Saturday, 17 March 2012 09:39

የላሊበላው የጉዞ ማስታወሻ

Written by  ነብይ መኮንን
Rate this item
(0 votes)

አበሻ ለአበሻ እንኳን ውስጥ ለውስጥ ላይ ላዩንም አልተሳሰረም አብያተ ክርስቲያናት ግን ተሳስረዋል !

በላሊበላ የቤዛ ኩሉ ዕለት ጉድ ነው የሚታየው፡፡ ዲቪዲ ሻጩ፣ “የላሊበላ ታሪክ እዚህ አለች” የሚል መስቀል ሻጭ፣ “ቃሉን እዚች ላይ ታገኛላችሁ” የሚል የፀሎት መጽሔት አዟሪ፣ ምኑ ቅጡ፡፡ ፈረንጆቹ ካሜራ ጠምደው አንዴ በህዝቡ መሀል፣ አንድ ጥርቡ አለት አናት ላይ ይታያሉ፡፡ የአገሬው ሰው ጥርቡ አለት ጠርዝ ላይ ሲሄድ ከሥሩ አዘቅት ያለ አይመስለውም፡፡ እንጣጥ እንጣጥ እያለ ተረተሩ ላይ ሲረግጥ የሰው እግር አይመስልም፡፡

ለከተማማ ጭራሽ ለማየትም ያስፈራል፡፡ ይግረማችሁ ብሎ ጥርቡን  አለት እየቧጠጠ እየቆነጠጠ፣ የሚወርድ የሚወጣ ሰው አለ፡፡ አንዳንዴ አይጦች ምንም መያዣ ጉጥ፣ መሠርሠሪያ ጉድጓድ በሌለው ግድግዳ ላይ ሲሄዱ እንደምናየው ነው፡፡ አለቱም መሬቱም የራሱ የአገሬው ነው ማለት የገባኝ ዛሬ ነው፡፡ የከተሜ ልቡ ቅርብ ናት ነብሱም እንደዚያው፡፡ “ኧረ ወደቀ” እያለ ነብሱን ያስጨንቃል ልቡን ብርክ ይይዘዋል፡፡ ምናልባት አገሬውም በግልባጩ ለመጀመሪያ ጊዜ ኤሌቬተር (አሳንሰር) ላይ ሲወጣ እንዲህ ሊያደርገው ይችላል፡፡

 

ወረቡ እንደቀጠለ ነው፡፡ ባለመስቀል፣ ባለዣንጥላ፣ ባለሥዕል መሪ፣ ካህናት ከፊት እየመሩ፤ ተከታይ - ወራቢዎች ከኋላ ዑደቱን ጠምጥመው ዙሪያ ሊገጥሙት ጥቂት ቀርቷቸዋል፡፡ በወረቡ የታጀቡ የታደሉ ሙሽራዎች መጡ፡፡ ዕልልታው ቀለጠ፡፡

“ባለቀን ናቸው” አለ አንድ አገሬ፡፡

“በዚህ ቀን የተጋባ ባለዕጣ ነው” አለ ሌላው፡፡

ወረቡ አሸበረቀ፡፡ ታዳሚው ዕልልታውን አላቋርጥ አለ፡፡

እኛ ከተሜዎቹ እጥርቡ አለት አናት ላይ ከጠርዙ ራቅ ብለን፣ አንድ ጊዜ ወረቡን፣ አንድ ጊዜ  ጠርዙ ላይ እየተንጠላጠሉ የሚወርዱትን የአገሬው ወጣቶች እናያለን፡፡

“ኧረ” አለች አንድ የአዲሳቤ፣ ልቧ ምንጥቅ ብሎ “መውደቅና መሞት አይፈሩም እንዴ” ጠየቀች፤ አሁንም ስቅቅ እያለች፡፡

“መኖር ስለማያውቁ ይሆናል፤ መኖር የማያውቅ’ኮ መሞት አይገባውም” አለ ጓደኛዋ - እሱም አዲሳቤ ነው፡፡

በመሀል አንድ መስቀል ሻጭ መጣና

“ብር መስቀል በሁለት ብር ብር! መስቀል በሁለት ብር!” አለ፡፡

“ዋጋው ሲያንስ ብር አለመሆኑ ይታወቃል’ኮ” አለች አዲሳቤ፡፡

“እሱ አዲሳባ ነዋ! እዚህ ብር ብር ነው፡፡ አዲሳባ ብር ብር አደለም” አለና አለፈን፡፡ ሳቅን፡፡

የወረቡ ጥምጥም ክቡን እየገጠመ ነው፡፡ ከፊሉ ሰው፤ በአብዛኛው እዛው ቤተክርስቲያን ውስጥ ያደረው፤ ወደየመጣበት እየተመለሰ ስለሆነ ቀለል እያለ መጣ ግፊያው፡፡

ወረቡ አለቀ፡፡ ጭብጨባው፣ ዕልልታው ሰማይ ነካ፡፡ እንግዲህ ወደየቤተክርስቲያናቱ እየሄደ እንደኛ የሚሳለመው፤ ወደዚያ ያመራል፡፡ ወደ ቤቱ የሚሄደውም ወደ ቤቱ ይቀጥላል፡፡

ወደነዚህ አብያተ ክርስቲያናት ስገባ እጅግ የሚገርመኝ ሰው ጫማ አውልቆ፣ ጫማውን ደጅ ትቶ፣ ፈታሽ ሳይኖርበት እራሱን ፈትሾ መሳለሙ ነው፡፡

በዓለም ደረጃ የተንሰራፋውን ሽብር ለመቋቋም በሚል ሰበብ በአሜሪካና በአውሮፓ አውሮፕላን ጣቢያዎች የሚደረገውን ጫማና ቀበቶ ማውለቅ፣ ሳንቲምና ሞባይል በላስቲክ ቅርጫት ማስቀመጥ፣ በሰውና በኤሌትሪክ ኃይል መፈተሽ፣ ሲያስፈልግ ድርብ ፍተሻ (Double X-Ray) ማካሄድ ይገርማኛል፡፡ ያስቀኛልም፡፡

ከአውስትራሊያ የመጣችውን ተሳላሚ፤

“ይሄን ጫማ አውልቆ ቤተክርስቲያን መግባት፤ የሥነስርዓቱን ክብርና የሰውን ታዛዥነት ሳይ የአሜሪካ ፍተሻ ነው የሚመጣብኝ” አልኳት፡፡

“ዕውነትክን ነው፡፡ እኔም የእንግሊዝ ኤርፖርት ትዝ እንዲለኝ አደረከኝ፡፡”

“የሚገርምሽ አሜሪካኖቹም ሆኑ እንግሊዞቹ ዓለምን ከአሸባሪዎች ለማዳን ነው ይህን ሁሉ ፍተሻ የምናካሂደው” ይሉናል፡፡

“ዓለምን የሚያድንስ ይሄ ቤተክርስቲያን ነው”

“ዕውነት ነው፡፡ እዚህ ጫማሽን ብቻ ሳይሆን፣ ኃጢያትሽን፣ ተንኮልሽን፣ ሌብነትሽን ሁሉ አውልቀሽ እርቃንሽን ነው የምትገቢው ለማለት ይቻላል፡፡ እዛ ፈታሾቹ ሳይፀዱ ዓለምን እናፀዳለን ነው የሚሉት! Who Guards the Guards እንደሚሉትኮ ነው፡፡ ዘበኞቹን እራሳቸውን ማን ይጠብቃቸዋል?”

“እዚህኮ ዕምነትህ ብቻ ነው ጠባቂህ፡፡ ማንም የሚያስገድድህ፤ ተሳለም አትሳለም የሚልህ የለም”

“አንድ የእናቴ ንሥሐ - አባት የተናገሩትን ልንገርሽ:- አንድ የአገሩን ሴት ሲያተራምስ የኖሩ ሰው የዘመኑ በሽታ ይይዘውና የመጨረሻ ይታመማል፡፡ ደብረ ሊባኖስ ሄዶ መንኩሶ ሞተ ብለው ይነግሩኛል - ሰዎች፡፡

ታዲያ ለእናቴ ንሥሐ - አባት ይሄንን እነግራቸውና ይሄ እንዴት ይሆናል? ብዬ ጠየኳቸው፡፡ እንደዛ ያለ አተራማሽ በኋላ መነኮሰ ማለት ልክ ነው ወይ ብዬ እንደቀልድ ጠየኳቸው፤ ምን አሉኝ መሰለሽ?

“ምን ባክህ፤ ደብረ ሊባኖስ ፍተሻ የለ”

አቶ መንግሥቱ ለማ የሚባሉ ደራሲ “ዘመነ ሥቃያት” በሚል ቴያትራቸው ላይ፤ አንዱን ምስኪን አዛውንት፣ ጣሊያን በእርግጫ ይመታቸዋል፡፡ አዛውንቱ ምን ይላሉ፤ “ባፋንኩሎ ብሎ ቂጤን በካልቾ ከመታኝ በኋላ ነው አገር ሊያቀኑ እንደመጡ የገባኝ” በፍተሻ ዓለምን የሚያቀኑት ፈረንጆችም ሽማግሌው እንዳሉት ዓይነት ናቸው”

***

እንግዲህ አብያተ - ክርስቲያናቱን እያዩ ነብስን ማስደሰት ነው የቀረን! አብያተ - ክርስቲያናቱ ውስጥ ለውስጥ በዋሻና በፍልፍል ደረጃዎች የሚገናኙ ናቸው፡፡ የአሜሪካው ሁዋይት ሀውስና ኮንግሬስ ላይብረሪም ውስጥ ለውስጥ ይገናኛሉ፡፡ (ከእኛ ኮርጀው ይሆን) የቤተክርስቲያናቱ ውስጥ ለውስጥ መገናኘት እትብታቸው የተሳሰረ ያስመስላቸዋል፡፡ ታድለው! አበሻ ለአበሻ እንኳን ውስጥ ለውስጥ ላይ ላዩንም አልተሳሰረም፡፡ እነዚህ ውቅር ህንፃዎች ግን አንድነትንና ውህደትን ከዘመናት ጀምረው ሲያስተምሩን ኖረዋል - የሚማር ቢያገኙ! በመንፈስም በሥጋም እንተሳሰር ዘንድ ይመክራሉ፤ ያስተምራሉ፡፡ ከሀገር አልፈው ለዓለም ግርማ ሞገሳቸው ማተባቸው፣ አይበገሬነታቸው፣ ከአለት ማህፀን በቅለው የአገር ታቦት፣ የአገር አርማ መሆናቸው፤ የጥበብ አምላክ የተመሰገነ ይሁን፤ ቅዱስ ላሊበላን እጁን ይባርከው፤ ያሰኙናል! የላሊበላ ትልቁ ፀጋ በረከቱ ነው፤ የሚባለው ለዚህ ነው!

ቱሪስቶች የሚቋምጡላቸው ያለ ነገር አይደለም፡፡ ግዙፍ ግዙፍ አንድ አለት የተፈለፈሉ ህንፃዎችን ማየት የወርቅ እጅ ምስክር ስለሆነ ያስደምማቸዋል! ግድ ነዋ!

ቤተ - ማርያም ሰው በዛ፡፡ ቤተ ሚካኤል ገባን፡፡

ቤተ - ሚካአል

ይህ ቤተመቅደስ ወደሚገኝበት ክፍል ሴቶች አይገቡም፡፡ በቤተመቅደሱ ውስጥ ሁለት መናብርት አሉ፡፡ በስተቀኝ ያለው የታቦተ ቅዱስ ሚካኤል ሲሆን በስተ ግራ በኩል የታቦተ ቅዱስ ላሊበላ ነው፡፡ በዚህ ቤተመቅደስ ውስጥ ከሌሎች ፍልፍል አብያተክርስቲያናት በተለየ መልኩ፣ በዚያው በቤተመቅደሱ ዙሪያ የተቀረፁ አስደናቂ ምስሎችን እናያለን፡፡ 12ቱን ቅዱሳን ሃዋርያት የሚወክሉ፣ በግራ ስድስት በቀኝ ስድስት ቅርፆች አሉ፡፡ አብሮ ደግሞ ቅዱስ ላሊበላ ከተቀበረበት መንበር አጠገብ የጌታን ግንዘት የሚያመለክት የአንድ መልዐክ ሐውልት ተቀርፆ ይታያል፡፡ ከዚህ ግርጌ የአንድ መልአክ ሀውልት አለ፡፡ በዚህ ቤተመቅደስ ውስጥ ያሉት አምዶች በእያንዳንዱ ላይ ባለአራት ማዕዘን ቅርጽ መስቀል ተቀርጿል፡፡ እንደአንዳንድ ጽሑፍ ማስረጃዎች፣ የቤተመቅደሱ ከፍተኛ ቁመት 4 ሜትር ከ24 ሳንቲ ሜትር ነው፡፡ እዚህ ቤተመቅደስ ውስጥ ግሩም የሆኑ መስቀሎች እና ንዋየ ቅዱሳት ይገኛሉ፡፡ በተለይ ቅዱስ ላሊበላ በፀሎት ጊዜ ይደገፍበት የነበረ መስቀል መቋሚያው፤ የቅዱሱ አስከሬን ያረፈበት መካነ መቃብር የሚገኘው በዚሁ ቤተመቅደስ ውስጥ ነው፡፡ በቤተ ሚካኤል ውስጥ በሚገኘው የቅዱስ ላሊበላ መንበር ከሚገኝበት በስተምሥራቅ አቅጣጫ ላይ ባለው በር በኩል ወደ ውስጥ ሲገባ፣ የቅድስት ሥላሴን ቤተ መቅደስ እናገኛለን፡፡

ቤተ - ሚካኤል የአምዶቹ ቅርጽ፤ የግዙፍነቱ፣ የሰላማዊነቱ (Serenity)  ማስደነቁ ብቻ አይደለም፡፡ ትልቁ ኃይሉ ግርማ - ሞገሱ ይመስለኛል - ወደ ጽርሃርያም መንፈስን ማምጠቁ!

 

 

Read 2666 times Last modified on Saturday, 17 March 2012 09:42