Saturday, 14 January 2017 16:11

የላቀ የቢዝነስ ሐሳብ የሚያቀርቡ የ5 ዩኒቨርሲቲ ተመራቂዎች 1.1 ሚ. ብር ይሸለማሉ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

ነዋሪነታቸው በአሜሪካ ያደረጉ አንድ ኢትዮጵያዊ ዘንድሮ ከአምስት ዩኒቨርሲቲዎች የሚመረቁ ተማሪዎች የሚኖሩበትን ማህበረሰብ ኑሮ ሊለውጥ የሚችል የቢዝነስ የፈጠራ ሀሳብ ለሚያቀርቡ የተመረጡ ተመራቂ ተማሪዎች ስራ መጀመር የሚያስችል የ1.1 ሚ. ብር ሽልማት ለመስጠት መዘጋጀታቸውን አስታወቁ፡፡
የቴራ ግሎባል ኢነርጂ ዲቬሎፐርስና የኤኤስሲ ኢንጂነሪንግ የግል ኩባንያዎች መስራችና ዋና ስራ አስፈጻሚ  ኢ/ር በኃይሉ አሰፋ ከትናንት በስቲያ ፕሮግራሙን በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ሲያስተዋውቁ ተነሳሽነቱ የመጣው፣ መንግሥት የወጣቱን ስራ አጥነት ለመቅረፍ በጀመረው ጥረት፣ በአሜሪካና፣ አውሮፓ ወይም በተቀሩት አገራት የሚኖሩ ዳያስፖራዎችና የግል ኩባንያዎች የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ አርአያ ለመሆንና በግላቸው የሚጠበቅባቸውን የዜግነት ኃላፊነት ለመወጣት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡   
የዕድሉ ተጠቃሚ የሚሆኑ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በተጨማሪ የባህር ዳር፣ የሀዋሳ፣ የአርባ ምንጭና የአዳማ ዩኒቨርሲቲዎች ሲሆኑ በዩኒቨርሲቲዎቹ የዘንድሮ ተመራቂ የሆኑ የኢንጂነሪንግና የቢዝነስ ተማሪዎች አምስት አምስት ሆነው በቡድን የሚኖሩበትን ማህበረሰብ ችግር የሚፈታ የቢዝነስ ፈጠራ ሀሳብ (ፕሮፖዛል) አቅርበው ይወዳደራሉ፡፡  ድርጅቱ ከአምስቱም ዩኒቨርሲቲዎች ከቀረቡ ተወዳዳሪዎች መካከል አዲስና የተሻሉ ናቸው ብሎ የመረጣቸውን ፕሮፖዛሎች ያቀረቡ አምስት የተመራቂ ተማሪዎች ቡድን የፈጠራ ሀሳባቸውን ተግባራዊ የሚያደርጉበት ገንዘብ እያንዳንዳቸው ይሸለማሉ፡፡ ከደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የሚመረጡ አሸናፊ ተማሪዎች 300 ሺህ ብር የሚሸለሙ ሲሆን ከተቀሩት ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ 200 ሺህ ብር እንዲሸለሙ ያደርጋል፡፡ የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲው የተለየ እንዲሆን የተደረገው ባለፉት 5 ዓመታት ከዩኒቨርሲቲው ጋር በርካታ ነገሮችች ስለሰሩ ነው፡፡
ተመራቂ ተማሪዎች በሚሸለሙት ገንዘብ በሚያቋቁሟቸው ድርጅቶች ራሳቸውን፣ ማኅበረሰባቸውንና አገራቸውን ይጠቅማሉ ያሉት ኢንጂነሩ፣ መንግስት ለወጣቶች ስራ ፈጠራ የሚያደርገውን ጥረት ዝም ብለን መመልከት የለብንም፡፡ እንደ ዜጋና እንደ ግል ዘርፍ ለወጣቱ ስራ ፈጠራ የራሳችንን ሚና መጫወት አለብን ብለዋል፡፡
የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የዘንድሮ ተመራቂ ተማሪዎችን የመጀመሪያው ፕሮፖዛል ማቅረቢያ ቀን የካቲት22 - መጋቢት 6,2009፣ የተሻሻለውንና የተጠናቀቀው ሙሉ ፕሮፖዛል ደግሞ እስከ ነሃሴ 4 ማስረከብ ሲጠበቅባቸው፣ የሽልማት ስነ - ስርዓቱ በመስከረም ወር 2017 እንደሚከናወን ታውቋል፡፡




Read 2025 times