Saturday, 14 January 2017 16:08

“ሽልማታችንን ይዘን መጥተናል፤ እውነታው ይሄ ነው”

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ለምዝገባ 500 ዶላር? የተሸላሚዎች ዝርዝር ውስጥ አልተካተቱም?


ባለፈው ህዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም በአሜሪካ ካሊፎርኒያ፣ትልቁ የአፍሪካ የፊልም ሽልማት “ናፍካ” ሥነ-ስርዓት ተካሂዷል፡፡ በየዓመቱ የሚካሄደው ይኼው የሽልማት ሥነስርዓት፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በወኪሉ “ቆንጆ ፕሮሞሽን”በኩል ኢትዮጵያውያን አርቲስቶች እንዲወዳደሩ በሰጠውእድል ተዋንያን፣ ዳይሬክተሮች፣ የሜካፕ አርቲስቶች፣ሲኒማቶግራፈሮችና አንድ የበጎ አድራጎት መስራች በድምሩ
9 ሰዎች በእጩነት ወደ አሜሪካ ተጉዘው ነበር፡፡በተለይም ዝነኞቹ ተዋንያን ግሩም ኤርሚያስና ሩታመንግስተ አብ፤“ምርጥ የህዝብ ምርጫ ተዋንያን” በሚለውዘርፍ አሸናፊ መሆናቸው ተገልፆ፣በአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ተዘግቦ ነበር፡፡ የሽልማቱ ቦታ ላይ ሲደርሱ ግን
ብዙ ችግር እንደገጠማቸው፣ የናፍካው የኢትዮጵያ ተወካይ ሀሰተኛ እንደሆነና በሽልማት ቦታው ላይ ግራ ተጋብተው
እንደነበር፣ ሲወራ ሰንብቷል፡፡ከሽልማት ሥነ ስርዓቱ መካሄድ በኋላ አንድ ወር ከ10 ቀን ያህል በአሜሪካ ቆይቶ የተመለሰው አርቲስት ግሩም
ኤርሚያስ፤ በሽልማቱ ዙሪያ ያለውን እውነታ እንዲገልጽ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛዋ ናፍቆት ዮሴፍ እንደሚከተለው አነጋግራዋለች፡


ለናፍካ ሽልማት ወደ አሜሪካ ያደረጋችሁት ጉዞ ምን ይመስል ነበር?
እንግዲህ ለሽልማት ወደ ካሊፎርኒያ የሄድነው ሐሙስ ዕለት ማታ ነው፡፡ ለ21 ሰዓት በረራ አድርገናል፡፡ አርብ ጠዋት ደረስን፤ ቅዳሜ ሽልማቱ ነበር፡፡ አመሻሽ ላይ ነው ሽልማቱ የተካሄደው፡፡ እኛ ካረፍንበት ራቅ ያለ ቦታ ላይ ነው፡፡ በትራፊክ መጨናነቅና በራሳችንም ምክንያት ወደ አዳራሹ ዘግየት ብለን ብንደርስም፣ ሽልማታችንን ግን ተቀብለናል፡፡
ከዚህ ስለ ሽልማቱ ብዙ ተወርቶ ብትሄዱም፣ እዚያ ከደረሳችሁ በኋላ ችግር እንደገጠማችሁና የእናንተ ስም በተሸላሚዎች ዝርዝር ውስጥ እንዳልተካተተ፣ በተለያዩ የአገር ውስጥ ሚዲያዎች ተወርቷል፡፡ ወሬው ከየት የመጣ ነው?
በዚህ መልኩ የተፈጠረ ችግር የለም፡፡ መድረክ አካባቢ ትንሽ ማስተባበር የጎደላቸው ነገሮች ነበሩ። ለምሳሌ ተሸላሚዎች ስማቸው መድረክ ላይ ተጠርቶ ሽልማቱ ሳይቀርብ፣ ከመድረክ ጀርባ የወሰዱ አሉ፡፡ በሌላ በኩል፤ መድረክ መሪዎቹ “ከ1-5 የወጡ ፊልሞች እነዚህ ናቸው፤ አንደኛ የወጣው ደግሞ ይሄ ነው” ማለት ሲገባቸው፣ ቀድሞ ስክሪን ላይ ይለቀቅ ነበር፡፡ ይሄ አጓጊነቱን ይቀንሰዋል። እና የሽልማት ሂደቱ ላይ በአዘጋጆቹ ችግር ትንሽ የተዘበራረቁ ነገሮች ነበሩ እንጂ እኔና ሩታ ላይ ብቻ ተለይቶ የደረሰ ነገር አልነበረም፡፡ ከዝግጅቱ በኋላ እንዲህ የተዘበራረቀበትን ምክንያት ለማወቅ ሙከራ ስናደርግ፣ ከዚህ በፊት የተካሄዱትን አምስት የናፍካ ሽልማቶች ራሱ ሸላሚው ድርጅት ያዘጋጃቸው ሲሆኑ ጥሩ ሂደት እንደነበራቸው ሰምተናል፡፡ የዘንድሮው ለሌላ ኤጀንት በመሰጠቱ፣ ኤጀንቱ እንደ ጀማሪነቱ ትንሽ ክፍተት እንደተፈጠረበት ነው የተገለፀልን፡፡
ሁለታችሁ ሽልማቱን እንዳላገኛችሁ----በተለይም ሩታ ታጨች በተባለችበት ዘርፍ አንዲት ናይጀሪያዊት ሽልማቱን ይዛ ፎቶ መነሳቷ---እየተወራ ያለው ከምን መነሻ ነው?
እኔ ይሄ ነገር በምን መነሻ እንደተወራ፣ ወሬውን ማን እንዳዛመተውም አላውቅም፡፡ እኛ የሄድነው መዘጋጀቱ እውን በሆነ የሽልማት ስነ-ስርዓት ላይ ለመገኘት ነው፡፡ ሽልማታችንን አግኝተን ተመልሰናል። ይሄ “በሬ ወለደ” አይነት ወሬ በጣም ገርሞኛል፡፡ ሙያችንን እናሳድጋለን ብለን በምንጥርበት ጊዜ፣ እንዲህ አይነት ወፍ ዘራሽ ወሬዎች መናፈሳቸው እጅግ አሳፋሪ ነው፡፡
በናፍካ የኢትዮጵያ ተወካይ ነው የተባለውና የ“ቆንጆ ፕሮሞሽን” ስራ አስኪያጅ አቶ ማይክ በናፍካ እንዳልተወከለ፣ በአሜሪካ የታክሲ ሹፌር እንደሆነና ከኪነ-ጥበብ ጋር ግንኙነት እንደሌለውም ተወርቷል፡፡ ለምዝገባ እያንዳንዳችሁ 500 ዶላር ከፍላችኋል የተባለውስ--- ሰምተኸዋል?
የመጀመሪያው ነገር የናፍካ ተወካይ የታክሲ ሹፌር ከሆነም ነውር አይደለም፡፡ ሹፍርናም የተከበረ ሙያ ነው፡፡ ዋናው ነገር ይህንን እድል ለአገራችን ማምጣቱና የያዘው ራዕይ ትልቅ መሆኑ ነው፡፡ አንድ ሰው ታክሲ እየነዳ ወይም ሌላ ስራ እየሰራ፣ ጎን ለጎን ሌላ ተጨማሪ ስራ ቢሰራ ችግሩ ምንድን ነው፡፡ አየሽ ወሬው ሰውንና የሰውን ሙያ ከመናቅ ይጀምራል፤ ይሄ በጣም ያሳፍራል፡፡ እንደኔ እንደኔ ማይክ ሁሉቃ ወደ ኢትዮጵያ ይዞት የመጣው እድል፣ ለአርቲስቱና ለአገር ይጠቅማል አይጠቅምም የሚለው ነው መታየት ያለበት እንጂ ሌላው ነገር አይደለም፡፡ እንዲህ አይነት ጥሩ ዕድሎች ሲመጡ፣ ለማበላሸትና የሚሰራን ሰው ሞራል ለመንካት የሚደረግ ሩጫ ያሳዝናል፡፡ ዌብ ሳይቱን ናፍካ ብሎ ገብቶ ማየት ይቻላል፤ ሁሉም ነገር በግልፅ ይገኛል፡፡
ሩታን በተመለከተ ስሟ በስነ ስርዓቱ ተጠርቶ፣ መድረክ ላይ ወጥታ ንግግር አድርጋ፣ ሽልማቷን ተቀብላለች፡፡ እኔም እንደዛው፤ ሽልማቴ በቤቴ ይገኛል፡፡ በመጀመሪያ ሚዲያዎች ይህን ወሬ ተቀብለው  ዜና ሲሰሩ፣  እኛን የጉዳዩን ባለቤቶች ለምን አልጠየቁንም? ልክ አሁን አንቺ እንደምትጠይቂን፣ ለምን አልተጠየቅንም፡፡ እኛ በቦታው የነበርነውን የጉዳዩን ባለቤቶች መጠየቅ ነበረባቸው፡፡ ከሆነ አካል ወሬ ሰሙ፤ ዋና ባለቤቶቹን ሳይጠይቁ፣ የአንድ ወገን ሃሰተኛ ወሬ ይዘው ወጡ። ይሄ ነው ሁላችንንም ወደ ኋላ እየጎተተን ያለው፡፡ ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ በዝግጅቱ በኩል አንዳንድ ክፍተቶች ነበሩ፤ ለምሳሌ ሰው ስሙ እየተጠራ መድረክ ላይ ሲወጣ፣ ገና አዋርዱ ወደ መድረክ አልመጣም፡፡ ብዙ ተሸላሚ ማለት ይቻላል … ሽልማቱን ከመድረክ ጀርባ ነው የወሰደው፡፡ ይሄ የእኔም ሆነ የሩታ ወይም የሌሎች ተሸላሚዎች ችግር ሳይሆን የአዘጋጁ ነው፡፡ እዚያም የሽልማት ቦታ ላይ የተፈጠረው አንዳንድ ክፍተት እንደዚህ ነው የሆነው፤ አዘጋጆቹ ናቸው ሊጠየቁ የሚገባው፡፡
ተወካዩን በተመለከተ የናፍካ አርማና ማህተም ባለው ደብዳቤ፤ ‹‹On behalf of Nafca›› ተብሎ ስሙ ተጠቅሶ፣ ውክልና የተሰጠበትን ደብዳቤ አይቼ ነው ወደ ጉዳዩ የገባሁት፡፡ እኔ ህፃን ልጅ አይደለሁም፤ በምንም መልኩ ልታለል አልችልም። ወይም ደግሞ ዋንጫ የመሸለም ሱስ የለብኝም። እንዴት የኢትዮጵያን ህዝብ አታልላለሁ፤ ሰው ድምፅ ሰጥቶናል፤ እንዲህ አይነት ወሬ ማውራት የደገፈንን ሰው መናቅ ነው፡፡ እያንዳንዱ ነገር በዶክመንት የተደገፈ፣ በተፈለገው ጊዜ ሊታይ የሚችል ነገር ነው የተካሄደው፡፡ እንደተባለው በአየር ላይ የተናፈሰ ወሬ፣ ወይም በክፍያ የተከናወነ አይደለም። ናፍካም ትልቅ የአፍሪካ የፊልም ሽልማት ነው፤ ለ6ኛ ጊዜ የተካሄደ። እኔም ሩታም ይዘን የመጣነው ኩራታችንን፣ የሚገባንን ሽልማት ነው፤ ይሄ ደረቴን ነፍቼ በኩራት የምናገረው ነው። አንድ ጥቁር አሜሪካዊ የሆነውን ልንገርሽ፡፡ ለሽልማት ስሙ ተጠራ፤ነገር ግን ሽልማቱ የለም፤ ለምን ብሎ ሲጠይቅ፤ ”የአንተን ሽልማት ኢ-ሜይል እናደርግልሃለን” አሉት፡፡ የእኔን ሽልማት ይዞ ነው ፎቶ የተነሳው፤ ይሄ የናፍካ ስህተት ነው። በእንዲህ አይነት ስነ-ስርዓቶች ላይ ትልልቅ ስህተቶች ይፈጠራሉ፡፡ ለምሳሌ በዓለም የቁንጅና ውድድር ላይ አንደኛ ለወጣችው ሽልማቱ መሰጠት ሲገባው፣ ሁለተኛ ለወጣችው ተሰጥቷል፡፡ ይሄ ያጋጥማል፤ ስህተት እየተሰራ ይቀጥል ለማለት ግን አይደለም፡፡
የሽልማቱ ሥነ ስርዓት ከተካሄደ በኋላ፣ ከ1ወር በላይ ቆይታችሁ ነው ወደ አገራችሁ የተመለሳችሁት። እግረ መንገዳችሁን ያከናወናችሁት ነገር ነበር?
ከሄድንበት ፕሮግራም መጠናቀቅ በኋላም እዚያው ሎስ አንጀለስ ስለነበርን መጀመሪያ ያደረግነው ‹‹ዩኒቨርሳል ስቱዲዮ›› የተሰኘውን ትልቅ የፊልም ኩባንያ መጎብኘት ነው፡፡ በጣም አስደናቂ ስቱዲዮ ነው፡፡ አሜሪካ በጣም ከተደነቅኩባቸውና ከተገረምኩባቸው ነገሮች አንዱና ዋነኛው “ዩኒቨርሳል ስቱዲዮ” ነው፡፡ ይህ ስቱዲዮ አንድ የፊልም ባለሙያ ማየት የሚገባው ወሳኝ ቦታ ነው፡፡ ብዙ ልምዶችን ቀስመናል፡፡ ከዚህ በኋላ ያደረግነው በበጎ አድራጎት ዘርፍ የመሰረት በጎ አድራጎት ድርጅት መስራችና ዳይሬክተር እጩ ነበረች፡፡ በእርግጥ በዚህ ዘርፍ አንዲት ጣሊያናዊት ካቶሊክ በጎ አድራጊ ሴት ናቸው የተሸለሙት፡፡ እናም የተለያዩ ግዛቶች እየተዘዋወርን፣መሰረት ለምትረዳቸው ህፃናትና እናቶች፣ የገቢ ማሰባሰቢያ ስራዎችን ሰርተናል፡፡
በሌላ በኩል፤ብዙዎቻችን የየራሳችን ህልም አለን፡፡ ወደ ህልማችን ለመጠጋት ብዙ ጥረናል። ከተለያዩ የአፍሪካ ፊልም ሰሪዎች ጋር በብዙ ስራዎች ዙሪያ ተነጋግረናል፡፡ በተለይ አንድ የጋና ትልቅ የፊልም ባለሙያ፣ ሆሜስ ማክቪል ይባላል። “One Night in Vegas” እና “Paparazi” በተሰኙ ፊልሞቹ ይታወቃል፡፡ ከዚህ ባለሙያ ጋር በጣም ተወያይተናል፡፡ በቀጣይ ስለምንሰራውም እየተነጋገርን እንገኛለን፡፡ ዲሲም ሄደን አቶ ታምራት የተባሉ፣ ላለፉት 42 ዓመታት በዲሲ የኖሩ ሰውን አነጋግረናል፡፡ ብቻ ብዙ ነገሮችን ከውነናል፡፡ መቼም ዋናው ህልማችን የናፍካን ሽልማት ወስዶ ለመመለስ ብቻ አይደለም፡፡ ወደ ህልማችን የሚያስጠጋንን ነገር እግረ መንገዳችንን ፈፅመን መጥተናል፡፡
በቆይታህ ካገኘኸው ልምድ የፊልሙን ኢንዱስትሪ ለማሳደግ ምን አስበሀል?
እኔ እንግዲህ ሁሌም ተማሪ ነኝ ብዬ ነው የማስበው፡፡ እኔ እንደ ችግር የማየው፣ ራሳችንን ለሌላው ዓለም አላሳየንም፤ ኤክስፖዠር ያስፈልገናል። እነዚህን ነገሮች ለማድረግ በግሌ እጥራለሁ፡፡ ነገር ግን እድሎች ሲመጡ እንዲህ አይነት ያልተፈጠረ ነገር እያወሩ ሙያውን ከማቀጨጭ፣ በቅን ልቦና ማሰብ፣ መቻቻልና መተራረም የተሻለ ነው፡፡ እድሎችን ባበላሸን ቁጥር፣ ሙያችንን ወደ ዓለም ገበያ ለማቅረብ እንቸገራለን፡፡ በተረፈ አገራችን ላይ ጥሩ ተሰጥኦ ያላቸው ተዋንያን፣ ደራሲያን፣ ዳይሬክተሮች አሉ፡፡ ከመላው ዓለም ጋር መፎካከር የሚችሉ ባለሙያዎች አሉን፡፡ ሌላው የሚጎድለን እርስ በእርስ በሙያችን መደጋገፍና አብሮ የመስራት ነገር ነው፡፡ የናይጄሪያና የጋና ፊልም ሰሪዎች፣ የዓለምን ገበያ የተቀላቀሉት አብሮ የመስራት ባህል ስላላቸው ነው፡፡   



Read 3249 times