Saturday, 14 January 2017 15:44

“የማራኪ አንቀጽ ምንተፋ ቅሌት” ከአፍሪካ እስከ አሜሪካ ታላላቅ መሪዎች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ባለፈው ቅዳሜ ማለዳ...
ምዕራብ አፍሪካዊቷ ጋና፣ ለሳምንታት ደፋ ቀና ያለቺበትን የአዲሱ መሪዋ በዓለ ሲመት በድምቀት አከበረች፡፡ አዲሱ የጋና ፕሬዚዳንት ናና አኩፎ አዶ፣ ከመዲናዋ አክራ ለሚወዱት ህዝባቸው በስሜት የታጀበና ልብ የሚነካ ንግግር አደረጉ፡፡ ህዝባቸውም የታላቁን ናና አኩፎ አዶን አነቃቂ ንግግር በጥሞና እያዳመጠ፣ ባለ ራዕይ መሪነታቸውንና አንደበተ ርቱዕነታቸውን ሲያደንቅ ዋለ፡፡
የዋሁ የጋና ህዝብ የአዲሱን መሪውን የንግግር ችሎታ እያደነቀ ባለበት ቅጽበት ግን፣ ጉድ መጎልጎል የሚወደው የፌስቡክ ሰራዊት፣ አዲሱን መሪውን ትዝብት ላይ የሚጥል ዘመቻ ከፈተ፡፡
“ፕሬዚዳንቱ በበዓለ ሲመታቸው ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ከሁለት የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ንግግር፣ የተመነተፏቸውን አንቀጾች ተጠቅመዋል” የሚለው ያልተረጋገጠ ውንጀላና ሃሜት፣ቅዳሜን ሙሉ በፌስቡክ ሲሰራጭ ዋለ፡፡
በነጋታው...
ነገርዬው ካልተረጋገጠ ውንጀላና ሃሜትነት፣ በማስረጃ ወደተደገፈ አነጋጋሪ ዜናነት ተቀየረ፡፡ የናና አኩፎ አዶ ንግግር፣ የበርካታ የዓለማችን መገናኛ ብዙሃን ትኩስ ዜና ብቻ ሳይሆን የአዲሱ የጋና መንግስት የሃፍረትና የይቅርታ አጀንዳ ሆነ፡፡
ቢቢሲ እንደዘገበው፣ የጋናው ፕሬዚዳንት በበዓለ ሲመታቸው ላይ ባደረጉት ንግግር፣ የቢል ክሊንተንን እና የጆርጅ ደብሊው ቡሽን ንግግሮች መንትፈው፣ የራሳቸው በማስመሰል ማቅረባቸው ተረጋግጧል፡፡ የአዲሱ ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤትም፣ አዲሱ ፕሬዚዳንት የተባለውን ነገር መፈጸማቸውን በማመን፣ እሁድ ማለዳ የይቅርታ መግለጫ አውጥቷል፡፡
የጋናው ፕሬዚዳንት በዕለቱ ባደረጉት ንግግር፣ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ቢል ክሊንተን ከ20 አመታት በፊት በበዓለ ሲመታቸው ላይ ካደረጉት ንግግር የወሰዱትን አንድ ማራኪ አንቀጽ የራሳቸው አስመስለው አቅርበዋል፡፡ ይሄም ብቻ አይደለም። ጆርጅ ደብሊው ቡሽ በ2001 ካደረጉት ንግግር፣ የወሰዱትን ሌላ ማራኪ አንቀጽም፣ ምንጩን ሳይጠቅሱ አነብንበዋል፡፡
ከሌላ ሰው የመነተፉትን ልብ አማላይና ማራኪ አንቀጽ የራሳቸው አስመስለው በማቅረብ፣ የጋናው ፕሬዚዳንት የመጀመሪያው የአገር መሪና ገናና ፖለቲከኛ አይደሉም የሚለው ቢቢሲ፤ ወደ ኋላ መለስ ብሎ ተጨማሪ ክስተቶችን ያስታውሳል፡፡
የትራምፕ ሚስት
የተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የዶናልድ ትራምፕ ባለቤት፣ ሚላንያ ትራምፕ በሃምሌ ወር ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ቀዳማዊት እመቤት ሚሼል ኦባማ በ2008 ካደረጉት ንግግር የመነተፏቸውን አንቀጾች የራሳቸው አስመስለው አቅርበዋል፣ በሚል የትችት ናዳ ሲወርድባቸው መሰንበቱን የቢቢሲ ዘገባ አስታውሷል፡፡
የማዳጋስካር መሪ
የማዳጋስካር ፕሬዚዳንት በበኩላቸው፤በጥር ወር 2014 በተካሄደው በዓለ ሲመታቸው ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ተመሳሳይ ምንተፋ መፈጸማቸው ተነግሯል፡፡ ፕሬዚዳንቱ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር ውስጥ፣ የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ከአስር አመታት በፊት ካደረጉት ንግግር የተወሰደና አንዳች እንኳን ለውጥ ያልተደረገበት አንቀጽ ተገኝቷል፡፡
የፕሬዚዳንቱ ተወካይ ግን፣ እንደ ጋናው አቻቸው ይቅርታ አልጠየቁም፡፡
“ከሌሎች ሰዎች ንግግር የተመረጠ አንቀጽ ወስዶ መጠቀም ምን ነውር አለው?!...” ብለው ድርቅ አሉ እንጂ፡፡
የናይጀሪያው መሪ
የናይጀሪያው ፕሬዚዳንት ሙሃመድ ቡሃሪ፤ በመስከረም ባደረጉት ንግግር፣ ባራክ ኦባማ በ2008 ካደረጉት ንግግር የወሰዱትን አንቀጽ ተጠቅመዋል፡፡
የአየርላንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር
የአየርላንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኤንዳ ኬኒ፤ ምንተፋ ግን ለየት ያለ ነው፡፡
እሳቸው በ2011 ደብሊን ውስጥ ባራክ ኦባማን ለህዝብ ሲያስተዋውቁ ባደረጉት ንግግር የተጠቀሙትን አንድ አንቀጽ የመነተፉት፣ ከራሳቸው ከባራክ ኦባማ መሆኑ ተነግሯል፡፡
ኦባማ ራሳቸው
ከንግግሮቻቸው በርካታ አንቀጾችን በሌሎች ሰዎች የተመነተፉት ኦባማ ራሳቸውም፣ ከሌሎች ሰዎች ተመሳሳይ ምንተፋ መፈጸማቸውን የቢቢሲ ዘገባ ያስረዳል፡፡
ዘገባው እንዳለው፣ ኦባማ በ2008 ባደረጉት ንግግር፣ የቀድሞው የማሳቹሴትስ ገዢ ዴቫል ፓትሪክ፤ ከአስር አመታት በፊት ካደረጉት ንግግር የወሰዱትን አንቀጽ የራሳቸው አስመስለው አቅርበዋል፡፡
ኦባማ ይህን በማድረጋቸው ለቀረበባቸው ወቀሳ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ “ይህን አንቀጽ በንግግሬ ውስጥ እንድጠቀም ምክር የሰጡኝ ራሳቸው ዴቫል ፓትሪክ ናቸው፤ ይሄም ሆኖ አንቀጹ የእሳቸው መሆኑን አለመጥቀሴና እውቅና አለመስጠቴ ስህተት መሆኑን አምናለሁ” በማለት፡፡
የቀድሞው የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር
የቀድሞው የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ስቴፈን ሃርፐርም በ2003 ባደረጉት ንግግር ተመሳሳይ ድርጊት ፈጽመዋል፡፡
ሰውዬው በወቅቱ ባደረጉት ንግግር ውስጥ የተጠቀሙት አንድ አንቀጽ፣ የያኔው የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆን ሃዋርድ፤ ከቀናት በፊት ካደረጉት ንግግር የተመነተፈ እንደሆነ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ ይህ የአንቀጽ ምንተፋ፣ እንደ ዋዛ ታልፎ አልቀረም፡፡ ድርጊቱ ከተፈጸመ ከአምስት አመታት በኋላ፣ ሌላ መዘዝ ይዞ መጥቷል፡፡ በወቅቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግሩን የጻፈላቸው ሰው፣ ያንን አንቀጽ ከሌላ ሰው መመንተፉ በመረጋገጡና ድርጊቱ ስቴፈን ሃርፐርንና ፓርቲያቸውን ሃሜትና ስላቅ ላይ በመጣሉ፣ ስራውን እንዲለቅ ተደርጓል፡፡












Read 1646 times