Tuesday, 24 January 2017 15:41

ይድረስ ለእግዚአብሔር!

Written by  ድርሰት- ጅ. ኤል. ፉዌንቴስ ትርጉም - ተፈራ ተክሉ
Rate this item
(8 votes)

    ቤቱ ዝቅ ባለው ኮረብታ ጫፍ ላይ ይገኛል፡፡ ከዚህ ከፍታ ላይ ሆኖ አንድ ሰው ወንዙን፣ የጥሩ አዝመራ ወቅት ተስፋን የሰነቀውን የደረሰ የበቆሎ ማሳና አልፎ አልፎ የበቀሉትን አበቦች ሊመለከት ይችላል፡፡ መሬቱ የሚያስፈልገው ብቸኛው ነገር ዝናብ ነበር፤ ቢያንስ ደግሞ ካፊያ፡፡ ማሳውን ጠንቅቆ የሚያውቀው ሌንቾ፣ ጥዋቱን በሙሉ ምንም አልሰራም፤ ከወደ ሰሜን ምስራቅ በኩል ያለውን ሰማይ ሲቃኝ ነው የዋለው፡፡.
“አሁን ጥቂት ውሃ ልናገኝ ነው፤ ሴትዮ”
“አዎ፤ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ” መለሱ እራት በማዘጋጀት ላይ የነበሩት ባለቤታቸው፡፡     
ሴትየዋ፤ “እራት ደርሷል” ብለው ሲጣሩ፣ ትልልቆቹ ልጆች ማሳው ውስጥ እየሰሩ ነበር፡፡ ትንንሾቹ ደግሞ ቤታቸው አቅራቢያ እየተጫወቱ።
ሌንቾ እንደገመተው እራት እየበሉ ሳለ፣ ሀይለኛ ዝናብ መጣል ጀመረ፡፡ ከወደ ሰሜን ምስራቅ ትልቅ የጉም ተራራ እየተቃረበ እንደነበር ይታያል። አየሩ ንጹህና ደስ የሚል ነበር፡፡ ሰውየው ዝናቡ ገላውን ሲነካው የሚሰጠውን ደስታ ለማጣጣም ሲል ብቻ የሆነ ነገር ለመፈለግ ወደ በረቱ ሄደ። ሲመለስም በደስታ እየተፍነከነከ እንዲህ አለ፡-
“እነዚህ ከሰማይ የሚወርዱ የዝናብ ጠብታዎች አይደሉም፤ አዳዲስ ሳንቲሞች ናቸው፡፡ ትልልቆቹ ጠብታዎች ባለ አስር-ሳንቲም ሽርፍራፊዎች ሲሆኑ ትንንሾቹ ደግሞ ባለ አምስት ናቸው”
የደረሰውን የበቆሎ ማሳና የዝናብ መጋረጃ የተከናነቡትን አበባዎች፣ እርካታን ተላብሶ በጥንቃቄ ተመለከታቸው፡፡ ነገር ግን በድንገት ጠንከር ያለ ነፋስ መንፈስ ያዘ፤ ከዝናቡም ጋር በጣም ትልልቅ በረዶ ይወርድ ጀመረ፡፡ እነዚህ በእርግጥም አዳዲስ የብር ሳንቲሞች ይመስሉ ነበር፡፡ ልጆቹ በዝናብ እየተደበደቡ፣ የረጉ ሉሎቹን ለመሰብሰብ ተሯሯጡ።
“አሁን እየከፋ ሄደ” አለ ሰውዬው ጮክ ብሎ፤ ድንጋጤ ይነበብበታል፡፡ “ቶሎ ያልፋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ”
ሆኖም ቶሎ አላለፈም፡፡ በረዶው በቤቱ፣ በአትክልት ቦታው፣ በኮረብታው ቁልቁለት፣ በበቆሎው ማሳ ላይና በመላው መንደር ለአንድ ሰዓት ዘነበ፡፡ መስኩ በጨው እንደተሸፈነ ሁሉ ነጭ ለብሷል፡፡ አንድም ቅጠል ከዛፎቹ ላይ አልቀረም፡፡ በቆሎው ሙሉ ለሙሉ ወድሟል። በተክሎቹ ላይ የነበሩት አበቦች ረግፈዋል፡፡ የሌንቾ ነፍስ በሐዘን ተሞልታለች፡፡ በበረዶ ውርጅብኝ የታጀበው ሀይለኛ ዝናብ ካለፈ በኋላ፣ በመስኩ መሀል ቆሞ ለልጆቹ እንዲህ አላቸው፡-
“የአንበጣ መንጋ ከዚህ የተሻለ ሊያስተርፍ ይችል ነበር፡፡ በረዶው ምንም አላስተረፈም፡፡ በዚህ ዓመት ምንም በቆሎ አይኖረንም”
 ምሽቱ በጣም አሳዛኝ ነበር፡፡
“ያ ሁሉ ሥራችን፣ ከንቱ ሆነ! ሊረዳን የሚችል አንድም ሰው የለም! በዚህ ዓመት ሁላችንም መራባችን ነው!”
ነገር ግን በዚያ በሸለቆው መሀል በሚገኘው ብቸኛ ቤት ውስጥ ይኖሩ በነበሩ ሁሉም ሰዎች ልብ ውስጥ አንድ ብቸኛ ተስፋ ነበር፤ የእግዚአብሔር እርዳታ፡፡
“ምንም እንኳን ተስፋ የሌለው ኪሳራ ቢመስልም፣ መበሳጨት የለብህም፡፡ አስታውስ፤ ማንም በረሃብ አይሞትም!”
“እንደዚያ ነው የሚሉት፤ ማንም በረሃብ አይሞትም!”
ሌሊቱን በሙሉ ሌንቾ ስለ ብቸኛው ተስፋው እያሰበ ነበር፤ የእግዚአብሔር እርዳታ፤ ዐይኖቹ (በተሰጠው ትምህርት መሠረት) ሁሉን ነገር ያያሉ፤ በአንድ ሰው ጥልቅ ህሊና ውስጥ እንኳን ያለውን ሁሉ፡፡
ሌንቾ በእርሻ መስኩ ላይ ሳይሰለች እንደ በሬ ነበር የሚሰራው፤ እንዲያም ሆኖ መጻፍም ይችል ነበር። በቀጣዩ እሁድ ንጋት ላይ፣ ጠባቂ መንፈስ እንዳለ ልቡን ካሳመነ በኋላ፣ ፖስታ ቤት የሚያስገባው ደብዳቤ መጻፍ ጀመረ፡፡ ተራ ደብዳቤም አልነበረም፤ ለእግዚአብሔር የተጻፈ ደብዳቤ ነው፡፡   
“እግዚአብሔር፤” ሲል ጀመረ፤ “እርዳታህን ካልለገስከኝ፣ እኔና ቤተሰቦቼ በዚህ ዓመት መራባችን ነው፡፡ በእርሻ መስኬ ላይ እንደገና ለመዝራትና ሰብሉ እስኪደርስ መቆያ የሚሆነን መቶ ፔሶዎች ያስፈልገኛል፤ ምክንያቱም በረዶው…”
በፖስታው ላይ፤ “ለእግዚአብሔር” ብሎ ጻፈ፡፡ ከዚያም ደብዳቤውን ፖስታው ውስጥ አስገብቶ፣ እርብሽብሽ እንዳለ ወደ ከተማ ሄደ። ከፖስታ ቤቱም ቴምብር ገዝቶ ከለጠፈበት በኋላ፣ የፖስታ ሳጥኑ ውስጥ ጨመረው፡፡
ከፖስታ ቤት ሰራተኞች መካከል አንዱ ከልቡ እየሳቀ፣ ወደ አለቃው ሄዶ፣ ለእግዚአብሔር የተጻፈውን ደብዳቤ አሳየው፡፡ በፖስተኝነት የሥራ ዘመኑ፣ ያንን አድራሻ በፍጹም አያውቀውም፡፡ ደንደን ያለውና ተወዳጁ የፖስታ ቤቱ ሹምም በሳቅ ተንከተከተ፡፡ ግን ብዙ አልቆየም፡፡ ከመቅጽበት ኮስተር ብሎ፣ ዴስኩ ላይ የነበረችውን ደብዳቤ እየነካካ እንዲህ አለ፡-
“እንዴት ዓይነት እምነት ነው! ይህንን ደብዳቤ የጻፈው ሰው ዓይነት፣ እምነት ቢኖረኝ ምኞቴ ነበር። እሱ እንደሚያምነው ማመን፡፡ በሙሉ ልብ ተስፋ ማድረግ፡፡ እሱ እንዴት ተስፋ ማድረግ እንዳለበት በተረዳበት መልኩ፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ደብዳቤ መጻጻፍ መጀመር!”
ጸሓፊው በእግዚአብሔር ላይ ያለውን እምነት ላለመነቅነቅ፣ የፖስታ ቤቱ ሹም አንድ ሐሳብ አመነጨ፡፡ የመልስ ደብዳቤ መጻፍ። ደብዳቤውን ከፍቶ መልእክቱን ሲያነብ ግን መልሱን ለመጻፍ ከቅንነት፣ ከብዕርና ወረቀት በላይ እንደሚያስፈልገው ግልጽ ነበር፡፡ ነገር ግን በቃሉ ጸና፤ ከሥራ ባልደረቦቹ ገንዘብ አሰባሰበ፣ ራሱም ከደሞዙ ላይ ቀንሶ ሰጠ፣ ብዙ ጓደኞቹም ጥቂት ለመለገስ ተገደዱ፡፡
መቶ ፔሶዎች ማሰባሰብ አልቻለም፤ ስለዚህ ለገበሬው ከግማሹ ትንሽ ከፍ ያለ ሊልክለት ቻለ። የገንዘብ ኖቶቹን ፖስታ  ውስጥ ጨምሮ የሌንቾን አድራሻ ከጻፈ በኋላ፣ ከላይ በፊርማ መልክ አንድ ቃል ብቻ ጻፈበት፡- እግዚአብሔር፡፡   
በሚቀጥለው እሁድ ሌንቾ ከተለመደው ቀደም ብሎ ወደ ፖስታ ቤቱ ሄዶ ደብዳቤ እንደመጣለት ጠየቀ፡፡ ራሱ የፖስታ ቤቱ ሹም ነበር ደብዳቤውን የሰጠው፡ አንድ የተቀደሰ ነገር በመፈጸሙ እርካታ እየተሰማው፣ መውጫው አካባቢ ሆኖ ይመለከተው ጀመር፡፡
ሌንቾ የገንዘብ ኖቶቹን ሲመለከት ቅንጣት ታክል እንኳን አልገረመውም፡፡ ልበ ሙሉነት ይነበብበት ነበር፡፡ ገንዘቡን ሲቆጥረው ግን በጣም ተናደደ። እግዚአብሔር ተሳስቶ ሊሆን አይችልም፤ ሌንቾ የጠየቀውንም ሊነሳው አይችልም!
ወዲያው ሌንቾ ወደ መስኮቱ ጠጋ ብሎ ወረቀትና ብዕር እንዲሰጡት ጠየቀ፡፡ ወደ ጠረጴዛው በመሄድም መጻፍ ጀመረ፡፡ ሐሳቦቹን ለመግለጽ በሚያደርገው ጥረት፣ግንባሩ ቋጠር ፈታ ይላል። ሲጨርስ ወደ መስኮቱ ተመልሶ ቴምብር ገዛና፣ በምላሱ ላስ ላስ አድርጎት፣ በፖስታው ላይ ከለጠፈው በኋላ በእጁ መታ መታ አደረገው፡፡
ደብዳቤውን ማጠራቀሚያ ሳጥኑ ውስጥ ጣል ባደረገበት ቅጽበት፣ የፖስታ ቤቱ ሹም አውጥቶ ከፈተው፡፡
እንዲህ ይላል፡-
“እግዚአብሔር፤ ከጠየቅሁት ገንዘብ የደረሰኝ ሰባ ፔሶዎች ብቻ ናቸው፡፡ እጅግ በጣም ስለምፈልገው ቀሪውን ላክልኝ፡፡ ነገር ግን በፖስታ ቤት እንዳትልክልኝ፤ ምክንያቱም የፖስታ ቤቱ ሠራተኞች አጭበርባሪዎች ናቸው፡፡ ሌንቾ”

Read 2782 times