵያዊ መሆኔ፤ አፍሪቃዊ መሆኔ፤ ኢትዮጵያም ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ መሆንዋ ትዝ አለኝ።
“የኛው ጉድ!” ማለት ይሻላል ብዬ መሆን አለበት። “ምነው  እንደ ምእራብ አፍሪቃው፣ በምስራቅ አፍሪቃም ባለጠመንጃ ትብብር ቢኖር?” አሰኘኝ።
*****
ሌላው የዶናልድ ትራምፕ ቅሌት ነበር። ሰውዬው ቅሌታም መሆኑን አንድም ቀን ክዶና አስተባብሎ አያውቅም። ባይሆን በላይ በላዩ ይጨምርበታል እንጂ።
የትራምፕ ቃል አቀባይ በመጀመሪያ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ “የትራምፕን መመረቅ ለማየት የወጣው ሕዝብ ብዛት እስከ ዛሬ ተሰምቶም ታይቶም አያውቅም” አለ። ጋዜጦችና መገናኛ ዘዴዎች ሁሉ የሕዝቡን ብዛት ከኦባማ ጋር በማነጻጸር፣ አውጥተውት የነበረውን በምስል የተደገፈ መረጃ  አወገዘ። ውሸት ነው አለ።
በነጋታው የትራምፕ አዲስ ሹም የሆነችን ሴት፣ አንድ ጋዜጠኛ ቴሌቪዥን ላይ አፋጠጣት።
“ይህንን በማስረጃ የተደገፈ እውነት እንዴት ትክዳላችሁ?” ሲላት፣ “እናንተ የምታዩት እውነትና እኛ የምናየው እውነት ይለያያል!” አለች። ሲተረጎም፤ “እውነት የሚባል ነገር የለምና እንደ ተርጓሚው ነው!” ማለትዋ ነው መሰለኝ።
ሌላው በምስል የተደገፈ ቅሌት፣ ትራምፕና ሚስቱ ሥልጣን ሊረከቡ ሲመጡ፤ አባማና ሚሼል ደረጃ ላይ ሆነው ሲጠብቋቸው የሆነው ነው። ትራምፕ ከመኪና ይወርድና ሚስቱን ዞር ብሎ እንኳን ሳያያት ደረጃውን ይወጣል። ቆይታ ተከትላው ትወጣለች።
ያኔም አልተቀበላትም። ከዚያ ለሚሼል ያመጣችውን ስጦታ ስትሰጥ አባማ ይረዳታል። ሰውየው የሚዘረጠጥው ሴት በጠቅላላውን ብቻ ሳይሆን የገዛ ሚስቱንም የሚያከብር አይመስልም።
ከዚያ ትራምፕና ባለቤቱ ግብዣ ላይ ሲደንሱ የሚያሳይ ፊልም አየሁ። ተዋደው ተጋብተው ሳይሆን ፖሊስ አስገድዷቸው የመጡ የሚመስል ነገር አለው።
ከቅሌትና አወናባጅ ይሠውረን!

Read 2692 times