Monday, 30 January 2017 00:00

“እናንተንም እግዜአብሔር ያጥናችሁ!”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(5 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እኚህ ትረምፕ ስለሚባሉት ሰውዬ ሁለት ሰዎች ሲያወሩ ምን ተባባሉ መሰላችሁ፤
“በዶናልድ ትረምፕና በእግዚአብሔር መካከል ያለው ልዩነት ምንድነው?”
“እግዚአብሔር ዶናልድ ትረምፕ ነኝ ብሎ አያስብም፡፡”
የምር ግን አንዳንዴ ሰውየውንና ዙሪያቸውን ያሉትን ሰዎች ስሰማቸው…አለ አይደል…እንትን የሚባል የአፍሪካ አገር መንግሥት የገለበጡ አሥር አለቆችና፣ ‘ሰርጃ ማጆሮች’ ይመስሉኛል። ብቻ እኛ ምን አገባን…ትዊተር ላይ ‘ምን በምን ይስቃል’ ብለው እንዳይተርቱብን! ቂ…ቂ…ቂ…
እኔ የምለው… ‘ቶክ’ አልበዘባችሁም! ልክ ነዋ…ሁሉም ነገር በ‘ቶክ’ ተጀምሮ በ‘ቶክ’ እያለቀ ሳህናችን ላይ ያለውን ጎመን መጠኑን ጨመር ከማድረግ ይልቅ ሌላ ‘ረከስ የሚል’ አትክልት ልናጠያይቅ ምንም አልቀረን፡፡
ሀሳብ አለን… በያንዳንዷ ቀን የምንናገራቸው ቃላት ብዛት ኮታ ይሰጠንማ! ከዛ በኋላ… አለ አይደል…
“አንድ ትርፍ ቃል ለተናገረ አስር ብር... ሁለት ቃላት ለተናገረ ሀያ አምስት ብር…” ምናምን ቢባል ትንሽ እናርፍ ነበር፡፡ የምር ግን እንዲህ ቢሆን ኖሮ ስንታችን ኪሳራ እንደምንገባ አስቡትማ!… ልክ ነዋ፣ “በላብህ ጥረህ ግረህ ብላ…” ተባለ እንጂ “በምላስህ ጥረህ ግረህ ብላ…” አልተባለም! ቂ…ቂ..ቂ…
‘የህይወት ተልእኳቸው’ በተገኙበት ስብሰባ ላይ ሁሉ ለሃያና ሠላሳ ደቂቃ ‘ሀሳብ መስጠት’ የሆኑ ሰዎች አያሳዝኑም! ለነገሩ… አለ አይደል…ስብሰባዎች ላይ ትርፍ ቃል መናገር ብሎ ነገር አይሠራማ! አሀ…ብዙ ስብሰባዎች ራሳቸው ‘ትርፍ’ ናቸዋ!  ቂ…ቂ…ቂ...
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…በአንድ የአገራችን ክፍል የሆነ ነገር ስሙልኝማ፡፡ አንድ አካባቢ የሆነ ሰው ቤት ሀዘን ካለ፣ ትውውቅ ባይኖር እንኳን ጎራ ብሎ ማጽናናት የተለመደ ባህል ነው፡፡ እናላችሁ… ሰውዬው ጧት ረፋድ ላይ ወደ ጉዳያቸው እየሄዱ ሳለ አንድ ዳስ ቢጤ ነገር ውስጥ በርካታ ሰዎች ተሰብስበው ቡና ይጠጣሉ፡፡ እሳቸውም መቼም ሀዘን ቤት ተራምጄ አልሄድም ይሉና ገብተው ተጣበው ይቀመጣሉ፡፡
ታዲያላችሁ…ቡና ቀርቦላቸው ይጠጡና ብድግ ብለው… “እግዚአብሔር ያጥናችሁ!” ብለው መውጣት ይጀምራሉ፡፡
ይሄኔ ከጀርባቸው አንዲት ልጅ … “አባባ! አባባ!” እያለች ከተል ትላለች፡፡ እሳቸውም ምን ተፈጠረ ብለው ቆም ይላሉ፡፡
“ምነው ልጄ፣ ደህናም አይደል!”
“አባባ ይከፈላል…”
“ለምኑ ነው የሚከፈለው?”
“አባባ፣ ለቡናው ይከፈላል…”
ሰውየው ይደነግጣሉ፡፡ ለምን አይደንግጡ…‘ለቅሶ ቤት’ ለተበላውና፣ ለተጠጣው ማስከፈል ከተጀመረ ከዚህ የባሰ ምን ጉድ ይመጣል!
“ልጄ ለቅሶ ቤት አይደለም እንዴ!”
“አባባ፣ ለቅሶ ቤት አይደለም፡ የጀበና ቡና መሸጫ ነው…”
“ይሄ ሁሉ ሰው በዚህ ሰዓት የተሰበሰበው ቡና ሊጠጣ ነው?”
“አዎ አባባ…”
እየተገረሙ ሂሳቡን ይከፍሉና ወደ ተሰበሰቡት ሰዎች ዘወር ብለው ምን ቢሉ ጥሩ ነው…
“እናንተንም እግዜአብሔር ያጥናችሁ!” ብለው ሄዱላችሁ፡፡
አሪፍ አይደል!  አሀ…በሥራ ሰዓት ወላ ጀበና ቡና፣ ወላ አረቢካ እየተባለ…እንዲህ ሆኖ ነው እንዴ መካከለኛ ገቢ የሚደረሰው!  ቂ…ቂ…ቂ…
ይቺን ነገር ብያት ከሆነም ደገምኳት…እዚሁ አዲስ አበባ ያሉ አዛውንት ናቸው፡፡ እናላችሁ…አንድ ጓደኛቸው አንድ ቀን የሆነ ጀበና ቤት ነገር “ና ቡና እንጠጣ…” ይሏቸዋል፡፡
እሳቸውም… “እዚህ!” ይላሉ፡፡
ጋባዡም… “አዎ፡፡ አንድ፣ አንድ ስኒ ብለን እንሄዳለን…”
ይሄኔ አዛንውቱ ምን ቢሉ ጥሩ ነው… “እኔ ዱርዬ ቡና አልጠጣም…”  ቂ…ቂ…ቂ… አሀ… ለእሳቸው ቡና በአደባባይ፣ በአውላላ ሜዳ ላይ ይሆናል ብለው አስበውትም የማያውቁት ነዋ!
እናላችሁ…በሥራ ሰዓት ትከሻ ለትከሻ ገጥመው ቡናቸውን ሲጠጡ… “እናንተንም እግዜአብሔር ያጥናችሁ!” እንደተባሉት ሰዎች… አለ አይደል… እኛንም፣ “እግዜአብሔር ያጥናችሁ!” የሚያስብሉን መአት ነገሮች አሉ፡፡
ታዲያላችሁ… ‘የሞኝ ዘፈን ሁልጊዜ አበባዬ’ እንደሚባለው በሆነ፣ ባልሆነው አሁንም ‘ትናንትን’ እያነሳን አጉራህ ጠናኝ የምንል “እናንተንም እግዜአብሔር ያጥናችሁ!”  ልንባል የምንገባ አለን፡፡ የምር ግን… በ‘ሪዋይንድ’ ስናስብ ለምን ‘ክፉ፣ ክፉውን’… ወይም በራሳችን መመዘኛ “ክፉ” የምንለውን ብቻ እንደምናነሳ አይገርማችሁም!
ለምንድነው ደግ ደጉን የማያሳስበን! አለ አይደል…
“ያኔ እንደዛ አይነት ችግር ገጥሞኝ የደረስክልኝን አልረሳውም…”
“ያን ጊዜ አንቺ ባትኖሪልኝ ኖሮ እኮ ጉድ ሆኜ እዚህም አልደርስም ነበር…”
አይነት…ነገሮች በብዛት የምንሰማበትን ጊዜ እስኪመጣ ድረስ ያው “እናንተንም እግዜአብሔር ያጥናችሁ!” እንጂ ሌላ ምን እንባላለን!
“የአንተ አያቶች የእኔን አያቶች እንዲህ አድርገው…”
“ያኔ ዘመድ የለውም ብቸኛ ነው ብለሽ አውላላ ሜዳ ላይ የጣልሽኝን የምረሳው መሰለሽ!”
“እናንተ ውስኪ ስትጠጡ ለእኔ ድራፍት ስታዙ የነበረውን ረሳችሁት እንዴ!”
“የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳም…”
አይነት ነገር አልለቅ ካለን… “እናንተንም እግዜአብሔር ያጥናችሁ!” እንጂ ሌላ ምን እንባላለን!
የምር ግን… ሌላ አገር እኮ ተከታክቶም፣ ምን ተባብሎም ይበቃውና ያለፈውን ለታሪክ ትቶ ስለ ዛሬ፣ ስለ ነገ ይጨነቃል፡፡ እኛ ዘንድ ግን አሁንም ድረስ….
“ድሮ እንዲህ አድርጋችሁን…”
“የዛሬ አርባ ምናምን ዓመት ባለስልጣን ዘመድ አለን ብላችሁ አጥራችሁን አስር ሳንቲ ሜትር ወደ እኛ ግቢ የገፋችሁትን የምንረሳ መሰላችሁ!…” አይነት ብል የበላው ዶሴ እያወጡ አቧራ ለማራገፍ መከራችንን የምናይ ሰዎች፣ “እናንተንም እግዜአብሔር ያጥናችሁ!” እንጂ ሌላ ምን እንባላለን!
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ለምሳሌ አንዳንዱ እንትና ትምህርት ቤት ስምንተኛ ክፍል ተማሪ ሳለ የተነጠቀችው ‘ጀርሉ’ ትዝ እያለችው ቂም ቋጥሮ ይኖራል። አሀ…እሱ ‘ሲንከረፈፍ’ የልብ ጓደኛየው ‘ባዳ’ ሰው ከሚወስዳት ብሎ ተተካ፣ አራት ነጥብ፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…፡፡ (“ፒሪየድ!” አይደል ያሉት የአዲሱ የዓላማችን ‘ገዢ’ ቃል አቀባይ!) እናላችሁ… የስምንተኛ ክፍል እንትናዬ ነገር…እሱ ሲንከረፈፍ ያስወሰዳትን ሦስትና አራት አስርት ዓመታት ቆይቶ “የአንተን ጭካኔ እኮ ያወቅሁት ያኔ እሷን ስትነጥቀኝ ነው…” ምናምን ሲል አሪፍ አይደለም፡፡ አይደለም እንትናዬ… በመካከል አማሪካን እንኳን አምስት ነው ሰባት ፕሬዝዳንት ለዋውጣለች! እናላችሁ… ‘ኤጅ’ አምስትና ስድስት አስርት ዓመታት ‘እየተንደረደረ’፣ ስምንተኛ ክፍል ስለተነጠቅናት እንትናዬ አሁንም ቂም የያዝን ሰዎች “እናንተንም እግዜአብሔር ያጥናችሁ!” እንጂ ሌላ ምን እንባላለን!
ስሙኝማ…“እናንተንም እግዜአብሔር ያጥናችሁ!” የሚሏት ነገር…አለ አይደል…በሆነ ቀን እንመለስባታለን እንጂ በዚችማ አናበቃም። ደግሞላችሁ…እስከዛ ድረስ የአማሪካኑ ሰውዬ ምን እንደሚያመጡ አይታወቅም  ቂ…ቂ…ቂ…
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 4553 times