Tuesday, 24 January 2017 15:22

“ሙጋቤ በጥቅምት ይሞታሉ” ሲል የተነበየው ፓስተር ታሰረ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 “የ92 አመቱ የዚምባቡዌ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ፣ በመጪው ጥቅምት ወር አጋማሽ እንደሚሞቱ ፈጣሪ አምላክ ነግሮኛል፣ ከዚያች ቀን አያልፉም” በማለት በአደባባይ ትንቢት የተናገረ አንድ የአገሪቱ ፓስተር፤ “በታላቁ መሪ ላይ አሟርተሃል” በሚል መታሰሩን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
ፓትሪክ ሙጋድዛ የተባለው ፓስተሩ ባለፈው ሳምንት በተናገረው ትንቢት፣” ሙጋቤ ጥቅምት 17 ቀን ከዚህ አለም በሞት እንደሚለዩ ፈጣሪ ነግሮኛል” ማለቱን የጠቆመው ዘገባው፤ የፓስተሩ ጠበቃም፣ “ጉዳዩን የያዙት መርማሪ ፖሊሶች፣ ፈጣሪ ለፓስተሩ ይህንን ነገር አለመናገሩን የሚያረጋግጡበት መንገድ ስለሌለ ደንበኛዬን ተጠያቂ ማድረግ አይችሉም” ሲሉ መከራከራቸውን ገልጧል፡፡
ፓስተሩ ከትንቢቱ በተጨማሪ “የአገሪቱን ሰንደቅ ዓላማ ለብሰሃል” በሚል ተከሶ ፍርድ ቤት ቀርቦ እንደነበር ዘገባው አስታውሷል፡፡ ሮበርት ሙጋቤ በተደጋጋሚ ለህልፈተ ህይወት ተዳርገዋል የሚሉ ሀሜቶች ሲነዙባቸው እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፤ እሳቸው ግን “ከእየሱስ ክርስቶስ ይልቅ እኔ በተደጋጋሚ ሞቼ ተነስቻለሁ” በማለት፣ መሰል ሀሜቶችን በማሾፍ ሲያጣጥሏቸው መደመጣቸውን ገልጧል፡፡

Read 2172 times