Saturday, 14 January 2017 16:07

የመጨረሻው እራት - ሰኞ ምሽት

Written by  ክብርዓለም ፋንታ
Rate this item
(1 Vote)

«አቤት» አልኩኝ፤ ሞባይል ስልኬን አንስቼ፡፡
«አብዝተኸዋል … በል አሁን ቶሎ ኦፊስ ና» አለኝ፡፡
 በተለምዶ ኦፊስ እያልን የምንጠራት ቦታ፣ የካልዲስ ካፌ በረንዳ ናት፡፡
 «እሺ ደግሞ ምን አጠፋሁ?» አልኩ፤ ካልዲስ እንደደረስኩ፡፡
እጁን ወደ ፊት ዘረጋና፤ «በል ና አሁን ---- እጅ ሳም» አለኝ፤ ከዛች አስገራሚ የቀልድ ፈገግታው ጋር።
የተለመደ በመሆኑ እሺ ብዬ ጎንበስ ስል፣ እጁ ሳልደርስ በፊት በትህትና ተነስቶ፣ ትከሻዬን መታ መታ በማድረግ ሞቅ ያለ ሰላምታውን ከሰጠኝ በኋላ፣ «ለምንድን ነው እንደዚህ እልም ብላችሁ የምትጠፉት?» ጠየቀኝ፡፡
ይህቺ ዕለት እኔም ከእነ ሙሉ ንቃተ ህሊናው ያየሁበት፣ ለእሱም የዚች ምድር የመጨረሻ ምሽቱ ነበረች፡፡ ሰኞ ማታ፡፡ ማክሰኞ ነበር ሩሁን ስቶ የወደቀው፡፡  
እኛ እርስ በርስ ተኮራርፈን ስንጠፋፋ፣ ሁላችንም ጋ ደውሎ የሚያሰባስበን እሱ ነበር። ከሸገር ህንጻ ወረድ ብሎ ወደሚገኘው አትክልት ቤት ሄድን፡፡ የእዮባን የመጨረሻ የአትክልት እራት፤ ከቀልድና ቁምነገሮች ጋር እያጣጣምን በላን። የሸክላ ሰሪው ጥሪ እንደተደወለ ግን ማናችንም አላወቅንም፡፡ እንዳጋጣሚ ሆኖ ከመጨረሻው ሳምንት ውስጥ አራቱን ቀናት ተገናኝተን ነበረ፡፡ ንግግሮቹንና ነገረ ስራውን ሳስታውስ፤ «እንዴ እዮባ የሆነ ነገር ታውቆት ነበረ እንዴ?” እላለሁ፡፡ ከሰኞ በፊት ረቡዕ‘ለት፣ ፒያሳ፣ በጃዝ አምባ ተጫውቶ ሲያበቃ፣ በእቴጌ ጣይቱ ግቢ ውስጥ እስከ ሌሊቱ  8፡30  ድረስ እኔ፣ ናቲ (ድራመሩ)፣ ሮቤል መሃሪ፣ ዘሌ ድራም እና መሀመድ ካሳ ከሚባሉ ወዳጆች ጋር የድሮ ነገር እየተነሳ ስናወጋ ነበር፡፡ በወሬ መሀል፤ “አንድ እግሬን ጎተተኝ” አለ፡፡ «በቃ አረጀህ ማለት ነው፤ ለማንኛውም ሪህ ሊሆን ይችላል፤ ተመርመር» አልኩት፡፡
ሳቅ አለና፤ «ምን እንዳይመጣ ነው፤ ሞት ትፈራለህ እንዴ?!» አለኝ፡፡
ያለበት መንገድ ገርሞኝ፤ «እንዴት አንተ አትፈራም?» መልሼ ጠየቅሁት፡፡
 «በፍጹም! በደስታ ነው የምቀበለው…  እረፍት እኮ ነው፤ ደግሞ ወደ ነገ ነው የምሄደው» አለ፡፡
ስቀን አለፍነው፡፡ በእርግጥ የንግግሩ ደማምነት፣ በልቤ እውነቱን እኮ ነው አስብሎኝ ነበረ፡፡ የእዮብ ነገ!  በፈገግታ ነው ይህቺን ርዕሰ ጉዳይ የሚያወራት፡፡ ይህቺ ምድር ደግነትን የሚሸከም ጫንቃ እንደሌላት ይገልጻል፤ ለማስረጃነትም ሕዝቅያስ ስለተባለ ንጉስ ከታላቁ መጽሐፍ ቅዱስ ያጣቅሳል፡፡ “ይህ ሰው መልካም ነበረ፣ ሞት በመጣ ጊዜ (መልካምነቱን አስታውሱ) እግዜርን ዕድሜ ለመነ፣ 15 ዓመት ተጨመረለት፣ ነገር ግን እነዚያን አስራ አምስት አመታት በሀጢያት አሳለፋቸው፡፡ ወደ ነገ ሳይነጻ ሄደ፡፡ ሳያስበው የለመነው ተጨማሪ ዕድሜ ለሚሰራው ሀጢያት ድርጎ ነበረ፡፡ ትርፍ ዕድሜ ለሀጢያት ዘመን አለመለመን ነው፤ ዛሬን በእግዚአብሔር መንገድ ከኖሩ፣ ወደ ነገ ሳይበላሹ መሄድ ይናፍቃል” በማለት አብራራ፡፡ በእርግጥም ስለ ምድራዊ ነገ ሳይሆን፣ ስለ ሰማያዊው ህይወት ነበር፤ «ይምሽልኛ ዛሬ ቀኑ፣ ያኔ የሚታየው ወጋገኑ» ያለው፡፡ ስለ ምድራዊ ነገ ብዙ አይጨነቅም፤ «ነገ የራሱ ክፋት ይበቃዋል» ይላል ቃሉ፤ ይል ነበረ፡፡
Stone/ ድንጋይ
ድንጋይ ጊዜን ይሻገራል፤ እኛን ግን ጊዜ እንደ ዋዛ ይሻገረናል፡፡ በተለየ መንገድ የሚጓዝ፣ ብዙ ትዝታዎችን የተሸከመ፣ ብዙ ቅኔዎችን ያተመ ብራና ነው፡፡ ፕ/ር ተሾመ ኃ/ገብርኤል Stone በተሰኘ መጽሔት ላይ ባሰፈሩት ጽሑፋቸው እንዲህ ይላሉ፡-
“It is common knowledge that stones do not lend themselves to speech; but because stones are mute, it does not mean that they do not speak; they actually do, only they speak in a language that we do not recognize, that we do not know. Here, the solidity of space can be reconsidered in terms of movement and mobility. Movement is not just a spatial displacement, or a matter of sequence, or of a linear history. While stones are generally associated with immobility, those that tend to remain still are in fact the ones that move the most throughout history. By not moving at all, they move in other directions, in other dimensions, in their own curious and often ironic way. Pyramids would seem to be the most immobile of things, yet they have been all over the world; there is no place in the world that does not carry archival memories of pyramids, for whom the pyramid does not signify something of deep cultural importance. One can argue that the same forces are at work in the Wailing Wall of Jerusalem and the Great Wall of China, and the Kaaba/Ka’ba of Mecca. Stones, like sacred relics, travel and induce us to do likewise; they move us emotionally, spiritually, and in many other ways. … Stones are the epitome of that which crosses over, even though they seem to remain ever the same. Stones mark the passages between phenomena, between life and death, material and spiritual.”
ገና እዛች በረንዳ ላይ እንደተቀመጥን፤ «የኔን ዓይነት አምጣለት ይላል - ሊታዘዝ የመጣውን አስተናጋጅ፡፡ እሱ በሌለበት እንኳን “የእዮብን ካፌ ላቴ አምጣልን” ብለን እናዝ ነበር፡፡ በተለምዶ ኦፊስ እያለ የሚጠራው ካልዲስ ኮፊ፣ ለሚያየው ድንጋይ ነው፣ ለሚያነበው  ግን ደግነትን፤ ትህትናን፣ ምግባርን - በፍቅር ያየንበት፣ መልካም ነገሮችንና ቁምነገሮችን ያገኝንበት፣ ብዙ ጉዳዮችን አንስተን የተከሳከስነበት ትልቅ የሐሳብ አውድማ ነው። አንብቦ ቅኔውን ለፈታው ከሰሙ/ ከድንጋዩ ስር “እዮብ መኮንን” የተሰኘ ወርቅ ያገኝበታል፡፡ እሱ ስለ - ነገ ብዙ ተከራክሮን፣ ብዙ ሞግቶን ---- ነገሩ እስኪሰርጽብን አልጠበቀንም፤ አውቀዋለሁ ወዳለው ነገ  ሄዷል፡፡ ምድሪቱ እንዲህ ያሉ ብርቱ ሰዎችን ብዙ ጊዜ መሸከም ሲከብዳት አይተናል፤ ሆኖም ግን ከእነዚህ ብርቱ ሰዎች  ድንገተኛ ስንብት፣ ሁለት ትላልቅ ቁም ነገሮችን መቅሰም/ ማስታወስ ግድ ይለናል፡፡ የመጀመሪያው ክቡር ዶ/ር ከበደ ሚካኤል ውብ አድርገው እንደገለጹት፤ «ጽድቅና ኩነኔ ቢኖርም ባይኖርም ከክፋት ደግነት ሳይሻል አይቀርም» የሚለው ነው፡፡ በደግነትና በመልካምነት መመላለስ ዋጋው ከፍ ያለ ነው፡፡ አንዳንዴ እንደውም፤ «በቃ እንዲህ ስታዩኝ አቀለላችሁኝ አይደል … እዮብ መኮንን እኮ ነኝ» እያለ ይቀልድ ነበር፡፡ ሌሎች ሰዎች ሲያገኙት ስናይ ነበር፣ ታዋቂ  መሆኑ ራሱ ትዝ የሚለን፡፡ ይህ የሆነው ግን የመታበይና የመኮፈስ የዝና ካባውን አውጥቶ ስለወረወረው ነው፡፡ እዚያው መኪና ለማቆም የተቸገረ ማንኛውም ሰው ሲመጣ፣ ከማንም ቀድሞ ተስፈንጥሮ ተነስቶ ሊረዳ ሲሞክር ላየው፣ ያ እዮብ መኮንን መሆኑን ማመን ይቸግር ነበር፡፡ በስራ መገለጥ፣ በእውነት ላይ መቆም ደማም ያደርጋል፤ ሞገስ ይሰጣል፤ ይህን ተምሬያለሁ፡፡ ሁለተኛውና ዋነኛው ትምህርት ግን “የብርቱ ሰው ሽልማቱ ሥራው ነው” የሚለው ነው፡፡ በተሰጠን ጊዜ፣ በሰዓቱ፣ ባለን ጸጋ መመላለስ መልካም ነው። እኛ እናልፋለን፤ በተለየ መንገድ የሚጓዘው ድንጋይ ግን ደግነታችንን፣ መልካም ምግባራችንን፣ ብርቱ ስራችንን እያተመ መጪውን ያንጻል፡፡ የእዮብ መልካምነትና ልዩ ስራ፣ በዚህ መልኩ መጪውን በበጎ ሲገራ ይኖራል፤ እርሱም በዚህ መንፈስ ሕያው ሆኖ ይኖራል!





Read 2849 times