Tuesday, 24 January 2017 15:16

ስታድዬምና የስፖርት ማእከሉን ምን ልዩ ያደርገዋል?

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(3 votes)

 የስታድዬሙ ሜዳ የተፈጥሮ ሳር ተተክሎለታል። በባየር ሙኒኩ ስታድዬም አሊያንዝ አሬና አምሳያነት የተሰራው የመጫወቻ ሜዳው በፍፁም ውሃ የማይቋጥር ነው፡፡ ሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ በግንባታው ፈርቀዳጅ ሆኖ ተግባራዊ ባደረገው የጂኦ ቴክስታይል ቴክኖሎጂ አማካኝነት ሲሆን ከሜዳው ስር የተቀበሩ ቱቦዎች ውሃ የሚመጡ እና ባእድ ነገሮችን የሚያስወግዱ በመሆናቸው ነው፡፡ ይህ ዘመናዊ ሜዳ በዙሪያው የዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (አይኤኤኤፍ) ደረጃ የጠበቁ በአንድ ጊዜ ስምንት ተወዳዳሪዎችን ማስተናገድ የሚችል የመሮጫ መም (ትራክ) የተሰራለት ነው፡፡
በምሽት ጨዋታዎችን በሙሉ የመብራት አገልግሎት ማካሄድ የሚቻልበት ይሆናል፡፡ ጎን ለጎን ስድስት ስድስት ሆነው በስታድዬሙ ጣሪያ ዙርያ  156 የመብራት ባውዛዎች ስለተገጠሙለት ነው፡፡ በተጨማሪም ስታድዬሙ  የምሽት ጨዋታዎችን ሲያስተናግድ ለቴሌቪዥንና መሰል አገልግሎቶች ጭምር የሚውል በቂ የኤሌክትሪክ ብርሃን ያለው ሲሆን ዘመናዊ የውጤት መግለጫ ስኮር ቦርድ የተገጠመለትና 11 ድምፅ ማጉያዎች ዙርያውን ተተክሎለታል፡፡
በአንድ ጊዜ የአራት ቡድን ተጨዋቾች እና የሁለት ጨዋታዎች ሙሉ የዳኞች ቡድኖችን ያስተናግዳል፡፡ ክፍሎቹ የመመካከርያ፤ የልብስና የጫማ ማስቀመጫ፤ መፀዳጃ ቤቶች እንዲሁም በአንድ ግዜ እስከ 1ሺ ሊትር ውሃ ማሞቅ የሚችል መሳርያ የተገጠመላቸው የገላ መታጠቢያዎችን ያካተቱ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ለአራት ቡድኖች ለእያንዳንዳቸው 12 በጠቅላላው 48 የልብስ መቀየሪያ ክፍሎች (ሎከሮች)፣ ለእያንዳንዳቸው ስድስት ስድስት በጠቅላላው 24 የገላ መታጠቢያ ክፍሎች፣ የተጎዱ ተጨዋቾች የመጀመርያ ዕርዳታ የሚያገኙባቸው የነርስ፣ የሐኪም ቢሮ፣ የማሳጅና የፊዚዮ ቴራፒ ክፍሎች ከሁለት የመሰብሰቢያ አዳራሾች ጋር አሟልቶ ይዟል፡፡
ለኢትዮጰያ የስታድዬም መሰረተ ልማቶች ተምሳሌት የሚሆነው ደግሞ የሚድያ ትሪቢውኑ ነው። ስምንት ክፍሎች ናቸው፡፡ አንዱ ክፍል አሰልጣኞችና ተጨዋቾች ጋዜጣዊ መግለጫ ሊሰጡበት ያስችላል፡፡ ሌሎቹ የሚዲያ ክፍሎች የድምፅ መከላከያ ያላቸው እና ለሬደዮ እና ቴሌቭዥን የቀጥታ ስርጭቶች እንዲመቹ ሆነው ተሰርተዋል፡፡ ከእነዚህ ክፍሎች አንደኛው የቀጥታ ስርጭቶችን የሚያከናውኑ ጋዜጠኞች ከእንግዶቻቸው ጋር ሊሰሩበት ያስችላቸዋል። የቴሌፎንና የኢንተርኔት አገልግሎት ለእያንዳንዱ ክፍል የተዘጋጀ ሲሆን፤ በተጨማሪም የኔትወርክና የኢንተርኔት አገልግሎት ለመስጠት የሚያገለግሉ መስመሮች ተዘርግተውለታል፡፡ ይህም ስታዲየሙ የአገር ውስጥ፣ የአህጉርና ዓለም አቀፍ ውድድሮችን በሚያስተናግድበት ወቅት ጨዋታዎችን በሬዲዮና በቴሌቪዥን ለማስተላለፍ የሚቻልበት ያደርገዋል፡፡  
የተመልካች እና መግቢያ እና መውጫ የሆኑት 10 የስታድዬሙ በሮችም የተለየ ተምሳሌትነት አላቸው፡፡ በሮቹ ለእያንዳንዳቸው 5ሺ ሊትር ውሃ የሚይዙ ታንከሮች የሚገኙባቸው የእሳት አደጋ መከላከያዎች የተገጠመላቸው እና 7ቱ አምቡላንስ የሚያስገቡ ናቸው፡፡ የበሮቹ ስያሜዎች በወልድያ ዞን በሚገኙ ታሪካዊ ቦታዎች፤ የአካባቢ ስሞች፤ በስታድዬሙ የግንባታ ሂደት አስተዋፅኦ ባደረጉ ግለሰቦች ተሰይመዋል፡፡ የበሮቹን ስያሜዎች ያፀደቀው የወልዲያ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ሲሆን መርጦ፤ አረጋ ይርዳው፤ ዳና፤ ሙጋድ፤ ላልይበላ፤ ፀጋ አራጌ፤ ሳንቃ የተሰኙት ይገኙበታል፡፡
በስታዲየሙና የስፖርት ማዕከሉ  ዙሪያ ስምንት የትኬት መቁረጫ ክፍሎች፣ ለተለያየ የንግድ አገልግሎት የሚውሉ ሱቆች፣ ምግብ ቤቶችና ለመሰል ሥራ የሚውሉ ክፍሎች ተሟልተው ተገንብተዋል፡፡ 13 ካፍቴራዎች ይኖራሉ፡፡ አንደኛው በክቡር ትሪቡን የሚገኝ ዘመናዊ ካፍቴርያ ነው፡፡  በአንድ ጊዜ እስከ 270 ሜትር ኩብ ወይም 270,000 ሊትር ውኃ ለማጠራቀም የሚያስችሉ 36 ታንከሮችም ይገኛሉ፡፡ በስታድዬሙና ማዕከሉ ቅጥር ግቢ ለባንዲራ መስቀያ የሚሆኑ 32 ቋሚ ብረቶች የቆሙ ሲሆን፤ የሄሊኮፕተር ማረፊያ፤ ለ308 መኪኖች፣ ለ14 አውቶብሶችና ለ16 ብስክሌቶች የተሟላ ማቆሚያ ተዘጋጅቶበታል፡፡
ከስታድዬሙ በተያያዘ በስታድዬሙና ስፖርት ማእከሉ ቅጥር ግቢ አምስት ተያያዥ የስፖርት መሰረተ ልማቶችም ተገንብተዋል፡፡ እስከ 36 እንግዶችን የሚያስተናግደው የእንግዳ ማረፊያ የመጀመርያው ነው፡፡ የቅርጫት ኳስ፤ የእጅ ኳስ እና የመረብ ኳስ ሜዳዎችን ያቀፈ ሁለገብ የስፖርት መሰረተ ልማትም ይገኝበታል፡፡ ሁለት የሜዳ ቴኒስ መጫወቻ ሜዳዎች እና ዘመናዊ የመዋኛ ገንዳም አለ። ርዝመቱ 47 ሜትር ጎኑ 26 ሜትር የሆነው ይህ የተሟላ ሁለገብ የስፖርት ማዕከልና ማዘውተሪያ  የእጅ ኳስ፣ የመረብ ኳስ፣ የቅርጫት ኳስ ውድድሮችን በከፍተኛ ደረጃ ማስተናገድ የሚችል ነው፡፡ በተለይ የኦሊምፒክ ደረጃውን ጠብቆ ውድድሮችን ማከናወን የሚችል መጠኑ 25 ሜትር፣ ስፋቱ 50 ሜትር፣ ጥልቀቱ ደግሞ ከሁለት እስከ አምስት ሜትር የሚደርስ የመዋኛ ገንዳው በጣም የሚማርክ ነው፡፡ የመወርወርያ ማማ ያለው ገንዳው በአንድ ጊዜ ዘጠኝ ተወዳዳሪዎችን ማስተናገድ የሚችል ሲሆን፤ ያጠራቀመው ውኃ በሚቆሽሽበት ጊዜ ማጣራት የሚችል ቴክኖሎጂ የተገጠመለት፤ 50ሺ ሜትርኪውብ ውሃ የሚይዝ፤  18 የገላ መታጠቢያዎች፤ 6 መፀዳጃዎች እና 20 የልብስ መቀየርያዎች በዙርያው የሚገኙበት ነው፡፡ በግራና ቀኝ 1,000 ተመልካቾችን የሚያስቀምጡ አምስት ደረጃዎች ተሰርተውለታል፡፡

Read 2163 times