Sunday, 22 January 2017 00:00

በኢትዮጵያ ግማሽ ሚሊዮን ሄክታር መሬት በጫት እርሻ ተሸፍኗል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(9 votes)

  ለኢትዮጵያና ለኬንያ ከፍተኛ የገቢ ምንጭ ሆኗል
                                   
       ኢትዮጵያና ኬንያ የጫት ምርታቸው በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ መሆኑን የጠቆመው ዘኢኮኖሚስት ለሁለቱም አገራት ከቡና ቀጥሎ በወጪ ንግድ ከፍተኛ ገቢ የሚያገኙበት ምርት እየሆነ መምጣቱን ዘግቧል፡፡
በኢትዮጵያ ከ15 አመታት በፊት በጥቂት ቆላማ አካባቢዎች ብቻ ተወስኖ የነበረው የጫት ምርት በአሁኑ ጊዜ በመላ ሃገሪቱ መስፋፋቱንና ከግማሽ ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት መሸፈኑን መፅሄቱ አመልክቷል፡፡
ቡና አምራች የነበሩ አካባቢዎችም በጫት ዋጋ በየጊዜው ማሻቀብና በአመራረቱ ቀላልነት እየተሳቡ ከቡና ምርት በመውጣት ወደ ጫት አምራችነት እየገቡ መሆኑንም ሪፖርቱ አስቀምጧል፡፡
የሃገሪቱ የወጪ ገበያን በሁለተኝነት ተቆጣጥሯል የተባለው ጫት፤ በሃገር ውስጥም ከፍተኛ ፍላጎት ያለው ምርት በመሆኑ በሃገሪቱ የተለያዩ ከተሞች የጫት መሸጫ አነስተኛ ኪዮስኮች አንደ አሸን እንዲበራከቱ ምክንያት ሆኗል ይላል፡፡
ዋጋው ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ መጠን እያደገ መሆኑንና ወጣት ተማሪዎችም ተጠቃሚነታቸው እየጨመረ መሆኑ ለሃገሪቱ አሳሳቢ መሆኑን ሪፖርቱ ያትታል፡፡
በሌላ በኩል ከጥቂት አመታት በፊት ስደተኛ ሶማሌያውያን ለጎረቤት ኬንያ ጫትን እንዳስተዋወቁ ያወሳው ኢኮኖሚስት አሁን ሃገሪቱ ከኢትዮጵያ ቀጥሎ ሁለተኛዋ ጫት አምራች ሆናለች ብሏል፤ የሃገር ውስጥ ተጠቃሚዎቿ ቁጥር በከፍተኛ መጠን እያደገ መሆኑን በመጠቆም፡፡
የሶማሊያውያን ስደተኞች መበራከትና ጫትን በትኩሡ ለገበያ ለማቅረብ አመቺ የሆኑ መንገዶች መስፋፋታቸው የኬንያ ገበሬዎች ወደ ጫት ምርት እንዲገቡ እያነሣሣቸው መሆኑን ሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡
ምንም እንኳን የኬንያ መንግስት የጫት ምርትን እየከለከለ ቢሆንም ለሃገሪቱ አሁንም ምርቱ የገቢ ምንጭ ሆኖ ቀጥሏል ብሏል - ሪፖርቱ፡፡
የአውሮፓ ሃገራት ጫት ወደ ሃገራቸው እንዳይገባ ከ3 አመት በፊት መከልከላቸውን ተከትሎ በኬንያም ሆነ በኢትዮጵያ ጫት አምራቾችና ሻጮች ላይ መጠነኛ የኢኮኖሚ ኪሣራ አስከትሎ የነበረ ቢሆንም የሃገራቱ ዜጎች የጫት ፍላጎት እየጨመረ በመምጣቱ በአሁኑ ወቅት አምራቾችና ሻጮች ትርፋማ ለመሆን ችለዋል ያለው ዘገባው፤ በዚህም የተበረታቱ አዳዲስ አምራቾች ወደ ዘርፉ በከፍተኛ መጠን እየተቀላቀሉ ነው ብሏል፡፡
በባለሙያዎች የኬንያና የኢትዮጵያ የጫት ምርት ለሃገራቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እያስገኘ ሲሆን በመላው ዓለም ገበያ በእጅጉ ተፈላጊ ከሆኑትና የአለምን ገበያ ከተቆጣጠሩት እንደ ቡና፣ ሻይና ስኳር ያሉ ምርቶች ጋር እየተስተካከለ ነው ተብሏል፡፡

Read 6001 times