Saturday, 14 January 2017 15:59

ሩስያ ከ2015 በኋላ ለተወለዱ ሁሉ ሲጋራ መሸጥ ልትከለክል ነው

Written by 
Rate this item
(3 votes)

አለማችን በሲጋራ ሳቢያ በአመት 1 ትሪሊዮን ዶላር ታጣለች
- በ2030 በየአመቱ የሚሞቱ አጫሾች ቁጥር 8 ሚሊዮን ይደርሳል

የሩስያ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እ.ኤ.አ ከ2015 በኋላ ለተወለዱ ሁሉም የአገሪቱ ዜጎች ሲጋራ እንዳይሸጥ የሚከለክል እጅግ ጥብቅ
ህግ በማውጣት ተግባራዊ ለማድረግ ማቀዱን የእንግሊዙ ዘ ታይምስ ዘገበ፡፡ ቀጣዩን የሩስያ ትውልድን ከሲጋራ ነጻ እንደሚያደርግ ቢታሰብም የአፈጻጸሙ ጉዳይ አጠያያቂ ነው የተባለው የሚኒስቴሩ ዕቅድ፣ እንደታሰበው ተግባራዊ የሚደረግ ከሆነ፣ ሩስያ ከአለማችን አገራት እጅግ ጥብቅ የጸረ-ትምባሆ ህግ ያወጣች የመጀመሪያ አገር ትሆናለች ያለው ዘገባው፤ አገሪቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በትምባሆ ዙሪያ ጉልህ እርምጃዎችን መውሰድ መጀመሯን ጠቁሟል፡፡ ዕቅዱ ጤናማ ዜጋ ለመፍጠር ቢያስችልም፣ በሌላ በኩል ግን ከጥራት በታች የሆነ የትምባሆ ምርት በጥቁር ገበያ ህገወጥ መንገድ እየተሸጠ የዜጎችን ጤና የከፋ አደጋ ላይ እንዲጥል ምክንያት ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት መፍጠሩን እንዲሁም ለሁሉም ዜጎች ሲጋራ አትሽጡ የሚለው ህግ በተጠቃሚዎችና በትምባሆ አምራች ኩባንያዎች ዘንድ ቁጣን ሊቀሰቅስ እንደሚችል መነገሩንም ዘገባው
አመልክቷል፡፡ የሩስያ መንግስት ባለፉት አመታት የሲጋራ አጫሾችን ቁጥር ለመቀነስ በሚል በወሰዳቸው የተለያዩ እርምጃዎች ከፍተኛ ውጤት
ማስመዝገቡን ያስታወሰው ዘገባው፣ ባለፈው የፈረንጆች አመት 2016 ብቻ የአገሪቱ አጫሾች ቁጥር በ10 በመቶ መቀነሱንም አክሎ ገልጧል፡፡
በተያያዘ ዜናም፣ የአለማችን ኢኮኖሚ በሲጋራ ሳቢያ በየአመቱ 1 ትሪሊዮን ዶላር ገደማ ኪሳራ እንደሚገጥመውና በሲጋራ ማጨስ
ሳቢያ በየአመቱ ለህልፈተ ህይወት የሚዳረጉ ሰዎች ቁጥር በመጪዎቹ 13 አመታት፣ 8 ሚሊዮን ያህል ይደርሳል ተብሎ እንደሚገመት
የአለም የጤና ድርጅት ሰሞኑን ባወጣው መረጃ ማስታወቁን ዘገባው አስረድቷል፡፡ ድርጅቱ ባለፈው ማክሰኞ ያወጣውን የጥናት ውጤት
ጠቅሶ ሮይተርስ እንደዘገበው፣ እስካሁን ባለው መረጃ በአለማቀፍ ደረጃ በሲጋራ ሳቢያ 6 ሚሊዮን ያህል ሰዎች በየአመቱ የሚሞቱ
ሲሆን፣ ይህ ቁጥር እስከ 2030 ድረስ 8 ሚሊዮን ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በሲጋራ ለህልፈተ ህይወት ከሚዳረጉት
ሰዎች መካከል ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት በመካከለኛና በዝቅተኛ ገቢ አገራት የሚገኙ እንደሆኑም ዘገባው ጠቁሟል፡፡

Read 2901 times