Saturday, 17 March 2012 09:57

“ዘ ሃንገር ጌምስ” ከፍተኛ ገቢ ያስገባል ተባለ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

ከሳምንት በፊት በተወሰኑ የዓለም ክፍሎች ለእይታ የበቃው “ዘ ሃንገር ጌምስ” ቀደም ሲል “ትዋይላይት” እና “ሃሪፖተር” ፊልሞች ያስገቡትን ከፍተኛ የገቢ መጠን ያህል ሊያስገባ እንደሚችል “ሎስአንጀለስ ታይምስ” አመለከተ፡፡ ከሳምንት በኋላ በሌሎች ተጨማሪ የዓለም ሲኒማዎች ለእይታ የሚበቃው “ዘ ሃንገር ጌምስ”፤ ባለፈው ሳምንት 70 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማስገባቱ ታውቋል፡፡ በሚቀጥለው ሳምንት የፊልሙ ገቢ ከ100 ሚሊዮን ዶላር ሊያልፍ እንደሚችልም ተገምቷል፡፡ በዲዝኒ ኩባንያ በ78 ሚሊዮን ዶላር በጀት የተሰራው ፊልሙ፤ በታዳጊዎች ዘንድ እጅግ ተወዳጅ በሆነው የሱዛን ኮሊንስ የልብ ወለድ መፅሃፍ ላይ ተንተርሶ እንደተሰራ ሲታወቅ መፅሃፉ በአሜሪካ ብቻ ከ24 ሚሊዮን በላይ ቅጂዎች እንደተሸጠ ይታወቃል፡፡

በሌላ በኩል በዋልት ዲዝኒ ፒክቸርስ የተሰራው “ጆን ካርተር” የተባለ የሳይንሳዊ ልቦለድ ፊልም ከፍተኛ በጀት ወጥቶበት ቢሰራም ለኪሳራ ሊዳረግ ይችላል ተባለ፡፡ ፊልሙን ለመስራት እና ለማስተዋወቅ 350 ሚሊዮን ዶላር ወጭ መደረጉን ያመለከተው “ዘ ሆሊውድ ሪፖርተር”፤ የመጀመርያ ሳምንት ገቢው 100 ሚሊዮን ዶላር እንደነበር ዘግቧል፡፡ ፊልሙ የሰው ልጅ ማርስን ለመጀመርያ ጊዜ ሲረግጥ በፕላኔቷ ፍጡራን የሚደርስበትን ጥቃት የሚያሳይ እንደሆነ ታውቋል፡፡ በከፍተኛ በጀትና የጥራት ደረጃ የተሰራው “ጆን ካርተር”፤ ከ600 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ያስገባል ተብሎ ተጠብቆ ነበር፡፡ ፊልሙ ሰሞኑን ለእይታ ሲበቃ ግን የተጠበቀውን ገቢ ሳያስገኝ በመቅረቱ ምናልባትም እስከ 165 ሚሊዮን ዶላር ሊያከስር ይችላል ብለዋል - የዎልስትሪት ኢኮኖሚስቶች፡፡

 

 

Read 2902 times Last modified on Saturday, 17 March 2012 10:01