Saturday, 14 January 2017 15:48

የታዋቂዎች አስገራሚ እውነታዎች

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

የሆሊውድ አክተሩ - ፊደል ካስትሮ
የኩባው ኮሙኒስት መሪ ፊደል ካስትሮና የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ሮናልድ ሬጋን አንድ የሚያመሳስላቸው ነገር አለ ከተባለ፣ የፊልም ባለሙያ የነበሩ መሆናቸው ነው፡፡ ሁለቱም በሆሊውድ ፊልሞች ላይ ተውነዋል - የየአገሮቻቸው መሪ ከመሆናቸው በፊት፡፡ በርግጥ የሬጋንን መሪ ተዋናይነት፣ የአዘቦት ቀን ተመልካች ያልሆኑ የድሮ ፊልም አድናቂዎች ሳይቀሩ አሳምረው ያውቁታል። የካስትሮ ግን የተረሳ የሆሊውድ ታሪክ ሆኗል፡፡ ለምን? ፊደል ካስትሮ እ.ኤ.አ በ1946 በተሰሩ ሁለት ፊልሞች ውስጥ ነው የተሳተፉት፡፡ አንደኛው “Holiday in Mexico” የሚል ሲሆን ሁለተኛው “Easy To Wed” ይሰኛል፡፡ ካስትሮ በሁለቱም ፊልሞች ላይ በአጃቢነት ነበር የተሳተፉት፡፡ በአንደኛው ፊልም ላይ አንድ መስመር ንግግር የነበራቸው ቢሆንም ከተቀረፁ በኋላ ዳይሬክተሩ ቆርጦ ካስትሮ ብግን ብለው ነበር አሉ፡፡ “አሜሪካ የምወዳት አገር ነበረች … አሁን ግን” … ብለው በንዴት ወደ አገራቸው ተመልሰዋል፡፡  
የመፅሃፍ ቀበኛው ፕሬዚዳንት
የአሜሪካ 26ኛው ፕሬዚዳንት ቴዎዶር ሩዝቬልት፤ በመፅሃፍ አንባቢነታቸው ዝነኛ ነበሩ፡፡ መፅሐፍ “የሰጠ ይድከም” የሚባልላቸው ዓይነት ሰው ናቸው፡፡ በህይወት ዘመናቸው በ10ሺዎች የሚቆጠሩ መፃህፍት እንዳነበቡ የሚነገርላቸው ሩዝቬልት፤ በአማካይ በቀን አንድ መፅሀፍ ያነቡ ነበር ተብሏል፡፡ በል በል ያላቸው ዕለት ደግሞ ከቁርስ በፊት አንድ መፅሀፍ፣ እስከ እራት ደግሞ ሁለት መፅሀፍት እምሽክ ያደርጉ ነበር፡፡ በፕሬዚዳትነት ዘመናቸውም ከንባብ ያላቀቃቸው አልተገኘም፡፡ የሥራ ጉዞ በባቡር ሲያደርጉ እንኳን ረዥም ሰዓት በንባብ ተመስጠው ነበር የሚያሳልፉት፡፡
የአገር መሪ ምን ዓይነት መፃህፍትን ማንበብ እንዳለበት ተጠይቀው ሲመልሱ፡- ሥነ ግጥምና ረዥም ልብ ወለዶችን እንዲሁም አጭር ልብ ወለዶችን ጠቅሰዋል። እኒህ ብቻ ግን አይደሉም፡፡ የሂብሩ ነቢያትንና የግሪክ ፀሐፌ ተውኔቶችን የማያደንቅ ከሆነ በራሱ ማዘን አለበት ብለዋል፡፡ በታሪክና በመንግስት እንዲሁም በሳይንስና በፍልስፍና ዙሪያ የተፃፉ መፃህፍትንም ማንበብ እንዳለበት ይመክራሉ - አንብበው የማይጠግቡት ሩዝቤልት፡፡
ተዋናይቷ ሂትለርን ለመግደል ትመኝ ነበር
ትውልደ - ስዊድን አሜሪካዊቷ የፊልም ተዋናይት ግሬታ ጋርቦ፤ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ ከአስርት ዓመታት በኋላ፣ ለቅርብ ጓደኞቿ አንድ ምስጢርና ምኞቷን አካፍላቸው ነበር፡፡ እንዲህ ስትል፤ “ሚ/ር ሂትለር በጣም ነበር የሚፈልገኝ፡፡ ሁልጊዜ ይፅፍልኛል፤ ወደ ጀርመን እንድመጣም ይጋብዘኝ ነበር፡፡ ጦርነቱ በወቅቱ ባይጀመር ኖሮ፣ እሄድለትና ከቦርሳዬ ውስጥ ሽጉጤን አውጥቼ እደፋው ነበር፤ ምክንያቱም እኔ ብቻ ነኝ ሳልፈተሽ ልገባ የምችል ብቸኛ ሰው፡፡”
በነገራችን ላይ በአሜሪካ በ1920ዎቹና 30ዎቹ ዓመታት ዝነኛ ተዋናይት የነበረችው ግሬታ ጋርቦ፤ በምርጥ ተዋናይትነት ሦስት ጊዜ ለኦስካር ታጭታ ነበር፡፡  
ለ20 ሚ. ዶላር ጀርባውን የሰጠ ኮሜዲያን
እንግሊዛዊው ኮሜዲያን ራስል ብራንድ፣ ከድምፃዊት ሚስቱ ካቲ ፔሪ ጋር የመሰረተውን ትዳር ከ14 ወራት በኋላ እ.ኤ.አ በ2012 በፍቺ ሲደመድም፣ ከ44 ሚ. ዶላር ሀብቷ ላይ ግማሹን የመውሰድ ህጋዊ መብት ነበረው - 20 ሚ. ዶላር ገደማ፡፡ ራስል ግን ከሚስቱ ገንዘብ ላይ ድምቡሎ መውሰድ እንደማይፈልግና በተቻለ መጠን መለያየታቸው ሰላም የሰፈነበት ይሆን ዘንድ እንደሚሻ መናገሩን TMZ.com በወቅቱ ዘግቦታል፡፡ በሴት አውልነቱ በእጅጉ የሚታወቀው ራስል፤ ፍቺው ከመጠናቀቁ በፊት እንኳን ከአንድ ከሁለት ሴቶች ጋር ግንኙነት ጀምሮ ነበር ተብሏል፡፡  የፖላንድ ተወላጇ ፈረንሳዊት ሳይንቲስት ሜሪ ኩሪ፤ የዘመኗ ዝነኛ የፊዚክስና ኬሚስትሪ ተመራማሪ ነበረች፡፡ ከባለቤቷ ከፒሬ ጋር እ.ኤ.አ በ1903 ዓ.ም በፊዚክስ የኖቤል ሽልማት ያሸነፈችው ኩሪ፤ በ1911 ዓ.ም ሁለተኛውን የኖቤል ሽልማት በኬሚስትሪ ተሸልማለች። ኩሪ ራዲየም የተሰኘውን የኬሚካል ንጥረ ነገር ያገኘች ዝነኛ ሳይንቲስት ናት፡፡ ሆኖም ከወንዶች የሙያ አቻዎቿ ተቃውሞና ተፅዕኖ ይደርስባት እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ከዚሁ ሁሉ ስኬትና ሽልማት በኋላ ስመ ጥር የሆነው የፈረንሳይ አካዳሚ አባል እንድትሆን አልተፈቀደላትም ነበር፡፡ በሌላ ምክንያት አልነበረም -  ሴት በመሆኗ ብቻ!  

Read 2401 times