Saturday, 14 January 2017 15:47

“2 ጊዜ 4”... ተማሪዎችን እያስጨነቀ ነው!

Written by  ዮሃንስ ሰ.
Rate this item
(7 votes)

በአንድ በኩል፡ አብዛኛው ነገር እየተሟላ ነው - በየዓመቱ ከመንግስት በጀት ውስጥ ሩብ ያህሉ ለትምህርት እየተመደበ ነው። በቂ ትምህርት ቤቶችና መማሪያ ክፍሎች፣ በዲፕሎማና በዲግሪ የተመረቁ መምህራን፣ ባለቀለም አዳዲስ መፃህፍት፣ ‘ፕላዝማ’ ቴሌቪዥኖችና ኮምፒዩተሮች... እየተሟሉ ነ …  የትምህርት ጥራትን፣ የተማሪዎችን ውጤት ለማሳደግ!
በሌላ በኩል፡ ከዚያ ሁሉ ወጪና መባተል የተገኘው “ውጤት”፣ አሳሳቢ ነው። ማንበብና መደመር የተሳናቸው ተማሪዎችን ማየት በእርግጥም ያሳስባል፣ ያሳዝናል፡፡ አንዲት ቃል ማንበብ የሚያቅታቸው፣ “2 ጊዜ 4” ስንት እንደሆነ ማስላት የማይችሉ የሦስተኛ ክፍል ተማሪዎች ብዙ ናቸው።
ይሄ ነው እንቆቅልሹ! ለትምህርት የሚያስፈልጉ ነገሮች በብዛት እየተሟሉ ቢሆኑም፣ ማንበብ የተሳናቸው ተማሪዎችም መበርከታቸው እንቆቅልሽ ነው፡፡     
ሚሊዮን መፃህፍት
140 ሚሊዮን መማሪያ መፃህፍት ታትመዋል (ባለፉት 8 ዓመታት)።
85 ሚሊዮን ዶላር (1.9 ቢሊዮን ብር) ፈጅቷል - የለመማሪያ መፃህፍት ህትመት።      
መማሪያ መፃህፍት፡ ለ‘ኤለመንታሪ’
በ2000 ዓ.ም፣ መማሪያ መፅሃፍ የሚያገኙ ተማሪዎች 8 ሚሊዮን ነበሩ።
በ2008 ዓ.ም፣ ለ19 ሚሊዮን ተማሪዎች የሚዳረሱ መፃህፍት ተሟልተዋል፡፡
እልፍ አእላፍ መምህራን፡
የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ መምህራን
በ1996 ዓ.ም፣ የመምህራን ቁጥር፣ 160ሺ ነበር።
በ2008 ዓ.ም፣ የመምህራን ቁጥር፣ 480ሺ ሆኗል።
ባለ ዲፕሎማ፣ ባለ ዲግሪ የ‘ኤለመንታሪ’ መምህራን
በ2000 ዓ.ም፣  50ሺ አይሞሉም ነበር።
በ2008 ዓ.ም፣ 300ሺ ደርሰዋል።
እነዚህን መረጃዎች ስትመለከቱ፣ የትምህርት ጥራትና የተማሪች ውጤትም በዚያው ፍጥነት አለመምጠቁ አይገርምም?
ነገር ግን፣ ማንበብ የማይችሉ የሁለተኛና የሦስተኛ ክፍል ተማሪዎች ብዙ መሆናቸውን የሚነግረን፣ ራሱ ትምህርት ሚኒስቴር ነው - አምና ባሰራጨው የሰባት አመታት የእቅድ ሪፖርት ገፅ 17 ላይ እንዲህ ይላል፡-
በ2002 ዓ.ም፣ ለተማሪዎቹ የትምህርት ደረጃ የሚመጥን ፈተና ተዘጋጅቶ እንደተሰጣቸው ሚኒስቴሩ አስታውሶ፣ ከፈተናው የተገኘው ውጤት አሳሳቢ እንደሆነበት ይገልፃል። ተማሪዎች መሰረታዊ ትምህርት እየቀሰሙ እንዳልሆነ ጥናቱ ያሳያል የሚለው ይሄው ሪፖርት፣ “ለምሳሌ 34 በመቶ የሁለተኛ ክፍል ተማሪዎች፣ አንዲትም ቃል ለማንበብ አልቻሉም፤ 48 በመቶ ያህሉ ተማሪዎች ደግሞ፣ አንብቦ የመረዳት ፈተና ላይ አንዲትም ጥያቄ መመለስ አልቻሉም” ብሏል (Education Sector Development Programme V (ESDP V)፤ 2008 - 2012 E.C፤ ገፅ 17)።
ችግሩ፣ የሁለተኛና የሦስተኛ ክፍል ተማሪዎች ላይ ብቻ አይደለም።
ለሌሎች ተማሪዎችም፣ እውቀትን ማካበትና ክህሎትን ማዳበር፣ ከባድ ፈተና ሆኖባቸዋል።
የአራተኛ ክፍል ተማሪዎች ላይ የተደረጉ ጥናቶች ላይ፣ ተመሳሳይ ዝቅተኛ ውጤት ነው የተገኘው። በ1992 ዓ.ም እና በ1996 ዓ.ም በተደረጉ ጥናቶች ላይ፣ የተማሪዎች አማካይ ውጤት 50 ከመቶ ነበር። ከዚያ በኋላ ወደ 40 ከመቶ ወርዷል። በትምህርት ሚኒስቴር እና በዩኒሴፍ አማካኝነት፣ በ300 ገደማ ትምህርት ቤቶች በተካሄደው “Mid-Term Evaluation ... June 2015” ጥናት ውስጥ የተካተቱ መረጃዎችን ተመልከቱ።
የአራተኛ ክፍል ተማሪዎች አማካይ የፈተና ውጤት።
     1992    1996    2000    2002
ውጤት
ከመቶ    48    49    41    40


የስምንተኛ ክፍል ተማሪዎች አማካይ የፈተና ውጤት።
     1992    1996    2000    2002
ውጤት
 ከመቶ    41    40    36    35


የተማሪዎች ውጤት፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ የወረደው ለምንድነው?
በእርግጥ፣ “ትምህርትን ለሁሉም ማዳረስ” በሚለው ዘመቻ፣ የተማሪዎች ብዛት በፍጥነት መጨመሩ፣ “ለትምህርት ጥራት ክፉ እንቅፋት ሆኗል” የሚል ምክንያት በተደጋጋሚ ይቀርባል።
ይህ ምክንያት፣ ከኢትዮጵያ መንግስትና ከትምህርት ሚኒስቴር ብቻ የሚሰነዘር “ማመከኛ” አይደለም። “ትምህርትን እንደግፋለን” በማለት፣ ብድርና እርዳታ የሚሰጡ በርካታ የውጭ መንግስታትና አለማቀፍ ተቋማትም ተመሳሳይ “ሰበብ” ያቀርባሉ - የአሜሪካና የአውሮፓ መንግስታት (የአሜሪካው ዩኤስኤአይዲ፣ የእንግሊዙ ዲኤች አይዲ)፣ የአለም ባንክ፣ ዩኒሴፍ፣ ዩኔስኮ፣ ሴቭ ዘቺልድረን... ወዘተ። የአለም ባንክ ብድር ለመስጠት ሲስማማ ባሰራጨው ሰነድ ላይ እንዲህ ብሎ ነበር - “Achievements in access have not been accompanied by adequate improvements in quality. In some areas, quality has deteriorated at least partly as a result of rapid expansion.”
ምን ማለት ነው? የተማሪዎች ቁጥር በፍጥነት ሲጨምር፣ ከዚሁ ጋር የሚመጥን በቂ የመማሪያ ክፍል፣ የመምህራን፣ የመፃህፍት ብዛት ያስፈልጋል። ይሄ ሳይሟላ ሲቀር፣ የትምህርት ጥራት ይቀንሳል። በአንድ ክፍል ውስጥ ብዙ ተማሪዎች ይታጎራሉ - ጥራት የሌለው አንድ የመማሪያ መፅሃፍ ላይ፣ ብዙ ተማሪዎች “በራሽን፣ በወረፋ” ይሻማሉ። ብቃት ያላቸው መምህራን ደግሞ ጥቂት ይሆናሉ። ይሄ ሁሉ ተደማምሮ፣ የትምህርት ጥራት ከመሻሻል ይልቅ ይሸረሸራል። ተማሪዎች፣ በየደረጃው እውቀትንና ክህሎትን እያካበቱ የሚራመዱበት እድል ያጣሉ። ውጤታቸው ይወርዳል።
ይሄን፣ ላይ ላዩን ስናየው፣ ምክንያታዊ ትንታኔ ይመስላል። ነገር ግን፣ አይደለም። ለምን ቢባል፣ ከተጨባጭ መረጃዎች ጋር ይጋጫል። ከ1996 ወዲህ ያሉትን ዓመታት እንመልከት።
አዎ የተማሪዎች ቁጥር በፍጥነት ጨምሯል። ከ10 ሚሊዮን ወደ 21 ሚሊዮን።
ነገር ግን፣ በዚያው መጠን፣ እንዲያውም ከዚያም በተሻለ ፍጥነት፣ የመምህራን ቁጥርና የትምህርት ደረጃ ጨምሯል። የመፃህፍት ቁጥርና “የመፃህፍት ጥራት”፣ በእጥፍ ፍጥነት ጨምሯል ማለት ይቻላል። የመማሪያ ክፍልም እንዲሁ።
የመማሪያ ክፍል (የአንድ ክፍል ተማሪዎችን ብዛትን ተመልከቱ።)
በ1996 ዓ.ም በአንድ ክፍል፣ 74 ተማሪዎች
በ2000 ዓ.ም በአንድ ክፍል፣ 62 ተማሪዎች
በ2007 ዓ.ም በአንድ ክፍል፣ 54 ተማሪዎች
ቁልጭ ያለ መረጃ ነው፡፡ የመማሪያ ክፍል እጥረት አልተባባሰም። እንዲያውም በፍጥነት ተሻሽሏል። ይሄ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን የሚመለከት መረጃ ነው። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችስ? በአንድ ክፍል 79 ተማሪዎች ነበር የሚታጎሩት - በ1996 ዓም። በአስር ዓመታት ውስጥ ወደ 57 ተሻሽሏል። መማሪያ ክፍሎች፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ በተማሪዎች ብዛት እየተጨናነቁ አይደሉም - እየተሻሻሉ እንጂ።
የመምህራን ብቃትና ብዛትስ?
የተማሪዎች ብዛት በአስር ዓመት ውስጥ ወደ እጥፍ ቢጨምርም፣ የመምህራን ብዛት ከሦስት እጥፍ በላይ ሆኗል።
በ1996 ዓ.ም፣ የአንደኛ ደረጃ መምህራን 140ሺ ገደማ ነበር። አንድ መምህር፣ ለ65 ተማሪዎች ማለት ነው። ዛሬ የመምህራኑ ቁጥር ወደ 400ሺ ተጠግቷል።
በ1996 ዓ.ም፣ የዲፕሎማ ደረጃ ያሟሉ መምህራን 5ሺ እንኳ አይሞሉም ነበር።
ዛሬ፣ 300ሺ ያህሉ ባለ ዲፕሎማ ናቸው።
የሁለተኛ ደረጃ መምህራንስ?
በ1996 ዓ.ም፣ የመምህራኑ ቁጥር 15 ሺ ነበር።
በ2007 ዓ.ም፣ ቁራቸው ዛሬ ከ80ሺ በላይ ሆኗል።
የመምህራኑ ብዛት ብቻ ሳይሆን የትምህርት ደረጃቸውም ከድሮው ተሻሽሏል።
ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የሚመጥን ዲግሪ ወይም ዲፕሎማ ያሟሉ መምህራን፣ ከ7ሺ አይበልጡም ነበር።
ዛሬ፣ ቁጥራቸው ወደ 75ሺ ጨምሯል።
(በእርግጥ፣ ዲፕሎማና ዲግሪ ማሟላት ማለት፣ የእውቀትና የክህሎት ብቃትን ሙሉ ለሙሉ ያሳያል ማለት አይደለም። የመንግስትና የትምህርት ሚኒስቴር መመዘኛዎችን የሚያሟሉ መሆናቸው ግን አያጠራጥርም። እንዲያውም፣ እነ ዩኔስኮ፣ የአሜሪካ መንግስት (ዩኤስኤአይዲ)፣ የዓለም ባንክ... በጋራ የሚስማሙባቸው መመዘኛዎችንና የማስተማሪያ ዘዴዎችንም መጥቀስ ይቻላል። መምህራኑ፣ በብዛት እነዚህን መመዘኛዎች በማሟላት በፍጥነት ተሻሽለዋል፡፡ መመዘኛዎቹ ትክክለኛ ናቸው ማለት ግን አይደለም፡፡)     
የመማሪያ መፃህፍት ጉዳይስ?
ይሄም፣ በእጅጉ ተሻሽሏል። ዋና ዋናዎቹን የትምህርት አይነቶች ከተመለከትን፣ ለሁለት ለሦስት ተማሪዎች አንድ መፅሃፍ ነበር የሚደርሳቸው ከ2000 ዓ.ም በፊት።
ባለፉት ስምንት ዓመታት ግን፣ ለስርዓተ ትምህርት ክለሳ፣ ለመማሪያ መፃህፍት ዝግጅትና ለህትመት ከ260 ሚሊዮን ዶላር በላይ የብድርና የእርዳታ ገንዘብ ወጪ ሆኗል - (ወጪው፣ አሁን ባለው ምንዛሬ፣ ወደ 6 ቢሊዮን ብር ይጠጋል። ለመፃህፍት ህትመት የወጣው ገንዘብም ወደ 2 ቢሊዮን ብር ገደማ ነው።)
በእነዚሁ ዓመታት ከ140 ሚሊዮን በላይ መፃህፍት ታትመዋል። በእያንዳንዱ የትምህርት ዓይነት፣ ለአንድ ተማሪ አንድ መፅሃፍ ማዳረስ ይቻላል ማለት ነው - የመፅሃፍ ስርጭት ካልተዝረከረከ በቀር።
ቢዝረከረክም እንኳ ሆኖ፣ ከድሮ ጋር ሲነፃፀር፣ የመማሪያ መፃህፍት እጥረት አልተባባሰም። ተሻሻለ እንጂ። የህትመት ጥራታቸውም በጣም ተሻሽሏል። ሽሮ በመሰለ ወረቀት ላይ፣ በጥቁር ቀለም የታተመባቸው ገፆች... ይሄ ድሮ ቀርቷል። የዛሬዎቹ መፃህፍት፣ በቀለማት የደመቁ ናቸው።
(በእርግጥ፣ የመፃህፍት ብዛትና ቀለም ተትረፈረፈ ማለት፣ የመፃህፍት “ትምህርታዊ ጥራት” ተሻሽሏል ማለት አይደለም። ቢሆንም ግን፣ የአገሪቱ የትምህርት ሚኒስቴር ብቻ ሳይሆን፣ የውጭዎቹ መንግስታትና አለማቀፍ ተቋማትም፣ ለአዲሶቹ የመማሪያ መፃህፍት፣ የአድናቆት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።)
የትምህርት ማደግና የመውደቅ እንቆቅልሽ  
በመማሪያ ክፍል፣ በመምህራን በመፃህፍት... ብዙ ብዙ ነገር ተሻሽሏል - ብዙ ብዙ ገንዘብ በየአመቱ እየተመደበለት።
ነገር ግን፣...
በ2002 ዓ.ም በተካሄደው ጥናት እንዳየነው ሁሉ፣ አምና በ2008 ዓ.ም በተካሄደ ጥናትም፣ አንዲት ቃል ማንበብ የማይችሉ የሁለተኛ ክፍል ተማሪዎች ብዙ መሆናቸው ተረጋግጧል (ከመቶ ተማሪዎች መካከል 40 እና 50 ያህሉ ተማሪዎች፤ አንዲትንም ቃል ማንበብ አይችሉም)። ከሦስተኛ ክፍል ተማሪዎች መካከልም እንዲሁ፣ ሩብ ያህሉ አንዲትንም ቃል ማንበብ የማይችሉ ሆነዋል (አምና የዩኤስኤአይዲ ጥናት በተካሄደባቸው የትግራይ፣ የደቡብና የሶማሌ ክልሎች)።
በዩኒሴፍና በትምህርት ሚኒስቴር አማካኝነት፣ በአማራ ክልል በ2007 ዓ.ም የተካሄደው አዲስ ጥናትም፣ ተመሳሳይና አሳሳቢ ችግሮችን የሚያሳይ ነው (Evaluation of Learning Achievement in Selected Woredas in Amhara and Sub-Cities in Addis Ababa, Ethiopia... Mid-Term Report)፡፡
የያንግ ላይቭስ የአስር ዓመታት ጥናትም፣ … የትምህርት ጥራትና የተማሪዎች ውጤት እንዳልተሻሻለ ያሳያል። እንዲያውም ተባብሷል። ከአስር ዓመት በፊት፣ ‘2 ጊዜ 4፣ ስንት ነው?’ ተብለው ከተጠየቁ የ12 ዓመት ተማሪዎች መካከል፣ ሰማኒያ በመቶ ያህሉ በትክክል መልሰዋል። 20 በመቶዎቹ ግን፣ በትክክል አልመለሱም።
በ2006 ዓ.ም፣ ተመሳሳይ ጥያቄ ከቀረበላቸው የ12 ዓመት ተማሪዎች መካከል ግሞ፣ 30% ያህሉ በትክክል መመለስ አልቻሉም።
እንግዲህ፣ እንቆቅልሹን ተመልከቱ።
የተማሪዎች ቁጥር ባለፉት አስር ዓመታት በፍጥነት በመጨመሩ ሳቢያ፣ የመማሪያ ክፍል እጥረት አልተባባሰም። እንዲያውም፣ ብዙ ትምህርት ቤቶች ስለተገነቡ፣ የመማሪያ ክፍል እጥረት ተሻሽሏል። የመምህራን ብዛትና የትምህርት ደረጃም ተሻሽሏል። የመማሪያ መፃህፍት ችግርም... ተሻሽሏል።
ነገር ግን፣ የተማሪዎች የእውቀት ደረጃ አልተሻሻለም። እንዲያውም ከጊዜ ወደ ጊዜ ቀንሷል።
ይሄ እንቆቅልሽ ነው፡፡
በእርግጥ፣ እንቆቅልሹ፣ “ድፍን እንቆቅልሽ” አይደለም።
ፍቺ አለው። ፍቺውን የምናገኘው የት ነው?
 የመማሪያ ክፍሎችን በመቁጠር ብቻ ሳይሆን፣ ክፍሎቹ ውስጥ የሚከናወነውን አዲስ “የትምህርት ውሎ” በመታዘብ ነው፣ ፍቺውን የምናገኘው።
የመምህራንን ብዛት ከመቁጠር አልፈን፣ መምህራኑ፣ በዲፕሎማና በዲግሪ ምን አይነት አዲስ “የማስተማሪያ ዘዴ” እየሰለጠኑ እንደሆነ በመመርመር ነው፣ ፍቺውን የምናገኘው።
የአዳዲስ መፃህፍት ብዛትንና ቀለምን ከማድነቅ ባሻገር፣ የመፃህፍቱን ይዘት በመፈተሽ ነው፤ እንቆቅልሹን የምንፈታው፡፡
አዲሱ የማስተማሪያ ዘዴ፣ አዲሱ የትምህርት ውሎ እና አዲሱ የመፃህፍት ይዘት፣ … በይፋና በግላጭ እውቀትን የሚያጣጥል መሆኑ ነው ዋናው ችግር፡፡ በሌላ አነጋገር፣ የተማሪዎች ውጤት ያልተሻሻለውና የወረደው አለምክንያት አይደለም። ይህንን በመረጃ ዘርዝረንና ተንትነን ለማየት፣ በቀጠሮ እንለያይ፡፡

Read 8483 times