Sunday, 22 January 2017 00:00

የተጠያቂነት ሥርዓት ያለመኖር፣ ያመጣው ዕዳ!!

Written by  ያሬድ አውግቸው
Rate this item
(3 votes)

    ኢህአዴግና የሚመራው መንግስት፣ የተጠያቂነት ስርዓትን ፈጥሮ፣ ችግሮችን በዘላቂነት ከመፍታት ይልቅ ህዝባዊ ጥያቄዎች ወይም የውስጥ ልዩነቶች ሲነሱ፣ «ጊዜ ስጡን» አይነት መግለጫዎችን  ሲያወጣ ቆይቶአል፤ አሁንም ይህንኑ ልምዱን ቀጥሎበታል፡፡ ባለፉት 25 ዓመታት እራሱን ወይም የተወሰነ ክፍሉን የሚኮንንባቸው እንደ መበስበስ፣ ተደራጅ፣ ስልጣንን የግል ኑሮ ማመቻቻ ማድረግ፣ ሙስና፣ ብልሹ አሰራርና መሰል ባህርያትና ድርጊቶች፣ በድርጅቱና በሚያስተዳድረው መንግስታዊ መዋቅር ውስጥ  በአንድ ጀንበር  የሚሰፍሩ መንፈሶች  አይደሉም፤ በዝምታ ካልተበረታቱ። በእነዚህና መሰል የሹማምንቱ ባህርያትና ድርጊቶች አማካኝነት በተለይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያለው ህዝብ ከፍተኛ የኑሮ ቀውስ ውስጥ  ገብቷል። ከሚንረው የኑሮ ዋጋ ጋር ሊራመድ ያልቻለ፣ ገቢውን ለማስማማት ሰዎች በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ወቅት የሚይዟቸውን የአመጋገብና አኗኗር ዘይቤዎች ለመከተል ተገዷል። የብዙ አፍሪካ ሃገራት ህዝቦች ለምግብ መጨነቅ ባቆሙበት በአሁኑ ወቅት፣ 5/11 የተባለውን የአመጋገብ ዘይቤ መከተልን ጨምሮ ይዘታቸውና መጠናቸው የወረደ ምግቦችን ይመገባል፤  የነገ ኑሮውን  በመፍራት ስነልቦና ውስጥም  ይኖራል።   ብዙ ጥያቄዎች ወደ አዕምሮአችን መምጣታቸው አይቀርም። በኔ እምነት የእነዚህና ተመሳሳይ  ችግሮች ዋነኛ ምክንያት፣ የተጠያቂነት  ስርዓት በድርጅቱና በመንግስት ክንፎች ውስጥ  አለመተግበር ነው፡፡   
አስፈጻሚውን አካል ለመቆጣጠር ስልጣን የተሰጠው  የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ የሚገኙ የድርጅቱ አባላት፣  የድርጅቱን መሰረታዊ ፖሊሲዎች እንዲቃወሙ ባይጠበቅም   ውስንነት ያለባቸው ስትራቴጂዎች፣ እቅዶች፣ አፈጻጸሞችና ሹመቶች  እንዲስተካከሉ መተቸት፤ ሲብስም መቃወም ይጠበቅባቸዋል። በዚህ ኢህአዴግና አጋር ድርጅቶቹ  በተቆጣጠሩት የወቅቱ  ምክር ቤትም፣ ቢያንስ በጣት የሚቆጠር  ተቃውሞዎችና ድምጸ ተአቅቦዎች  መስማት እንፈልጋለን። ምክንያቱም አስፈጻሚው አካል  በቅጡ ያልታሹ፣ የይድረስ ይድረስ እቅዶችን ተግብሮ፣ ለብዙ ጊዜያት ደካማ አፈጻጸሞች አስመዝግቧልና። የእንፋሎት ሃይል ማመንጫና  የስኳር ልማት ፕሮጀክቶችን መጥቀስ ይቻላል። ጅማሬያቸው በተቃርኖ ተሞልቶ ከተገኘ፣ ለመጽደቅ ወደ ምክር ቤቶች ያልመጡ ስራዎችንም ቢሆን፣ አስፈጻሚውን ጠርቶ ማብራሪያ መጠየቅ ይገባል። ለምሳሌ  ገዥው ፓርቲ  ከህዝብ ጋር በቂ ውይይት  ሳላደርግ በመቅረቴ፣ ተከሰተ  ያለውን በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ አካባቢዎችን  ወደ ከተማዋ የማጠቃለል እቅድ፣ የሚቃወሙ ብጥብጦችን መጥቀስ ይቻላል።  ከህዝቡ ውስጥ ከወጡት ተወካዮች  በላይ የህዝቡን ፍላጎት የሚያውቅ ስለሌለ፣ ተመሳሳይ ችግሮች ከመከሰታቸው በፊት አስፈጻሚውን በመጥራት፣ የህዝቡን ፍላጎት እንደ አጀንዳ አቅርበው  መምከርም ሆነ ማስጠንቀቅ ይገባል።  
አስፈጻሚው አካልም ተጠያቂነት  ቢኖርበት፣  የአለማችን የዲሞክራሲ ስርዓት፣ በረጅም ጉዞው ሙስናንና በስልጣን መባለግን  በማያፈናፍን መልኩ እንዲከላከሉ ወደ ስራ ያመጣቸው ህጎች፣ አደረጃጀቶችና አሰራሮችን መከተል ይቻላል፡፡
ያን ጊዜ፤ “መረጃ አለን፤ ማስረጃ ግን  ስለሌለን ፍትህ ፊት  አቅርበን ሙሰኞችን ማስቀጣት አልቻልንም» የሚሉ ሰበቦች አይሰሩም፡፡ ምክንያቱም የሙስናና ብልሹ አሰራር መከላከልና መቆጣጠር ስርዓታችን ጠንካራ ቢሆን፣ በመጨረሻው ሰዓት መረጃ ለመፈለግ ከመሯሯጥ እንድን ነበር፤ ቁርጠኝነቱ ካለ።   በተለይ በአመራሩ አካባቢ የሚኖር ሙስናና የስልጣን ብልግናን፣ ከግለሰባዊነት በጸዱ ምህረት የለሽ ህጎች መቀነስ ይቻላል፡፡ እዚህ ላይ  ማስታወስ ያለብን፣ ዛሬ የተጠያቂነት ስርዓታቸው ጠንካራ ደረጃ ላይ የደረሰ ሃገሮች ከችግሮች ለመማር የተገደዱት፣ የቀደመ ተሞክሮ ባለመኖሩ ነበር። የነዚሁ ሃገሮች ከፍተኛ ባለስልጣናትና የፓርላማ አባላት፣ የብዕርን ያህል  ዋጋ ያላቸው ስጦታዎችን  እንኳን  እንዳይቀበሉ የህግ ክልከላ አለባቸው። ስጦታዎችን የግድ መቀበል ካለባቸውም፣ ለመንግስታቸው ማዕከላዊ ግምጃ ቤት ገቢ ይሆናሉ።
በአንድ ወቅት ቬትናም የምትባል የምስራቅ እስያ ሃገር የመሄድ እድል ነበረኝ።  የሶሻሊስቱን ጎራ መፍረስ ተከትሎ  የቅይጥ ኢኮኖሚ መሰል ስርዓት ለመከተል በቆረጠችው ቬትናም፤ የኮሚኒስት ፓርቲው  ነባር አመራሮች  የመንግስት ልማት ድርጅቶችን በእጅ አዙር  በመግዛት፣ ብዙዎቹ የተንደላቀቀ ኑሮ እንደሚመሩ  የሃገሬው አስጎብኚ ገልጾልኝ ነበር።  የፓርቲው አባላት ባላቸው ያለመጠየቅ ስነልቦናና መደላድል፣ ይመጣል ለሚሉት የካፒታሊስት ስርዓት፣ እራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን እያመቻቹ መሆኑን ነው ይህ ተሞክሮ የሚያሳየው። የተጠያቂነት ባህልን  ለማስፈን ያልፈለገ አስፈጻሚ አካል፣ እራሱን  ወደ ተገልጋይነት ማዞሩ የማይቀር ሀቅ ነው፡፡
በተመሳሳይ የሃገራችን ተቋማትም እንደሚሰጣቸው  ሃላፊነት ተጠያቂነት ቢኖርባቸው፣   የአለማችን   የቴክኖሎጂ ታሪክ፣  በብዙ ድካም ያፈለቃቸው የስራ አመራር እውቀቶችና ቴክኖሎጂዎች እየተገኙ፣» እያጠፋን እንማራለን» የሚል ቃና  ያላቸው መልሶችን አንሰማም ነበር።  ለምሳሌነት  በተገነቡ በጥቂት አመታት ውስጥ  ፈርሰው፣ የባቡር ሃዲድ እንዲዘረጋባቸው የተደረጉ በብዙ መቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ብር  የፈሰሰባቸው የአስፋልት መንገዶችን ማንሳት ይቻላል። በተጨማሪ ከተዘጋጁበት ደረጃ እጅግ የገዘፈ የአገልግሎት ፍላጎት አጋጥሟቸው፣ እየተደናበሩ ያሉ መንግስታዊ አገልግሎት ሰጭ ተቋሞቻችንንም እንዲሁ ተጠቃሽ ናቸው። ለምንስ  ተቋሞቻችን፣ ከተማችንና  መንግስታችን የነገን ፍላጎት  በስትራቴጂክ እቅዳቸው ማየት ተሳናቸው? ለምንስ እቅዶች በድንገት ብቅ ይላሉ? መልሱ፤ ህይወት ያለው  የተጠያቂነት ስርዓት ስለሌለ ነው። ተጠያቂነት በስራ ላይ ቢውል መጀመሪያውኑ የማይመጥኑ ወደ መድረኩ አይመጡም፤ አምልጠው  ከመጡም ይጠየቃሉ።
ለማጠቃለል፣ ቁርጠኝነቱ ካለ የተጠያቂነትን ስርዓት ማስፈን ቀላል ነው፤ የተደራጁ አለም አቀፍ ተሞክሮዎች ሞልተዋል፡፡ ስርዓቱ ደግሞ የፍትህ የበላይነትን ያረጋግጣል። በዚያ ቦታ  ዘረፋ፣ የመንግስት ስልጣንን ለግል ኑሮ ማደላደያ ማድረግና አውቅልሃለሁ አይነት ተግባራት አይታሰቡም፤ ከታሰቡም ዋጋ ያስከፍላሉ።

Read 2901 times