Sunday, 22 January 2017 00:00

አንጋፋ ፓርቲዎች በከሰሩበት ዘመን - የዶናልድ ትራምፕ በዓለ ሲመት

Written by  ዮሃንስ ሰ.
Rate this item
(3 votes)

    የዘንድሮው የአሜሪካ ምርጫ፣ ከቀድሞዎቹ ጋር ሲነፃፀር፣ “በጣም የወረደ ነው” ቢባልም፣ ከሌሎች አገራት ምርጫ ጋር ሲነፃፀር ግን፣... ግሩም ትንግርት ነበር። ያልሰከረ ጤናማ ሰው፣... የአሜሪካን ምርጫ አይቶ፣... ከመደመምና ከመቅናት  ‘አይድንም’። በአሜሪካ ፖለቲካ ባይቀና... በጣም በጣም ይገርማል።
የሆነ ሆኖ፣ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ለመሆን፣ ለሁለት ዓመታት የዘለቀው የተጧጧፈ የምርጫ ዘመቻ፣ ይሄውና... በዶናልድ ትራምፕ “በዓለ ሲመት”፣ ትናንት በሰላም፣ በስርዓትና በፌሽታ ተከብሯል። ያው... ጎን ለጎን፣ በተቃውሞ፣ በውዝግብና በቅሬታ እንደታጀበ። ድንቅ ነው።
“አይደንቅም” የሚል ካለም፣ “ቀረበት”። ግን በአንድ ነገር መስማማት የሚቻል ይመስለኛል - “የምርጫው ውጤት፣ ለብዙዎች አስደናቂ ነበር”።
አሃ፣ ዶናልድ ትራምፕ፣ ከቢዝነስ የስኬት ማዕረግ በተጨማሪ፣ ለፕሬዚዳንትነት ማዕረግ ይበቃሉ ብሎ ማን ጠበቀ? ምናልባት የዶናልድ ትራምፕ ባለቤትና ጥቂት በጣት የሚቆጠሩ ሰዎች ብቻ! ትራምፕ ሊያሸንፉ ይችላሉ ብሎ መናገር ይቅርና ማሰብም አስቸጋሪ ነበር። ግዙፎቹ የሚዲያ ተቋማት፣ በቲቪ ሲሰራጯቸው የነበሩ የእለት ተእለት ፕሮግራሞችን መጥቀስ ይቻላል።
ባለፈው ሰኔ ወር፣ አንዱ ጋዜጠኛ፣ በMSNBC ስርጭት ላይ፣ እንዴት እንደተሳቀበት አስታውሳለሁ።
የአመቱ ትልቅ ቀልድ
ያኔ፣ ስቱዲዮ ውስጥ ተደርድረው ዘወትር የሚራቀቁ አብዛኞቹ የፖለቲካ ተንታኞችና ጋዜጠኞች፣ ዶናልድ ትራምፕን እንደ ጊዜያዊ “መዝናኛና ማዳመቂያ” ነበር የሚቆጥሯቸው። እንደ መሳለቂያም ጭምር እንጂ። በዚህ መሃል፣ አንዱ ጋዜጠኛ፣ ያለተጠበቀ ነገር ተነፈሰና ስቱዲዮው ተናወጠ።
“ዶናልድ ትራምፕ፣ እንደዋዛ መታየት የለባቸውም። ከጊዜ ወደ ጊዜ፣ ብዙ ደጋፊ እያገኙ ስለሆነ...” በማለት ነው ንግግሩን የጀመረው። እዚያው፣ እንደጀመረ ቀረ። ንግግሩን መጨረስ አልቻለም። ግራና ቀኝ የተደረደሩት ጋዜጠኞችና ተንታኞች... “በሳቅ ፈረሱ”። ሊስቁበትና ሊሳለቁበት ፈልገው አይመስልም። እንዲያውም፣ ራሳቸውን እንደምንም ተቆጥረው፣ በጥንቃቄ ነው የሳቁት፣... በጨዋ አሳሳቅ። ግን፣ ሳቃቸውን ሙሉ ለሙሉ ሊያፍኑት አልቻሉም። ከሚቋቋሙት በላይ ሆነባቸው። “ትራምፕ እንደዋዛ መታየት የለባቸውም...”... ይህንን እየሰሙ፣ በሳቅ አለመንከትከት... በቃ ከበዳቸው።
እንግዲህ አስቡት። ዋናው የምርጫ ዘመቻ ላይኮ፣ አልተደረሰም። ገና የማጣሪያ ምርጫ እየተካሄደ ነበር። እና፣ የማጣሪያ ምርጫው ላይ፣... “ትራምፕ፣ ከምር ተፎካካሪ ሊሆኑ ይችላሉ” የሚል ሃሳብ የሚሰነዝር ጋዜጠኛ መገኘቱ... በዚያን ወቅት፣ በጣም አስቂኝ የሆነ ገጠመኝ ሆነባቸው። ከደርዘን በላይ፣ እሳት የላሱ ታዋቂ ሴናተሮችና ገቨርነሮች በሚፎካከሩበት፣ የሪፐብሊካን ፓርቲ የማጣሪያ ምርጫ ላይ፣... ዶናልድ ትራምፕ፣ አሸናፊ ሊሆኑ? እና ከዚያ በኋላ፣ ሪፐብሊካን ፓርቲን በመወከል፣ ወደ ዋናው የፕሬዚዳንት ምርጫ ሊገቡ? እና ዲሞክራቲክ ፓርቲን ወክለው ከሚመጡት ሂላሪ ክሊንተን ጋር ሊፎካከሩ?
ፈፅሞ ሊታሰብ የማይችል ነገር! ስቱዲዮው በሳቅ ተሞላ። “አፈንጋጩ” ጋዜጠኛ፣ ጅምር ንግግር፣... በሳቅ ተውጦ፣ በአጭሩ ተቀጨ። ለዚያውምኮ እንዲህ የተናገረው፣ በMSNBC ቲቪ ነው፤... ሪፐብሊካን ፓርቲን እንደ ባላንጣ የሚመለከት እጅጉን “ግራ ዘመም” የሆነ ቲቪ ላይ! ከሲኤንኤን እና ከዋሽንግተን ፖስትም፣ ከዋናዎቹ “ግራ ዘመም” አቀንቃኞች (ከኒውዮርክ ታይምስ እና ከዘ ጋርድያን) በጣም የባሰ የሚዲያ ተቋም ላይ፣ ስለ ዶናልድ ትራምፕ በቁምነገር የተተነፈሰ ንግግር... የአመቱ ትልቅ ቀልድ ሆኖ ይመዘገባል።
ለነገሩ፤ ከግራ ዘመሞቹ መካከል፣ በጣም ለዘብተኛና በሳል እንደሆኑ የሚነገርላቸው ታዋቂ የሚዲያ ሰዎችም፣ ዶናልድ ትራምፕን ከቁም ነገር አልቆጠሯቸውም። በእርግጥ፣ “በሳል” በመሆናቸው፤ የአሜሪካ ፓለቲካ ላይ ብቻ ሳይሆን፣ በአጠቃላይ በአለም ፖለቲካ ውስጥ፣ ከነባሩ ስርዓት ያፈነገጠ አዲስ የፖለቲካ አዝማሚያ በየአቅጣጫው እየነፈሰ፣ በየቦታው እያንዣበበ መሆኑን አላጡትም። አዝማሚያውንም ስላስተዋሉ፣ “ነገሩ አላሳቃቸውም”። የሚያሳስብ እንጂ የሚያስቅ አልሆነባቸውም። ከእነዚህ አንዱ፣ የዋሺንግተን ፖስት ፀሐፊ፣ የሲኤንኤን ተንታኝ፣ ፋሪድ ዘካሪያ ነው። አምና በሚያዚያ ወር ያቀረበውን ፕሮግራም ትዝ ይለኛል።
የነባሩ አቅጣጫ ቀውስና አሳሳቢው አዝማሚያ
የአሜሪካና የአውሮፓ መንግስታት፣ በየጊዜው... “የጤና፣ የትምህርት፣ የስራ አጥነትና የምናምን”... በሚል ሰበብ፣ መዓት የድጎማ አይነቶችን እየፈለፈሉ፣ በየአመቱ የሚመድቡት በጀት፣ ከጣሪያ በላይ አልፏል። ለዚሁ በጀት የሚሆን ገንዘብ ለመሰብሰብ ደግሞ፣ ከዜጎች ምርትና ገቢ ውስጥ ግማሽ ያህሉን መንግስታት በታክስ ይወስዳሉ። ይህም አልበቃቸውም። በየአመቱ ብዙ ቢሊዮን ዶላር ይበደራሉ።
የአሜሪካ መንግስት ብድር 20 ትሪሊዮን ዶላር ደርሷል። በየአመቱ ለወለድ ብቻ ከ450 ቢሊዮን ዶላር በላይ ለመክፈል የሚገደድበት ደረጃ ላይ ደረሰ ማለት፣... ማምለጫ ከሌለው አስፈሪ ቅዠት አይተናነስም። የአውሮፓ መንግስታት የእዳ ክምርና የወለድ ክፍያ ደግሞ፣ ከአሜሪካም የባሰ ነው።
ኢንቨስትመንትን የሚያቀጭጩ ስፍር ቁጥር የሌላቸው የቢሮክራሲ ቁጥጥሮች ከመበራከታቸው ጎን ለጎን፣ በየጊዜው በሚቆለለው የበታክስ ጫናና የመንግስታት እዳ ሳቢያ፣ የአውሮፓና የአሜሪካ ኢኮኖሚ፣ ቀውስ ውስጥ ገብቶ ማገገም አቅቶታል። በድንዛዜ ከመንፏቀቅ ማለፍ አልቻለም። ምን ይሄ ብቻ! መንፏቀቅም ተስኖታል እንጂ። በደንብ ካስተዋልነው፣ የአሜሪካና የአውሮፓ ኢኮኖሚ፣ ወደ ታች የቁልቁለት ጉዞ ጀምሯል።
የአሜሪካ የህዝብ ብዛት፣ ባለፉት 15 ዓመታት፣ በ40 ሚሊዮን ጨምሯል (በ15% መሆኑ ነው)።
የኢኮኖሚ ምሶሶ የሆነው የኢንዱስትሪ እንቅስቃሴ ግን፣ ከስር እየተቦረቦረ ነው። ከማደግ ይልቅ እየተሸረሸረ። በእነዚሁ አመታት ውስጥ፣ የፋብሪካ የስራ እድሎች፣ ከ20 ሚሊዮን ወደ 15 ሚሊዮን ቀንሷል (በ25%)።
የህዝብ ብዛት ሲጨምር፣ የፋብሪካ ሰራተኞች ቁጥር ግን፣ ከመጨመር ይልቅ፣ በሩብ ያህል አሽቆልቁሏል። ብዙ ሚሊዮን የፋብሪካ ሰራተኞች፣ መተዳደሪያ ያጡ ስራ ፈት ሆነዋል። የብዙ ሚሊዮን ሰዎች ቤተሰብና ኑሮ፣ ክፉኛ ተናግቷል። ብዙ ሚሊዮን ወጣቶች፣ ህይወትን ለማሻሻል እድል የሚከፍት፣ የስራ ተስፋ አጥተዋል።
ከአሜሪካ ዋነኛ ምልክቶች አንዱ፣ ለምዕተ ዓመታት የብልፅግና ጉዞ አልነበር? ይሄ፣ ከነፃ ገበያ ስርዓት የተገኘ ድንቅ የአሜሪካ ምልክት፣ ዛሬ ደብዝዟል። ለምን?
“ድሆችን፣... ሕዝቡን... በጤና፣ በትምህርት፣ በኑሮ ለመደገፍና ለመደጎም”... በሚሉ ተደራራቢ ሰበቦች የተነሳ፣ የአሜሪካ የኢኮኖሚ ገፅታ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተለወጠ መጥቷል። የነፃ ገበያ ስርዓት ይበልጥ እየተሸረሸረ፣... በኢኮኖሚ ውስጥ፣ የመንግስት ድርሻ ከአመት አመት፣ ይበልጥ እየተንቦረቀቀ፣ ገደል አፋፍ ላይ ደርሷል።
ነገርዬው ውስብስብ አይደለም። ቁልጭ ብሎ የሚታይ ነው። ለመዓት የድጎማ አይነት፣ እልፍአእላፍ በጀት ለመመደብ፣... በዜጎች ላይ በየጊዜው ተጨማሪ ታክስ መጫን የግድ ነው። ከመቶ ዓመት በፊት፣ ከዜጎች ጠቅላላ ገቢ ውስጥ፣ መንግስት በታክስ የሚወስደው፣ 5% ብቻ ነበር (ከመቶ ዶላር አምስት ዶላር)። ዛሬ፣ ከ40% በላይ ሆኗል።
ከመቶ ዶላር የዜጎች ገቢ ውስጥ፣ መንግስት አርባ ዶላር እየወሰደም፣ አልበቃውም። ለዚህ ነው በየአመቱ፣ ከ500 ቢሊዮን ዶላር በላይ ብድር፣ በላይ በላዩ ሲቆልል የሚታየው። ግን እስከ መቼ? እንዲህ በየአመቱ ብድር እየከመሩ እስከወዲያኛው መቀጠል ይቻላል እንዴ? እንደማይቻል ለማወቅ፣ የኒዩክሌር ሳይንቲስት መሆን አያስፈልግም።
እና ምን ተሻለ? እንደ ድሮው፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ፣ አዳዲስ የታክስ ጫናዎችን እየደረቡ መቀጠልም፣ አይቻልም። ለምን? እንደማይቻል፣ በእውን እየታየ ነዋ። የታክስ ጫና የከበዳቸው የአሜሪካ ፋብሪካዎችና ኩባንያዎች፣ አገር ጥለው የሚሄዱት ለምን ሆነና! እልፍ አእላፍ ፋብሪካዎች እየከሰሩና እየተዘጉ፣ በዝገት አፈር መስለው፣ በአረም ተወርረው የሚታዩት ለምን ሆነና!
ይሄ የአሜሪካ ችግር ብቻ አይደለም። እንዲያውም የአውሮፓ ይብሳል። እንደ ራሺያና ብራዚል የመሳሰሉ ሌሎቹ አገራትማ፣ ቀድመው፣ ቁልቁለቱን ተያይዘውታል። ቻይናም፣ ከቀውስ የማምለጥ እድሏ በጣም ጠባብ ነው። ለቀውስ በጣም ቅርብ ናት። ገና ካሁኑ፣ የኢኮኖሚ እድገቷ ስለተቀዛቀዘ ብቻ፣ መወዛወዝ ጀምራለች። ያው፣ ሻል ያሉት እነ አሜሪካና እንግሊዝ ሲደናቀፉ ነው፣ ሌሎቹ አገራት ለመፈጥፈጥ የሚቃረቡት። የአሜሪካና የእንግሊዝን ቀውስ በዝርዝር ማየት፣ ጠቃሚ የሚሆነውም በዚህ ምክንያት ነው።
ኑሮን ያናጋ ቀውስ እና የአንጋፋ ፓርቲዎች ምላሽ  
የአሜሪካ ፋብሪካዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ምን ያህል እንደተብረከረኩ አይተን የለ! እስቲ፣ ጥቂት የቁጥር መረጃዎችን በማየት፣ የአውሮፓ ኢኮኖሚ እንዴት እንደተናጋ ለማገናዘብ እንሞክር።
ከ10 ዓመት በፊት የፈረንሳይ የፋብሪካ ሰራተኞች ቁጥር፣ ከ4 ሚሊዮን በላይ ነበር። ዛሬ ወደ 3 ሚሊዮን ወርዷል። የሕዝብ ብዛት በ10% ሲጨምር፣ የፋብሪካ ሰራተኞች ቁጥር ግን፣ በ25% ቀንሷል።
በጣሊያንም፣ የህዝብ ብዛት መጨመሩ አልቀረም። የፋብሪካ የስራ እድል ግን፣ ከ5 ሚሊዮን ወደ 4 ሚሊዮን ወርዷል።
በብሪታኒያስ?
ከ10 ዓመታት በፊት፣ በብሪታኒያ ከአራት ሚሊዮን በላይ የፋብሪካ ሰራተኞች ነበሩ። ዛሬ ወደ 3 ሚሊዮን ቀንሷል። የህዝብ ብዛት ግን፣ ጨምሯል። በሌላ አነጋገር፣ ከአመት አመት ብዙ ፋብሪካዎች እየተዘጉና የስራ እድል እየተናደ፣ የሚሊዮኖች ኑሮ ከአመት አመት እየተናጋ ነው።
ይሄ ሁሉ ቀውስ፣ በአሜሪካና በአውሮፓ በግላጭ የሚታይ ግዙፍ ችግር ቢሆንም፤ እስካሁን፣ “ይህ ነው” የሚባል፣ ተጨባጭ የመፍትሄ ምልክት አልታየም። ለምሳሌ፤ የአሜሪካ የዲሞክራቲክ ፓርቲ ፖለቲከኞችና በብሪታኒያ የሌበር ፓርቲ ፖለቲከኞች፣... በአብዛኛው፣ “ሁሉም ነገር አማን ነው” ባይ ናቸው። “አማን” ከመሆንም አልፎ፣ በትክክለኛው አቅጣጫ እየተጓዙ እንደሆነ ያምናሉ። እንዲያውም፣ “ጉዞውን ይበልጥ ማፋጠን ነበረብን” የሚል ነው ቅሬታቸው። ተጨማሪ የድጎማ አይነቶች፣ ተጨማሪ የታክስ ጫናዎች፣ በተጨማሪ ፍጥነት ማራባት ነው ህልማቸው። ኩባንያዎች እየከሰሩ ከአገር ቢሸሹ፣ ተጨማሪ የመንግስት የብድር ክምሮች ቢቆለሉ፣... ብዙም አሳሳቢ ሆኖ አይታያቸውም። ይሄ የፖለቲከኞቹ፣ “የምናብ ዓለም” ነው።
እውነተኛ ዓለም ውስጥ ግን፤ በየአካባቢው፣ ብዙ ሚሊዮን ሰዎች፣ በስራ እጦት ኑሯቸው ተናግቶ ይማረራሉ። ፓርቲዎቹና ፖለቲከኞቹ፣ ይህንን እውነተኛ ዓለም ለማየት የሚፈልጉ አይመስሉም። “አማን በአማን ነው” እያሉ፣ ኒውዮርክና ዋሺንግተን፣ ለንደንና ፓሪስ ውስጥ፣ የብቻቸው ምናባዊ አለም ፈጥረው፣ ያጨበጭባሉ። ይሄ፣ ለብዙ ሚሊዮን ዜጎች፣ “ስድብ” ነው። ኑሯቸው መናጋቱ ሳያንስ፣ ፖለቲከኞችና ፓርቲዎች፣ “አማን በአማን” እያሉ ሲደንሱ ማየት በእርግጥም ያናድዳል። በጉዳት ላይ ስድብ ተጨምሮበት እንዲሉ።
በእርግጥ፣ በአሜሪካ የሪፐብሊካን ፓርቲ ፖለቲከኞችና በእንግሊዝ የኮንሰርቫቲቭ ፓርቲ ፖለቲከኞች፣... በአብዛኛው፣... በአመዛኙ፣... ለፋብሪካ ቢዝነስ... ደህና ይቆረቆራሉ። ግን ምን ዋጋ አለው?
ለአመታት የተከማቸው እልፍአእላፍ የድጎማ አይነት ካልተቀነሰ፤ የታክስ ጫናዎችን ማቃለል አይቻልም። መንግስት ለድጎማ የሚውል ገንዘብ ለመሰብሰብ፣ ብዙ የታክስ ጫና መከመሩ፣ አይቀሬ ነው። የታክስ ጫና ሲደራረብ ደግሞ፤ ፋብሪካዎች በኪሳራ ከስራ ውጭ ይሆናሉ። ኩባንያዎች አገር ጥለው ይወጣሉ። ኢንቨስትመንት ይዳከማል፤ የስራ እድል ከመስፋፋት ይልቅ፣ ቁልቁል ይሸረሸራል።
በሌላ አነጋገር፣ ድጎማዎችን ሳይቀንሱ፣ ኢኮኖሚያቸውን ከቀውስ ማዳን አይችሉም፤ ኢንቨስትመንትንና የስራ እድልን ማስፋፋት አይችሉም። ግን፣ ድጎማዎች፣ “አይነኬ” ሆነዋል። “ድጎማዎችን እቀንሳለሁ፣ እሰርዛለሁ” ብሎ መቀስቀስ፣ መመረጥና ተግባራዊ ማድረግ፣... ጨርሶ “የማይደፈር፣ የማይታሰብ” ህልም ነው - ለብዙዎቹ ሪፐብሊካኖችና ኮንሰርቫቲቦች።
በአጭሩ፣ የአሜሪካ ሪፐብሊካኖችና የእንግሊዝ ኮንሰርቫቲቮች፣... ድጎማዎችን ላለመንካት እየፈሩ፣ ለቢዝነስ ላይ ላዩን መቆርቆራቸው ብቻ፣... በቂ አይደለም። መፍትሄ አይሆንማ። እናም፣ የቢዝነስ ተቆርቋሪ ነን የሚሉት ሪፐብሊካኖችና ኮንሰርቫቲቮች፣ ብዙም የሚፈይድ ነገር ለመስራት አልቻሉም። ባለፉት አመታት በታየው ነባር አቅጣጫ መጓዝን፣ “አሜን” ብለው የሚቀበሉ ሆነዋል።
“አማን በአማን” እና “አሜን አሜን”
ብዙዎቹ የአሜሪካ አብዛኞቹ ሪፐብሊካኖች፣ እንደዲሞክራቶች ነባሩን የጉዞ አቅጣጫ እያደነቁ ባይደንሱም፤... ብዙዎቹ የእንግሊዝ ኮንሰርቫቲቮች እንደ ሌበር ፖለቲከኞች ባይጨፍሩም፤... “ሁሉም ነገር፣ አማን ነው” እያሉ ባያዜሙም፣ “አሜን ነው” ብለው ዜማ የሚቀበሉ ሆነዋል።
ከስራ እየተፈናቀሉና የስራ እድል እየራቃቸው፣ ኑሮ የተናጋባቸው ብዙ ሚሊዮን ዜጎች ግን፣ “አማን ነው” እና “አሜን ነው” የተሰኙ ዜማዎችን እየሰሙ መቀጠል አይችሉም። ጉዳዩ፣ የኑሮ ጉዳይ ነዋ። አንዳች መፍትሄ ይፈልጋሉ። ብዙ ሚሊዮን ዜጎች፣ በአንጋፋዎቹ ፓርቲዎች ላይ እና በፓርቲዎቹ ዜማ ላይ ያመፁትም፣ በዚህ ምክንያት ነው። በአጭሩ፣ የአሜሪካና የአውሮፓ ኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን፣ ፖለቲካቸውም ፈታኝ ቀውስ ገጥሞታል። ይሄ ቀውስ ነው፣ እነ ፋሪድ ዘካሪያን ያሳሰባቸው። ነገር ግን፣ ዘካሪያ፣ ቀውሱ እጅግ ፈታኝና አሳሳቢ እንደሆነ በመግለፅ ብቻ እንዳልተቆጠቡ አስታውሳለሁ።
የአውሮፓና የአሜሪካ ቀውስ በጣም አሳሳቢ ነው ካሉ በኋላ፤ ቢሆንም ግን፤... እንግሊዝ፣ ከአውሮፓ ህብረት አትወጣም በማለት በእርግጠኝነት ተናግረዋል - ዘካሪያ። ይህም ብቻ አይደለም።
ዶናልድ ትራምፕ፣ የአሜሪካን ድንበር በግንብ ለማጠር እያዛቱ ቢሆኑም፣ በምርጫ እንደማያሸንፉ፣ ዘካሪያ በልበሙሉነት ትንታኔ አቅርበው ነበር - አምና።
የዘካሪያን ትንታኔ፣ “የአለማችን የቀውስ አዝማሚያ አሳሳቢ ቢሆንም፣ ብዙ አትጨነቁ... ሁሉም ነገር አማን ነው”... ብሎ አገሬውን እንደማረጋጋት ልትቆጥሩት ትችላላችሁ። “በነባሩ አቅጣጫ፣ መጓዝ እንችላለን” ብሎ እንደማፅናናትም ነው።  
ፅሁፌ መግቢያ ላይ፣ “የተቃወሰ ነገር የለም። የሌለ... ያልፈጠረ ችግር ነው የምታወራው” በሚል ስሜት፣ “በሳቅ የፈነዱ” ጋዜጠኞችንና ተንታኞችን በማየት ነው የጀመርነው። ነባሩን አቅጣጫ እጅጉን የሚያደንቁ ከመሆናቸው የተነሳ፣ የእስከዛሬውን አቅጣጫ የሚፈታተን ነገር ይመጣል ብለው አያስቡም። የሚያስብ ሰው ሲያጋጥማቸው ደግሞ፣ “በሳቅ ይፈርሳሉ”።
በፖለቲካው ውድድርና ፉክክር ውስጥስ?
በአንድ በኩል፣ ነባሩን አቅጣጫ በፊታውራሪነት የሚመሩ ፓርቲዎችን እናገኛለን - “አማን በአማን” እያሉ የሚደንሱ ግራ ዘመም አንጋፋ ፓርቲዎችን።
በሌላ በኩል ደግሞ፣ ነባሩን አቅጣጫ መለወጥ አስቸጋሪ ነው ብለው እየፈሩ፣ “አሜን ነው፣ የባሰ አታምጣ” እያሉ የሚቆዝሙ ቀኝ ዘመም ፓርቲዎችን ነው ያገኘነው።
እነዚህ ሁሉ ‘ፉርሽ’ ሆነዋል። ከሰሞኑ በእንግሊዝና በአሜሪካ ያየናቸው፣ ዋና ዋና ስነስርዓቶችም፣ የዚህ እውነታ ባንዲራዎች ናቸው።
የታሪኩ ዋና መልክእክት
በእንግሊዝ፣ የአገሬው ጠቅላይ ሚኒስትር ተሬሳ ሜይ፣ ታሪካዊ የተሰኘውን ንግግር፣ ማክሰኞ እለት አቅርበዋል። ንግግራቸውን የጀመሩት፣ ከ6 ወራት በፊት፣ በእንግሊዝ የተከሰተውን አስገራሚ ለውጥ በማስታወስ ነው። አብዛኞቹ ዜጎች፣ እንግሊዝ ከአውሮፓ ህብረት እንድትወጣ በምርጫ የወሰኑበት የያኔው ምርጫ፣... በብዙዎች ፈፅሞ ያልተጠበቀ ክስተት ነበር። የአገሪቱ አንጋፋ ፓርቲዎችና ዋና ዋና መሪዎች በሙሉ፣ እንግሊዝ በአውሮፓ ህብረት ውስጥ እንድትቀጥል፣ ሰፊ ቅስቀሳ አካሂደዋል። አብዛኛው ዜጋ ግን፣ በአንጋፋዎቹ ፓርቲዎች ላይ አመፀ። ከአውሮፓ ህብረት ለመውጣት ወሰነ።
ይህንን ውሳኔ ለማስለወጥ፣ ብዙ አጓጉል ሙከራዎች ተደርገዋል - ምርጫው እንዲደገም የጠየቁ፣ ውሳኔው በፓርላማ ወይም በፍርድ ቤት ተሽሮ ውድቅ እንዲደረግ... ብዙ አይነት ቅስቀሳ ተካሂዷል። የአውሮፓ ህብረትን በከፊል መልቀቅ፣ ተባባሪ አባል መሆን፣ በእንጥልጥል ማቆየት... ያልተሰነዘሩ የሃሳብ አይነቶች የሉም - ከድንጋጤና ከመደናበር የመነጩ ብዙ ሃሳቦች በየእለቱ ጎርፈዋል።
ጠ/ሚ ተሬሳ ሜይ፣ ማክሰኞ እለት ባቀረቡት ‘ታሪካዊ’ ንግግር ግን፣ እንግሊዝ ከአውሮፓ ህብረት ለቅቃ እንድትወጣ፣ በምርጫ ተወስኗል። መልቀቅ ማለት ደግሞ መልቀቅ ነው። በከፊል፣ በግማሽ፣ በአንድ ጎን ብቻ መልቀቅ... የሚባል ነገር የለም። ሙሉ ለሙሉ ከአውሮፓ ህብረት ለመልቀቅ ነው የተወሰነው በማለት፣ “እንቅጩን” ተናግረዋል - ሜይ።
በአሜሪካ ደግሞ፣ የዶናልድ ትራምፕ በዓለ ሲመት እውን ሆኗል። ብዙ አሜሪካዊያን፣ በአንጋፋዎቹ ፓርቲዎች ላይ በማመፅ ነው፣ ለዶናልድ ትራምፕ ድምፅ የሰጡት።  ለምን?
በቀውሱ ሳቢያ ኑሯቸው ክፉኛ የተናጋባቸው ብዙ ሚሊዮን ዜጎች፣ ከአንጋፋ ፓርቲዎች በሚሰሙት፣ “አማን አማን ወይም አሜን አሜን” የሚል ምላሽ ተናደዋል። ይህንንም በተግባር አሳይተዋል። በፖለቲከኛነት የማይታወቁት ዶናልድ ትራምፕ፣ ግራና ቀኝ በአንጋፋዎቹ ፓርቲዎች ክፉኛ ቢብጠለጠሉም፣ በምርጫው አሸንፈዋል።
አሜሪካ እና አውሮፓ፣ ለአመታት በተጠራቀመ ቀውስ ውስጥ መዘፈቃቸውን መካድ፣ አንዳችም ፋይዳ አያመጣም - መፍትሄ ላለማበጀት ከማስነፍ ያለፈ ቅንጣት ትርፍ የለውም። የታሪኩ ዋና መልክእክት፣ “ከእውነታ መሸሽ የትም አያደርስም” የሚል ነው።

Read 1303 times